በሀገራችን ላይ የተለያዩ ሴራዎችን ሲያካሂድ የቆየው የአሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፊት ለፊት ከሚያካሄዱት ጦርነትጋር ተያያዥ ሴራዎቻቸው ጎን ለጎን፤ የአገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም በሰፊው ሲሰሩ ቆይተዋል፤ እየሰሩም ይገኛል።
በዚህ ተግባራቸው መካከል የውጭ ምንዛሬን የመቆጣጠሪያ ስልታቸው የጥቁር ገበያ አንዱና ቀዳሚው ሲሆን፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርና ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲማረር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ አሳውቋል። የተለያዩ መረጃዎችም ይሄንኑ ያሳያሉ።
በዚህ መሰረት የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረባቸው አመታት በዘረጋቸው ኔትዎርኮችና ቅጥረኞች አማካኝነት ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌን፣ መተማንና ሌሎች የመውጫ በሮችን በመጠቀም የኮንትሮባንድ ዝውውር ላይ በመሳተፍና ዶላርን በጥቁር ገበያ እየገዛ የዶላር እጥረት እንዲከሰት እያደረገ ይገኛል።
እኛም ለዛሬው እትማችን የጋበዝናቸው እንግዳ አቶ ሙሉጌታ ተመስገን ሲሆኑ፤ በፋይናንስና ደህንነት መረጃ ማዕከል የተግባርና ክትትል ቡድን መሪ ናቸው። እርሳቸውም የአገርን ኢኮኖሚ በማዳከም ህዝብና መንግስትን የማቃረን እንቅስቃሴ ላይ በማተኮር የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ደባ እና አጠቃላይ በአገሪቱ እየተፈጸመ ያለው የኢኮኖሚ አሻጥር ምን እንደሚመስል ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል። ከእንግዳችን
አቶ ሙሉጌታ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን:- የኢኮኖሚ አሻጥር ሲባል ምን ማለት ነው? መገለጫዎቹስ?
አቶ ሙሉጌታ:– የኢኮኖሚ አሻጥር ማለት የግብይትን ዋጋ በማሳነስና በማናር የሚፈጸም ሲሆን፤ በአጠቃላይ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ገበያውን በመቆጣጠር የገበያ ዋጋ እንዲዋዥቅ ማድረግ ነው። ይህን የሚያደርጉትም መንግስትን የማዳከም እና የተረጋጋ ገበያ እንዳይኖር በማድረግ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ የሚፈጸም ተግባር ነው የኢኮኖሚ (የገበያ) አሻጥር የሚባለው።
አዲስ ዘመን:- በአገሪቱ እየተደረገ ያለው የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጸምባቸው ዋና ዋና መንገዶች/ስልቶች ምን ምን ናቸው? በተጨባጭ የሚከናወኑ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ቢገለጹ?
አቶ ሙሉጌታ:- በአገሪቱ እየተደረገ ያለው ዋነኛው የኢኮኖሚ አሻጥር ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር ነው። በገንዘብ ማጭበርበሩ ስልት ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ወይም ማሽኖችን አርቲፊሻል የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከዋጋቸው በላይ በእጥፍ እንዲገቡ በማድረግ አጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ጠራርጎ ወደ ውጭ የማሸሽ ስራ ይሰራል።
በአንጻሩ ደግሞ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች ከዋጋቸው በታች በመሸጥ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው (ኤክስፖርት ከምታደርጋቸው) ምርቶች የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ የማድረግ ስራ ይሰራል። ይህም በብሄራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጁ 592 ስር እንደተደነገገው፣ አስመጭና ላኪዎች ከዋጋ በታች ወይም ከዋጋ በላይ (under or over invoice) ምርት፣ እቃዎችንና ማሽኖችን ሲያስገቡ ወይም ሲልኩ ከተገኙ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት እስር የሚያስቀጣ ትልቅ ወንጀል አድርጎ በአገር አቀፍ ደረጃ ተደንግጓል።
ነገር ግን በአገሪቱ በተለይ ከለውጡ በፊት ባሉ ሁኔታዎች የመንግስት ግዥ ይሁን የግለሰብ እቃ ግዥ ዋጋ ስላልተተመነና የዋጋ ዝርዝር (price index) ስላልወጣላቸው፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ዕቃዎችና ምርቶችን አለም አቀፍ ዋጋዎችን ያለማወቅ ሁኔታዎች አሉ። የሚገቡ እቃዎች ከዋጋቸው በላይ በተጋነነ ዋጋ ( over invoice) የሚገቡ እቃዎች ላይ ቁጥጥር ያለማድረግ። በተጋነነ ዋጋ የሚገቡ እቃዎች ወይም ከፍተኛ ዋጋ የወጣባቸው እቃዎች ታክሳቸው (ግብራቸው) ከፍተኛ ስለሆነ ታክስ የሚያደርጉ አካላት ታክሱ ላይ ነው የሚያተኩሩት። እነዚህ አካላት ታክሳቸውን ከመቁረጥ ባለፈ እቃዎቹ በምን ያህል ዋጋ እንደተገዙና ምን ያህል ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆነ የማረጋገጥ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው አይሰሩም።
በዚህም ከለውጡ በፊት በተለይ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ አልሚዎች ያስገቧቸው ማሽኖችና እቃዎች አሮጌ ናቸው። ይህም በምርመራ የተጣራ ሲሆን፣ እቃዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ በገቡ በአስርና በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ሳይሰራባቸው የወደቁ እቃዎች አሉ። ለምሳሌ፣ በአንዋር ሳዳት የስልጣን ዘመን ግብጽ ላይ የተመረተ አሮጌ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ። አሁንም ብዙ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸው ማሽኖች አሮጌ ናቸው።
በዚህም እቃው አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ደግሞ አሮጌ ስለሆነ ዋጋው የሚቀንስበትና ወጪው የሚበዛ (high depreciation cost) ይሆናል። የገቡት አሮጌ ማሽኖችም ተበላሽተው ስራ መስራት አይችሉም። አልሚው ስራ ካልሰራ ደግሞ ታክስ አይከፍልም። በዚህም የአገሪቱ አመታዊ ታክስ ሪፖርት ላይ ዜሮ ወይም ደግሞ ዝቅተኛ ሪፖርት የምታስተላልፍባቸው ሁኔታዎች አሉ።
በአጠቃላይ ከዋጋው በላይ በተጋነነ ዋጋ ጥራት የሌላቸውና ደረጃቸውን ያልጠበቁ እቃዎችን ማስገባት አደገኛ የሆነ የአገርን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሌሎች አገሮች እንዲወጣ የሚደረግበት መንገድ ነው። በአንጻሩ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከዋጋቸው በታች መሸጥ አገሪቱ ኤክስፖርት ከምታደርጋቸው ምርቶች ማግኝት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ የሚያደርጋት የኢኮኖሚ አሻጥር ነው።
