በቅርቡ በተጠናቀቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣1 ብርና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎች መመለሷን ተከትሎ የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ኢትዮጵያውያንን ማስቆጣቱ ይታወቃል። ይህን ውድድር የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤትና በአጠቃላይ በኦሊምፒኩ ወቅት ውዝግብ ፈጥረው በነበሩ ጉዳዮች ላይ ከውድድሩ መልስ የሚሰጠው ምላሽ ሲጠበቅ ነበር። በዚህም መሰረት ኮሚቴው ከትናንት በስቲያ በጽህፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ በኦሊምፒኩ መንግስት ከምን ጊዜውም በተለየ ድጋፍ አድርጎ ለረጅም ጊዜ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን በመግለጽ፣ ሕዝብና መንግስት በጠበቀው መልኩ ውጤት ባለመመዝገቡ ይቅርታ ጠይቀዋል። ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ በኋላ ሃላፊነታቸውን ይለቁ እንደሆነ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ስልጣናቸውን እንደማይለቁ ተናግረዋል። ኮሚቴው ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶችን ያስቀመጠ ሲሆን ከይቅርታው ባሻገር ምክንያት ተብለው የተዘረዘሩ ጉዳዮች እንዲሁ በይቅርታ ብቻ የሚታለፉ ሳይሆኑ መንግስትም ጭምር የስፖርቱን ገለልተኛነት ጠብቆ ምርመራዎችን በማድረግ ከአገር ክብር ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ያስቀደሙ ግለሰቦች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ የሚጠቁሙ ናቸው።
የኮሚቴው ምክትል ፀሐፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በመግለጫው ላይ በኦሊምፒኩ ዝቅተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ምክንያት የሆኑትን ነጥቦች ሲዘረዝሩ አብዛኞቹ ስህተቶች በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ አሰልጣኞችና ባለሙያዎች ጭምር የተፈፀሙ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። ለዚህም ማስረጃዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ያም ሆኖ በተፈፀሙት ጥፋቶች ኦሊምፒክ ኮሚቴም የራሱን ድርሻ እንደሚወስድና መጠየቅ ባለበት ደረጃ እንደሚጠየቅ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥበት ወቅት ተጠቁሟል።
ኮሚቴው አብዛኛውን የጥፋት ድንጋይ ወደ ፌዴሬሽኑ ወርውሯል። ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽ በቅርቡ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ኮሚቴው የውሳኔ ሰጪነት ክፍተቶች እንዲሁም ውጤት እንዲመዘገብ የተለያዩ ውሳኔዎችን በድፍረት ሃላፊነቱን ወስዶ (risk) የማሳለፍ ችግር እንደነበረበት በመግለጫው ለማስቀመጥ አልደፈረም። እንደ አጠቃላይ ለውጤቱ መበላሸት የተቀመጡት ነጥቦች አንዳንዶቹ በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቁና የወደፊቱም የአገሪቱ አትሌቲክስ እጣፋንታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አመላካች ናቸው።
በተለይም ለውጤቱ መበላሸት ሁለተኛ ምክንያት ተደርጎ የተነሳው የአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ገበያ (global market) ያስከተለው ፈተና ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ለኦሊምፒኩ አትሌቶችን የመምረጥ ስልጣን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ የተደራጀ የመንግስት ሃላፊ የሚመራው ንፁስ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራውን በአግባቡ መምራት አለመቻል፣ እቅድ አውጥቶ በተደራጀ መንገድ አለመምራት፣ ብቃት ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን ሙያተኞች መግፋት እንዲሁም ከኮሚቴው ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ ምክንያት ተደርጎ ተነስቷል።
