ከ57 ዓመት በፊት ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ለራሱና ለሃገሩ ሁለተኛውን የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ማስመዝገቡ ይታወቃል፡፡ ይህ ታሪክ የተሰራባት ቶኪዮ ደግሞ ከዓመታት በኋላ በድጋሚ ኦሊምፒክን የማስተናገድ እድል ስታገኝ፤ ለኢትዮጵያዊያን በአዲስ ትውልድ ታሪክ በተመሳሳይ ስፍራ የሚደገምበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በመንግስትና በስፖርት ተቋማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ኦሊምፒኮች የተሻለ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በህዳር ወር/2013ዓም የተጀመረው የኦሊምፒክ ዝግጅት በገንዘብ አቅም፣ በአቅርቦት፣ በስልጠና እና በትኩረት የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝም ነበር፡፡ በታሰበው መሰረትም የማያጣሪያ ውድድሮች እየተካሄዱ በመጨረሻ የተሻሉ ናቸው የተባሉ አትሌቶች ወደ ቶኪዮ ተጉዘዋል። ይሁን እንጂ በሃገር ዓቀፍ ደረጃ ሲሰራበት በቆየውና በሚጠበቀው ልክ ያልሆነ ውጤት ተመዝግቦ ኦሊምፒኩ ተደምድሟል፡፡ ይህም ረጅም ወራት የፈጀው ዝግጅት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን፤ በውድድሩ ወቅት የታየው እንደቀድሞ በቡድን ተጋግዞ አለመስራትና ባልተለመደ መልኩ በርካታ አትሌቶች ውድድሮችን የማቋረጣቸው ምክኒያት ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አባልና አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ዝግጅቱን በተመለከተ፣ ከዚህ ቀደም አትሌቶች ወደ ኦሊምፒክ የሚጓዙት በኢትዮጵያ ቻምፒዮና እንዲሁም ሄንግሎ በሚካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እንደ ሻምበል ቶሎሳ አስተያየት ከዚህ ቀደም በማጣሪያ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉትና ለቡድኑ የሚታጩ አትሌቶች በወቅቱ ባስመዘገቡት አጠቃላይ ሰዓት ተመዝነው ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ተሰባስቦ ወደ ኦሊምፒክ ለመሄድ የብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የሚያደርገውም ሁለትና ሶስት ወራት ብቻ ሲቀሩት ነው፡፡
በዚህ ኦሊምፒክም ቡድኑ የ8 ወራት ዝግጅት ሲያደርግ የቆየበት ምክንያት ከኮቪድ 19 ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ አንጋፋው ኦሊምፒያን እንደ ሙያተኛ ጉዳዩን ሲመለከቱትም ዝግጅቱ ለረጅም ወራት መቆየቱ በአትሌቶቹ ላይ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ እንደ ሃገርም በውጤት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንጂ የጠቀመ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ አትሌቶቹ ጥሩ አቋም ላይ የነበሩት በሄንግሎ ማጣሪያ ወቅት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ከተወሰኑት በቀር የአብዛኛዎቹ አትሌቶች አቋም እንደወረደ ያስቀምጣሉ፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በዓለም አትሌቲክስ አሰልጣኝነት ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂም ይህንኑ አስተያየት ይጋራሉ፡፡ ከዚህ ቀድሞ በተካሄዱ ኦሊምፒኮች ቡድኑ ልዩ ዝግጅት የሚያደርገው ሶስትና ሁለት ወራት ሲቀሩት ነው፤ በዚህ መንገድ ተጉዘውም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በዚህ ኦሊምፒክ አትሌቶች ለ8 ወራት እንዲሰለጥኑ የተደረገው ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አትሌቶች ወደ ልዩ ስልጠና ከመግባታቸው አስቀድመው በፌዴሬሽኑ ይያዛሉ፤ ወደ ዝግጅት እስኪገቡም ኦሊምፒክ ኮሚቴ አይረከባቸውም፡፡ ከቤታቸው እየተመላለሱ በብሄራዊ ቡድን እየሰሩ ቆይተው ሶስትና አራት ወራት ሲቀሩ ማጣራት ይጀመራል፡፡ ከዚያም በየርቀቱ አንድ አንድ ተጠባባቂ ያለበት ቡድን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተረክቦ ወደ ልዩ ዝግጅት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ኦሊምፒክ ግን አትሌቶች ቀድመው ወደ ሆቴል እንዲገቡ የተደረገው በተናጥል ከቤታቸው እየተመላለሱ መስራት ስለማይችሉ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት እንዲሁም ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባወጣው በስፖርት ዝግጅት ፕሮቶኮል መሰረት ነው፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸው አደጋ በመሆኑም ንክኪ በሌለበት ካምፕ ተቀምጠው በየጊዜው ጤናቸውን እየተመረመሩ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
