ህፃናት ላይ
ሄድ መጣ የሚል
የአፍንጫ መታፈን እና
ሳል ምክንያቶቹ ብዙ
ቢሆኑም በአብዛኛው ግን
ምክንያቱ የአፍንጫ አለርጂ
ሆኖ ይገኛል የሚሉት
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል
የህፃናት ስፔሻሊስት እና
ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር
ፋሲል መንበር ናቸው::
አፍንጫ አለርጂ ምንድነው? መንስኤው? መፍትሄውስ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ዶክተር ፋሲል የአፍንጫ አለርጂ ላይ እንደ አስም ሁሉ ትክክለኛ መንስኤው ባይታወቅም ብዙ ጊዜ በቤተሰብ ወይም በዘር ሐረግ ሊተላለፍ የሚችል ነው ይላሉ:: አንዳንድ የአለርጂ አይነቶች ወቅትን ጠብቀው ሲመጡ የተወሰኑ ደግሞ አመቱን ሙሉ ሊኖሩ ይችላሉ።
የህመሙ ምልክቶች በአዋቂዎችም በህፃናት ላይም ተመሳሳይ ናቸው። ምልክቶቹም አፍንጫ ማፈን፣ የበዛ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ማስነጠስ፣ የአፍንጫን ዓይንና ጉሮሮን ማሳከክ፣ ራስ ምታት እና ነስር የመሳሰሉት በሙሉ ሄድ መጣ የሚሉ ምልክቶች ናቸው ::
ልጆች ላይ በተለይ የሚታየው ምልክት በአፍ መተንፈስ ሌሊት ማንኮራፋት ተደጋጋሚ የጆሮ ኢንፌክሽን የአፍንጫ ቆዳ መሽብሸብ ሲሆኑ አለርጂ የሚነሳው በቀዝቃዛ አየር፣ የሲጋራ ጭስ፣ የአበባ ብናኝ፣ በረሮዎች፣ የውሻና የድመት ዕዳሪ ሲኖር ነው። ከዚህም ባሻገር ኃይለኛ ሺታ ለምሳሌ ሽቶ፣ ኬሚካሎች፣ የጫማና በሽንት ቤት ሺታ እንዲሁም ከከብቶች በረትም የሚመጣ ሽታ ለአለርጂ መንስኤ ነው፡፡
መፍትሄውስ የአለርጂ በሺታዎችን (አስም የአፍንጫ አለርጂ) ሙሉ ለሙሉ ማዳን አይቻልም፤ ሆኖም ምልክቶችን መቆጣጠር ይቻላል:: የሚከተሉትን ጠቃሚ ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ምልክቶችን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በሀኪም የታዘዘን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ፣ ውሃ አፍልቶ ባዶውን መታጠን፣ ውሃና ጨው አፍልቶ መታጠን፣ የሚያባብሱ ነገሮችን ማስወገድ፣ ከተቻለ የመኖሪያ ቦታን መቀየር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በየቀኑ መሥራት፣ በብርድ ጊዜ አፍንጫን መወተፍ ወይም መሸፈን፣ ድመት ወይም ውሻ ከነኩ በኃላ ወዲያውኑ እጅዎን መታጠብ የሚሉት መደረግ የሚኖርባቸው ጥንቃቄዎች ናቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የጆሮ ኢንፌክሽን “የህፃናት ጆሮ ኢንፌክሽን” በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ህፃናት የጆሮ ውስጥ ኢንፌክሽን (Otitis Media) አንዱ ምልክት ነው። የጆሮ ኢንፌክሽን በአብዛኛው በባክቴሪያዎችና በቫይረሶች አማካኝነት ይከሰታል።
እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት የ3ኛ አመት ልደታቸውን ከማክበራቸው በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ በዚህ ችግር እንደሚጠቁ ጥናቶች ይጠቁማሉ። እነዚህ ለጋ ህፃናት ያልዳበረ የበሽታ መከላከያ ስርአት ስለሚኖራቸውና እንዲሁም ኢስታችያን ቲዩባቸው (ጆሮ፣ አፍና አፍንጫን የሚያገናኝ ቱቦ) አግድም የሆነ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለዚህ ችግር ይጋለጣሉ።
ሌሎች አጋላጭ የሆኑ ነገሮች ደግሞ አስተኝቶ ልጅን ማጥባት፤ የእንጀራ እናት ጡጦን አብዝቶ መጠቀም፤ የጣሳ ወተት መጠቀም፤ በህፃናት ማቆያ ውስጥ መዋል፤ በጉንፋን ህመም መያዝ እና የመሣሠሉት ናቸው፡፡
የጆሮ ኢንፌክሽን ምልክቶች፤ ጆሯቸውን መጎተት፤ የጆሮ ህመም፤ መነጫነጭ፤ ትኩሳት፤ ከጆሮ መግል ወይም ፈሳሽ መውጣት፤ ትውከትና ተቅማጥ፤ ማልቀስ፤ በኦቶስኮፕ (ጆሮን በሚያሳይ መሣሪያ) የሚታይ የታምቡር ማበጥ፣ መቅላት እንዲሁም ፈሳሽ መውጣት ጥቂቶቹ ናቸው።
ወላጆች እነዚህን ምልክቶች ካስተዋሉ በቶሎ ወደ ሀኪም ቤት በመውሰድ ልጃቸውን ማሣከም አለባቸው። ህፃናትን የመጀመሪያዎቹን 6 ወራት ጡት ብቻ ማጥባት፣ ማስከተብ፣ እንዲሁም ንፅህናን መጠበቅ የጆሮ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይጠቅማሉ።
በጊዜ ያልታከመ የጆሮ ኢንፌክሽን ለታምቡር መቀደድ፣ ለማጅራት ገትር፣ እና የመስማት ችግር ሊዳርግ ስለሚችል ህክምናን በተገቢው ሰአት ማግኘት አለባቸው ብለዋል፡፡
አስመረት ብሰራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም