መንትዮቹ ሃኪሞች ዶክተር ኢየሩሳሌም ጌታሁን እና ዶክተር ቃልኪዳን ጌታሁን ሻሸመኔ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሻሸመኔ ካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኩየራ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሜዲካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ማዕረግ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሀያት ሜዲካል ኮሌጅ በህክምና በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል። በአሁኑ ወቅት በግላቸው «ትዊንስ ክሊኒክ»ን በመክፈት በሙያቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። መንትዮቹ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በየክፍሉ ደረጃ በአንድ ወንበር ላይ ተቀምጠው ተምረዋል። ፍላጎታቸውና የልጅነት ህልማቸው አንድ አይነት በመሆኑ ሀኪም መሆንን ይመኙ ነበር። ምርጫቸውም አንድ አይነት ነበር። የሚፎካከሩት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሳይሆን እርስ በርሳቸው ነበር። አንድም ጊዜ በመካከላቸው ሌላ ተማሪ ሳያስገቡ እየተፈራረቁ ነበር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የሚይዙት። ልዩነት ቢመጣም እጅግ በጣም ጥቂት ነጥቦች ይሆናል። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እሥከሚጨርሱ ድረስ የመምህሮቻቸው ድጋፍ አልተለያቸውም። የፈተና ውጤታቸው አንድ አይነት እየሆነ ያስቸገራቸው መምህራን ቦታ በመቀያየር ቢፈትኗቸውም ውጤቱ ያው ነበር የሚሆነው። ሲሳሳቱም ተመሳሳይ፤ ሲሰርዙም እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ ከመጀመሪያ ደረጃው ብዙም የተለየ አልነበረም። ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥባቸው ከፍተኛ ቢሆንም በአጋጣሚ ወደ ህክምና ትምህርት የሚያስገባቸው አልነበረም። ሁለቱም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ነበር ምርጫቸው ያደረጉት።
ላቦራቶሪን ለመማር ፈለጉ ተሳካላቸው። በምርጫቸው መሰረትም አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንዳይነት የትምህርት ክፍል፤ ብሎም አንድ ዶርም በአንድ ተደራራቢ አልጋ ላይ ተኝተው ተማሩ። ተጋግዘው ስለሚያጠኑም በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቁ። በዚህ ወቅት ነበር በህይወታቸው አስቸጋሪ የሚባለው ጊዜ የተከሰተው። ዶክተር ኢየሩሳሌም በጥቂት ነጥብ በልጣ ስለነበር ትምህርት ሚኒስቴር ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ይመድባታል። ለመጀመሪያ ጊዜ መለያየታቸው እርግጥ የሆነው ያኔ ነበር። ዶክተር ኢየሩሳሌም ለስልጠና ወደ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታመራ ለዶክተር ቃልኪዳን ውስጧ እየሩሳሌም ካላንቺ መኖር አይሆንላትም ይላት ነበር። እርሷ ሀያት ሜዲካል ኮሌጅ ለህክምና ትምህርት ስትመዘገብ እህቷንም አስመዘገበቻት። እንዳሰበችውም ሆነና ዶክተር ኢየሩሳሌም የጅማ ዩኒቨርሲቲን መምህርነትን ትታ ወደ አዲስ አበባ መጣች። አስቸጋሪ የሆነባቸውን የመለያየት አጋጣሚ አስወግደው ዳግም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሀያት ሜዲካል ኮሌጅ ተማሩ። መንትዮቹ ዶክተሮች እስካሁን ባለው የህይወት ጉዟቸው ለአንድ ወር ብቻ ተለያይተዋል። ያንንም እንደ አስቸጋሪ ጊዜ ያስታወሱታል። 