ወደ ክልሉ እየገቡ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው

ጋምቤላ፡– ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው የሚገቡ ሰርጎ ገብ ታጣቂዎችን በተደጋጋሚ የሚፈጽሙትን ህጻናትን የመውሰድና ከብቶችን የመዝረፍ ወንጀል ለማስቀረት እየተሠራ ነው ሲል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተወካይ አቶ ኡዶል ኡጁሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ ሰርገው የሚገቡ ውስን ታጣቂዎች አሉ፤ እነዚህም ህፃናትን የመውሰድ፣ እንስሳትን የመዝረፍ እና የሰው ሕይወትን የማጥፋት ወንጀሎችን ይፈጽማሉ።

እነዚህ ታጣቂዎች ህጻናትን መውሰድና ከብቶችን መዝረፍን እንደባህል የሚቆጥሩት እንደሆነ አመልክተው፤ ክልሉ ባለው ረዥም አዋሳኝ ምክንያት ወንጀል ፈጻሚዎቹ ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም ድርጊቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል የመንግሥት ለመንግሥት ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ ጠቅሰው፤ የተወሰኑ አስቸጋሪ ታጣቂዎች እንደ ባህል አድርገው ህፃናትን የመውሰድ፣ ከብቶችን የመዝረፍ እንዲሁም ሰውን የመግደል ተግባራትን በተደጋጋሚ እየፈፀሙ መሆኑን አመልክተዋል።

በደቡብ ሱዳን በተፈጠሩ የፖለቲካ ልዩነቶች በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚደረጉ የጦርነት እንቅስቃሴዎች በክልሉ ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሮች እንዳይባባሱና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ በቦታው በመድረስ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን እና ከደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ጥምር ሃይል ጋር የጋራ መድረኮችን በመፍጠር ውይይት የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በቅርቡም ከደቡብ ሱዳን መንግሥት እና አማፂ ቡድን ጋር በተፈጠረ ግጭት አብዛኛው ሰው እስከ ድንበር አካባቢ መግባቱን እና ለመቆጣጠር መቻሉን አስታውሰዋል።

በደቡብ ሱዳን በሚከሰቱ ጦርነቶች በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የመሣሪያ ዝውውር እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። በዚህም የተነሳ ከመሣሪያ ጋር ተያይዞ በሚደረጉ ኮንትሮባንድ ዝውውሮች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በተለይም ከመረጃ ልውውጥ ጋር ተያይዞ ክፍተት መኖሩ እና የክልሉን ስፋት ተጠቅመው ወንጀለኞች ሾልከው እያመለጡ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም አሠራሮችን የማዘመን እና በተማረ የሰው ኃይል የመገንባት ሥራ እየተሠራ እንዳለ ጠቅሰዋል።

አቶ ኡዶል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለአብነትም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በወር አንድ ጊዜ በመገናኘት የጋራ ምክክር እንደሚደረግና ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ጋር የጋራ መድረከ በማዘጋጀት ለጋራ ሰላም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You