የየትኛውም አትሌት ራእይና የስኬት መገለጫ በኦሊምፒክ ተሳትፎ ለሃገር ድልን ማስመዝገብ በግሉ ደግሞ ክብርን መጎናጸፍ ነው። በመሆኑም ሃገራት እንደ ቡድን ስፖርተኞችም በግላቸው ለዚህ መሰሉ ታላቅ ውድድር ዝግጅታቸውን አስቀድመው በማካሄድ በጥሩ አቋም ለመፎካከር ከኦሊምፒክ ይቀርባሉ።
በእርግጥ የኦሊምፒክ ግብ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ብቻ አይደለም፤ ተሳትፎ ማድረግም የራሱ ዋጋ አለው። ለዚህም ነው ብዙዎች ውድድር ማጠናቀቃቸውን እንደ አንድ ስኬት የሚቆጥሩት። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ደግሞ በኦሊምፒክ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ከመነሻው የተለመደ በሂደትም የጎለበተ እንደመሆኑ ይበልጥ ቦታ የሚሰጠው ለወርቅ ሜዳሊያና ለብዛቱ ነው።
በመሆኑም የስፖርት ቤተሰቡ የለመደው ሜዳሊያ በቁጥር ሲያንስበት ቅሬታውን ይገልጻል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሆነውም ይኸው ነው፤ ብሄራዊ ቡድኑ የተመለሰው በ1 ወርቅ፣ 1 ብር እና 2 ነሃስ አጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎች ይዞ መሆኑ ደስተኛ አላደረገውም።
በእርግጥ ኦሊምፒኩ ያነሰው ውጤት ብቻም አልነበረም፤ ሃገር በምትወከልበት ትልቁ የስፖርት መድረክ አንሳ ታይታለች የሚለውም የብዙዎች ቅሬታ ነው። ለዚህ እንደምክንያት የሚነሳው ደግሞ ከአመራሮች ጋር በተያያዘ የነበረው ውዝግብና አለመግባባት ባህር ተሻግሮም ቶኪዮ ላይ መንጸባረቁ ነው። እንደ ሃገር በየርቀቱ ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶችን አለማወቅና ከአትሌቶችም ብቃት ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚያስነሱ ሁኔታዎች መታየታቸውም ተጠቃሽ ነው።
በመሆኑም የምንጊዜም ጀግና አትሌት ሻለቃ አበበ ቢቂላ ታሪክ በሠራበትና ኢትዮጵያም በእጅጉ በተከበረችበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከ57 ዓመት በኋላ ስለምን ግራ አጋቢ ጉዳዮች ተፈጸሙ የሚለውን መፈተሽ አስፈላጊ ይሆናል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መምህር አቶ አድማሱ ሳጂ፤ በቶኪዮ የተመዘገበው ውጤት ከተጠበቀው እጅግ የወረደ ነው ሊባል እንደሚችል ይገልጻሉ። ቡድኑ ወደ ቶኪዮ የተጓዘው ከ800 ሜትር የወንዶች ቡድን ውጪ እስከ ማራቶን ባሉት ሁሉም ርቀቶች ሙሉ የቡድን አባላትን ይዞ ነው።
ከዚህ ቀደም አሁን ወደ ስፍራው ከተጓዙት አትሌቶች በቁጥር ያነሰ ቡድን በማሳተፍ ከዚህ የተሻለ ሜዳሊያ ተመዝግቧል። ከአምስት ዓመት በፊት የተካሄደውን የሪዮ ኦሊምፒክ እንደ ማነጻጸሪያ ማንሳት ቢቻል እንኳን በወርቅ ቁጥር እኩል ቢሆንም የተገኘው ግን 8 ሜዳሊያ በመሆኑ ቶኪዮ ላይ በግማሽ የወረደ ነው። ዝግጅቱ ሲጀመር ፌዴሬሽኑም ሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ይዘው የተነሱት መሪ ሃሳብ ቶኪዮ በሻምበል አበበ ቢቂላ ታሪክ የተሠራበት በመሆኑ በተሻለ ዝግጅት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነበር። ሆኖም የታየው ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ውጤት ነው ሲሉ አቶ አድማሱ ያብራራሉ።