15 ቀን ለስልጠና አዳማ ዩኒቨርሲቲ እያለች፤ ቀጣዩን 15 ቀናትም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስራ ስትጀምር። እንደዛም ሆኖ ቢያንስ በሳምንት ሁለትና ሶስት ጊዜ ይገናኙ ነበር። ከዚህ ውጭ አስካሁን በመንፈስም ሆነ በአካል የለያቸው አጋጣሚ አልተፈጠረም። የተግባር ትምህርታቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተማሩ።
የአንድ ዓመት ልምምዳቸውንም እዛው አገልግለዋል። በማዕረግ ተመርቀው ከወጡ በኋላም ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሻሸመኔ በመልካ ኦዳ ሆስፒታል ተመድበው ለተወሰነ ጊዜ አገልግለዋል። ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ክሊኒክ በመክፈት በግላቸው መስራት ጀመሩ። መንትዮቹ ዶክተሮች ክሊኒክ ለመክፈት ሲያስቡ የመጀመሪያ ስራቸውን ያደረጉት ብዙ ህዝብ የሚኖርበትንና ክሊኒክ የማይበዛባቸውን አካባቢዎችን በማጥናት ነበር። በጥናታቸው መሰረት ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ገና በመልማት ላይ ያለ፤ የህክምና ተቋማትም ያልተስፋፉበት በመሆኑ ምርጫቸው አደረጉት። ስያሜውንም «ትዊንስ ክሊኒክ» አሉት። የትዊንስ ክሊኒክ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅነቱን ኃላፊነት በአምስት ደቂቃ ቀድማ የወጣችው ዶክተር ኢየሩሳሌም ተረከበች።
ክሊኒኩ በህክምና መሳሪያዎች የተሟላ ነው። የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል። በላቦራቶሪ፣ በአልትራሳውንድ በመታገዝ የእናቶች እርግዝና ክትትል፣ መለስተኛ የቀዶ ህክምና ከጳውሎስ ሆስፒታል በሚመጡ ስፔሻሊስት ሀኪሞች በመታገዝ ሙሉ ህክምና ይሰጣሉ። በታካሚዎች ፈቃድ ሁለቱም ዶክተሮች በአንድ ላይ የሚመረምሩበት አጋጣሚም ብዙ ነው። በቋሚነት ለ10 ባለሙያዎች፤ በትርፍ ሰዓት ለ6 ሰራተኞች የስራ እድል በመፍጠር እራሳቸውን አግዘው የአካባቢውን ማህበረሰብ በማገልገል ላይ ናቸው።አሁን ያሉበትን ደረጃ መነሻቸው መሆኑን በማመናቸው የማህበረሰቡን ፍላጎትና ያለውን ክፍተት በመለየት በተለያዩ ሙያዎች ስፔሻላይዝ ለማድረግ ይፈልጋሉ። መንትዮቹ ዶክተሮች የሚዝናኑት እርስ በርሳቸው ነው። ዶክተር ቃልኪዳንን የምታዝናናት ኢየሩሳሌም ስትሆን፤ ዶክተር ኢየሩሳሌምን የምታዝናናት ደግሞ ቃልኪዳን ብቻ ናት። የሁለቱም ደስታ ያለው በሁለቱ ውስጥ ነው። ሁለቱም እናታቸው ጋር ወይም ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ጋር በማሳለፍ ይዝናናሉ። ሻይ ቡና የማለት ሀሳብ ካላቸው ይቀዳደሙ ይሆናል እንጂ ምርጫቸው አንድ ቦታ ይሆናል። የቴሌቪዥን ፕሮግራም ምርጫቸው፣ የመጽሀፍ ምርጫቸው፣ ስፖርት የመስራት ፍላጎታቸው አንድም ቀን ተጋጭቶባቸው አያውቅም። በቀለም፣ በምግብ፣ በቦታ ምርጫ ሳይቀር አንዷ ያሰበችውን የአንዷም ምርጫ ይሆናል።
