የአገርን አንድነት ለማስጠበቅ የወጣቱ ተሳትፎ በስፋት ያስፈልጋል:: በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ወጣት በብዛት የሚገኝባቸው አገራት ለልማትም ሆነ ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ወጣቱ ሃይል ጥቅም ላይ መዋል አለበት:: በአገሪቱ የሽብርተኛው የህወሓት ቡድንን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ከተለያዩ ክልሎች ወጣቱ እየተመመ ይገኛል:: ወጣቱ ከህግ ማስከበሩ ስራ በተጨማሪ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅና የዲጅታል ፕሮፓጋንዳውን ለማክሸፍ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ እየቀረበ ይገኛል:: የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወጣት አክሊሉ ታደሰ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: መልካም ንባብ::
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ በሽብርተኛው ህወሓት ላይ እየተፈፀመ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዴት ይታያል? አጠቃላይ ሁኔታውን ሊጉ እንዴት ይረዳዋል?
ወጣት አክሊሉ፡– በመንግስት ደረጃ ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል:: ከመጀመሪያው ጀምሮ ህወሓት ኢትዮጵያን በሚጠላ መንገድ መንግስት የመሰረተበት ሁኔታ ነበር:: የኢትዮጵያ ህዝብና ወጣቶች እንደሚረዱት ባለፉት አስርት ዓመታት አገሪቱን በመራበት ወቅት ስሙን ሳይቀይር የአንድ ብሄር ነፃ አውጪ ሆኖ ቆይቷል:: በኃላፊነት በቆየባቸው ዓመታት በተለይ አዲሱ ትውልድ ላይ ኢትዮጵያዊነት የሚል የአንድነት መንፈስ እንዳይኖር አድርጎ ሰርቶታል:: ሽብርተኛ ቡድኑ ይህን ሲያደርግ የነበረው ከኢትዮጵያ ጠልነት የመነጨና አገሪቱን ለማፈራረስና በሂደት ለማዳከም ወሳኙ ሂደት አድርጎ የተጠቀመበት እንደሆነ ይታወቃል:: የጠላትነት፣ የልዩነት አንዱ ብሄር ሌላውን ህዝብ እንዲጠራጠርና በጋራ አብሮ እንዳይቆም የማድረግ ስራ ሲሰራ ቆይቷል::
በየትኛውም የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ አንድን ህዝብ የማዳከሚያ ትልቁ መንገድ ህዝብ ከህዝብ ጋር እየተጠራጠረ፣ አንዱ አንዱን እየፈረጀ የጋራ ራዕይ እንዳይኖረው አድርጎ ማቀራረብ ህዝብን የማዳከም ትልቁ መንገድ ነው:: ስለዚህ ሽብርተኛው ህወሓት በመንግስት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የተገበረው ይሄንን ነው:: ሁሉንም ህዝብ አንዱን ጠባብ ብሎ ታርጋ በመለጠፍ ሌላውን ትምክህት ይባላል፣ ሌላውን ደግሞ ቀጥተኛ ሳይሆን አጋር ህዝብ ተደርጎ ይወሰድ ነበር:: ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉም የማህበራዊ መሰረቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥና በአገር ግንባታ ውስጥ የጋራ የሆነ እኩል ራዕይና ግብ እንዳይኖራቸው ተደርጎ ላለፉት አስርት ዓመታት ሲተዳደር ነበር:: ህወሓት ከጅምሩ ኢትዮጵያን ማፍረስና በኢትዮጵያ ጠልነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ፍልስፍናና ትግበራ ሲያራምድ የቆየ ፓርቲ ነው::
