የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ማጽደቁ ይታወሳል። እነዚህ ቡድኖች ሃገርን የማፍረስ የጋራ አጀንዳቸውን ለማስፈፀምም በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በተለያዩ ጊዜያት ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ከፍተኛ በደሎችን እያደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ እያሳወቀ ይገኛል። እኛም ቡድኑ ሲፈጽማቸው የቆዩ ጥፋቶች፣ በተለይ ኦሮሚያ ላይ ያደረሳቸው በደሎች እንዲሁም ከሸኔ ጋር ስለፈጠረው ጥምረት እና የውጭ ኃይሎች ቡድኑን ስለሚደግፉበት ምክንያት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተን ከኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በብሔሮች ላይ የፈጸማቸው በደሎች በአግባቡ ተገልጸዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ታዬ፡– ህወሓት በስልጣን ዘመኑም ሆነ አሁን ላይ በየስርቻው ተደብቆ ሲንቀሳቀስ በብሔሮች ላይ የፈጸማቸው በደሎች ተቆጥረው አያልቁም። በርካቶች የእርሱን ቃል ያልተቀበሉትን በየጉድጓዱ እንዲወድቁ አዟል። ስለብሔራቸው መብት እና ስለሀገራቸው ያነሱትን እየለየ ደብዛቸውን አጥፍቷል። ይህ ሁሉ ግፉ ግን በየጊዜው ይነገራል እንጂ በአንዴ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
በኢኮኖሚውም ካየነው ለእራሱ ጥቅም እስከሆነ ድረስ የሀገር ሀብትን ሙልጭ አድርጎ በመዝረፍ የሚታወቅ ነው። የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች ገንዘባቸውን ወደ ኢንዶኔዥያ እና ሌሎች ሀገራት በማሸሽ ህዝብን ወደድህነት ሲያሸጋግሩ ነው የኖሩት። እራሳቸው ካልነገዱ እራሳቸው ብቻ ህግ ካላወጡ ደስ የማይላቸው የአሸባሪው ህወሓት አባላት ሁሉን እኔ አውቅልሃለው በሚል የኖሩ ናቸው።
በብሔሮች መካከል ግጭት በመቀስቀስ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ኦሮሞ ከሶማሌ፣ ጌዲዮ ከኦሮሞ፤ አማራን ከኦሮሞ፣ ሱማሌው ጋር ብትሄድም ሆነ ደቡብ ክልል ብትገባ ብቻ ምን አለፋን መላ ኢትዮጵያ ውስጥ እሳት ያልጫሩበት ቦታ የለም።
2009 ዓ.ም ማብቂያ እና 2010 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ ከወንድሞቹ ሶማሌዎች ጋር እንዲጋጭ እና እልቂት እንዲፈጠር ህወሓት ከአብዲ ኢሌ ጋር ሠርቷል። በወቅቱ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ ቤተሰባቸውን አጥተዋል። በየዓመቱ ለመብቱ የታገለውን ግለሰብ ህይወት እያጠፉ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን በእስር ቤት እያጎሩ ሲንደላቀቁ ነው የቆዩት።
ይህን በደላቸውን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በየደጁ ስለደረሰበት ያውቀዋል። አንፈልጋችሁም በሚል ነው አሽቀንጥሮ የጣላቸው። ስለዚህ ዳግም የእነሱ ጭቆና እና ግፍ እንዲወድቅበት የሚፈልግ ህዝብ ባለመኖሩ ሁሉም ሊታገላቸው ተነስቷል፤ ይህንን ደግሞ በተግባር እያሳየ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ህዝብ ላይ በደል ሲፈጽም ከጀርባ የሚያሳብብበት አንድ ምክንያት ይፈጥራል፤ በዚህ ረገድ ኦሮሚያ ላይ የታየው ምንድን ነው?
