ነገሩ “እሳት አመድ ወለደ” እንዲሉት አይነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ምስረታ እና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ በመቆየቷ ሂደት ጉልህ ሚና የነበረው የትግራይ ህዝብ፤ እሳት ሆኖ ዳር ድንበሩን እንዳልጠበቀ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ እንዳልከፈለ፤ ዛሬ ላይ ከእሳት አመድ እንደሚወለድ ሁሉ፤ ከአገር ወዳዱና ደግ ኢትዮጵያዊ ከሆነው የትግራይ ህዝብ መሃል አመድ ወጥቶ አገር እያመሰ፤ ወገን እያረደና እየጨፈጨፈ ይገኛል፡፡
አገር ያጸና ህዝብ አገር አፍራሽ ልጅ ያየበት፤ ወገን ጠባቂው ህዝብ ወገኑን አራጅና ጨፍጫፊ ያፈራበት፤ ታሪክ የጻፈ ህዝብ ታሪክ አጉዳፊ ከጉያው ያበቀለበት ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ እናም ከስንዴ መሃል እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ፤ ከዚህ ህዝብ መሃል ህወሓት የሚባል አሸባሪና አገር ሻጭ ቡድን ተወልዶ፤ ኢትዮጵያውያንን በየቦታው እያረደና እየጨፈጨፈ የጭካኔውን ጥግ ሲያሳይ፤ ህዝብን ገድሎ አገር የማፍረስ ጥማቱን ለማርካት መልሶ የትግራይን ህዝብ ልጆች ዳግም እየበላ ይገኛል፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን ቀድሞ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት፤ ሀብቱም፣ ቴክኖሎጂውም፣ ስልጣኑና ሁሉም ነገር ያለው ስለነበር፤ አገር የማፍረስ፣ ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፍሎ በማባላት የደም ጥማቱን የሚወጣው ሀብትና ስልጣኑ በሰጡት አቅም ቅጥረኞችን እየገዛ ነበር፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ሸኔ የተባለ ተላላኪ ሰይሞ፣ በቡራዩ፣ በሻሸመኔ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በሃረርጌ፣ በወለጋ፣ በጉጂ፣ በጥቅሉ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን በዘራቸው ምክንያት እየተለዩ እንዲጨፈጨፉ ሰርቷል፡፡
በሶማሌ ክልል ሄጎ የተባለ ገዳይ ቡድን በማቋቋምና በቀጥታም፤ በወቅቱ የክልሉ አመራሮችም በኩል መመሪያ በማስተላለፍ በተመሳሳይ የንጹሃንን ደም በዘርና ሃይማኖታቸው ምክንያት በማስጨፍጨፍ የደም ጥማቱን በጊዜያዊነት አስታግሷል፡፡ በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል በተመሳሳይ አማጽያንን በማስታጠቅ ማንነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ከህጻን እስከ አዛውንት ተደጋጋሚ የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም አድርጓል፡፡
በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ስልጣንና ሀብት ይዞ በቆየባቸው ጊዜያት የፈጸማቸው እነዚህ ተግባራት ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ፤ የአሸባሪው ቡድን የግፍ ተግባራት እጅጉን የገዘፉ ከለውጡ ማግስት ባሉ የተወሰኑ ወራት ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ቅጥረኞቹን በማዘዝ አያሌ ንጹሃን ተጨፍጭፈዋል፤ በመቶ ሺዎችም ሀብት ንብረታቸው ወድሞ ለስደት ተዳርገዋል፡፡
