ጸሐፊና አዘጋጅ፡- ሞገስ ታፈሰ(ፒ.ኤች.ዲ) የፊልሙ ርዝማኔ፡- 1፡40 የፊልሙ ዘውግ፡- ትውፊታዊ ፊልም ተዋንያን፡- ዘሪሁን ሙላቱ (እንደ ጎበዜ)፣ የምሥራች ግርማ (እንደ አለሜ)፣ ተስፋዬ ይማም (እንደ ጎንጤ)፣ ፍሬሕይወት ከልክሌ (እንደ ንግስት ዘውዲቱ) እና ሌሎች
‹‹ፊልም ለምን ታያላችሁ?›› ብለን ወጣቶችን ብንጠይቅ ‹‹ለመዝናናት›› የሚሉን ይበዛሉ። ለዚህም ይመስላል ብዙ ጊዜ ፊልም የሚያዩት ቅዳሜና እሁድ ወይም በሌሎች የዕረፍት ቀናት የሚሆነው። ምናልባት በሥራ ቀን ስለማይመች ይሆናል። ለመዝናኛ መሆኑን የምናውቀው ግን ብዙ ወጣቶች ‹‹ምን ያዝናናሃል?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ፊልም›› ስለሚሉ ነው። ለመከራከር እነዳታስቡ! ፊልምን ለመዝናኛነት ብቻ ሳይሆን ለመማሪያም የሚያዩት እንዳሉ አሳምሬ አውቃለሁ። ለዚህም ምሳሌ ይኖረኛል። ወጣቶች ተሰባስበው በሚያወሩበት አጋጣሚ ሀሳብ ከተነሳ የፊልም ታሪክ ማንፀሪያ ይሆናል። እንደፊልሙ ይዘት ፍቅር፣ ታሪክም ይሁን ፖለቲካ ለሀሳብ ማጠናከሪያነት ይጠቀሙበታል። የፊልሙ ገጸ ባህሪያትም በቀልድም ይሁን በቁም ነገር በገሃዱ ዓለም ላይም ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። እነዚህ ወጣቶች ለምን በፊልም ተፅዕኖ ሥር ወደቁ? ይሄ የኪነጥበብ ጉልበት ነው። ለዚህም ነው የፊልሞች ይዘት ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚነሳው። ወጣቶችን የመቀልበስ ሃይል ስላላቸው።
ለዛሬው ከፊልም ወቀሳ ልወጣ ነው (እሰየው ነው!)። በቅርቡ ‹‹ቁራኛዬ›› የተሰኘ ፊልም ሲኒማ ቤቶችን ተቀላቅሏል። ፊልሙ እስካሁን ከተደጋገሙት ፊልሞች ለየት ያለ ነው። ስካርን፣ ዝሙትን፣ ሴተኛ አዳሪነትን ከሚያሳዩና መቼታቸው ከጭፈራ ቤት ከማይወጣ ፊልሞች የተለየ መሆኑ አንድ አዲስ ነገር ነው። ከይዘቱ በፊት ግን የፊልም ባህሪ ነውና አንድ ነገር ልበል። ቁራኛዬ ፊልም አዝናኝ ነው። መዝናናት የሚለው ቃል ከጫጫታና ሆይ ሆይታ ጋር ብቻ የሚገለጽ አይደለም። መዝናናት አዕምሯችን ያለመደውን ነገር ሲያይ ነው። ቁራኛዬ ደግሞ እንደዚያ ነው። ፊልም የምንወድበት አንዱ ምክንያት እኛ የማንኖረውን ሕይወት ስለሚያሳየን ነው። በልቦለድ ሥራዎች ውስጥ ምናባዊ ፈጠራዎች ቀልባችንን ይይዙታል። ያንን ኑሮ መኖር እንፈልጋለን፤ ወይም ደግሞ በተቃራኒው ‹‹ሰው እንዲህ ይኖራል!›› ብለን እንደነቃለን።
ቁራኛዬ ፊልም እኛ ወጣቶች ያልኖርንበትን ሕይወት ነው ሚያሳየን። ፊልሙ ለወጣቶች ፊልም ይሁን እንጂ ያን ዘመን ለኖሩ ግን ዘጋቢ ፊልም ነው። ቁራኛዬ ፊልም ምናባዊ ሳይሆን እውናዊ የአገርቤት ሕይወት ነው። ከመቶ ዓመት በፊት የነበረው የአገር ቤት ሕይወት ማለት ነው። ከመቶ ዓመት በፊት የነበረን ታሪክ የምናውቀው መጽሐፍ በማንበብ ነው። ቁራኛዬ ፊልም ላይ ደግሞ ሕይወቱን በመኖር ነው። ፊልሙን ማየት ምንኛ በሀሳብ እንደሚያሰምጥ! የፊልሙ ይዘት ታሪክ፣ ባህልና ፖለቲካ ነው። ከመቶ ዓመት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። የፊልሙን ይዘት መተንተን የታሪክ ባለሙያ ይጠይቃል። በውስጡ ብዙ የሚተነተኑ ነገሮች ሲኖሩ፤ የፊልሙ ዋና ታሪክ ግን ጎበዜ የተባለ የቆሎ ተማሪ ፍቅረኛውን አለሜን ከእብሪተኛው ጭቃሹም ጎንጤ ለማስመለስ ጥረት ያደርጋል። የሚያስመልሳትም የወቅቱን የፍትሕ ሥርዓት ጠብቆ ነው። ባላንጣውን ተቆራኝቶ ፍትህ ፍለጋ ወደ ንግስት ዘውዴቱ ችሎት የአጼ ስርዓቱን ተከትሎ በሙግት መርታት ነበረበት። ሥርዓቱን ተከትሎም ፍትሕ አግኝቷል። በቁራኛዬ ፊልም ውስጥ የምንማረው ነገር ዋናውን ታሪክ ብቻ አይደለም። በውስጡ ያሉ ብዙ ነገር አለ። እንደሚታወቀው የተለያዩ አገራት በፊልም አገራቸውን ያስተዋውቃሉ። በዚህ በኩል ቁራኛዬ ፊልም የተሳካለት ነው። መልክዓ ምድር ፊልሙ አንኮበር ላይ ያተኩር እንጂ ብዙ የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎችን የሚወክል ነው። የውጭ ፊልሞችን ስናይ በረሃማ አካባቢዎች፣ ጫካው፣ ገደሉ…ሁሉ ይታያል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፊልሞች ግን ከሆቴልና ጭፈራ ቤት አይወጡም። የሚያተኩሩትም የከተማ ሕይወት ላይ ነው። ቁራኛዬ ፊልም ላይ የገጠሩን መልከዓ ምድር እናያለን። መልክዓ ምድር ቀላል ነገር አይደለም። የገጠር ቤቶች ምን እንደሚመስሉ፣ እንዴት እንደሚኖሩ፣ ምን አይነት የመገልገያ ዕቃዎችን እንደሚጠቀሙ ያሳየናል።
ይሄ እንግዲህ ለዚህ ዘመን ነዋሪ (በተለይም ለከተሜው) መዝነኛም ነው ማለት ነው። መቼም ቪላ ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ቪላ ቤት ማየት አያዝናናውም፤ አዲስ ነገርም አያሳየውም። አዕምሮ ደግሞ የሚዝናናው ከለመደው ነገር ወጣ ያለ ሲያይ ነው። ቁራኛዬ ፊልም ለዚያ ዘመን ነዋሪዎች ዘጋቢ ፊልም ነው የሚመስለው። እንኳን ለዚያ ዘመን ነዋሪዎች አሁንም ቢሆን የገጠሩ ሕይወት እንደዚሁ ነው። ፊልሙ የተቀረጸው ልክ እንደዘጋቢ ፊልም ነው። የመገልገያ ዕቃዎች፣ መልክዓምድሩ በገሃድ ያለው ነው። የታሪኩን ሁነት ተከትሎ ሜዳውን፣ ገደሉን፣ ወንዙንና ተራራውን ያሳየናል።
ቋንቋና ባህል
በፊልሙ ውስጥ አንድ ነገር በጣም ገርሞኛል። የፊልሙ ገጸ ባህሪያት የሚናገሩት ቋንቋ ንጥር ያለ የአገርቤት አነጋገር። እዚህ ላይ ግን ደራሲው ሞገስ ሲናገር የሰማሁትን ላካፍላችሁ። አነጋገራቸውን በተመለከተ 11 ጊዜ ደግሞ ደጋግሞ አርሞታል። በተለይ የመጀመሪያው አስቂኝ እንደነበረም ያስታወሳል። ያንን ታሪክ ድንቅ ባህልና ወግ ይዞ የአራዳ ቃላት ሁሉ ነበሩበት። ለዕይታ የቀረበውን ፊልም ግን በቀጥታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት ነው የሚመስለው። ከተዋናዮች አንዱ (ጎበዜን ሆኖ የተወነው) በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲናገር ሰምቼው ነበር። ያንን ሲናገር የሰማሁትን ቋንቋና ባህል ስለማውቀው የፊልሙ እውናዊነት የበለጠ አስገረመኝ። በገጠር አከባባቢ(በተለይም በሰሜን ሸዋ) በከተማ ውስጥ የማይታወቁ እንደ «ኮቼ» እና «ዝግን» የሚባሉ የምግብ አይነቶች አሉ። «ኮቼ» የሚባለው ከጥብስ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ሥጋው ለብቻው ነው እንጀራ ላይ የሚደረገው። «ዝግን» የሚባለውና ፊልሙ ላይ ያለው ግን ከወጥ ጋር ነው። ስሙ እንደሚያመለክተው ዝግን ማለት ከወጡ ውስጥ ያለው ሥጋ በእጅ መዝገን(ማፈስ) የሚቻል ነው። ይህን ወጥ እናቶች በእጃቸው (በሁለት እጆቻቸው መዳፍ) እያፈሱ እንጀራ ላይ ያደርጋሉ። ተዋናዩ አዲስ የሆነበትና የገረመው ይሄ ነበር። ፊልሙ ምን ያህል የአካባቢን ባህል እንዳጠና በግልጽ ያሳየናል። ‹‹በሕግ ከሄደች በቅሎዬ ያለሕግ የሄደች ጭብጦዬ›› ባህርዳር የሚሰራ አንድ የህግ ባለሙያ በአማራ ቴሌቭዥን እንግዳ ሆኖ ሲናገር በሰማሁት አንድ ገጠመኝ አስታወሰኝ። የፍርድ ቤት ዳኛ እያለ ያጋጠመው ነው። ሁለት ሰዎች ተካሰው መጡ። የተካሰሱት በሃምሳ ብር ነው። ሃምሳ ብር ተበድሮ ስላልመለሰለት ማለት ነው። ዳኛው ነገሩ ስላስገረመው በሽማግሌ (ወይም ጓደኝነት ነገር) አወራቸው።
ማንም ያሸንፍ ማን የፍርድ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ የሚያባክኑት የጊዜና የገንዘብ መጠን ከሃምሳ ብር ጋር አይነጻጸርም፤ በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ‹‹እሱን አልሳትኩትም›› ነበር ያለው ከሳሹ። ሃምሳ ብር ያለአግባብ ከሚወሰድበት ተጨማሪ ወጭ አውጥቶ እውነቱን ማሳወቅ ነው የፈለገው። ወደፊልሙ ስንመለስ ‹‹በህግ ከሄደች በቅሎዬ ያለህግ የሄደች ጭብጦዬ›› የሚለው የአበው አባባል የፊልሙ ማስተዋወቂያ(ፖስተር) ላይ እናገኘዋለን። አባባሉ ደግሞ ፊልሙ ውስጥ ተተግብሮ እናገኘዋለን። ሚስቱን በጭቃ ሹሙ ጎንጤ የተቀማው ጎበዜ ፍትሕን ፍለጋ የወቅቱን ሥርዓት ተከትሎ ወደ ንግስቷ ይሄዳል። ፍርዱ የሚሰጠው ከሳሽና ተከሳሽ (በወቅቱ የሚጠቀሙት ቃል ይሄ ባይሆንም) የነጠላቸው ጫፍና ጫፍ አንድ ላይ ታስሮ ነው። እስከፍርዱ ፍጻሜ የየዕለት እንቅስቃሴያቸው ሁሉ እንደተቆራኙ ነው። ሲጸዳዱ እንኳን እንደተቆራኙ ነው። እንደዚያ ተሳስረው ሜዳና ገደሉን፣ ወንዙን አቋርጠው ይሄዳሉ። ‹‹በህግ ከሄደች በቅሎዬ ያለህግ የሄደች ጭብጦዬ›› የሚለውን አባባል እዚህ ጋ በግልጽ እናገኘዋለን። ጎበዜ እና ጎንጤ ተቆራኝተው ፍትሕን እየፈለጉ ሳለ ጎበዜ ታመመ፤ ጎንጤ በጣም ጨነቀው። ፍትሕን ሳናገኝ ይሞትብኛል ብሎ ነው የተጨነቀው።
ሁለቱም ፍትሕን ማግኘት የፈለጉት በሚሰጣቸው ፍርድ ብቻ ነው። ለህሊናቸው ታማኝና ተገዢ ነበሩ ማለት ነው። ባላንጣውን እዚያ ጫካ ውስጥ መግደል ይችል ነበር። ዳሩ ግን እርሱን ቢገድለው በህግ ተከራክሮ አሸናፊነቱ አይታወቅለትም። መግደል ማንም ሊያደርገው የሚችለው ነው፤ ተከራክሮ ማሸነፍ ግን የብልሆች ነው። ሥርዓተ ሙግቱም በበልሃ ልበልሃ ነው። በዚህ ፊልም ውስጥ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ምን ያህል ለህሊናቸውና ለህግ ተገዥ እንደነበሩ ያሳያል። ሰለጠኑ በሚባሉት አገሮች ሳይቀር በዚህ ዘመን አደገኛ አጥር ሁሉ ወንጀልን ማዳን አልቻለም። በዚያን ጊዜ ግን ለአንዲት የነጠላ ጫፍ ቁርኝት ተገዢ ነበሩ። 15 ቀን ሙሉ በነጠላ ጫፍ ታስረው ሲቆዩ ያንን መፍታት ተስኗቸው አይደለም። ሌላው ይቅርና በዚያ ወጣ ገባ በበዛበት አካባቢ ውስጥ ብቻቸውን ሲሄዱ የነጠላውን ጫፍ ፈተው ሰው ያለበት ሲደርሱ ማሰር ይችሉ ነበር። ግን የህግ ተገዥነታቸው ለህሊናቸው ነበርና ይህን የሚያስብ ተንኮል ልቦናቸው አይፈቅድማ! አተዋወን እንደአንድ የፊልም ተመልካች (ባለሙያ አይደለሁም ለማለት ነው) ስለአተዋወኑ አንድ ነገር ልበል። በፊልም ውስጥ የሚደረግ የአተዋወን ድርጊት ‹‹አርቲፊሻልነት›› ይበዛዋል። ያ ማለት ብስጭትን ወይም ደስታን ወይም ሌላ የሆነ ስሜትን ለመግለጽ በገሃዱ ዓለም የሌለ ይሆናል።
ድንገት ተቆርጦ ብናገኘው ፊልም እንደሆነ ይታወቃል ማለት ነው። በቁራኛዬ ውስጥ ግን እንደዚያ አይደለም። አተዋወኑ በቀጥታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩትና የሚያደርጉት ነው የሚመስል። ፊልሙ እንዴት ተሰራ? ይሄን ፊልም ለመሥራት በጠቅላላው የአምስት ዓመት ጊዜ ወስዷል፤ አምስት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ጸሐፊና አዘጋጁ ሞገስ ታፈሰ(ፒ.ኤች.ዲ) በማህበረሰብ ጥናትና ልማት (Social Work and Social Development) ምሩቅ ነው። በማህበረሰብ ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን እና ዘጋቢ ፊልሞችን ሰርቷል። ቁራኛዬ ፊልምን ለመሥራት የተጠቀመው ጥናት መረጃ በማሰባሰብ ጥናት ብቻ ሳይሆን አብሮ በመኖር ነው። የሚበሉትን እየበላ፣ የሚጠጡትን እየጠጣ እና የሚኖሩትን ሁሉ እየኖረ ነው።
ፊልሙን የሰራው በቀጥታ የሚኖሩትን ኑሮ ነው። ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው አዛውንትንም አግኝቶ መረጃ ያሰባሰበበት አጋጣሚ ነበር። ከእነዚህ የዕድሜ ባለጸጎች ያገኘው ነገር ደግሞ ከአንዳንድ ሰዎች ለተነሳ አንድ ጥያቄ መልስ ሆኖታል። የፊልሙ ታሪክ በንግስት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት ላይ የሚያተኩር ነው። እንደ «ቁራኛዬ» እና «ሌባሻይ» ያሉ ሥርዓቶች ደግሞ ከንግስት ዘውዲቱ በፊት በነበሩት በልጅ ኢያሱ ጊዜ በአዋጅ የቀረ ነው፤ ታዲያ ለምን ያ ሥርዓት በንግስት ዘውዲቱ ጊዜ ሆነ? የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ። ሞገስ እንደሚለው ልጅ ኢያሱ በአዋጅ ያስቀሩት እንጂ ማህበረሰቡ ሥርዓቱን ይጠቀምበት ነበር። እንዲያውም እስከ ቀዳማዊ ኃይልሥላሴ ድረስ ይከናወን ነበር።
አስተያየት
ቁራኛዬ ፊልም እውነተኛውን የአገርቤት አኗኗር በማሳየቱ ወደዘጋቢ ፊልምነት የተጠጋ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ፊልሙን የሰራው ሰው፤ አንድም የማህበረሰብ አጥኚ ስለሆነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥናቱን የሰራው ዝም ብሎ በመጠየቅና መረጃ በማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን በመኖር መሆኑ ነው።
ሁለት ማሳረጊያ
አንድ ኪነ ጥብብ የማንም ሰው ሕይወት ነውና ፊልም በስነ ጽሑፍ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በየትኛም ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢሰሩት እንደዚህ ገላጭ ይሆናልና ሌሎችም ቢነሳሱ፤ ሁለት፡- ራሳቸው የፊልም ሰዎች ይስሩት ከተባለም በመጠየቅና በአንድ ሰሞን ጥናት ብቻ ሳይሆን እንዲህ በጥልቀት በማጥናትና ኖሮ በማየት ቢሆን! ለፊልም ሰሪዎች ልቦና ይስጥልን!
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ዋለልኝ አየለ