ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም በሀገሪቱ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ለመምከር እና ገዥ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ ለ3ኛ ጊዜ በመምከር ላይ ናቸው፡፡
ውይይቱ በፓርቲዎች በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሸጋገር በር የከፈተ መንግድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ሐሳቦች በነጻነት ተነስተው ውይይት በተደረገበት በ3ኛው ዙር ምክክር በአራት ሐሳቦች ላይ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
“ሀገረ መንግሥትና- ብሔረ መንግሥት ግንባታ በኢትዮጵያ ፈተናዎችና የግንባታው ስትራቴጅ ምን ሊሆን ይገባል?” በሚል ጽሑፍ ያቀረቡት የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ናቸው፡፡
አቶ ብናልፍ ‹‹ጠንካራ ሀገር መገንባት ያልቻለ ሕዝብ ትልቅ ሀገር ሊኖርው አይችልም›› ነው ያሉት፡፡ ‹‹ሀገረ መንግሥትን ከሥርዓተ መንግሥትና ከመንግሥት አስተዳደር ነጥሎ በማየት በኩል ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ አገር ያፈርሳል›› ብለዋል አቶ ብናልፍ፡፡
‹‹የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ሚና በአንድ ሀገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል›› በሚል ጽሑፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ማፍራት እና ዕውቀት ማስረጽ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ሥርዓትን የማስረጽ ግዴታም እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሀገር ግንባታ ላይ መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ዶክተር ዲማ ነገዎ በኩላቸው ‹‹በሀገሪቱ የፖለቲካ አደረጃጃት ውስጥ ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ ሥራዎች ሊቀድሙ ይገባል ነው›› ያሉት፡፡
‹‹የመናገር ነጻነትና ማኅበራዊ ሚዲያ›› በሚል ሐሳብ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ አብርሃ ደስታ ደግሞ በኢትዮጵያ የሐሳብ ነጻነትን ለማረጋገጥ ነጻ የሆኑ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ውይይቶችም ሀገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል አብመድ ዘግቧል፡፡