በዓለማችን በተለያዩ አገራት ከሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ውስጥ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በኢንቪስትመንት መስክ የተሰማሩ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የዲያስፖራ አባላት በአንድ አቅፎ የሚያዝ ጥምረት ደግሞ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ቀደም ሲል በየክልሉ የተመሠረቱ የዲያስፖራ ማህበራት ያሉ ቢሆንም እነዚህን ማህበራት በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ ማህበር በማስፈለጉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ጥምረት ተመሰረተ፡፡ ከተመሰረተ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ማህበር አሁን ላይ አገራዊ ጉዳዮችን እያከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ ከማህበሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሶስና ወጋየሁ ጋር ቆይታ አድርገን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል፡፡
ወይዘሮ ሶስና እንደሚሉት፤ የማህበሩ ምሥረታ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በየክልሉ በተናጠል የሚሰሩ ቢኖሩም አገራዊ ሥራ ለመሥራት ደግሞ የጋራ ጥምረት መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ከጥምረቱ ምስረታ በኋላ ማህበሩ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃ እየሰራ ነው ማለት ባይቻልም ፤ በሥሩ ያሉት ማህበራት ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የጥምረቱ አባላት በህዳሴ ግድብ፣ በትምህርት ቤት እድሳት ፣ በችግኝ ተከላ እና በመሳሳሉት ተግባራት ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪ በውጭ ካሉት የዲያስፖራ አባላትና ምሁራ ጋር በመገናኘት በርካታ ሥራዎችን ይሰራል ብለዋል፡፡
በውጭ ያሉ የዲያስፖራ ማህበራት ወይም ምሁራን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በሀገራቸው ላይ ለመስራት ሲፈልጉ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበራት ጥምረት ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም መሠረት ማህበሩ ወደ አገር ቤት መጥቶ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማህበረሰብን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲገናኙ ያደርጋል። ለአብነት ባለፈው ዓመት በውጭ የሚኖሩ ተስፋ የሚባል የዲያስፖራ ማህበር አባላት በመቀበል ከአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበራት ጋር በማገናኘት ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት ብዙ የዲያስፖራ አባላት አገር ውስጥ የሉም የሚሉት ወይዘሮ ሶስና፤ ሆኖም ግን በውጭ ካሉት የዲያስፖራ ማህበራት ጋር ንቅናቄ በመፍጠር ፤ በዲፕሎማሲው ረገድም በተደራጀ መልኩ ለመውጣት የሚያስችል ሥራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዲፕሎማሲው ረገድ ሰው በሚጽፈው ሃሳብ ላይ አስተያየት መስጠት ወይም መጻፍ ሳይሆን የራስን ሃሳብ መግለጽ ላይ አጽኖኦት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የራስን ሃሳብ ይዞ አቋምን በመግለጽ እራሱ የቻለ ግብ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን በኢትዮጵያ የምንገኝ ዲያስፖራዎች በግልም ሆነ በማህበር አገራችንን ለማስተዋወቅ የተቻለንን እየሰራን ነው ያሉት ወይዘሮ ሶስና ፤ በውጭ የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት ስለአገራቸው ጉዳይ መጀመሪያ በቀጥታ የሚጠይቁት እነርሱን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከማወቅ አንጻር በተገቢ መንገድ ትክክለኛ መረጃ በማስተላለፍ ረገድ የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በሌላ በኩል በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራዎች በሀገራቸው ጉዳይ ተስፋ እንዳይቆርጡ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማድረግ፣ እንዲሁም የሚያደርጉት ድጋፍ ህጋዊ በሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያውቃቸው መንገዶች በሙሉ እንዲለግሱ ምክረ ሃሳብ በመስጠት ረገድ የሚሰሯቸው ሥራዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