በኦሊምፒኩ ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለውጤቱ ማሽቆልቆል እንደ አንድ ምክንት የሚያነሳው አትሌቶች በሚገባቸው ስፍራ አለመሮጣቸውና የምርጫ ጉዳይን ነው። ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት አስተያየቱን የሚሰጠው አትሌቱ፤ ሄንግሎ ላይ በተደረገው የሰዓት ማሟያ ውድድር የተሳተፈው በ10 ሺ ሜትር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኦሊምፒኩ ላይም በዚህ ርቀት ብቻ እንዲወዳደር የተገደበው በዚህ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። በ5ሺ ሜትር ድጋሚ የመሳተፍ ዕድሉን ቢያገኝ ሜዳሊያ ውስጥ የመግባት የተሻለ ዕድል ሊኖር ይችል እንደነበርም ይገልጻል። በውድድሩ ወርቅ እና ብር ያመጡ አትሌቶችን ብቃት የሚያውቅ መሆኑ ደግሞ ለዚህ ያግዘው እንደነበርም አልሸሸገም። ይህ ቁጭት የተሞላበት የአትሌቱ ንግግርም በአትሌቶች ምርጫ ላይ ስህተት መኖሩን በግልጽ ያመለክታል።
ውድድሩን አስመልክቶ መልከታቸውን ያጋሩት አንጋፋው አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣በብሄራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሆነው ሠርተዋል። በዝግጅቱ ወቅትም ሦስት ወር ለሚሆን ጊዜ ከቡድኑ ጋር አሳልፈዋል። ሄንግሎ በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ላይም ተሳታፊ ነበሩ።
አትሌቶቹ በኢትዮጵያ ቻምፒዮና እና ሄንግሎ በነበረው ማጣሪያ በጥሩ አቋም ላይ እንደነበሩ አሰልጣኙ ይናገራሉ። ይህ አቋማቸው ግን እስከ ኦሊምፒኩ ሊቆይ እንዳልቻለ ይገልጻሉ፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ለረጅም ጊዜ የቆየውን ዝግጅት ነው።
የቡድኑ አባላት በኮቪድ 19 ምክንያት ተሰባስበው ለ8 ወራት ዝግጅት ላይ እንዲቆዩ ተደረጉ እንጂ፤ እንደብሄራዊ ቡድን ለሦስትና ሁለት ወራት ዝግጅት ቢያደርጉ በቂ ነበር ሲሉም ያብራራሉ። ምክንያቱ ደግሞ አሁን ያሉት አትሌቶች እንደ ቀደምቶቹ ከዓመት ዓመት የሚቆይ አቋም የሌላቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የአትሌቶቹ አቅም እስከ ኦሊምፒኩ ሊዘልቅ አለመቻሉን እንደተገነዘቡ ያስረዳሉ።
ሌላኛው ችግር የአየር ሁኔታው ስለመሆኑ በተለያዩ አካላት ይነሳል። በርካታ አትሌቶች በማራቶንም ሆነ በመም ውድድሮች ላይ አቋርጠው መውጣታቸው አንድም ለውጤቱ መዳከም ምክንያት ሲሆን፤ ይህም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድም ከፍተኛ ቅሬታን የፈጠረ ነው።
ሃገሩን ወክሎ በኦሎምፒኩ በ10 ሜትር የሮጠው ሰለሞን ባረጋ በበኩሉ፤ ሙቀት ብቻም ሳይሆን አንዳንዴ ዝናብ ይጥል እንደነበርና ቅዝቃዜ እንደነበረ ይናገራል። ይህ ሁኔታ የአተነፋፈስ ስርዓትንም እስከ ማዛባት የሚደርስ እንደነበር ያስታውሳል። ይህም በውድድር ብቻም ሳይሆን ልምምድ በሚደረግበት ወቅትም ይሰማቸው የነበረ ሁኔታ መሆኑን ያብራራል።
ችግሩ ሙቀት ብቻ ቢሆን ቡድኑ በዝግጅቱ ወቅት ከአየሩ ጋር ለመላመድ እንደ አዳማ ባሉ ስፍራዎች ልምምድ መሥራቱን ይጠቅሳል። ከሙቀቱ በተቃራኒ ቅዝቃዜም መኖሩ ትልቅ ተጽእኖ እንደነበረው ቡድኑ ወደ ሃገሩ በተመለሰበት ወቅት አስረድቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሻምበል ቶሎሳ የአትሌቶች አቅም ማነስ ምናልባት በቦታው በነበረ ሙቀት የተከሰተ ከሆነ አስቀድሞ የቦታውን የአየር ሁኔታ አውቆ ተቀራራቢ በሆነ ሁኔታ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደነበር ነው የሚያመላክቱት።
በኦሊምፒኩ ላይ እንደተመለከቱት በርካታ አትሌቶች ውድድሮችን አቋርጠው የመውጣታቸው ነገር ሻምበል ቶሎሳን አሳዝኗቸዋል። በተለይም በማራቶን በሁለቱም ጾታ አንዲት አትሌት ብቻ ውድድሩን መፈጸሟ አጠያያቂ መሆኑን ተናግረው፣ አሰልጣኞች ለዚህ ኋላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የስፖርት ሳይንስ ባለሙያውና የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ አድማሱ በበኩላቸው፤ ቡድኑ እዚህ የነበረው ዝግጅት በቶኪዮ ከሚኖረው የአየር ንብረት ጋር የሚጣጣም ካልሆነ አትሌቶች በውድድር ወቅት የሚቸገሩ መሆኑን ይጠቁማሉ። ለአትሌቶች አቋም ማነስና በውድድሩም ላይ ጫና ያሳደረው በሚጠብቃቸው ውድድር ልክ አለመዘጋጀታቸው መሆኑን ይገልጻሉ። አቶ አድማሱ ምናልባትም የአየር ሁኔታው ዝግጅት ሲያደርጉ ከቆዩበት የአየር ሁኔታ ጋር ተቀራራቢ ቢሆን በቂ አቅም ይዘው በመሄድ የተሻለ ውጤት ሊመጡ ይችላሉ የሚል እምነትም አላቸው።
ለዚህ ችግር መነሻ የሚሆነው ደግሞ በፌዴሬሽኑም ሆነ በኮሚቴው ውስጥ ከሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ በዚህ ዙሪያ ጠለቅ ያለ አስተሳሰብ ይዞ በቆራጥነት የሄደ ሰው አለመኖሩ ነው ይላሉ። ቀደም ሲል ሃሳቡ በተለያዩ አካላት መነሳቱን አስታውሰው፤ ይህንን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ክፍተት በመኖሩ በውጤቱም ላይ ጫና አሳድሯል ሲሉ ያብራራሉ።
በሁለቱም ተቋማት በኩል ያሉ ሥራ አስፈጻሚዎች ከቀድሞ አትሌቶች በቀር ምንም ዓይነት የስፖርት እውቀትና የኋላ ታሪክ የሌላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህንንም ጠንቅቀው የሚያውቁ አለመሆናቸውንም ባለሙያው ይጠቁማሉ። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ከቶኪዮ የአየር ሁኔታ ጋር ሊስማማ የሚችል ስልጠና እንዲያገኙ በቁርጠኝነት ወስኖና ቆርጦ እንዳልገባበት ያላቸውን ጥርጣሬ ይጠቁማሉ።
ከዓመት በላይ ያስቆጠረውና ከሃገር አልፎ በቶኪዮም የተስተዋለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውዝግብም ከውጤቱ ማሽቆልቆል ጋር በተያያዘ የሚነሳ መሆኑን ሦስቱም ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
ይህ አለመግባባት በተለይ በአትሌቶች ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እንደነበረው ሰለሞን ሲያስረዳም፤ አትሌት በትንሽ ነገር ሊረበሽና ዕረፍት ላያገኝ እንደሚችልም ይናገራል። በአንዳንድ ርቀቶች በተለይ በ5ሺ ሜትር ማን እንደሚሮጥ አይታወቅም ነበር ያለው አትሌቱ፣ ይህም ‹‹እዚያ ድረስ ተጉዘን እንዴት ሳንወዳደር እንመለሳለን›› የሚለው ስለሚያስጨንቃቸው እንቅልፍ እስከማጣት የደረሱ አትሌቶች ነበሩ ሲል አብራርቷል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ በውጤቱ ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፉን ይገልጻል።
አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱም ላልተጠበቀ ውጤት መመዝገብ በር የከፈተው በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበረው አለመግባባት መሆኑን ያመለክታሉ። በኦሊምፒክ ኮሚቴውና ፌዴሬሽኑ መካከል በነበረው የይመለከተኛል ሽኩቻ፤ በተለይ እንደ 5ሺ ሜትር ባሉት ርቀቶች ፌዴሬሽኑ የመረጣቸውና ኦሊምፒክ ኮሚቴው ሊያሳትፋቸው የነበሩ አትሌቶች በመወዳደርና ባለመወዳደር መካከል ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው በስነልቦና ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ሲሉ ያብራራሉ። ሁለቱም ተቋማት በአንድ አለመሥራታቸው በአትሌቶችና በውጤቱም ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው፤ በጉዳዩ ላይ መንግሥትም ሊገባበት እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት።