በሌላ በኩል የመንግስት የዕቃ ግዥዎችን ስንመለከት በተለይ ከለውጡ በፊት ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ተያይዞ ማሽኖች ገቡ ይባላል። ነገር ግን እነዚህ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ አይሰሩም። ይህ የሆነበት አንዳንድ ጊዜ ለኢትዮጵያ ብድር የሚሰጡ አገራት ቅድመ ሁኔታ (requirement) ካስቀመጡ በኋላ ብድር ያበድራሉ። በዚህም እጃችን ቆልምመው እቃ ከኛ ግዙ የሚሉባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ስለዚህ ከአበዳሪ አገራት በሚገዛበት ጊዜ አሮጌ ወይም ያገለገሉ እቃዎች ነው የሚሸጡልን። በዚህም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ያላቸው የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ እንዲወጣ በማድረግ በኢኮኖሚ አሻጥሩ የደቀቀ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸው ይደረጋል።
ስለዚህ ኢንፖርት ኤክስፖርት እቃዎችን በተለያየ መንገድ አለማቀፍ ዋጋቸውን ከኢንተርናሽናል ፕራይስ ትራንስፓራንት (international price transparent) ወይም እቃዎቹ ከሚገቡበት አገር ዋጋቸውን የማወቅና የዕቃዎቹን ዋጋ ባንኮች እንዲያውቁት የዋጋ ዝርዝሩን ለባንኮች እንዲደርሳቸው በማድረግ፤ በዋጋዎቻቸው መሰረት እቃዎች የሚገቡበት ሁኔታ ቢመቻች የበለጠ አገሪቱን ከሚፈጸምባት የኢኮኖሚ አሻጥር ማዳን ይቻላል።
ከዚህ ባሻገር በተለያየ መንገድ ከመንግስት ጋር ቅራኔ ያላቸው አገሮች የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማውጣት መሥራታቸው የንግዱ ዘርፍ እንደመሆኑ፤ ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የፍተሻ ስርዓቱን ጠንካራ ማድረግና በባለሙያዎች መፈተሽ አለበት። የገባው እቃ ከዕቃው ዝርዝር መግለጫ (specification) ጋር ይመሳሰላል ወይ? የገባው በዋጋው ነው ወይ? የሚል አጠቃላይ የመረጃ አያያዝና የፍተሻ ስርዓቱ ሊጠናከር ይገባል።
ሌላው የኢኮኖሚ አሻጥር ወደሚፈጸምበት ወደ ጥቁር ገበያው ስንመጣ ደግሞ፤ ዶላር በጥቁር ገበያው የት ነው የሚሸጠው ሲባል በትልቁ ሁለት ቦታዎች ላይ ነው። አንደኛው በአገር ውስጥ ገበያ ሲሆን፤ ሁለተኛ በውጭ አገር ነው። መጀመሪያ የውጭ አገር ሽያጩን ስንመለከት፤ አሁን ላይ አገሪቱ ከጦርነቱ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ጦርነት እንደተከፈተባት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የውጭ ጥቁር ገበያ ግብይቱ ነው።
ለአብነት ሰሞኑን ዱባይ አንድ ዶላር 74 ብር ገብቶ ነበር። ይህም አርቲፊሻል ወይም ሰው ሰራሽ ጭማሪ ሲሆን፤ ዱባይ 74 ብር ገባ ማለት የአገር ውስጥ ምንዛሬውም 74 ብር ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ የዶላር ምንዛሬ ዋጋውን ከፍ በማድረግ አገር ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ የመሰብሰብ ስራ ይሰራሉ። በዚህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋው ሲጨምር የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ይወርዳል። አገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ይጠፋል ማለት ነው።
ይህ ከሆነ ደግሞ ከውጭ የሚገቡ የህክምናና የፍጆታ እቃዎች ዋጋቸው ይንራል። የነዚህ ዋጋ ጨመረ ማለት ደግሞ ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ ተማሮ ህይወቱን መምራት ሲያቅተው በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያነሳል ማለት ነው። ስለዚህ ውጭ ያሉ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎች ከጦርነቱ ጎን ለጎን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ የኢኮኖሚ አሻጥር መክፈታቸውን የሚያሳይ ነው።
ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ ውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥ የዶላር ምንዛሪው ሲጨምር ከውጭ በርካሽ ዋጋ ዶላር ይገዙና አገር ውስጥ ለቤተሰብ በመላክ በከፍተኛ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ይሸጣሉ። አገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ዋጋው ወደቀ ሲባል ደግሞ አገር ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ በመግዛት ወደ ውጭ ያስወጣሉ።
ይህ የሆነው ደግሞ ማንኛውም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ ሶስት ሺህ ዶላር፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ከሆነ ደግሞ አንድ ሺህ ዶላር ብቻ ይዞ እንዲገባ ስለሚፈቀድ ነው። ነገር ግን ትኩረት ባለመስጠት መንገደኞች ሳይፈተሹ የሚያልፉበት ሁኔታዎች ስላሉ የውጭ ምንዛሪ በኪስ ይዘው ያልፋሉ። ስለዚህ የውጭ ምንዛሪው በመንገደኞች እጅ ይገባና ወደ መደበኛ ገበያው ያለመግባት ሁኔታዎች አሉ። ወደ መደበኛው ገበያ አልገባም ማለት መንግስት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያጋጥመዋል ማለት ነው።
ሌላው በአገሪቱ ላይ ለሚስተዋለው የኢኮኖሚ አሻጥር መገለጫው፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የፍጆታ እቃዎች በጅምላ በግለሰብ እጅ የመያዝ ሁኔታዎች አሉ።
ከማከፋፈያ ወጥቶ ግለሰቦች እጅ ላይ ከገባ በኋላ ዋጋው በእጥፍ የሚጨምርበት ሁኔታ አለ። በዚህም ገበያው በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም በቤተሰብ ትስስር ውስጥ ይገባና ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ሲፈጠር ይስተዋላል። ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚጎዳና ችግሩ በተባባሰ ቁጥር ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ በተቀናጀ መንገድ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ነው የሚያሳየው።
አዲስ ዘመን፡- ይሄን የኢኮኖሚ አሻጥር ከመከላከል አኳያ እንደ መንግስት የችግሩን ምንጭ ለይቶ እርምጃ ከመውሰድ አኳያ ምን እየሰራ ይሆን?
አቶ ሙሉጌታ፡- መንግስት ይህንን የኢኮኖሚ አሻጥር በመታገል በተጨባጭ የሚታይ ስራዎችን በመስራት ላይ ሲሆን፤ በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ የጥቁር ገበያ ምንዛሪዎችን አቅም ለማዳከም የሚያስችሉ ሥራዎችን እየወሰደ ይገኛል። ለምሳሌ በውጭ አገራት ያለውን የጥቁር ገበያ ምንዛሪ በተመለከተ ለተሰራው ስራ ማሳያው ከሰሞኑ ዱባይ ላይ አንድ ዶላር 74 ብር ሲመነዘር የነበረውን ወደ 62 ብር እንዲወርድ አድርጓል። ይሁን እንጂ ይህ ወንጀል በአንድ አካል የሚሰራ አይደለም። በጣም ድብቅ በሆነ መንገድ በባንክ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጭምር ተሳታፊ የሆኑበት ነው። ሆኖም በህገወጥ የውጭ ምንዛሪው ላይ የሚሳተፉ አይነኬ የተባሉ ሰዎች እየተነኩ ነው። ከማን ጋር ኔትወርክ እንዳላቸውም የማጥራት ስራ በጥልቀት እየተሰራ ነው። ባንክ አካባቢ ላይም በቀጣይ በስፋት መፈተሽ የሚገባቸው ነገሮች ስላሉ ባንክ ላይ በስፋት ይሰራል።
በአገር ውስጥም ዶላር በጥቁር ገበያው በስፋት የሚሸጥ ሲሆን፤ ብሄራዊ ባንክ ፊት ለፊትና ስቴዲየም አካባቢ ያሉ ሱቆች ፊት ለፊታቸው ውስኪ ደርድረው ከመጋረጃ ጀርባ ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ስራ ነው የሚያከናውኑት። በአገር ውስጥ በተለያየ መንገድ ከጥቁር ገበያው የሚሰበሰበው ዶላርም በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ ድንበር ላይ ወደምትገኝው ወደ ቶጎ ውጫሌ ነው የሚጓጓዘው።
ለምንድነው ወደ ቶጎ ውጫሌ የሚጓጓዘው? ሲባል፤ ቶጎ ውጫሌ ላይ የድንበር ንግድ አለ። በዚያ አካባቢ የሱማሌ ላንድ ነጋዴዎች አሉ። እነዚህ ነጋዴዎች ከአገራቸው ምንም አይነት የውጭ ምንዛሪ ይዘው አይመጡም። በአገር ውስጥ በጥቁር ገበያው የተሰበሰበው ዶላር ወደ ሱማሌ ላንድ ወዳሉ ነጋዴዎች ያልፍና እንደገና እነዚህ ነጋዴዎች በዶላር ግዥ እንደፈጽሙ ተደርጎ ይዘውት የመጡት የውጭ ምንዛሪ ነው ተብሎ ተመልሶ ወደ ባንክ ይገባል። ስለዚህ በቶጎ ውጫሌ የሚገኙ 16 ባንኮች የሚሰሩት ይሄንን ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ እየተሰበሰበ ድንበር ላይ የሚሸጠው አጠቃላይ ወደ መንግስት ካዝና ውስጥ የውጭ ምንዛሪው እንዳይገባ የሚደረግ የኢኮኖሚ አሻጥር ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪው ህጋዊ የፋይናንስ ስርዓቱ ባጣ ቁጥር ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ማስመጫ ያጣሉ። በዚህም ፋብሪካዎች ይቆማሉ፤ ሰራተኞችም ይበተናሉ። ይሄ ደግሞ ስራ አጥነትን ይፈጥራል። ስለዚህ አስመጪና ላኪዎች ባንክ ላይ የውጭ ምንዛሪ ባጡ ቁጥር ወደ ህገወጥ ገበያው የመሄድ አዝማሚያዎች አሉ። በመሆኑም ጥቁር ገበያው በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የአገራችን አንገብጋቢ ችግር ነው።
ስለዚህ ከለውጡ በፊት የጥቁር ገበያው ተዋናዮች ውጭ ያሉት ናቸው በሚል የአገር ውስጥ ቁጥጥሩ የላላ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ አገር ውስጥ ያሉ አቀባባዮች ላይ በሰፊው ቁጥጥር በመደረጉ ከሰሞኑ በሚዲያዎች እንደተነገረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጭ ምንዛሪና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ በህግወጥ መንገድ የተከማቹ እንደ ብረት ወዘተ የመሳሰሉ የግንባታ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ከዚህ አኳያ የደህንነትና የቁጥጥር ስራው በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን:-የኢኮኖሚ አሻጥሩ ተዋናዮች እነማንናቸው? ወደዚህ ተግባርስ እንዴትና መቼ እንደገቡ የታወቀ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ሙሉጌታ:- የኢኮኖሚ አሻጥር የተቀናጀ ወንጀል ነው። የኢኮኖሚ አሻጥሩ ላይ ሻጭና ገዥ፣ አስመጪና ላኪዎች፣ ህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እንዲሁም የመንግስት አካላት ጭምር ተቀናጅተው ነው የሚሰሩት። ለአብነት ከለውጡ በፊት አስመጪዎች ከህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተመሳጥረው አባዱላ መኪና በመቶ ዶላር ያስገቡ ነበር። ይህንንም የሚያደርጉት አገር ውስጥ በብር ከከፈሉ በኋላ ቀሪ የውጭ ምንዛሪ የሚሰጡት ውጭ ላይ ተሰብስቦ ነበር።
ሌላው መንግስት ተረጋግቶ አገር እንዳይመራ የተቀናጀ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ ተጻራሪ ኃይሎች አሉ። ከዚህ አኳያ አሁን ላይ በአገሪቱ የሚታየው ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ተዋናዩ አሸባሪው ህወሓት ነው። ምክንያቱም ይህ የሽብር ቡድን ከጦርነቱ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ጦርነት በመክፈት ህዝቡ ኑሮ እንዲመረውና በኑሮው ተማሮ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ እና መንግስት ህዝባዊ ድጋፍ አጥቶ በጦርነቱ ተሸናፊ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ ነው።
ከዚህ ባሻገር “ጠግቤ ካልተፋሁ” የሚል ለአገርና ለህዝብ ደንታ የሌለው ስግብግብ ነጋዴም ፍላጎት አለ። እንዲሁም ከባንኮችም በግለሰብ ደረጃ ለኢኮኖሚ አሻጥሩ ተባባሪ የሆኑ አሉ። በተጨማሪ በግልጽ እገሌ ብሎ ለጊዜው ስማቸውን መጥቀስ ባይቻልም ትልልቅ ታዋቂ ሰዎችና ባለስልጣናት በዚህ ላይ ተሳታፊ ናቸው። እነዚህን አካላት ለይቶ ለማውጣት መመሪያ ሊያስፈልገው ይችላል። በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱ አካላት በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ የሚፈጽሙት ወንጀል ነው።