እንደወይዘሮ ሶስና ገለጻ፤ በውጭ ያለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ብዙ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ሆኖም ከዚህ በላይ በጣም መሥራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በቅርብ እየታየ እንዳለው ኢትዮጵያውያኑ የውጭ ጫናን ለማርገብ እስከ አሜሪካ ሴኔት ድረስ ጥያቄያቸውን በማቅረብ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው፡፡
በተመሳሳይ ደግሞ የአገራችን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ የሀገር ሰላም በመሻት ሁሉም ሰው በሰላም ሰርቶ መኖር የሚችልበት ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊውን ሁሉ ሥራዎች መስራት ይጠበቅብናል፡፡ አሁን ላይ የተፈጠሩ ችግሮች ያሉብንን ክፍተቶች የምናይባቸውና ለወደፊት ከዚህ ተምረን አንድነታችን አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን ትምህርት ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡ በዲፕሎማሲ ረገድ የሚታየው ነገር ከዚህ በላይ ጠንካራ ሥራ መስራት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ሰላም የሚጠይቅ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ያለነው ኢንቨስት እያደረግን እየሰራን ነው የሚሉት ወይዘሮ ሶስና፤ ሩቅ ለሆነ ሰው ግን ነገሮችን አግዝፎ ስለሚያየው ስጋት ውስጥ ይገባል ይላሉ ፡፡ ስለዚህ የእኛ አንዱ ሥራ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ያንን ሥጋት መቀነስ ሲሆን፤ ሌላው ጥሩ ነገር ደግሞ በየክልሉ የዲያስፖራ ማህበራት መኖራቸው ዲያስፖራው የሚፈልገው ክልል ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡ ዲያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ መጥቶ በሚገጥሙት ሂደቶች ተስፋ ቆርጦ ተሰላችቶ ወደኋላ እንዳይመለስ በማገዝ ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ይሰራል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሥራን መሥራት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን እና በተረጋጋ መንፈስ ነው የሚሉት ወይዘሮ ሶስና፤ ሀገር ስትታመም በውጭ ያለው ሰው ወዲያወኑ ይታመማል፤ ይህ ህመም ደግሞ መታከም ያለበት እዚሁ ሀገር ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ትንሹ ነገር ተጋኖ፤ ሌላ ነገር ሆኖ ሀገርን አደጋ ላይ እስከመጣል ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመው፤ በሀገር ውስጥ ያለው በውስጣዊ ነገር በማከም የሚታገዘውን በማገዝ በተቻለ መጠን እራሳችንን አክመን በዓለም ላይ ሁሉ እንዲታከሙ ማድረግ አለብን ይላሉ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያሰብ ሰው ሃሳቡን በሥርዓት በመግለጽ ትውልዱን በማሰብ በሚጽፈው ነገር ኢትዮጵያ ትጎዳለች፤ ልጆቿ ሊጎዱ ይችላሉ የሚለውን አስቦ አመዛዝኖ መጻፍ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
በተጨማሪም ዲያስፖራው ዲጂታል ሚዲያውን በመጠቀም በሁሉም የሶሻል ሚዲያ ፕላት ፎርሞችን የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለአብነትም የዛሬ ዓመት አካባቢ በአውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማህበረስብ ለአባይ ዘመቻ አድርገው እንደነበር አስታውሰው፤ ህጻናት ሳይቀሩ የዘንድሮ የልደት ስጦታዬ ለአባይ ግድብ ግንባታ ይሁንልኝ በማለት በጣም በርከት ያለ ዶላር ለሀገራቸው ድጋፍ ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በአሜሪካ ወይም በሌላ ሀገር ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው በመላክ እነሱም እንዲሁ የልደት ስጦታ ለአባይ እንዲያበርክቱ በማድረግ በዘመቻ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይሄ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ አስፈላጊ መሆኑ የታየበት እንዲሁም የተማርንበት ነው የሚሉት ወይዘሮ ሶስና፤ ብንሠራበት ከዚህ የተሻለ አቅም እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በሀገሩ ውስጥ በውጭም ያለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ለሚናገረው ሆነ ለሚጽፈው ነገር ሰከን ብሎ ነገሮች በማመዛዘን የሚያደርግና ለሚያደርጋቸው ድጋፎች ደግሞ ህጋዊ የሆነ መንገድ መከተል አለበት፡፡ ዲያስፖራው ማህበረሰብ በመተባበር ሀገሩን ከፍ በማድረግ ጽምጽ እንዲሆን እጠይቃለሁ ሲሉ አሳሳበዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013