የህወሓት አሸባሪ ቡድን ዋነኛ ዓላማ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት መሆን አይደለም:: ይህ በፍጹም ሊሆን እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል:: ይህን የሚያውቀው ለውጡን ተከትሎ ብቻ ሳይሆን ጥንት በጫካ ሲጠነሰስም አንዴ ከስልጣን ከተወገደ ቀጥሎ ምን እንደሚሰራ በጽሁፍ ሳይቀር ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል:: ዓላማው ኢትዮጵያን በመበታተን ታላቋን ትግራይ መመስረት የሚል ቅዠት ነው:: ይህንን ቅዠት እውን ለማድረግ አሲሮ ሲሰራ ኖሮ አሁን ወደ ተግባር ለመለወጥ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል::
ይህንን መሰረት አድርጎ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ ለመበጥበጥ ያስችል ዘንድ አስተዳደሩ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን ከመከተል ይልቅ፤ ባህላዊ አኗኗርንም ችላ ብሎ የብሔር ብሔረሰቦች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በማለት ኢትዮጵያን መከፋፈሉ የመጨረሻ ግቡ ኢትዮጵያን መበታተን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው:: ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታትም ኢትዮጵያውያን የተሳሰሩባቸውን ክሮች በመበጣጠስ የተዳከመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሞክሯል:: በመጨረሻም ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብሎ በማሰቡ ሀገሪቱን ሰባት ቦታ ለመሰነጣጠቅ እቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው:: ነገር ግን በእውኑ ኢትዮጵያን ማፍረስ ይቻላል? ኢትዮጵያን ማፍረስ ምን ማለት ነው?
ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ናት:: የሰው ልጅ መነሻ የሆነችው ሉሲ (ድንቅነሽ) እድሜ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት እንደሆናት ይገመታል:: ተመራማሪዎቹ አሁንም በቅርቡ በተመሣሣይ መልኩ የሰው ዝርያ ሊኖርበት ይችላል ተብሎ ከተገመተበት ጊዜ በአራት መቶ ሺህ ዓመት የቀደመ ቅሪተ-አካል አግኝተዋል:: የአሁኑ ግኝት ደግሞ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ነች የሚለውን መላ ምት ይበልጥ አጠናክሮታል:: ታዲያ ዓለምን የተቆጣጠረ የሰው ልጅ መነሻ እና መገኛ የሆነችውን አገር ከምድረገጽ ለማጥፋት እንዴት ይታሰባል? ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንዴት ይሞከራል?
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ አይደለችም፤ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ መፍለቂያም ጭምር ናት:: በዓለም በማይዳደስስ ቅርስነት የተመዘገበው የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚከተለው ባህላዊ የአስተዳደር እና የሥልጣን ሽግግር ሥርዓት ገዳ ትልቅ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ምንጭ ነው። የገዳ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ፤ ፖለቲካዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ የቀጠለ፤ በህዝብ የሚጠበቅና ህዝባዊ ሥርዓት መሆኑ በጥናት ተረጋገጦ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል::
ነባሩ የኦሮሞ የአስተዳደር፤ የእርቅ፤ የሽምግልና እና የሥልጣን ሽግግር ስርዓት ማሳያ የሆነው የገዳ ሥርዓት የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ነው:: አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ሀብት ሆኗል:: ታዲያ ይህን የዓለምን ሀብት ማፍረስ እንዴት ይቻላል? ኢትዮጵያን ማፍረስ እኮ ይህን የመሰለ የዓለም ሀብት የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ሀብት የሆነውን የገዳ ሥርዓት ማውደም ነው:: ይህ እንዴት ይሞከራል?