ከዚህ ባሻገር ከጨረታና ከተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክት ስራዎችን ለማከናወን ከሚገቡ የተለያዩ ካምፓኒዎች ጋር ተያይዞ ትልልቅ ድራማቲክ የሆኑ ስራዎች ይሰራሉ። ለአብነት ከለውጡ በፊት ገቢዎች ላይ የነበረውን አሰራር ብናነሳ አረንጓዴ፣ ቀይና ቢጫ ተብሎ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች የሚሰጥ ኮድ አለ። አረንጓዴ የማይፈተሹ፣ ቢጫ የሚፈተሹ እና ቀዩ ደግሞ የሚጠረጠሩና ከፍተኛ ፍተሻ የሚደረግባቸው እቃዎች ናቸው።
ስለዚህ ከለውጡ በፊት በነበረው አሰራር ዲፕሎማቶች የሚያስገቡት እቃ አረንጓዴ የሚል ኮድ ያለው ሲሆን፤ እቃ ከውጭ ሲያስገቡም ሲያስወጡም አያስፈትሹም። በዚህም የማይፈተሹ የሚባሉ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አሟጠው ይዘው የሚወጡበት እና ከውጭም የማይፈተሽ እቃ ይዘው የሚገቡበት ሁኔታዎች ነበር። ይህም አገሪቱን ተባብረው የሚመዘብሩበት አሰራር ነበር። አሁን በውጭ አሸባሪው ህወሓት ተነካ ብለው የሚንጫጩት ምዕራባውያንና አሜሪካ በግልጽ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አብረው የነገዱ አካላት ናቸው።
አጠቃላይ ህወሓት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥሮ ያሻውን ያደርግ የነበረ ቡድን ነው። በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ ስልጣን ልናጣ እንችላለን በሚል የአገሪቱ ሃብት በግለሰቦች እጅ ገብቶ ያልተረጋጋ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት በአገሪቱ እየተስተዋለ ይገኛል። በዚህም የውጭ ንግድም ሆነ የአገር ውስጥ ንግዶች በግለሰቦች ተይዘው አሁን ድረስ በአገሪቱ ላይ የተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ።
አዲስ ዘመን:-የኢኮኖሚ አሻጥሩ በአገርና በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳትና ኪሳራ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሙሉጌታ:- ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ከዋጋቸው በላይ በተጋነነ ዋጋ ወይም ከዋጋቸው በታች በወረደ ዋጋ ማስገባት በጉምሩክ አዋጁ 859 ወንጀል ተደርጎ አልተቀመጠም። ይህም አገሪቱ ማግኝት የሚገባትን ታክስ እንዳታገኝ ከማድረጉ ባሻገር ከፍተኛ ካፒታል ወደ ውጭ እንዲወጣ መንገድ ከፍቷል።
በዚህ የህግ ክፍተት ምክንያት ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ከዋጋቸው በላይ በተጋነነ ዋጋ ገባ ማለት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ይወጣል። ለአብነት እቃው የሚያወጣው ወይም የተገዛበት ዋጋ 20 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ እያለ ነገር ግን የግዥ ፋይሉ 50 ሚሊዮን ዶላር ተብሎ ተጽፎ ወደ አገር ውስጥ ይገባል። በዚህ ስራ ላይ የተደራጁ ሰዎች የ20 ሚሊዮኑን እቃ የ50 ሚሊዮኑን ዶላር ብለው ሁለተኛ ደረጃውን ወይም አሮጌውን ዕቃ ይልካሉ። ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ስርአታቸው ደካማ የሆኑ እንደነ ዱባይና ቻይና የመሳሰሉ ለዚህ መሰሉ የኢኮኖሚ አሻጥር ምቹ ናቸው። በዚህም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ከመውጣቱ ባለፈ የሚገባው እቃ ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ አገሪቱን ለኪሳራ ይዳርጋታል።
ዕቃውም አገር ቤት ከገባ በኋላ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ሳይሰጥ ለብልሽት ስለሚዳረግ ፋብሪካው ስራውን ያቆማል። ፋብሪካው ስራ አቆመ ማለት የሚጠበቅበትን ታክስ አይከፍልም ማለት ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱ ማግኝት የሚገባትን ግብር እንዳታገኝ ከማድረጉ ባሻገር ስራ አጥነትን የሚያስፋፋ ነው። አገርን በታክስ ድርቅ የሚመታበትና ያለንን ዶላር ወደ ውጭ የሚወጣበት ሁኔታ የሚፈጥር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ የምትልከው ምርት ከዋጋ በታች ይላክና ማግኝት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን:- የኢኮኖሚ አሻጥር ዓለማቀፋዊ ገጽታው እና በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ነገር ቀደም ሲል በኢኮኖሚ አሻጥር ተጽዕኖ ካደረባቸው አገራት ልምድ አንጻር ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉጌታ:- የታወቀ ነው፤ ብዙ ጊዜ ሁከትና ብጥብጥ የሚነሳባቸው አገሮች የኢኮኖሚ አሻጥር ያለባቸው አገሮች ናቸው። የወንጀለኛ የመጨረሻ ግቡ አገር ማፍረስ ነው። የወንጀለኛ ግቡ መንግስትን መቆጣጠር ነው። በፈለገው አቅጣጫ ገንዘብ እየበተነ አገርን ያፈርሳል። በትልልቅ የወንጀል ጉዳዮች የተዘፈቁ ሰዎች የተረጋጋ አገር አይፈልጉም።
ለአብነት በሱዳን በአስር ሳንቲም የዳቦ ጭማሪ የተነሳው ቀውስ ለሶስት አስር ዓመታት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩትን አልበሽር ከዙፋናቸው ገሸሽ እንዲሉ አድርጓል። እንዲሁም የአርጀንቲና መንግስት እኤአ በ2001 አገሪቱ ላይ ብድር ከመብዛቱ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጋጥሞት ነበር። በዚህም በወቅቱ የነበሩት የአገሪቱ መንግስት በተሰራባቸው የኢኮኖሚ አሻጥር አገሪቱን መምራት ተስኗቸው ስልጣን ተቀበሉኝ እስከማለት ደርሰው ነበር።
ስለዚህ አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተሰራባት ካለው የኢኮኖሚ አሻጥር አኳያ የተከፈተባት ጦርነት ቀላል ነው ማለት ይቻላል። አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲገጥማት በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ነው። መንግስት የውጭ ምንዛሪ ካጣ ሌላው ቀርቶ መድሃኒት ለማስገባት ይቸገራል። ይህ ከሆነ ደግሞ አገሪቱን እንደ አገር ለማስቀጠል መንግስት ይቸገራል።
በተለይ ምዕራባውያንና አሜሪካ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸውን አሻንጉሊት መንግስት ነው የሚፈልጉት። ይህንን አርቲፊሻል መንግስት ባጡ ጊዜ ወይም የነርሱን ጥቅም የማያስጠብቅና የእነርሱን ሃሳብ የማይቀበል መንግስት ከሆነ የሚፈልጉትን አሻንጉሊት መንግስት ለማቋቋም በኢኮኖሚ አሻጥር አሻፈረኝ ያለውን መንግስት የሚያዳክሙበት ስርዓት አለ። በዚህም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አገሮች በሚያደርጉት የኢኮኖሚ አሻጥር ብዙ አገሮች ፈርሰዋል። ስለዚህ ከተለያዩ ከፈረሱ አገሮች ጀርባ የኢኮኖሚ አሻጥር መኖሩ ቁልጭ ብሎ የታየባቸው አገሮች አሉ።
ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ምዕራባውያንና አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት ከፍተውብናል። አሜሪካ በግልጽ በአገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥላለች። ስለዚህ አገሪቱ በውጭ አገር ያሏትን አካውንት እንዳታንቀሳቅስ ከተቆለፈ ዕቃ መግዛት የማትችልበት ደረጃ ነው የምትደርሰው። ስለዚህ ምዕራባውያንና አሜሪካ ተላላኪያቸውን አሸባሪውን ህወሓትን ወደ ስልጣን ለመመለስ በግልጽ በአገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር ከፍተዋል።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት ጭምር እንደከፈተ ይነገራል። በዚህ መልኩ አሸባሪው ቡድን የኢኮኖሚ ጦርነት ለመክፈቱ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ሙሉጌታ:- ለአብነት፣ አሁን ያለው የዶላር ጭማሪ ፍጥነት ሰሞኑን ዱባይ አንድ ዶላር በኢትዮጵያ ብር 74 ብር ተመነዝሯል። ዱባይ ላይ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ሰፊ የሆነ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች ቢዝነስ ወይም ንግድ የከፈቱበት ቦታ ነው። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ላይ ያሉ ንብረቶቻቸውን ሽጠው ዱባይ ላይ ዶላር በከፍተኛ ብር ይመነዝራሉ። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ወደውጭ በማስወጣት አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲያጋጥማት የሚደረግ ሴራ ነው። ስለዚህ ዱባይ ላይ በተሰራው የኢኮኖሚ አሻጥር በተመሳሳይ በአገር ውስጥም አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ እስከ 74 ብር ምንዛሪ የገባበት ሁኔታ ነበር። መንግስት ይህንን ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ አሁን ላይ ወደ 62 ብር እንዲወርድ ተደርጓል።
ሌላኛው ደግሞ ጥቁር ገበያው ላይ ያለውን ዶላር ጠርጎ የመግዛት ነው። ይህ ደግሞ አገር ውስጥ ያሉ የአሸባሪው ቅጥረኞች የዶላር ምንዛሪ እንዲጨምር አርቲፊሻል ግዥ መፍጠር ስራ ሲሰሩ ይስተዋላል። በዚህም የዶላር ዋጋ ከጨመረ አስመጪዎች እቃን በዶላር ገዝተው የሚያስገቡ እንደመሆኑ አገር ውስጥ የምርት ዋጋ እንዲንር ያደርጋል። የአገሪቱ ብርም የመግዛት አቅሙ ወርዶ እንዲወድቅ የማድረግ ሁኔታዎች አሉ።
ከዚህ ባሻገር ከዚህ ቀደም በተለያየ መንገድ የግንባታ ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ ገብተዋል። ለአብነት በአፋር ክልል ዞን ሁለት አካባቢ ወደ 50 የሚጠጉ ሆቴል ለመክፈት ተብሎ ከቀረጥ ነጻ የገባ ብረትና ልዩ ልዩ የግንባታ ዕቃዎች ነበር። ነገር ግን በዛ አካባቢ አንድም ሆቴል አልተከፈተም። ስለዚህ በተለያየ ቦታ ለተለያየ ግንባታ ተብሎ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ብረቶች አሉ። እነዚህ የግንባታ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ከቀረጥ ነጻ ከገቡ በኋላ እነዛን ምርቶች የመቸርቸር ሁኔታዎች አሉ። ለአብነት፣ ብረት አዲስ አበባ ጠፍቶ ከትግራይ ሲመጣ እንደነበር ይታወሳል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በተለያየ መንገድ ከጦርነቱ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ጦርነት መክፈታቸውን የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪው ህወሓት በዚህ ወቅት የኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ የገባበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ሙሉጌታ:- አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት ከጦርነቱ ጎን ለጎን በአገሪቱ የኢኮኖሚ ጦርነት የከፈተው ሌላ ሚስጥር የለውም፤ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ነው። ከአቅርቦትና ከፍላጎት አለመጣጣም ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚታይ የዋጋ ንረት ቢኖርም፤ አሁን በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ወድነትና የዋጋ ንረት ሰው ሰራሽ ነው።
ምክንያቱም አሸባሪው ህወሓት ህዝቡ መንግስትን እንደደገፈው ስላወቀ የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት ህዝብና መንግስትን ሆድና ጀርባ በማድረግ የህዝብ ድጋፍ ለማሳጣት ነው። በጥቅሉ ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነቱ ተበሳጭቶ ህዝብ በመንግሰት ላይ እንዲነሳ ነው። በዚህም አሸባሪው ህወሓት ፊት ለፊት ከሚያደርገው ጦርነት ጎን ለጎን በተለያየ መንገድ የኢኮኖሚ ጦርነቱን እያጧጧፈ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የጥቁር ገበያው መናር በገበያው ላይ እያሳደረ ያለውን ተጨባጨ ተጽዕኖ ቢያስረዱን?
