መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በአንደበተ ርቱዕነታቸው ይታወቃሉ። ስማቸውን በተመለከተ በስህተት ይሁን በልማድ ‹‹መጋቤ ሐዲስ›› በሚለው ብቻ የሚጠሯቸው ብዙ ናቸው። ምናልባት እንደ እርሳቸው የታወቀ ሌላ መጋቤ ሐዲስ ስለሌለ ሁላችንንም ያግባባናል እንጂ መጋቤ ሐዲስ የእርሳቸው መጠሪያ ስም ሳይሆን ማዕረጋቸው ነው። ትርጓሜውም ሐዲስን የሚመግቡ ማለት ነው። የእርሳቸው ሙሉ ስም እሸቱ አለማየሁ ነው። ማዕረጋቸውን አስቀድመን መጋቤ ሐዲስ እሸቱ እያልን መጠቀም እንችላለን። መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ይኖራሉ የተባለበት መድረክ መቆሚያ መቀመጫ ይጠፋል።
ለዚህም ነው መድረኮች ሲዘጋጁ የሚያስተዋውቁት ‹‹መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ይገኛሉ›› እያሉ ነው። የሚገኙበትን መድረክ ልብ ብላችሁ ከሆነ ለታዳሚ መያዣ የእርሳቸው ንግግር መጨረሻ ላይ ነው የሚደረገው። ገና ወደ መድረክ ሲጠሩም በጭብጨባና ፉጨት አዳራሾቹ ይደምቃሉ። ብዙ ጊዜ የሚገኙት ለአንድ ጉዳይ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ እንጂ፤ እርሳቸው እንዲናገሩ ተብሎ ለብቻው መድረክ ሲዘጋጅ ብዙም አይስተዋልም። የእርሳቸው ንግግር ግን ራሱን ችሎ መድረክ የሚያዘጋጅ ነው፤ ይሄ ማለት በቃ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ እንዲናገሩ መድረክ ማዘጋጀትና እርሳቸው ብቻ የሚናገሩበት መድረክ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በለውጥ ላይ ነው። ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችል አስተሳሰብ መፍጠር ተቀዳሚ አላማው አድርጓል። ይህን ተከትሎም ለሰራተኞቹ አነቃቂ ሀሳቦችን ሊመግብ ፈለገና መጋቢ ሃዲስ እሸቱን በእንግድነት ጋበዛቸው። እኛም ከዛሬ ጀምረን ለምናሳትማት አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጋዜጣ «መጋቤ አዕምሮ» በተሰኘው አምዳችን እንደሚከተለው አሰናዳነው። ለድርጅቱ ሰራተኞች ይህኛው መድረክ ለየት ያለ ነበር። እንደወትሮው መድረክ ‹‹ተጀምሯል ሂዱ!›› ወደ አዳራሽ ሂዱ የሚል ቅስቀሳ አልተደረገበትም። በዚያ ላይ ቀኑ ብዙ ሰራተኛ የማይገኝበት ቅዳሜ ነበር፤ የዚያን ዕለት ግን ይህ አልሆነም። ሰራተኛው የተባለውን ሰዓት ጠብቆ በአዳራሹ ተገኘ። ከወትሮው የሚለይበት ሌላው ድባብ ደግሞ መግባትና መውጣት አለመኖሩ ነው፤ የመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ንግግር ይህን ያህል ቀልብን የገዛ እንደነበር ምስክር አይሻም። ራሱን ችሎ እንዲህ አይነት መድረክ ቢዘጋጅላቸው ምን ያህል ታዳሚ እንደሚገኝ አሳይቷል።
እውቅና ስለመስጠት
ከፊት ያሉ ሰዎችን ማበረታታት ከኋላ ለሚሮጠው ሰው በረከት ነው። እነ ሃይሌ እና እነ ደራርቱ ሮጠው ሲጨርሱ የሚገረፉ ቢሆን ኖሮ ማንም ሩጫ የሚሞክር አይኖርም ነበር። ሮጠው ከጨረሱ በኋላ ወርቅና ብር ስለመጣ እኛም ብንሮጥ እናገኛለን ብለው ሰዎች ይሮጣሉ። አይተናል ከፖለቲካ ብዙ የሸሹ ሰዎች፤ ጫፉ እስራት ነው ሲባሉ ይሸሻሉ። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ያለ ነው። ስለዚህ የፊተኛውን ማበረታታት የኋለኛውን ማበረታታት ነው። አሁን የመጣው ትውልድ ብልጥ ነው። ኪሱንና ነፍሱን ያስታረቀ ነው። አሳቢ ነው፤ ትምህርት ሲማር በምን ብመረቅ ስንት ብር አገኛለሁ ብሎ ነው። ድሮ እንደዚህ አልነበረም፤ በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ስንማር መቼ እንደምንጨርስ አናውቀውም ነበር፤ ከጨረስን በኋላም ምን እንደምናገኝ አናውቀውም። ለማወቅ ብቻ ነበር ትምህርቱ። የአሁን ትውልድ ግን 12ኛ ክፍል ሲጨርስ ምን ቢማር ምን እንደሚያገኝ አስልቶ ነው።
ጭብጨባ እና መድረክ
እኔ መድረክ ላይ ጭብጨባ ለምጃለሁ፡፡ ጭብጨባ ለሁለት ነገር ያገለግላል። አንድ ለራሱ ለታዳሚው ነው፤ ያነቃቃዋል። እዚህ ሆኖ ቤቱ ቡና የሚያፈላ አለ፤ ስብሰባ ውስጥ ቁጭ ብለው ብዙ ሴቶች ቤታቸው አልጋ የሚያነጥፉ አሉ፤ ቤት ይጠርጋሉ። እነዚህ ሰዎች በጭብጨባ ካልተቀሰቀሱ ይጠፋሉ። አንዳንድ ሰዎች ጆሯቸው አለ፤ ግን ጥሪ አይቀበልም። አንዳንዱ ሰው እኮ መንገድ ላይ እየሄደ እንኳን ስታናግሩት አይሰማም። ሁለተኛው የጭብጨባ ጥቅም ለተናጋሪው ነው። ተናጋሪውን አለን እየሰማንህ ነው ለማለት ያግዘዋል።
መለወጥ
እንጨት የወየበ (የጠወለገ) ቅጠሉን ማርገፍ አለበት፤ አበባ አበባውን አርግፎ ፍሬ ማፍራት አለበት። ብዙ ጊዜ ሰዎች ውበትን ለማድነቅ ‹‹አይኑ ወይም አይኗ የባቄላ አበባ ይመስላል›› ይላሉ። ለገበሬ የባቄላው አበባ ውበት ሳይሆን ተስፋ ነው። አበባ በከተማ ማጌጫ ነው፤ ለገበሬ ግን ተስፋ ነው፤ ሕይወት ነው። በአበባው በኩል ወደፊት የሚያየው ተስፋ አለው። ምክንያቱም ባቄላው አበባውን ካረገፈ በኋላ ፍሬ ያፈራል። ገበሬው ሲመነጥር፣ ሲያርስ፣ ሲያርም የሚከርመው አበባ ለማግኘት ሳይሆን ፍሬ ለማግኘት ነው። መሬቱን አለሳልሶ ማዳበሪያውን አድርጎ የሚዘራው ፍሬ ለማግኘት ነው። ዛሬ ጊዜ መሬቱ ራሱ ሙስና ለምዶ ያለማዳበሪያ ምርት አልሰጥም እያለ ነው። አንድ ዛፍ የወየበ ቅጠሉን ካላረገፈ አዲስ ቅጠል አያወጣም፤ አንድ ተክል አበባውን ካላረገፈ ፍሬ አያፈራም። የሰው ልጅም ያረጀ፣ ያፈጀ፣ የቆሸሸ እና የተበላሸ አስተሳሰቡን ካላራገፈ አይለወጥም።
አዲስ ሀሳብ ለሌለው አዲስ ሰው መሆን አይችልም። በዓለም ላይ ብዙ አይነት ለውጥ ይታያል። ለውጥ ተፈጥሯዊም ነው። ቀን አልፎ ጨለማ ይመጣል፤ ክረምት አልፎ በጋ ይመጣል፣ ሰኞ አልፎ ማክሰኞ ይመጣል። ይሄ ሁሉ ለውጥ አስፈላጊ ነው። በለውጥ ውስጥ ደግሞ የሰው ሁኔታም ይለወጣል። ለምሳሌ ሰኞ የተበሳጬ ሰው ማክሰኞ ሊደሰት ይችላል። ስለዚህ በሁሉም ነገር ለውጥ ያስፈልጋል። ለውጥ ሲባል ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ለውጥ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ያስፈልጋል ከተባለስ ምን አይነት ለውጥ የሚለው ነው። በፖለቲካችን ውስጥ ብዙ ለውጥ አለ፤ ለምሳሌ አጼ ኃይለሥላሴን ስንቀይር ደርግ ይመጣል ብሎ ያሰበ አልነበረም፤ ግን እንደዚያ ሆነ፤ ከዚያ በኋላም እንደዚያ ሆነ፤ ከዚያም እንደዚያ ሆነ። በአሮጌ ሱሪ ዕቃ ስንለውጥበት አዲስ ሱሪ መገኘቱን ማረጋገጥ አለብን፤ ምክንያቱም የሚመጣው ለውጥ ምንድነው ተብሎ መታወቅ አለበት።