በቅኝ ያልተገዛች፤ የነፃነት ተምሳሌት የሆነች፤ በጭቆና ስር ለነበሩ አፍሪካውያንም ሆነ ለጥቁር ህዝቦች የሰውነት ክብር መለኪያ የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ እንዴት ትፈርሳለች? ስለምን የአድዋ ድልን የመሰለ ቅኝ ገዢዎችን በሙሉ አንገት ያስደፋ ትልቅ የታሪክ ገድል ያላት አገር ስለምን ስሟ ከምድረገፅ ይጠፋል? ስለምን ትፈራርሳለች? ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን መኩሪያ ብቻ አይደለችም:: መላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ መኩሪያም ጭምር ናት:: ይህን ለማረጋገጥ ብዙ ማገላበጥ እና መድከምን አይጠይቅም:: ሰንደቅ ዓላማዋ የበርካታ አገሮች ሰንደቅ ዓላማ መነሻ መሆኑን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል:: አገራት በቅኝ ግዛትነት ተይዘው ወይም በኃይል በተፅዕኖ ሥር በመውደቃቸው ሰንደቅ ዓላም ባይኖራቸውም ኢትዮጵያን መነሻ አድርገው ብዙዎቹ የሰንደቅ ዓላማ ባለቤት ሆነዋል::
ይህች አርበኞች በዱር በገደል እየሸለሉና እየፎከሩ ሰንደቅ ዓለማቸውን ከፍ አድርገው የሚያሳዩባት፤ ሴቶችና በእድሜ የገፉ አዛውንቶችም በያሉበት በክብርና በኩራት የሚያውለበልቡት ሰንደቅ ዓላማ ያላት፤ ሌሎች አገሮች ተምሳሌት የሆነችን አገር ኢትዮጵያን ማፍረስ የጥቁሮችን አልፎ ተርፎ የዓለምን መነሻ መደምሰስ መሆኑ መዘንጋት የለበትም::
ኢትዮጵያ የአንድ ወቅት የስልጣኔ ማማን ተቆናጣ እንደነበር የፋሲል ግንብ፤ የሀረር ግንብ እና የአክሱም ሀውልት ምስክሮቿ ናቸው:: ከባህር ጠለል በላይ በ2ሺህ 200 ሜትር ከፍታ ላይ የተገነባው የፋሲል ቤተ መንግስት ዙሪያውን እስከ 3 ሺህ ሜትር ከፍታ ያላቸው ተራራዎች ከበውታል። እነዚህ ተራራዎች የአየር ወለድ በሽታ ቢመጣ ወደ ቤተመንግስቱም ሆነ ወደ ከተማዋ አያስገቡም ተብሎ ይታሰባል:: ከጦር ስትራቴጂ አንፃርም በተራራ መከበቧ ጠላት በቀላሉ እንዳይገባ የሚከላከል ከመሆኑም ባሻገር፤ ተራራዎቹ በትልልቅ ዛፎች የተጠቀጠቁ መሆናቸውን ተከትሎ ጎንደር በ1628 ዓ.ም ተመስርታለች:: አፄ ፋሲለደስ በ1660 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ቤተ መንግስቱ የወቅቱን ስልጣኔ ለዓለም በማሳየት ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ እና የዓለም ሀብት ሆኖ ተመዝግቦ ከተማዋም እየተጎበኘች ትገኛለች:: ይህን የመሰለ ለዓለም ሀብትነት የበቃ ጥንታዊ ቤተመንግስትን የገነባች እና በዓለም ሀብትነት ያስመዘገበች አገር ኢትዮጵያ እንዴት እና ለምን ትፈርሳለች?
የሀረር ግንብም የጥንት ኢትዮጵያን ጠላትን የመከላከያ ዘዴዎችን አስቀድማ የገነባቸውና በዘርፉም የካበተ ልምድ እንደነበራት የሚያሳይ ነው:: ኢትዮጵያ የፋሲል እና የሀረር ብቻም ብቻ ሳይሆን የአክሱም ሀውልትና የላሊበላ ውቅር ቤተ መቅደስ ባለቤት ናት:: አክሱም በ4ኛው ምእተ ዓመት በአክሱም ዘመነ መንግስት አካባቢ የጥንታዊ አክሱም ስልጣኔ ምን ያህል እንደነበር ጠቋሚ ነው። ይህ ሃውልት ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው መሳፍንቶች መቃብር ላይ የሚቆም በሀሰት በር እና መስኮቶች ያጌጠ ነው። ላሊበላ በዓለም ላይ ካሉ ውድ ሰባት ቅርሶች አንዱ ነው:: ይህን ሀውልት ጨምሮ ሌሎችም ሀውልቶች በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል:: እነዚህ ሀብቶች የኢትዮጵያውያን ናቸው:: ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማፍረስ እነዚህን ሀብቶችንም እንደማውደም ይቆጠራል:: ምክንያቱም ሀብቶቹ የግለሰብ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሀብቶች ናቸው::
ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ በዓለም በተሰራጨው መጽሃፍ ቅዱስ ስሟ 41 ጊዜ ተጠቅሷል:: ለምሳሌ በመዝሙር ዳዊት 68÷ 31‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ይላል:: በትንቢተ ኤርሚያስ 13÷23 ላይም ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይቻላልን?›› በማለት ይጠይቃል:: በትንቢተ ሶፎንያስ 2÷12 ላይ ‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሰይፍ ትገደላላችሁ›› ይላል:: ይህ ሲታይ ይህችን አገር ማፍረስ እና ስሟን ማጥፋት ጥፋቱ ምን ያህል የዘለቀ እንደሆነ የሚያመለክት ነው::
በመጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም በተሰራጨው ቅዱስ ቁርዓንም የኢትዮጵያ ስም በጉልህ ተጠቅሷል:: አንዳንድ መፃሕፍት እንደሚያወሱት ነብዩ መሐመድ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ተነስተዋል:: በዚህ ጊዜ ጠላቶች ሊያጠቋቸው ሲያሳድዷቸው ኢትዮጵያ ተቀብላቸዋለች:: በመጨረሻም ኢትዮጵያ እርሳቸውን በማስተናገዷ ‹‹ኢትዮጵያን እንዳትነኩ›› የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ በስፋት ይገለፃል:: ይህ ሁሉ ሲታይ ኢትዮጵያ የሚደንቅ ታሪክ እና በሃይማኖቶችም የተለየ ስፍራ ያላት አገር ናት:: ኢትዮጵያ ፈረሰች ማለት መላው ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን አጡ ማለት ነው:: ዓለምም ትልቅ ሀብትን አጣች ማለት በመሆኑ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ቅዠት መቼም ዕውን እንዳይሆን እንታገላለን:: ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም