ሰሞኑን የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳና የቢቢሲው ሀርድቶክ አዘጋጅ ስቴፈን በከፍተኛ ደረጃ የመወያያ ርእስ ሆነው ሰንብተዋል።
ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያው ሞቅ ደመቅ ብሎ እየተስተናገደ ያለ ሲሆን በተለይ አንዳንዶች ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ከማየትም ባለፈ መረጃዎችን እያጣቀሱ ሞግተዋል፤ ጌችን “ምነው ቢቀርብህ” ከማለትም አልፈው “ሲያልቅ አያምር” አይነት አስተያየታቸውን ሁሉ የሰጡ አሉ። ከእነዚህም አስተያየት ሰጪዎች መካከል ሀሳባቸውን ከዚህ በታች ያሰፈርንላቸው ፌስቡከር ሀይማኖት ዘለቀ ይገኙበታል።
የጌችን በሀርድቶክ ሀርድ መብላት ጥንቅቅ አድርገው የተመለከቱና ያዳመጡት ወ/ሮ ሀይማኖት የጌችን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ነበር የገለፁት፤
ጌታቸው ረዳ ከBBC Hard talk አዘጋጅ Stephen Sackur ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ተመለከትኩት፤ ከ35 ደቂቃ በላይ በፈጀው በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ጌታቸው ‘ዐቢይ አሕመድ’ የሚለውን ስም ከ100 ጊዜ በላይ እየመላለሰ ከመደጋገምና ከማመንዠኩ በቀር ጠብ የሚል ቁም ነገር አላገኘሁበትም።
እውቁና በምርመራ ጋዜጠኝነት ፈር ቀዳጅ የሆነው Stephen Sackur ዐቢይ አሕመድ እያልክ ለምን ታላዝናለህ፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የአንተም መሪ ነው፣ ወደድክም ጠላህም በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጠ ህጋዊ (Legitimate) መሪ ነው በማለት ኩምሽሽ አድርጎታል። Stephen Sackur በዚህ ቃለ ምልልስ በበቂ ዝግጅት በሰከነ መልኩ፣ ሪሰርች አድርጎ፣ በሙሉ የራስ መተማመን መንፈስ ላነሳቸው ጥያቄዎች ጌታቸው እንኳን ምላሽ ሊሰጥ ይቅርና ሲንተባተብና ሲዘላብድ ነበር የተስተዋለው።
የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ሊበታትንና ሊያፈርስ መነሳቱን፣ ለመገንጠል እየሰራ እንዳለ፣ በማይካድራ ጁንታው የፈፀመውን ዘር ማጥፋት፣ በቅርቡም በአፋር የፈፀመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ላብ ላብ እያለው እንዲውጠው አድርጎታል። ቁና ቁና አስተንፍሶታል።
ጦርነቱን በማባባስ እዚህም እዚያም አጎራባች ክልሎችን በመውረር ህዝባችሁንና የኢትዮጵያን ህዝብ ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለተለያዩ እንግልት እየዳረጋችሁት ነው በሚል በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የሚለው አጥቶ እስኪንተባተብ ሞግቶታል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለዚህ ነው መላው ህዝብ ከከሃዲውና አሸባሪው ቡድን ራሱንና ሀገሩን እንዲከላከል ጥሪ ያቀረቡት ሲልም አስረግጦ ነግሮታል።
በአጠቃላይ ሲታይ ይህ እውቅ ጋዜጠኛ Stephen Sackur በበቂና ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ጁንታው ወራሪና ተናካሽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳ ባንዳና ተላላኪ ኃይል እንደሆነ ለዚህም የትግራይ ምንም የማያውቁ ህፃናትን ለጦርነት ያሰለፈ መሆኑን በጥያቄዎቹ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው እየደጋገመ ከማስረጃዎች ጋር ቢያቀርብም ከእብሪት ድንፋታ ውጭ ትርጉም ያለው ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ጋዜጠኛው ጁንታውን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ በአሸባሪው ማንነቱ እንዲጋልጥ አድርጎታል። እናም እንዲህ አይነቱን በምክንያታዊነት የሚያምን ለእውነትና ለፍትህ የቆሙ ሚዛናዊ አእምሮ ያላቸውን ጋዜጠኞች ያብዛልን እላለሁ።
ይሄው ነው። በሀርድቶክ ሀርድ ለበላው ጌች (የአቶ ረዳ ልጅ) የሀርድቶክ ቆይታውን በተመለከተ ከዚህ፤ ከወ/ሮ ሀይማኖት ዘለቀ ከገለፁት በላይ ማለት “አልኩ ለማለት” ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ማለት አይቻልምና ስለቅድመ ሀርድቶኩ ጌታቸው ረዳ አንዳንድ ገጠመኞቻችንን እያነሳን እንጨዋወት።