የዚህ አሸባሪ ቡድን የጥፋት ጉዞ ቀጥሎ አፍራሽነት እና ሰው ገድሎ በሰው ደም የመርካት ባህሪ በከፋ መልኩ ተገለጠ፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ሌሊት በተኙበት ጥቃት ፈጸመ፡፡ በዚህ ተግባሩ የጨፍጫፊነት ብቻ ሳይሆን የአገር አፍራሽነት ጥማቱ ከልክ ማለፉ ተገለጠ፡፡ እናም ህዝብና መንግስት ይሄን ቡድን ለማጥፋት ቆርጠው በመነሳታቸው በአጭር ጊዜ ድል ተገኘ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አሸባሪ ኃይል ተግባርና መገለጫው መግደልና ማጥፋት ነበርና፤ በጉዞው ሁሉ ንጹሃንን መግደል፤ ታዳጊዎችን መድፈርና ማሰቃየት፤ የዜጎችን ህብት ንብረት ማውደምና ማፍረስ ዋና ተግባሩ ሆነ፡፡ በዚህ ወቅት ከፈጸማቸው አስከፊ ጭፍጨፋዎች መካከል የማይካድራው ጭፍጨፋ ታሪክም፤ ትውልድም የማይዘነጋው ነው፡፡ ማይካድራ በአንድ ሌሊት በአማራነታቸው ብቻ ተለይተው በተፈጸመባቸው ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ 1 ሺህ 563 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ80 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡ በርካቶችም ከፍ ላለ ስነልቡናዊ ጫና ተዳርገዋል፤ ሀብት ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡
ይህ ወቅት የሽብር ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ በተለያዩ ክልሎች ከፈጸማቸውና ካስፈጸማቸው ጅምላ ጭፍጨፋዎች በብቸኝነት ይዞት በከረመው የትግራይ ክልል ውስጥ በከፋ መልኩ የፈጸማቸው ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች መኖራቸው የተጋለጠበት ነበር፡፡ በዚህም ከራያ እስከ ሁመራ አያሌ በደሎች ተገለጡ፤ የበዙ የጅምላ መቃብሮች ታዩ፡፡ በማይካድራም እልፍ ወገኖች በሽብር ቡድኑ ተጨፍጭፈው የጥማቱ ማወራረጃ መሆናቸው አደባባይ ወጣ፡፡
እነዚህ እኩይ ተግባራት መገለጫው የሆኑት አሸባሪው ህወሓት ታዲያ፤ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ ደርሶ መከላከያ ሰራዊቱን ከክልሉ ማውጣቱን ተከትሎ አፈር ልሶ በመነሳት ዳግም የጥፋት ተግባሩን መፈጸም ጀምሯል፡፡ በማይካድራው የጅምላ ጭፍጨፋ ቁጥራቸው ከ200 በላይ ዜጎች እንደተገደሉ የተነገረውንና ህጻናት የሚበዙበት ጅምላ ጭፍጨፋ በጋሊኮማ ፈጸመ፡፡ በአማራ ክልልም በሰፋ መልኩ ጭፍጨፋ፣ ሴቶችን መድፈርና ሀብት ንብረትን ዘርፎ ማፈናቀሉን ቀጠለ፡፡
የሽብር ቡድኑ በተለይ በሰሜን ወሎ ዞን በደረሰበት ሁሉ ተኩስ በመክፈት የነዋሪዎች መንደሮች ላይ በጅምላ እና ቤት ለቤትም በመሄድ በፈፀማቸው አሰቃቂ ጥቃቶች በርካቶችን ለሞት፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለስደት ዳርጓል፡፡ አሸባሪው ህወሓት ጅምላ ጭፍጨፋና ውድመት ከፈፀመባቸው አካባቢዎች መካከል ከአጋምሳ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ የአርሶ አደሮች መኖሪያ መንደር በከባድ መሳሪያ ተደብድቦ፤ መንደሯ እንድትወድም፤ ነዋሪዎቿም እንዲጨፈጨፉ ሆኗል፡፡ ይህ ጥቃት ከወሎ ወደ ጎንደር ዞን ተሸጋግሮ በዕለተ ደብረ ታቦር፤ በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ተደጋጋሚ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
እነዚህ እና ያልተነገሩለት ሌሎች በርካታ እና ተከታታይ የጭፍጨፋ፣ ግድያ፣ ማፈናቀልና ቤት ንብረት የማውደም ብሎም ዘረፋ ተግባራት የአሸባሪው ህወሓት እኩይ ተግባራት መገለጫዎችና የቡድኑን የጭካኔ ጥግ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህ ቡድን ከዚህም በላይ ጊዜ ካገኘ ደግሞ ከፍ ያለ ጭፍጨፋ የሚያካሂድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እናም የዚህን አውሬ ቡድን እድሜ ማሳጠርና የንጹሃንን እንባ ማበስ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013