ለ2021 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ከስምንት አመት በኋላ ማለፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ በምድብ ድልድል ጨዋታ የሚፋለማቸውን አገራት አውቋል። የምድብ ድልድሉ ውድድሩን በምታስተናግደው ካሜሩን መዲና ያዉንዴ ከትናንት በስቲያ ይፋ ሲደረግ ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድለዋል። ከምድብ ድልድሉ አስቀድሞ በቋት አራት ከማላዊ፣ሱዳን፣ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያና ኮሞሮስ ጋር ተደልድለው የነበሩት ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ድልድል ጨዋታዎች የሞት ምድብ ባይባልም ከጠንካራ አገራት ጋር ነው የተደለደሉት። በተለይም ካሜሩን ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊና አዘጋጅ አገር እንደመሆኗ ዋልያዎቹ ከምድብ ለማለፍ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይጠበቃል።
ቡርኪናፋሶም ቀላል ግምት የማይሰጣት ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላት አገር ስትሆን ዋልያዎቹ ከስምንት አመት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፉበት የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ሁለቱ አገራት በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ተገናኝተው ዋልያዎቹ አራት ለዜሮ በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል። ሌላኛዋ ከዋልያዎቹ ጋር በምድብ ድልድሉ የተካተተችው ኬፕቨርዴም በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች ያሏትና በአፍሪካ ዋንጫ ከቅርብ አመታት ወዲህ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነች አገር መሆኗ ይታወቃል።
የአፍሪካ ዋንጫው በመጪው ጥር የመጀመሪያ ሳምንታት ሲጀመር አዘጋጇ ካሜሩን ጥር 11/2014 ቡርኪናፋሶን ስትገጥም ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ጥር 9/2014 ኬፕቨርዴን በመግጠም እንደሚጀምሩ ታውቋል። በምድብ ሁለት ሴኔጋል፣ዚምባቡዌ፣ ጊኒና ማላዊ የተደለደሉ ሲሆን በምድብ ሶስት ሞሮኮ፣ጋና፣ ኮሞሮስ፣ጋቦን ተደልድለዋል። በምድብ አራት ናይጄርያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ጊኒ ቢሳው ተደልድለዋል። ምድብ አምስት ላይ አልጄርያ፣ ሴራሊዮን ፣ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮትዲቯር ተካተዋል። በመጨረሻው ምድብ ስድስት ቱኒዚያ፣ ማሊ፣ሞሪታኒያ፣ጋምቢያ ተገናኝተዋል።
በምድብ ድልድሉ መርሃግብር ላይ ለመገኘት ወደ ያውንዴ ያቀኑት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሳምንት በፊት በዚህ ወር መጨረሻ ከጋና ጋር ለሚያደርጉት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለሃያ ስምንት ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በአዳማ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። አሰልጣኝ ውበቱ ለአለም ዋንጫ ማጣሪያው ጥሪ ያደረጉላቸው ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ቡና አስራት ቱንጆ፣አማኑኤል ዮሀንስ፣ታፈሰ ሰለሞን፣ ዊሊያም ሰለሞን፣ አቡበከር ናስር ተካተዋል።ከወልቂጤ ከነማ ጀማል ጣሰው፣ረመዳን የሱፍ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ሲሆኑ ከጅማ አባጅፋር መሱድ መሀመድተካቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሱሌማን ሀሚድ፣ምኞት ደበበ፣ጋቶች ፓኖም፣ሀይደር ሸረፋ፣አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ጌታነህ ከበደ፣አቤል ያለው ተካተዋል። ከሲዳማ ቡና ተክለማሪያም ሻንቆ፣ከድሬዳዋ ከተማ ፍሬው ጌታሁን፣ከሀዋሳ ከነማ ደስታ ዮሀንስ፣ከፋሲል ከነማ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ይሁን እንደሻው፣ሀብታሙ ተከስተ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ሽመክት ጉግሳ፣ሙጂብ ቃሲም ተመርጠዋል።ከባህር ዳር ከነማም ፋሲል ገ/ሚካኤል፣ኤፍሬም አለሙ መናፍ አወል መመረጣቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ዋልያዎቹ ለዚህ ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድ ከዮጋንዳ ወይም ከሊቢያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በቅርቡ አሰልጣኝ ሚሉቲን ሰርጆቪች ሚቾ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው የዮጋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዚህ ወር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ተዘግቧል።
ዩጋንዳ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን በመጀመሪያ ወደ ሶሪያ ተጉዞ ሁለት ጨዋታዎች አድርጎ ሁለት ቀናት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ የዮጋንዳ ሚዲያዎች ገልፀዋል።አሰልጣኝ ሚሉቲን ሰርጆቪች ሚቾ የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ባለፈው አመት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም መጫወታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተመሣሣይ ከሊቢያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ በውጭ ሚዲያዎች ቢነገርም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከመቃረቡ በተነሳ በኢትዮጵያ በኩል የወዳጅነት የጨዋታ ዕቅዶች ገና ይፋ አልተደረጉም።
ቦጋለ አበበ