
አመት የተራዘመው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከሰሞኑ ሲካሄድ ሰምብቶ መቋጫውን አግኝቷል። ጃፓንም ከበርካታ ሀገራት ሲደርሳባት የነበረውን ጫና ተቋቁማ ኦሎምፒኩን በስኬት አካሂዳ ደምድማለች። የአለማችን ሶስተኛዋ ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ቁንጮ ጃፓን እንደ ኦሎምፒክ አዘጋጅነቷ በእጅ አዙር ዳጎስ ያለ ገቢ ታገኛለች ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን በኮቪድ- 19 ፕሮቶኮል መሰረት ሀገራት ሙሉ የልኡክ ቡድናቸውን ባለመላካቸው ያሰበቸውን ያህል አላገኘችም። እንዲም ሆኖ ግን በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተንሸራቶ የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከኦሎምፒክ ውድድሩ በፊት አስቀድሞ ወደ ቦታው መመለሱን ቢቢሲ በድረገፁ ከትናንት በስትያ አስፍሯል።
የጃፓን ኢኮኖሚ በወረርሽኙ ይደርስበታል ተብሎ ከታሰበው ማሽቆልቆል ከኦሎምፒክ ውድድሩ በፊት በፍጥነት ማገገሙን ያስታወቀው የቢ ቢ ሲ መረጃ፤ ከሀገሪቱ በተገኙ ይፋዊ መረጃዎች መሰረት የአለማችን ሶስተኛዋ ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ቁንጮ ጃፓን ኢኮኖሚዋ ከሚያዝያ አስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ከተተነበየው በሁለት እጥፍ ማደጉን ገልጿል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ዳግም የተቀሰቀሰውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለማረጋጋት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በድጋሚ እንዲታወጅ በመደረጉ በአራተኛ ሩብ አመት ላይ የኢኮኖሚ እድገቱ በመካከለኛ ደረጃ ላይ እንደሚሆን ከወዲሁ ተንታኞች መናገራቸውን አመልክቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ አዲሱ አሃዝ የጃፓን ትልቋ ጎረቤት ሀገር ቻይና ኢኮኖሚያዊ ማገገም እየተዳከመ ስለመምጣቱ ማሳየቱንም መረጃው ጠቁሟል።
የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች የጃፓን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርት በተያዘው የፈረንጆቹ ሁለተኛ ሩብ አመት የ1 ነጥብ 3 ከመቶ እድገት እንደሚያሳይ መጥቀሳቸውንም መረጃው ያመለከተ ሲሆን ይህም የሆነው ካለፉት ሶስት ቀዳሚ ወራቶች በፊት ከነበረው የ3 ነጥብ 7 ከመቶ ቅናሽ በኋላ መሆኑንም አስታውቋል።
የቅርብ ጊዜዎቹ አኃዞች ከሚጠበቀው የ 0 ነጥብ 7 ከመቶ እድገት እጅግ በጣም የተሻሉ እንደነበሩና የግለሰቦችና የቢዝነሶች እለታዊ ወጪዎች ኢኮኖሚው ኮቪድ- 19 ሊያሳድርበት የሚችለውን ተፅእኖ እንዲቀንሰውና ወደ ነበረበት የእድገት ደረጃ ላይ እንዲመለስ ማስቻሉንም መረጃው አመልክቷል።
ሆኖም የጃፓን ኢኮኖሚያዊ ማገገም ከሌሎች በኢኮኖሚ ከመጠቁና የጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው በሁለተኛው ሩብ አመት ከ6 ነጥብ 5 ከመቶ በላይ ሆኖ በተመዘገበበት እንደ አሜሪካን ከመሰሉ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ቀርፋፋ መሆኑም በመረጃው ተብራርቷል። የጃፓን ኢኮኖሚያዊ ማገገም ቀርፋፋና ደካማ መሆን የሀገሪቱ መንግስት የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለማስቆም እያደረገ ያለውን ትግል እንደሚያሳይም በመረጃው ተጠቁሟል።
ይህ መረጃ ይፋ ከሆነ በኋላ የጃፓን ኢኮኖሚ ሚንስትሩ ያሱቶሺ ኒሺሙራ ‹‹ስለሀገራዊ ጠቅላላ ምርቱ የተደበላለቀ ስሜት ነው ያለኝ›› ሲሉ መግለፃቸውንም ዘገባው ተናግሮ፤ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራው ሥራ የቫይረሱን ሥርጭት መግታት ነው። የቫይረሱ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጣም ከባድ ይሆናል ሲሉ መደመጣቸውንም ዘገባው ገልጿል።
እ.ኤ.አ በ2020 የጃፓን ኢኮኖሚ ከ4 ነጥብ 8 ከመቶ በላይ የተኮማተረ ሲሆን ይህም በአስር አመታት ግዜ ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑንም መረጃው ለትውስታ አቅርቧል። ምንም እንኳን በጃፓን የክትባት መርሃ ግብሩ አዝጋሚና ጠንካራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች የሰዎች የቀን ተቀን የወጪ ፍጆታውን ቢጎዱትም ለወጪ ንግድ መነቃቃት ምስጋና ይግባውና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፈው አመት ከነበረበት የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ አጣብቂኝ መላቀቅ እንደቻለም ዘገባው አብራርቷል።
በተመሳሳይ በሌሎች የእስያ ሀገራት የሚታየው ልውጥ የኮቪድ- 19 ዝርያ/ ኮቪድ ዴልታ/ በተለይ የጃፓን አምራቾችን የአቅርቦት ሠንሰለት ይበልጥ እንዳይረብሸውና ይህም በተለይ የፋብሪካ ውጤቶችን ሊጎዳ እንደሚችል ከዚህ ባለፈም ወጥነት የጎደለው የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ማገገም ይበልጥ አደጋ ውስጥ እንዳይከተው ስጋት እንዳለም በመረጃው ተጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በቻይና የፋብሪካ ውጤቶችና የችርቻሮ ሽያጭ ከባለፈው ወር አንፃር ቀስ በቀስ እየተነሳ ስለመምጣቱም በዘገባው ተጠቅሷል። ይህም የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና አዲስ የኮቪድ- 19 ዝርያ መከሰት ቢዝነሶችን በመረበሹ የአለማችን ሁለተኛዋ ግዙፍ ምጣኔ ሀብታዊ ባለቤት ቻይና ኢኮኖሚያዊ ማገገም እየተዳከመ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ምልክት ነው ሲል የቢ ቢ ሲ ዘገባ በመቋጫው አስቀምጧል።
የጃፓን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በሁለተኛው ሩብ አመት የ1 ነጥብ 3 ከመቶ እድገት እንደሚኖረው ይጠበቃል፤
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013