ይህም ችግር የሚመነጨው አንዳንድ አሰልጣኞችና አመራሮች በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ገበያ ተሳታፊ በመሆናቸው የጥቅም ግጭት በመፈጠሩ እንደሆነ ተጠቁሟል። ለራስ ጥቅም ብቻ በማሰብ ከህክምና ክፍሉ ጋር የጥቅም ትስስር በግልጽ በሚታይ መልኩ በመፍጠር ሦስት ወር በሕመም ላይ ያለች አትሌት በአስር ሺ ሜትር እየታወቀ እንድትሳተፍ ማድረግ የአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ገበያው የፈጠረው ችግር ማሳያ መሆኑን አስቀምጧል።
አገርን በማስቀደም ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም ብቃት ያላቸው አትሌቶች ሙክታር ኢድሪስ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ሐጎስ ገብረሕይወት፣ ጉዳፍ ፀጋይና ለሜቻ ግርማን የመሳሰሉ አትሌቶችን ከዝርዝር ውስጥ ማስወጣትም ነበር ተብሏል። ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያልተካተቱ አትሌቶችን ለማካተት ጥረት ሲያደርግም ከ3ሺ ሜትር መሰናክል አሰልጣኞች ውጪ ሌሎቹ አሰልጣኞች የተመረጡት አትሌቶች ወርቅ የሚያመጡ በመሆናቸው ማንም እንዳይነካቸው፣ ከተነኩ ውጤት ይበላሻልና ሃላፊነቱን አንወስድም ማለታቸውም ተጠቁሟል።
ይህ ኦሊምፒክ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮችም አቅሙና ብቃቱ ያላቸው አትሌቶች አገራቸውን ወክለው ውጤት እንዳያመጡ ግልጽ አደጋ የደቀነ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መውሰድ ያለበትን ሃላፊነት ወስዶ ውጤት እንዳይበላሽ አለማድረጉም ከተጠያቂነት ሊያድነው አይችልም። ያምሆኖ አሰልጣኞች፣የፌዴሬሽን አመራሮችና የተለያዩ ባለሙያዎች እንደተባለው በዚህ አሳፋሪ የጥቅም ትስስር ውስጥ ገብተው ከሆነ መንግስት ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ የለበትም፣ ይህ ችግር የአገሪቱን አትሌቲክስ የወደፊት እጣፋንታ የሚወስን በመሆኑም ሳይውል ሳያድር ከመንግስት በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃንም የምርመራ ዘገባ በመስራት ይህን ቅሌት ማጋለጥ ይኖርባቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቶኪዮ አየር ንብረት ሞቃታማና ወበቃማ መሆኑ የሚታወቅ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ አትሌቶች መዘጋጀት ያለባቸው ተመሳሳይ የአየር ንብረት ባላቸው የአገራችን አካባቢዎች መሆን አለበት የሚል አቋም ተይዞ እንደነበርም በመግለጫው ተጠቁሟል። ኦሎምፒክ ኮሚቴውም በዚሁ መሰረት ከአሰልጣኞች፣ ከአመራሮችና ከህክምና ባለሙያዎች የተውጣጣ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ሃዋሳ መላኩ የተገለፀ ሲሆን፣ በጥቅም ግጭት ሃዋሳና ሌሎች ተመሳሳይ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች እንዳይዘጋጁ ተደርጓል። ይህ ችግርም የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው ከአዲስ አበባ አለመውጣትን ደጋፊ በመሆናቸውና ካለው የአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ገበያ ተፅዕኖ ጋር ተደምሮ ውጤት ያሳጣ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል። ይህም በማራቶንና በርምጃ ውድድር ከተሳተፉ ሰባት አትሌቶች ስድስቱ ውድድራቸውን አቋርጠው እንዲወጡ ማድረጉ በማሳያነት ተቀምጧል።
ይህም አትሌቶች ከአገር ይልቅ ለሌሎች የገንዘብ ውድድሮች እንዲውሉ በአሰልጣኞች፣ ማኔጀሮችና ወኪሎች እንዲሁም በባለሙያዎችና በፌዴሬሽን አመራሮች መመሳጠር የተፈጠረ ክፍተት ካለ በምርመራ ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል። ጉዳት ላይ የነበሩ አትሌቶች በውድድር ላይ ምንም እንደማይፈጥሩ እየታወቀ ራሳቸውን በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ እንዲሸጡ ብቻ ይዞ መጓዝም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። በዝግጅት ዙሪያ አትሌቶች በተገቢው የአየር ንብረት እንዳይዘጋጁና አዲስአበባ ላይ ብቻ እንዲከትሙ መደረጉም ከሆቴል ጨረታ ጋር የተሰራ ሸፍጥ ሊኖር ስለሚችል አንዱ የመንግስትና የመገናኛ ብዙሃን የምርመራ ትኩረት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013