አሁን አንድ ላይ ስለሚኖሩ ስለሚመካከሩም የአለባበስ ምርጫቸው አንድ አይነት ነው። ወደፊት ህይወት በትዳር ልትለያያቸው ግድ ይላልላና ምን አስበው ይሆን? የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው። «የግል ኑሮ መኖሩ አይቀርም ግን በእርግጠኝነት አንድ ዓይነት አለባበስና አንድ ዓይነት የጸጉር ስታይል ይኖረናል። ምክንያቱም እኔ ልለብስ ያሰብኩትን ልብስ እሷ አውጥታ ትጠብቀኛለች። አሁንም አንዳችን ነን የሁለታችንንም ልብስ የምንመርጠው። ስለዚህ ተለያይተን ብንኖርም እኔ የምፈልገውን ልብስ ለብሳ እንደምትወጣ እርግጠኛ ነኝ» በማለት የመለሰችልኝ ዶክተር ቃልኪዳን ነበረች።
ሌላ ጥያቄ ለዶክተር ቃልኪዳን አስከተልኩላት በጣም የወደድሽው ልብስ አንድ ብቻ ቢሆን ምን ታደርጊያለሽ? መልሷ ፈጣን ነበር። «በርግጠኝነት አልገዛውም! አሁን ትልቅ ሆንን ያን ያህል የምርጫ ችግር ላያጋጥመን ይችላል፤ ነገር ግን ልጅ እያለን እናታችን ስትገዛልን አንዳይነት ልብስ ሆኖ መጠነኛ የአበባ ልዩነት ቢኖረው እንኳን አንለብሰውም። ታስቀይረዋለች እንጂ አንለብሰውም» መንትዮቹ ሀኪሞች ከፍተኛ የሆነ የጊዜ እጥረት እንደሚኖርባቸው ይታመናል። ነገር ግን እውቀታቸውን ለማህበረሰቡ ለማካፈል መሻታቸው ብዙ በመሆኑ ካላቸው ጊዜ ቀንሰው ሳይሆን ማህበራዊ ኃላፊነታቸው የሚወጡበት እንደሆነ አምነው በቂ ጊዜ መድበዋል። ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የዘመን ሀኪም ሆነዋል።
የዘመን ሀኪም ለመሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣን እንዴት መረጣችሁት?
‹‹አዲስ ዘመን ጋዜጣን የመረጥንበት ምክንያት 78ኛ ዓመቱን የያዘ ሀገራዊ ጋዜጣ ነው። እዚህ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ መስራት እንደ እድል ነው የቆጠርነው። ብዙ አንባቢ እንዳለው ስለምናምን በቀላሉ ማህበረሰቡን ለማገልገል የተሻለ አማራጭ ይሆንልናልና ቀዳሚ ምርጫችን አድርገነዋል»
ከአንባቢ ምን ትጠብቃላችሁ?
«ከአንባቢያን ጥሩ ምላሽ እንደሚኖር እንጠብቃለን። ለሚመጡ ማናቸውንም ጥያቄዎች በምንችለው አቅም ለመመለስ ዝግጁ ነን። የሚሰጡንን ማንኛውንም አስተያየት በመቀበል ፍላጎታቸውን ለማርካት ጥረት እናደርጋለን»
አንባቢዎች ጥያቄዎቻቸውን በምን መልኩ ቢልኩ ይመቻችኋል?
«አንባቢዎቻችን ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን እንዲያገኙ ጥያቄዎቻቸውን በተቀመጡት የጥያቄ ማቅረቢያ አማራጮች ቢልኩ ይመቸናል። ጥያቄዎቹን በማደራጀትና መረጃዎችን በማሰባሰብ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን››
መልዕክት
‹‹ እኛ የዘመን ሀኪም በመሆናችን እጅግ በጣም ደስተኞች ነን። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አክብሮ ይሄን እድል ስለፈጠረልንም ከልብ እናመሰግናለን። አንባቢዎችም ማወቅ የሚፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ ተከታትለን ምላሽ እናቀርባለን። አንባቢዎቻችንም ጥሩ የጤና ግንዛቤ እንደሚያገኙ እናምናለን። እንደምትማሩበትና እንደምትጠቀሙበት እርግጠኞች ነን» ውድ አንባቢዎቻችን አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአዲስ ዘመን ቅዳሜ ከሚስተናገዱት አሳታፊ አምዶች መካከል ይህ «የዘመን ሀኪም» የተሰኘው አምዳችን ከእናንተ ለሚቀርቡ ጤናና ጤና ነክ ጥያቄዎች ምላሽ የሚቀርቡበት ነው።በየትኛውም የጤና ችግርዎ ለሚያነሷቸውጥያቄዎች በመንትዮቹ ዶክተሮች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጥበታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ዳንኤል ወልደኪዳን