አቶ ሙሉጌታ፡- የጥቁር ገበያው እንደሚታየው ነው። አሁን በአጠቃላይ የምናደርጋቸው ግብይቶች በሙሉ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ባንክ ላይ የውጭ ምንዛሪ ከሌለ ወጪና ገቢ ንግዱ (ኢንፖርት ኤክስፖርት) ምንም መስራት አይቻልም። ስለዚህ በጥቁር ገበያው ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ዝውውሩ ከመደበኛ ግንኙነቱ ወደ ኢመደበኛ ግንኙነቱ ካጋደለ ህጋዊ የፋይናንስ ስርዓቱ የገንዘብ እጥረት ያጋጥመዋል። በህጋዊ የፋይናንስ ስርአቱ ውስጥ የገንዘብ እጥረት አጋጠመ ማለት ደግሞ የእጥረቱ ዳፋ እስከ ህክምና እቃዎች እጥረት ማስከተል ድረስ ሊሄድ ይችላል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የምታመርተው ነዳጅ የላትም። ነዳጅ ከውጭ የሚገባው በውጭ ምንዛሪ ነው፤ እናም የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ ነዳጅ አልገባም ማለት ደግሞ መንቀሳቀሻ መኪና እንኳን ይጠፋል ማለት ነው። ባለፋብሪካዎችም ለፋብሪካቸው የሚሆን ጥሬ እቃ በሙሉ ሀገር ውስጥ አያገኙም። እናም የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ ጥሬ እቃ ማስገባት ካልቻሉ እና ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ ካላገኙ ፋብሪካው ስራ አቆመ ማለት ነው።
ይህ ፋብሪካ ስራ ሲያቆም ደግሞ ስራ አጥ ተፈጠረ ማለት ነው። ስራ አጥ ተፈጠረ ማለት ደግሞ አመፅ ተፈጠረ ማለት ነው። ችግሩ በዚህ መልኩ አንዱ ከአንዱ ጋር እየተሳሰረ የሚሰፋ፤ ተጽዕኖውም በዛው ልክ እያደገ የሚሄድ ነው። ስለዚህ የኢኮኖሚ አሻጥር እያደረጉ ያሉት ኃይላት በፊዚካል ጦርነት ተዋግተው ከማስወገድ ይልቅ ቀላል በሆነው መንገድ በኢኮኖሚ ጦርነት ለማስወገድ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ሰን ሰለት ድንበር ተሻጋሪ ባህሪው ለአሸባሪው ህወሓት እኩይ ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል። ይህ ከኢትዮጵያ አንጻር እንዴት የሚገለጽ ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ ተግባሩ አለም አቀፍ ወንጀል ነው። በመሆኑም በዚህ መልኩ ከኢትዮጵያ ቀድሞ የወጣ ገንዘብ አለ ካልን፤ አንደኛ፣ እነኛ ገንዘቦች እንዴት አድርገን እናስመልሳቸው የሚል ሂሳብ መስራት ይኖርብናል። በሁለተኛ፣ ከውስጥ ያሉትን ህገወጦች እንዴት እናጥፋ እና እናዳክም የሚል ስራ ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ፣ ከውጭ ያሉ የሽብር ቡድኑ ሰዎች ቀደም ብለው ከሀገር ባስወጡት ገንዘብ አሁን ላይ ለፕሮፓጋንዳ የውጭ ሚዲያዎችን ለመግዛት እየተጠቀሙበት ነው። ምክንያቱም የውጭ ዲፕሎማሲውን በገንዘብ ነው የምታሸንፈው። አክቲቪስቱንም የምትገዛው በገንዘብ ነው።
እነዚህ አካላት ቀድሞ ያስወጡትንና የዘረፉትን ገንዘብ ተጠቅመው በተለያዩ ሪሚታንስ ኤጀንቶች ወደ ሀገር እየላኩ ለተለያዩ ሽብር ማስፈጸሚያነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የውጭ ገንዘቦች በባንክ በኩል ወደ ትግራይ ይሄዱ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አገሪቱ ሲፈጠሩ የነበሩ ረብሻዎች በሪሚታንስ በመጡ ገንዘቦች ድጋፍ የሚፈጠሩ ናቸው።
በሪሚታንስ የገንዘብ ማዘዋወሪያዎችን ተጠቅሞ ማንም ሰው ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ገንዘብ ይልካል። ለአንድ ሰው ተልኮ ሀገር ውስጥ ላሉ ሰዎች ሊበተን ይችላል። እነዚህ እንዳጠቃላይ የሽብርተኛውን ፍላጎት በተፈለገው መንገድ የማሳደግ ባህሪ አላቸው። አሁንም ሀገር ውስጥም ለሚፈልጉት የኢኮኖሚ አሻጥሮች ይጠቀምባቸዋል። ከዚህ አንጻር ለሽብርተኛው ቡድን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ትልቁ ጦርነት የኢኮኖሚ አሻጥር ነው። በውጭ ሀገር ባለ ገንዘብህ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በማሳደግ ሀገር ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በማናር የሚፈጸም ውጊያ ነው። የዶላር ምንዛሪህ እየጨመረ ከመጣ አገራዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ይጨምራል። ብር ደግሞ የመግዛት አቅሙ ይቀንሳል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በመንግስት እና ህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እየሰፋ ይመጣ እና አሸባሪው ቡድን የፖለቲካ እና የፕሮፓጋንዳ የበላይነት የሚያገኙበት ሁኔታዎች ይፈጠራል።
ከዚህ በፊት በቶጎ ውጫሌ የነበረውን የኢኮኖሚክ አሻጥሩን ብንመለከት ትልልቅ ጀኔራሎች ከአብዲ ኢሌ ጋር በመተባበር ህገወጥ ንግድ ሲያከናውኑ ስለነበር፤ ቶጎ ውጫሌ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ትልልቅ ንግድ የነበረበት ቀጠና ነበር። በዚህ ረገድ አካባቢው ሲሰራበት የከረመ የአሸባሪው ህወሓት ብዙ ሰዎች የተቋቋሙበት እና ብዙ ሰዎች የከበሩበት አካባቢ ነው። እነኚህ አካላት አሁንም በውስጥም በውጭም ሆነው ያን አካል ይደግፉታል ተብሎ ይገመታል። ምክንያቱም በፖለቲካም ሆነ በሌላ ጥቅም የተሳሰሩ ስለሆኑ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለመከላከል በተለይ ለውጡ ከመጣ ወዲህ ምን ተሰራ? ምን ተጨባጭ ውጤትስ መጣ?