ሁሉም የሚያውቀውና በተቋማቱ መካከል ያለው ያለመግባባት በውጤት ላይ ትልቅ ጫና ማሳደሩን የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አድማሱ ሳጂም ያነሱታል።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፤ በአትሌቶቹም ላይ ሆነ እንደ አንድ ቡድን ተስማምቶና ተደጋግፎ በአግባቡ አለመምራት የተወዳዳሪዎቹን ስነልቦና በእጅጉ ይጎዳል። ስፖርት አዕምሮ የሚያስበውን አካል ሲተገብር ነው፤ ይህን ለመፈጸምም በስነልቦና ጠንካራና ቆራጥ ሆኖ በውድድር ላይ መገኘት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ከመጀመሪያው ዝግጅት ጀምሮ እንደ አንድ ቡድን በአንድነት መጓዝን ይጠይቃል።
ሁለቱም ተቋማት የአትሌቶቹን ሞራል ገንብተው አለመሄዳቸው በእርግጥም በአትሌቶቹ ውጤት መፈረካከስ ወይም መልፈስፈስ እንዲከሰት ሚና ነበረው ሲሉ አቶ አድማሱ ይጠቁማሉ። የአየር ሁኔታው ካደረሰባቸው ጫና ባሻገር በስነልቦና በኩል የነበረው ችግር ጨክነው ውድድሮችን ለመፈጸም ቁርጠኛ እንዲሆኑ አላደረጋቸውም ሲሉም ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ አብራርተዋል።
ሻምበል ቶሎሳ፤ በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ኦሊምፒክ ምን ተማርን የሚለው ላይ አተኩሮ መሥራት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ፌዴሬሽኑና ኦሊምፒክ ኮሚቴው የገቡበት ውዝግብ ሌላ ጉዳይ ሆኖ፤ ለወራት ያህል ከፍተኛ ወጪ ተደርጎ ምን ተገኘ የሚለው ላይም መሥራት ይገባዋል ይላሉ። ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይቶ በማውጣትና በመገምገም መመልከት እንደሚገባውም ያመለክታሉ።
አቶ አድማሱ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና ባላት የኦሊምፒክ ታሪክ አሁን ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ምክንያት የሆነውን ችግር ነቅሶ በማውጣት የተጎዳውን የአትሌቶች ስነልቦና የሚጠግን ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
ከተቋማቱ አለመግባባት ጋር ተያይዞ ሁለትና ሦስት ሰዎች ብቻ ሲነሱ ይስተዋላል ያሉት አቶ አድማሱ፣ በጉዳዩ ውስጥ በሁለቱም ተቋማት ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ የሥራ አስፈጻሚ እጅ አለበትም ባይ ናቸው። አቶ አድማሱ እንደ አንድ ሃገር ችግሮቻቸውን በውይይት ከመፍታት ይልቅ በየሚዲያው ቃላትን መወራወር ምርጫቸው ማድረጋቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል ነው የሚሉት።
በእርሳቸው ምልከታ አሁን የሚታየው ሁኔታ እያንዳንዱ ፌዴሬሽን ያለበትን ችግር በየራሱ ሲያንጸባርቅ ነው፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚዋቀረው በእያንዳንዱ ፌዴሬሽን ባሉ ሥራ አስፈጻሚዎች ነው። በመሆኑም እነዚህን የሚመራው ስፖርት ኮሚሽን ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ እና ጥንቅር ላይ ለወደፊቱ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013