እንደ አንጋፋው ኦሊምፒያንና የረጅም ርቀት አሰልጣኝ ቶሎሳ እምነት፣ ቀድሞ ሲሰራ እንደነበረው ለኦሊምፒክ ለሁለትና ሶስት ወራት ዝግጅት ማድረግ በቂ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንደ ቀድሞው አትሌቶችን በብሄራዊ ቡድን አካቶ ከዓመት ዓመት በዝግጅት ላይ እንዲቆዩ ማድረግ ይገባል፡፡ አንጋፋ አትሌቶች በቋሚነት ብቃታቸው ለዓመታት የዘለቀው ይህንን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነም በማሳያነት ያስቀምጣሉ፡፡ ሌላኛው አማራጭ ደግሞ አሰልጣኞች ኃላፊነት ተሰጥቷቸው አትሌቶችን መርጠውና አሰልጥነው ለውጤት እንዲያበቁ ማድረግ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻላቸውም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ከታዘቡት ነገር ተነስተው ሲሆን፤ የአትሌቶች ተበታትኖ መስራት ለውጤት መጥፋት ዋናው ችግር እንደሆነ ይስማማሉ፡፡
ዝግጅቱ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ረጅም ጊዜን የወሰደ ይሁን እንጂ ከተወሰኑት አትሌቶች በቀር የተቀሩት ይሰሩ የነበሩት ለየብቻና በተበታተነ መልኩ ነበር፡፡ አትሌቶችን በጋራ በማሰራት የቡድን መንፈሱን ማጠናከር የሚቻል ቢሆንም በተግባር የታየው ግን ቡድን በማይመስል መልኩ ለየብቻ በመስራቱ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ አትሌቶች የሚሰለጥኑት በግል አሰልጣኞቻቸው ነው፡፡ እንደ ቡድን ዝግጅት ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ ለወደፊቱም አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥምና ውጤቱም ከዚህ በበለጠ ሊዘቅጥ እንደሚችል ሻምበል ቶሎሳ ስጋታቸውንም አጋርተዋል፡፡
የስፖርት ሳይንስ ባለሙያውም ስልጠናው የተበታተነና ዲሲፕሊን በጎደለው መልኩ ይካሄድ እንደነበር ያነሳሉ። እንደ ቡድን አትሌቶች ሙሉ ለሙሉ ሆቴል ገብተው አሰልጣኞች ያወጡትን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በአንድነት የሚሰሩበት ሁኔታ መኖር ነበረበት። ይሁን እንጂ ይህ እንዳልነበረ መገንዘብ እንደሚቻል ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ለአብነት ያህል የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር አትሌቶች በአንድ ላይ መስራት ይገባቸው እንደነበርም ያስቀምጣሉ፡፡ ሆኖም በተበታተነ መልኩ አሰልጣኞች የየራሳቸውን አትሌት ይዘው የአንደኛውን ስራ ሌላኛው በማያውቅበት መልኩ ነበር የሚካሄደው፡፡ ይህም ለቡድኑ መዳከምና ስነልቦና ዝግጁ አለመሆን ምክንያት እንደነበረም ያምናሉ፡፡
ውድድር ከማቋረጥ ጋር በተያያዘም አንድ አትሌት ውድድር ሲያቋርጥ ታሳቢ የሚደረገው ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳት ሲደርስበት፣ የአቅም ማነስ እንዲሁም የስነ ልቦና ችግር ሲኖርበት ነው፡፡ ይህ አስተያየት ከነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት የሚሰጥ መላምት በመሆኑ በስፋት ለመገንዘብ አትሌቶቹን አግኝቶ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ብቻም ሳሆን ተሳትፎም ዋጋ ያለው ቢሆንም ተፎካካሪ በመሆን የሃገርን ገጽታ መገንባት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ አካሄድ ለወደፊት አደገኛ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ባለሙያው ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ውጤት ማጣት ብቻም ሳይሆን አትሌቶቹ ለወደፊትም ተፎካካሪ የሚሆን አቅም አይኖራቸውም፡፡ የአሸናፊነት መንፈስና ስነልቦና ይዘው መወዳደር አይችሉም፣ ፈሪ ይሆናሉ፣ ከፈሩ ደግሞ ውጤት አይመጣም፡፡›› የሚሉት ባለሙያው ለምሳሌ ያህል እአአ በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ በወንዶች ማራቶን በተመሳሳይ ሁሉም አትሌቶች አቋርጠው የወጡበትን አጋጣሚ ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላም እነዚህ አትሌቶች አቅማቸውን አጎልብተው ውጤት በማምጣት ሃገራቸውን መወከል አልቻሉም፡፡ ምክንቱ ደግሞ ስነልቦናቸው በመጎዳቱ ነው፡፡
አሰልጣኝ ቶሎሳ በተነሱት ችግሮች ላይ ‹‹ፌዴሬሽኑ ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል፤ ኋላፊነቱን የወሰደው አሰልጣኝም ተጠያቂ መሆን አለበት›› ሲሉም ይጠቁማሉ። ከመነሻው እንደ አሰልጣኝ አትሌቶችን ተቆጣጥሮ በጋራ ማሰራት አለመቻል ከምን የመነጨ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡ አሰልጣኙ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት የአሰልጣኞች አመራረጥን ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ እየተተገበረ የሚገኘው በርካታ አትሌቶችን ባስመረጠ የሚል መሆኑ፤ አሰልጣኞች በራሳቸው አትሌቶችን መቆጣጠር በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ አሰራር የራሱ ጉዳት ያለው መሆኑን እንደ ቴክኒክ ኮሚቴ የተስተዋለ ጉዳይ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊስተካከል የሚገባ እና እርሳቸውም እንደ ኮሚቴ አባልነታቸው የሚሰሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብርሀን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013