አቶ ሙሉጌታ፡- የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ወንጀለኛ ላይ ብቻ የምታቆመው አይደለም፤ ተከታትሎ ማሳደድ ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ዶላር ዘርዛሪዎችን በማሰር ብቻ ብዙ ላይፈታ ይችላል። የዚህ ሁሉ ዋና ተዋናዩን (master mind) መያዝ ያስፈልጋል ።
ይሄን ከማድረግ አንጻር ግን በቶጎ ውጫሌ አካባቢ ላይ የድንበር ንግዱን ለመቆጣጠር በጥብቅ አልተሰራም። ለምሳሌ፣ አድቫንስ ፔይመንት እንዴት ይከፈላል? እዚህ ላይ የንግድ ሚኒስቴር እና የተለያዩ አካላት ሚናቸው ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎችንም ጉዳዮች ማየት ይቻላል። ሆኖም በአካባቢው የንግድ ስርዓቱ መልክ የሚይዝበት አሰራር አልነበረም።
አሁን ግን መንግስት አንድ ትልቅ ስራ ሰርቷል። ለምሳሌ ብሄራዊ ባንክ ሰሞኑን ያወጣው አንድ ሰው በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ገንዘብ ማስተላለፍ አይችልም የሚል ነው። ለምን ሆነ? የሚለውን መያዝ ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው የቁጠባ ደብተር ይከፍታል። የቁጠባ ሂሳብ ከከፈተ በኋላ ግለሰቡ በቀን አንድ ሺህ ጊዜ የገንዘብ ልውውጥ ሲያደርግ ይስተዋላል። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው እነኘህ በቀን አንድ ሺህ ጊዜ የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ሰዎች ህገ ወጥ የሃዋላ አገልግሎት የሚሰሩ ናቸው።
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የሚሰሩ ሰዎች ምንድን ነው የሚሰሩት? እንዴት በዚህ ልክ ሊሰሩ ቻሉ? የሚሉት ደግሞ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ፣ በውጭ ሀገር ዶላር ይሰበሰባል፤ ሀገር ውስጥ ደግሞ በብር ይከፈላል። ይሄ ደግሞ በውጭ ያሉ አካላት የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ የፋይናንስ ስርኣት ውስጥ እንዳይልኩ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው የዶላር መወደድ ዋነኛው ምክንያት ነው። ይህን ህገወጥ አካሄድ ለማስቆም እስከ ተርሚኔሽን የሚደርስ እርምጃ መውሰድ ስለሚያስፈልግ፤ ህገ ወጥ ሃዋላን ለማስቆም በሰፊው እየሰራን ነው። በሰፊው በመስራታችንም ሰዎችን እየያዘን ነው።
ነገር ግን የሚያዙት ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ኤጀንት ናቸው። ዋናው አስመጪውን ግን አታገኘውም። አይታይም። ምክንያቱም ዶላሩ የሚሰበሰበው ውጭ ሀገር ነው። እዚያ ሂደህ አታስረውም። እዚህ በካሽ የሚከፍለውን ግን ታገኘዋለህ። እነኝህን ደግሞ የሚያሰሯቸው ሰዎች አሉ። ይህን ስራ የሚያሰሩአቸው ደግሞ ትልቅ አስመጭዎች እና ባለሃብቶች ናቸው። አሁን ላይ በሀገሪቱ በጥቁር ገበያ ሊለውጡ የሚመጡ ሰዎች ግን ኤጀንት ናቸው። ዋናውን አታየውም። እናም የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በባህሪው ዋናውን ሰው ካልያዝክ ትቸገራለህ።
ይህን የህገወጥ ምንዛሪ የሚያካሂዱ ሰዎች በሚሊዮን የሚቀያየሩበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ነገሮች ግን አጠቃላይ ለማቆም እና ለመያዝ ዋናውን ወንጀለኛው ሳይገኝ ሲቀር ለብሄራዊ ባንክ ለትንተና እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ መልኩም ለብሄራዊ ባንክ ህግ እንዲያወጣባቸው በግብዓትነት ተሰጥተዋል። ከዚህ በመነሳት ብሄራዊ ባንክ የህግ አቅጣጫ አስቀምጦላቸዋል። በአቅጣጫው መሰረትም አንደኛ፣ በሚሊዮን የአካውንት የሚያንቀሳቅሱ ሰዎችን በብሄራዊ ባንክ በተወሰደ እርምጃ በኢትዮጵያ ውስጥ መስራት እንዳይችሉ ተደርጓል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ሰዓት ወደ 74 የሚደርሱ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ባሉ ባንኮች ውስጥ ማንኛውም አይነት ግልጋሎት እንዳያገኙ ተደርጓል። ሁለተኛ ደግሞ የፋይናንስ ደህንነት ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ግለሰቦች ሂሳባቸውን ፍሪዝ በማድረግ ሰዎቹ በህግ እንዲጠየቁ እና ሃብታቸው እንዲወረስ ለማድርግ ክሳቸው ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተልኳል።
ስለዚህ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው አቅጣጫ መሰረት ሳምንታዊ የገንዘብ ዝውውር ድግግሞሽን በሚመለከት “weekly multiple cash transfer” በሚል እንደ አቅጣጫ ሁኖ በመቀመጡ አንድ ሰው በአንድ ሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ መላክ አይችልም። ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ዝግ አይደለም።
ችግሩን ከመከላከል አኳያ የለውጡ መንግስትን የሚያስመሰግነው ሌላው ነገር የገንዘብ ቅያሪው እና ከገንዘብ ቅያሪው ጋር ተያይዞ የመጡት አሰራሮች ናቸው። የብር ቅያሪው በብዙ መንገድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ጥቅም ይዞ መጥቷል። አንደኛ፣ ከብር ቅያሪው በፊት በፋይናንስ ተቋማት ላይ የገንዘብ እጥረት ነበር። ባንኮች የማበደር አቅማቸው ወድቆ ነበር። የአስቀማጮቻቸውን ገንዘብ አንኳን መክፈል አቅቷቸው ነበር። ነገር ግን ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው መያዝ ያለበት ገንዘብ እስከምን ድረስ ነው? በሚለው ላይ አቅታጫ ተቀምጦ ስለነበር በሰዎች የሚዘዋወር እና ሊይዙት የሚገባው የብር መጠን ገደብ ሲበጀትለት በጥቁር ገበያ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። ይሄ ደግሞ ሊደረስበት የማይችለውን (አንትሬሲቭል ካሽ) የጥሬ ገንዘብ ዝውውር መገደብ ችሏል።