ህወሓት እንደሚታወቀው የአሸባሪነት ባህሪው የተለየ የሚያደርገው በዓለም ላይ ስልጣን ይዞ አሸባሪ የሆነ ድርጅት መሆኑ ነው:: ህወሓት አሸባሪነቱንም የመንግስት ስልጣንንም የያዘ ፓርቲ ነው:: ለፖለቲካ መሳሪያነት፣ ለስልጣን ማቆያና ለስልጣን መያዣ እስከጠቀመ ድረስ የትኛውንም የአሸባሪነት ተግባር ሲፈጽም ከርሟል:: ከጅምሩ በራሱ ህዝብ ላይ የሀውዜን ጭፍጨፋ እንዲከናወን ያደረገ ነው:: ከዚህም ቀጥሎ በ1977 ዓ.ም አካባቢ በድርቁ ወቅት ለመሳሪያ መግዣና ስልጣን ይዤ አዳክማታለሁ ብሎ የሚያስባትን ኢትዮጵያ ለመያዝ ህዝብ እየሞተ እህል እየተሸጠ መሳሪያ ሲገዛ የነበረ ፓርቲ ህወሓት ነው:: የህወሓት የስልጣን ቆይታ ሲታይ አምርሮ የሚጠላውን ህዝብ ለሰላሳ ዓመታት የመራ ፓርቲ ነው:: በአሸባሪነት ስሪት ስልጣን ይዞ የቆየ መሆኑ ለማየት ተችሏል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው የኢትዮጵያን አንድነት የማዳከም፣ ኢኮኖሚውን በአንድ አካል የመቆጣጠር፣ ሌሎችን በኢኮኖሚ ይሁን በፖለቲካው መስክ ሁለተኛ ዜጋ አድርጎ የሚቀርጽበት አይነት የመረረው ህዝብ ትግል አድርጎ የሚሞተው ሞቶ ዋጋ ተከፍሎ ከማዕከላዊ በትረ መንግስቱ እንዲወገድ ተደርጓል::
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት የሽብርተኛው የህወሓት ቡድን እንቅስቃሴ እንዴት ይገለፃል? መንግስት የወሰዳቸው ርምጃዎችስ እንዴት ይታያሉ?
ወጣት አክሊሉ፡- ህወሓት ከማዕከላዊ መንግስቱ ከተወገደ በኋላ በርካታ የአሸባሪነት ስራዎችን ፈጽሟል:: ለምሳሌነት በማይካድራ የተፈፀመውን ማንሳት ይቻላል:: በሌላም በኩል በወለጋ የተፈፀመው፣ መተከል እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ላይ በስልጣን ወቅት ባግበሰበሰው ገንዘብ ስፖንሰር እያደረገ በመላ አገሪቱ በተለይ በለውጥ ተገፍቶ ጥጉን ከያዘ በኋላ የህዝቦች መፈናቀልና ሞት ምክንያት ሆኗል:: እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሲደመሩ ህወሓት በአሸባሪነት የቆየው አሁን ብቻ ሳይሆን በህግ ደረጃ አሸባሪ ከመባሉም በፊት የስልጣን ጊዜውን ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በዚህ ባህሪው የቀጠለ ድርጅት ነው:: ከዛም በኋላ የማይካድራውና በቅርቡ ደግሞ በአፋር ክልል የተፈፀመው እንደ ማሳያ መውሰድ ይችላል::
በአገሪቱ ውስጥ እዚህም እዛም የነበረውን መፈናቀልና ሞት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲታይ አገሪቱ ያልተረጋጋች ሰዎቹ በየእለቱ የሚሞቱባት አገር ሆና መታየቷ ጥግ የያዘ የአሸባሪው ቡድን ስፖንሰር እያደረገ የሚፈጸም ወንጀል ስለመሆኑ ለመቀበል የሚቸገሩ ሰዎች ነበሩ:: አብዛኛው ቢገባውም ለመቀበል የሚቸገረው ውስን ሃይል ነበር:: እንደ ማሳያ ያለፉትን ስምንት ወራት መመልከት ቢቻል መንግስት ሁሉንም በትዕግስት አይቶና የህዝቡ ግፊት እየጨመረ ሲመጣ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጸመው ወንጀል በተለይ የሚሞተውና የሚንገላታው ወጣት አበሳ እንዲበቃ ከምንጩ ማድረቅ ሲጀምር በባለፉት ጊዜያት ሞትና መፈናቀል ቀንሷል::
በገንዘብና በተልዕኮ የሚሰራው ስራ ቆሟል ባይባልም ወለጋ፣ መተከልና በጉራፈርዳ አካባቢ የነበሩ ችግሮች ቀንሰዋል:: ስለዚህ ይህን ማን ያደርግ እንደነበር በአደባባይ ጎልቶ የወጣበት ሁኔታ አለ:: ከዚህ ውጪ ሌሎች ማሳዎችን ማንሳት ይቻላል:: በቅርቡ ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን በራሱ አንደበት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚያግዝ ሃይል ጋር በጋራ እንሰራለን ብለው ጥሪ አቅርበው ነበር:: በዚህም ኦነግ ሸኔ ጥሪውን ተቀብሎ ግባችን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው በሚል አብረው ለመስራት ተስማምተዋል:: እነዚህን ሂደቶች መንግስት ያስተናገደበት መንገድ እንደ ወጣት አደረጃጀት ሲታይ ባለፉት ሶስት ዓመታት የነበረውን ሁኔታ እጅግ በሰፋ ሆደ ሰፊነት እንደተመለከተው ለመገንዘብ ተችሏል:: መንግስት ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ መንግስት ሁኔታዎችን ለማርገብ ሞክሯል:: አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከማዕላዊ ስልጣን ከወረደ በኋላ በተለየ ቦታ ያለ እስኪመስለው ድረስ አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽም ቆይቷል:: ከዚህም ባለፈ ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም እስከማለት ደርሷል:: መሪዎች ላይም የግድያ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል::
ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ በወሰደው እርምጃ ምክንያት መንግስት ህግ ወደ ማስከበሩ ገብቷል:: ከዚህ በላይ አገርን የማስደፈር ሁኔታ ስለሌለ መንግስት እርምጃ መውሰድ ጀመረ:: የአገሪቱም ወጣቶች ከመንግስት ጎን ቆመው ሽብርተኛው ቡድን እንዳይመለስ ተደርጎ እየተቀጣ ይገኛል:: በዚህ ሂደት ውስጥ ይሄ አሸባሪ ሃይል እንደ መደበቂያ አድርጎ ሲጠቀም የነበረው የትግራይን ህዝብ ነው:: የትግራይ ህዝብና ወጣት ብልፅግናን መደገፍ ባይችሉ እንኳን አገርን ከጥቃትና ከወራሪ እንዲሁም ከውክልና ጦርነት ሊታደጉ ይገባቸዋል:: አገሪቱ አንድነቷን አስጠብቃ እዚህ መድረስ የቻለችው በቀድሞ አባቶች ተጋድሎ ነው:: ይህን መስዋዕትነት የከፈሉ የመላው አገሪቱ አባትና እናቶች ናቸው:: በዚህም ውስጥ የትግራይ እናትና አባቶች ይገኙበታል:: የትግራይ ህዝብ ለፖለቲካ መወገንንና አገር ማዳንን ለይቶ ማየት አለበት:: ሽብርተኛው ህወሓት ሲነካ ጥቅማችን ተነካ ብለው ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሚያነሱ አገራት አሉ::
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ህግ ወደ ማስከበሩ ከገባ በኋላ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንቅስቃሴ እንዴት ይገለፃል?
ወጣት አክሊሉ፡– በአገሪቱ በነበረው ሂደት ውስጥ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡበት ያለው ሁኔታ በአግባቡ መረዳት ያስፈጋል:: የውጭ ተቋማት በአገሪቱ ጉዳይ የሚያንፀባረቁትን በደንብ መመልከት ያስፈልጋል:: ሁሉም አገር የራሱ የሆነ ጥቅም ይፈልጋል:: ሁሉም ዓለምአቀፍ ተቋማት ከጥቅማቸው አንፃር ነው ውግንናቸውን የሚያሳዩት:: ከዚህ በመነሳት የምዕራባውያን ባህሪን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል:: በአፍሪካ ውስጥ አንዳንድ የምዕራባውያን አገሮች በአገር ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር መሪ ማየት አይፈልጉም:: በፖሊሲዎች ላይ የማይደራደር መንግስትና ህዝብ እንዲሁም ወጣቶችን ያደራጀ መንግስት ማየት አይፈለግም:: ይህ ከሆነ በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት ለሚደረገው እንቅስቃሴ ምቹ ነገር መፍጠር አይቻልም:: ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አገራት ላይ እየተሞከረ እንደሆነ የሚታወቅ ነው::
የዓለም አቀፉ ጩኸት የሚበረክተው በአፍሪካ ውስጥ ለፖሊሲ ነፃነትና ሉዓላዊነትን አላስነካ በሚል መንገድ የህዝብ ፍቅር አግኝቶ የሚንቀሳቀስ መንግስት ሲኖር ነው:: ነገር ግን በዚህ ውስጥ ሚዛናዊ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አገራት አሉ:: ሌላው ከአገሪቱ የተዘረፈው ገንዘብ በተለይ ሽብርተኛው የህወሓት ባለስልጣናት ብዙ ገንዘብ ማሸሻቸው የተረጋገጠ ሀቅ ነው:: ሽብርተኛው ቡድን በዘረፈው ገንዘብ ሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ የውጭ አገራት አክቲቪስቶች ይቀጥሩበታል:: ከዚህ በዘለለ የመንግስት ባለስልጣናትን በገንዘብ በመደለል ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ሲደረግ ቆይቷል:: የውጭ መገናኛ ብዙሃን በነፃነት ከመዘገብ ይልቅ ገንዘብ እየተከፈላቸው የተዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከርመዋል::