አዲስ ሱሪ ሳይገዛ አሮጌውን ቢጥሉት ራቁት መሄድ ይመጣል። አሮጌን ሲጥሉም አዲስ አዘጋጅቶ ነው። ስለዚህ ስንለወጥ የሚጠቅመንን ነገር ማወቅ አለብን። ኢትዮጵያውያን ለለውጥ እንግዶች ናቸው ሲባል እንሰማለን፤ ለውጥ አንወድም። ጥንታውያን አባቶቻችን ለለውጥ እንግዶች አልነበሩም። ከውጭው ዓለም ያለውን እውቀት ለማስገባት የተጻፈውን ጽሑፍ ስትመለከቱ ለውጥ ፈላጊ ነበሩ። የግሪክን ፍልስፍና እስከነትርጓሜው ያስገቡ ሊቃውንት አሉ። የነሶቅራጠስንና የነፕሌቶን ፍልስፍና ትርጓሜ ውስጥ አስገብተው መማሪያ አድርገውታል። ከዚህም የተነሳ ትርጉም ሁሉ አይመስሉም፤ እዚሁ አገር በቅለው ያደጉ ነው የሚመስሉት። ትልቁ ችግራችን መወያየት አንችልም፤ በፖለቲካችን የመወያየት ባህል የለንም። በትዳር እንኳን የመወያየት ባህል የለንም። ባልየው መጥቶ መመሪያ ነው የሚሰጥ። የባልና የሚስት ጉዳይ አብሮ የማደርና ያለማደር ጉዳይ ሆኖ ነው የሚታየው፤ እንዲያውም አሁን አሁን እርሱም እየተደበላለቀ ነው፤ አሁን አሁን በሚስትና በቤት ሰራተኛ መካከል መቀላቀል እየታየ ነው።
ሀሳባችንን ሰው ላይ መጫን ነው የምንወድ። በንጉሡም ጊዜ፣ በዚያኛውም ጊዜ፣ በዚያም ጊዜ በዚያም ጊዜ…. አንዱ የሌላውን እስኪ አስረዳኝ የመባባል ነገር የለም። ሙስሊሙ ኦርቶዶክሱን፣ ኦርቶዶክሱ ሙስሊሙን፣ ፕሮቴስታንቱ ሙስሊሙን… አንዱ ሌላውን እስኪ ይሄን አስረዳኝ አንባባልም። እስኪ ቁርዓን ምንድነው የሚል፣ እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ ምንድነው አንባባልም። በፖለቲካ አንዴ የደገፍነውን አካል እዚያው ላይ ሙጭጭ ነው፤ እገሌ የእንትና ደጋፊ ነው ከተባለ ዶግማ አርጎት ቁጭ ነው። የተቃወምነውንም አካል ተቃውሞው ላይ ሙጭጭ ነው። እንደነ አሜሪካ ባሉ አገራት ግን እንዲህ አይደረግም። ሪፐብሊካንን ይደግፍ የነበረ ሰው የፖለቲካውን ርዕዮተዓለም አይቶ ዲሞክራት ሊሆን ይችላል፤ ዲሞክራት የነበረውም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ባለበት አክርሮ ዝም ነው፤ አያነብም። ከብዙ ዓመታት በፊት የተከናወነ ሁነት ላይ ነው ያለው ። አገሪቱ ውስጥ ምን እየሆነ እንዳለ የማይሰማ ሁሉ አለ። አጼ ኃይለሥላሴ በ1967 ዓ.ም ሞተው በ1975 ዓ.ም አንድ የዋድላ ገበሬ ‹‹በኃይለሥላሴ አምላክ›› ይል ነበር። አጼ ኃይለሥላሴ መሞታቸውን የሚነግረው አልነበረም። ያኔ ደግሞ እንደዛሬው ፌስቡክ እንኳን የለም። የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሩ ሰዎች የሕዝቡን ችግር አያውቁም፤ እነርሱ ጥሩ ቢሮ ካገኙ ህዝቡ ጥሩ ኑሮ እየኖረ ይመስላቸዋል። በቅርቡ ኳታር ነበርኩኝ። 300 ሺህ ዜጋ ነው ያላቸው፤ ሀብት የተትረፈረፈ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ግን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስደተኛ ይኖርበታል። እነርሱ ግን በጣም የሰለጠኑ ስለሆኑ ‹‹ለምን መጣህ! ከየት መጣህ! ምንድነህ! ቋንቋህ ምንድነው›› አይሉም። በአገሪቱ እስልምና መንግስታዊ ሃይማኖት ነው፤ ህዝቡ ሙሉ በሙሉ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው። እኛ ግን ቦታ ተዘጋጅቶልን ስንሰብክ ስንዘምር አንድ እንኳን የገላመጠን የለም፤ ልባሞች ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ እኛም ከሚለወጡ ነገሮች ግን አብረን ካልተለወጥን፤ አስተሳሰባችንን ካላሻሻልን አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011