ሀገራትን የሚጥለው የጥሬ ገንዘብ ግብይት ነው። በህጋዊ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ገንዘብን በማንቀሳቀስ ወንጀል ቢሰራ እንኳን የወንጀሉን ተዋናይ በቀላሉ ማግኘት ወይም በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻላል። ከዚህ አንጻር የብሄራዊ ባንክ ከፋይናንስ ደህነነት ማዕክል ጋር በመሆን እየሰራበት ነው። አሁን ባለው ሁኔታም እስከ ቶጎ ውጫሌ ድረስ ለመስራት እያሰብን ነው።
ለምሳሌ፣ ህጋዊ የንግድ ፈቃድ ያወጡ እና ጫት ኤክስፖርት እናደርጋለን የሚሉ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ከጫት ኤክስፖርት ብዛት ያለው የውጭ ምንዛሪ ተገኘ የሚባለው ጋር በተገናኘ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር አለ። ይህም ዶላር ከእኛ ሀገር ለሶማሊያ ህገወጥ የዶላር አዘዋዋሪዎች በድብቅ ይሸጣል። ሶማሊያዎች ደግሞ ከእኛ ሀገር ያገኙትን ዶላር አዙረው ትርፍ አትርፈው ለእኛ የጫት ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ይሸጡታል። ገንዘቡም ተመልሶ ወደ እኛ ሀገር ባነኮች እንዲገባ ይደረጋል። እዚህ ላይ የሚያተርፉት ህገወጦች ናቸው። ይህ ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። በዚህ ረገድ የጥቁር ገበያው የኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ የሚወሰነው ሶማሊ ላንድ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለውጡ ከመጣ በኋላ እንዲሁም ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው ሲገባ የኢኮኖሚ አሻጥር እንደሚፈጠር ይጠበቃል። ይህንን ቀድሞ ተረድቶ የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመከላከል ከጅምሩ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል? ምንስ ውጤት ተገኝቷል?
አቶ ሙሉጌታ ፡-የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቆጣጠር ሰርዓት ማበጀት በጣም ጠቀሜታ አለው። በስርኣት የሚመራ የንግድ ስርዓት መፍጠር ተገቢ ነው። ምክንያቱም በሃብታም እና በድሃው መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፍቷል። የሰፋን ነገር ደግሞ ለማጥበብ ትቸገራለህ። በአንድ ጊዜም አይመጣም።በሌላ በኩል፣ አሁን ላይ ነጻ ገበያው በሀገራችን የለም። ምክንያቱም ምርቶች ለተወሰኑ ሰዎች ይሰጣል። እነኝህ የተወሰኑ ሰዎች በተወሰኑ ደላሎች አማካኝነት በፈለጉት ዋጋ የሚቸበችቡበት ስርዓት ነው ያለው። ይህን ለማፍረስ ጊዜ ይፈልጋል። ሞኖፖሊ አቅም ያላቸውን ሃይሎች እያፈረሱ መምጣትን ይጠበቃል። እነኝህ ደግሞ በቀላል አታፈርሳቸውም። ምክንያቱም የግንኙነት መረባቸው በጣም ሰፊ ነው። አሁን ላይ አንተንም ሊያጠፉህ ይችላሉ። በትልቅ ገንዘብም ሊገዙህ ይችላሉ።
ለውጡ እንደመጣ አካባቢ የዶላር ዋጋ እጅግ የቀነሰበት ሁኔታ ነበር። የውጭ ምንዛሪያቸውንም ወደ ባንክ በመሄድ የሚመነዝሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን እነኝህ ኢኮኖሚውን በሞኖፖል የያዙ ሰዎች ሁኔታውን ወዲያውኑ ቀየሩት። ይህንን የጋንግስተር ቡድን ለማስቆም መንግስት የተረጋጋ ጊዜ ያስፈልገዋል።
የለውጡ መንግስት ከመጣ ጀምሮ አሸባሪው ህወሓት እና ተባባሪዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት ሲከፍቱ ነው የኖሩት። በዚህም መንግስት እነኝህ ጋንግስተሮች ለመቆጣጠር ጊዜ የማጣት ነገር አለ። መንግስት እኮ የእፎይታ ጊዜ አግኝቶ ይህን ቡድን የሚያፈርስበት እድል አልተሰጠውም። እንደአጠቃላይ ግን እነኝህን ጋንግስተሮች ለመቆጣጠር በብሔራዊ ባንክ እና በፋይናንስ ማእከል የተሰሩ በርካታ ስራዎች አሉ።
አዲስ ዘመን ፡– እንደአጠቃላይ በሀገሪቱ እየተከናወነ ላለው የኢኮኖሚ አሻጥር ዘላቂ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ሙሉጌታ፡– አንደኛው ህብረተሰቡ ህጋዊ የፋይናንስ ተቋማት አለመጠቀም የራሱ የሆነ አደገኛ ውጤቶች እንዳሉት ተገንዝቦ ህጋዊ የፋይናንስ ተቋማትን መጠቀም መቻል ነው። ይህ ሲሆን በጥቁር ገበያ ዶላር በሚሸጥበት ሁኔታ እና በሚገዛበት ሰዓት ዶላሮች ፎርጅድ የመሆን ባህሪ እንዳላቸውም አውቆ ለመጠንቀቅና ራስንም አገርንም ከችግር መታደግ ይቻላል።
ህግ ማስከበር ብቻውን እንደሀገር ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎም መወሰድ የለበትም። አይደለምም። በመሆኑም አንደኛ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ በባላንስ ኦፍ ፔይመንት በኢምፖርት ኤክስፖርት ላይ መስራት ያስፈልጋል። በዚህም መንግስት የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ማሳደግ ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር አንዳንድ የቅንጦት እቃዎች ወደ ሀገር የማስገባቱ ነገር የሚቀንስባቸው አሰራሮችን መፍጠር ያስፈልጋል።
ሌላው በአረብ ሀገር የሚገኙ ወገኖቻችን ህጋዊ የፋይናንስ ስርዓቱን የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። በአረብ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖቻችን እድሉን እያገኙ ባለመሆናቸው ደግሞ ገንዘባቸውን በህገ ወጦች ሲያዘዋውሩ ተመልክተናል። ስለዚህ ለእነዚህ ወገኖቻችን ህጋዊ የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ፈቅደውና ጊዜዎትን ሰውተው ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን!
አቶ ሙሉጌታ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
በሰሎሞን በየነ እና በሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013