የሰብዓዊ መብት ተቋማትም በተመሳሳይ ጥቅማቸውን ለሚያስጠብቅላቸው ቡድን ሲጮሁ ይስተዋላል:: በማይካድራ የተካሄደው ዘር ላይ ያተኮረ ግድያ ላይ ምንም አይነት ትኩረት ሳይሰጡ እንዲሁም በአፋር ክልል ሽብርተኛ ቡድኑ ያደረጋቸውን ጭፍጨፋዎች አይተው እንዳላዩ አልፈዋል:: በተጨማሪም ህወሓት ያሰለፋቸውን ህፃናት ለጦርነት እየማገደ ይሄም አያሳስባቸውም:: የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚያሳስባቸው የቦርደር መዘጋት ነው:: ተዘጋ የሚሉት ቦርደር በጊዜም በገንዘብም አክሳሪ የሆነውን ነው:: ይህ የሚያሳየው ሰብዓዊ መብት ተቋማት ለጥቅማቸው ከሽብርተኛው ቡድን ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ነው::
ሌላው አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ባህሪ የውጭ አገራት በሚፈልጉት መልኩ አለመሄዱ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል:: ለምሳሌ ህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተያዘው አቋም እንዲለወጥ ምዕራባውያን ከፍተኛ ውትወታ ሲያደርጉ ነበር:: መንግስት ሃሳቡን ባለመቀበሉ ከፍተኛ ጫና ሲደርስበት ቆይቷል:: አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መንግስት ላይ የውሸት ዘገባ እንዲሰሩ ገፋፍቷቸዋል::
አዲስ ዘመን፡- አገሪቱን ለማረጋጋትና ሽብርተኛ ቡድኑን ለማጥፋት ከወጣቱ ምን ይጠበቃል?
ወጣት አክሊሉ፡- የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ከአስር ሚሊዮን በላይ አባላትና ደጋፊዎች አሉት:: ይህ አደረጃጀት ለአገር በጋራ የቆመ ወጣት የትኛውንም ተአምር መስራት ይችላል ማለት ነው:: የአገሪቱን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ወጣቱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የዓለም አቀፉን አቋም መረዳት አለበት:: ከዚህ በዘለለ ወጣቱ ሁኔታዎችን በንቃት መጠበቅ አለበት:: ሽብርተኛው ቡድን ከሚነዛቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ወጣቱ መጠበቅና እራሱን መከላከል አለበት:: ሽብርተኛ ቡድኑ የሚከተለው የፕሮፓጋንዳ ሁኔታ ቀደም ብሎ ሲያደርግ እንደነበረው ያልተፈጠረን እንደተፈጠረ አድርጎ ወጣቱን ለጦርነት መማገድ ነው:: ወጣቱ ህወሓት የሚነዛውም የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመረዳት እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል::
በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወጣቱ ተሳትፎ በማድረግ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን መወጣት አለበት:: በሁሉም ክልሎች የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ብዛት ያላቸው ወጣቶች ሀብት በማሰባሰብና በመዝመት ግንባር ቀደም ተሳትፎ አድርገዋል:: ይህም ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል:: ከዚህ አንፃር መከላከያውን ማገዝ ያስፈልጋል:: ሌላው ከወጣቱ የሚጠበቀው ሁሉም ወጣት አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አለበት:: ምክንያቱም ሽብርተኛው ቡድን ጦርነቱን አንድ ቦታ ማድረግ ስለማይፈልግ በተለያዩ አካባቢዎች ብጥብጥ ሊፈጥር ይችላል:: የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከቀድሞ በተሻለ መንገድ እንዲቀጥል ሁሉም ወጣት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ እናመሰግናለን
ወጣት አክሊሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013