ጌች በጁንታው አማካሪነቱ ምክንያት የጁንታው ጣራ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ አንደበቱ መለያ ድንበር የሌለ ያህል እስኪቆጠር ድረስ ሰፍቷል። ንግግሩ ሁሉ ወደ ጠብ እንጂ ወደ ሰላምና ፍቅር የሚያመጣ አንዳችም ነጠላ ቃል የለውም። የቃላት ምርጫው ሳይቀር ደመ ነፍሳዊ ነው፤ አካሄዱ ሁሉ የጎድን ሲሆን አስተያየቱ ሁሉ አውዳሚ ነው። ይህ አውዳሚነቱ ደግሞ በቅድሚያ ቆሜለታለሁ ለሚለው ለምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ሲሆን፤ ጦሱ ለጎረቤት አካባቢዎችም፣ በተራዛሚውም ለአገራችንና በተለይም ለቀንዱ ቀጠና የሚተርፍ ነውና (“ፓርቲው ከነጭራሹ ነው መጥፋት ያለበት” የሚሉ ወገኖች አንዱ ምክንያታቸው ይሄው ነው) ሊቀጣ እንደሚገባው ህዝባዊ ስምምነት ላይ ከተደረሰ ሰንብቷል።
ጌች በአካልና አምሳል አይሁን እንጂ በወኔ፣ ቃላት ምርጫና በደረቅ ፕሮፓጋንዳ ነዥነት፤ እንዲሁም በመጨረሻዋ ደቂቃ ውስጥ ሆኖ የመጀመሪያውን አይነት ወኔና ሞራል ለማምጣት ከመፎከር አኳያ የሳዳም ሁሴንን ማስታወቂያ ሚኒስትር ቁጭ ነው።
የሳዳም ሁሴን ማስታወቂያ ሚኒስትር በቅጽል ስማቸው ኬሚካል አሊ ጎርፉ ከስር እየሸረሸራቸው፣ ሁኔታዎች እየሆኑ እንዳልሆኑ እየሆኑ፤ ቀኑ እየመሸ ብቻ ሳይሆን እየጨለመባቸው ሁሉ “አሸንፈናል” በማለት መሳቂያ መሳለቂያ መሆናቸው እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ የፖለቲካ ክስረትና ውድቀት ማስተማሪያ ሀ — ሁ—- ሆኖ ይገኛል።
“የእድሩ ስንፈት ነው እንጂ …” እንደሚባለው ሆነና ቀባሪ አጥቶ ነው እንጂ ህወሓት ከሞተ ቆይቷል። “በአካል አለ አይደለም እንዴ?” የሚል ካለም እሱ “የፖለቲካ ሞት” (ፖለቲካል ዴዝ) ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባውምና ወደ ኋላ ቀርቷል ማለት ነው።
ጁንታው ከድፍን 27 አመታት በላይ “መንግስት” ሆኖ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ አገርና ታላቅ ህዝብ የእውር ድንብሩን አስተዳድሯል። በሰራው ሀጢያት ወደ ገሀነም ሲወረወር ግን የሰራውን ከሀጢያቶች ሁሉ የከፋ ሀጢያት ረሳና፤ በነጭ ሰረዘ ደለዘና “ማንም ከነበርኩበት መንበርና ወንበር ሊገለብጠኝ ቀርቶ ሊነቀንቀኝ አይገባም” በማለት (ፍትህ መጽሔት በሽፋን ሥእሏ “ከደደቢት እስከ ደደቢት” እንዳለችው) ተመልሶ ወደ ደደቢት። “የፖለቲካ ሞት” ያልገባው ካለ ይህ የአሸባሪው ቡድን “ከደደቢት እስከ ደደቢት” ጉዞ በሚገባ ይመልስለታል ብለን እናስባለን።
ጌታቸው ወታደር አይደለም፤ ጌታቸው የፖለቲካ ሰው አይደለም፤ ጌታቸው ታጋይ ከሚባሉትም አልነበረም። ጌታቸው ምንም አልነበረም። ጌች እዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ የገባው ቀጥታ ከመምህርነት ወደ ሚኒስትርነት ይመጣ ዘንድ፤ የስልጣን አክሊሉን ይደፋ ዘንድ ፓርቲው መሰላል ሆኖ ስላገለገለው ብቻ ነው፡፡ያለመክሊቱና ክህሎቱ ሀገርን በኮሚኒኬሽን ሚኒስትርነት ሲመራም እንደነበር የቢቢሲ ሃርድ ቶክ አጋልጦታል፡፡ ዛሬ ይህ ሁሉ እሳት የሚነድበትና የፖለቲካ ሞቱን እለት በእለት እየተጎነጨ ያለውም ከክህሎት አልባነቱ በተጨማሪ የያዘውም አንዳች እውነት ባለመኖሩ ነው።
ጌች በገዛ አገሩ ላይ በማሟረት የእስከዛሬዎቹን ባንዳዎች ሁሉ ክፉኛ፣ ላይደርሱበት ሰቅሏል (እንደ መምህርነቱ “መስቀል”ን ያውቀዋልና አናብራራውም)። “ክፉኛ” ስንል ያጋነንን የመሰለው ካለ እሱ እዚህ አገር አልነበረም፤ ወይም ሰሞኑን በሀርድቶክ ሀርድ የበላውን ጌች አያውቀውም፤ ወይም የጌች ቲፎዞ ነው ማለት ነውና እዳው ገብስ ስለሆነ እንለፈው። ስናልፈው ግን ለአስተያየትም፣ ለፍርድም፣ ለታሪክም በሚበጅ መልኩ ለሰቃይነት ያበቃውን “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን” ያለውንና ከአንድነት ሀይሎች “ኢትዮጵያን ለማዳን እስከ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን” ተብሎ የተሰጠውን መልስ ጠቅሰን ነው።
ባጭሩ፣ ጌታቸው ረዳ የብዙዎቹን ስህተት እየደገመ ነው ያለው። ከራሱ ባልደረባ ሴኩቱሬ ጀምሮ የሳዳም ማስታወቂያ ሚኒስትር፤ ከሱም በፊት የሂትለር ህዝብ ግንኙነት ሹም የፈፀሙትን ታሪካዊ ስህተት እየደገመ ሲሆን፤ እነሱ የተጎነጩትን ፅዋም ለመጎንጨት የአንድ እርምጃ ግማሽ የቀረው ሁሉ ይመስላልና መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት ስንል እንደማንኛውም ሰው በሰብአዊ ርህራሄ ነው።
Mኣr
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013