አቶ ታዬ፡- ህዝብ በደዴሳ እና በተለያዩ እስር ቤቶች በማጎር አሰቃይቷል። አርቲስቶችን ጭምር አሳፍኗል። ህወሓት አርቲስቱንና ጀግናውን ኤቢሳ አዱኛን ጨምሮ በርካታ ጀግኖችን ገድሏል። አሁን ቅርብ ጊዜ እንኳን በሺዎች የሚቀጠሩ ወጣቶች በአደባባይ ተገድለዋል።
በርካታ ባለሀብቶች በህወሓት ተዘርፈዋል። የኦህዴድ አመራሮች ሳይቀሩ እንዲገደሉ እና ከሀገር እንዲጠፉ ተደርጓል። ያሰቃየው አሸባሪው ህወሓት ነው፤ የሚያሰቃይበት ምክንያት ደግሞ አሁን ባለው ሸኔ ምክንያት ነው።
አሸባሪው ህወሓት ሸገር ላይ ኦሮሞ አፈናቅሎ የእራሱን ቤተሰብ ነው የተከለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር የሆኑበት ኦሮሞ ደግሞ የደኸየበት ስርዓት ነበር። ኦሮሞ እንዳይነግድ እና እንዳይማር ብቻ ሳይሆን በህይወት እንዳይቆይም ተወስኖበት ነበር። በእያንዳንዱ የማዕከላዊ እስር ቤት ክፍሎች መከራቸውን ያዩ ወጣቶች ባርካታ ናቸው።
ህወሓት ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም የኦሮሞን የመብት ጥያቄ ለማፈን እንደምክንያት የሚጠቀመው የኦነግ ታርጋን በመለጠፍ ነበር። ተማሪም ይሁን አስተማሪ የኦሮሞን መጎዳት የሚናገር ከሆነ አንተ ኦነግ ነህ፤ ባትሆን እንኳን ኦነግ ኦነግ ትሸታለህ በሚል ሲገረፍና ሲሰቃይ የነበረ ማህበረሰብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪነት የተፈረጁት ኦነግ እና ህወሓት በጋራ ለመሥራት ወስነናል ማለታቸውን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ታዬ፡– ከዚህ በፊትም ግንኙነታቸውን አውቅ ስለነበረ ጉዳዩ ብዙም አልገረመኝም። አብረው ሲሰሩ የቆዩ ቡድኖች ናቸው። ሸኔና ህወሓት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ለአብነት ማንሳት ቢቻል በ1996 ዓ.ም በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው የህወሓት መንግሥት 350 የኦሮሞ ተማሪዎችን ሲያባርረን እና ኮልፌ ላይ ሲደበድበን እንታገል ብለን በሀረር መስመር ወደኦነግ ነበር የሄድነው።
በወቅቱ ከወያኔ ሸሽተን ብንሄድም እዚያም ያገኘነው ወያኔን ነው። ይዘውን ለወያኔ ነው የሰጡን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሸኔና ወያኔ አንድና ያው መሆናቸው ግልጽ ነበር ለእኔ። በሌላ መልኩ ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ላይ ደግሞ ሰሜን ገብረጉራቻ አካባቢ ከአማራ ክልል የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ሲደርስ ሸኔና ህወሓት ናቸው በጋራ ጥቃት ሲያደርሱ የነበረው።
ምክንያቱም በወቅቱ የኦሮማራ እንቅስቃሴ የጀመረበት ወቅት በመሆኑ ያንን በማኮላሸት አማራ እና ኦሮሞን ለማለያየት ሲባል ህወሓትና ሸኔ በአስፓልት መንገዱ ላይጥቃት እንዲፈጽም አድርገዋል። ከዚህ አንጻር ግንኙነታቸው ዛሬ የጀመረ አይደለም ብሎ መናገር ይቻላል።
ላለፉት 27 ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ተጎድቷል፤ ተገድሏል፤ ከቀዬውም ተፈናቅሏል በሚል ይህ መቆም አለበት ብለው በቅንነት በኦነግ ውስጥ ሲታገሉ የነበሩ ግለሰቦች ነበሩ። ድርጅቱ ግን እንደ ድርጅት የህወሓት ተላላኪ ሆኖ ሲሠራ የኖረ ነው። በኋላም ሸኔ ብለው እራሳቸውን ገንጥለው ወጥተው የባሰ ጥፋት ሲያደርሱ እና ከህወሓት ጋር ሲሠሩ የኖሩ በመሆናቸው ግንኙነታቸው አዲስ አይደለም።
የሸኔው አመራር አጠቃላይ ከህወሓት ጋር ነው የሚሠራው። የኦሮሞ ወጣት በቅንንነት ከሸኔ ጋር ለመታገል ሲሄድ ወይ እራሳቸው ይገድሉታል አሊያም በወያኔ ያስይዟቸው ነበር። ህወሓትና ሸኔ አንድና ያው ነበሩ፤ አሁንም አብረው መሆናቸውን በግልጽ አምነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በኦሮሞ ላይ ብዙ በደሎችን አድሷል እየተባለ፤ ሸኔ ከህወሓት ጋር አብሬ እሠራለሁ ማለቱ ምን ዓይነት የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ?
አቶ ታዬ፡- ሸኔ አንድም ቀን ወደህወሓት ሳይተኩስ ነው ለውጥ የመጣው። ኢሬቻ ላይ ከ700 በላይ ሰዎች በጉድጓድ ገብተው በገደል እንዲያልቁ ሲደረግ ነበር፤ በወቅቱ ሸኔ ምንም አላደረገም አንድም ጥይት እንኳን አልተኮሰም።
ሸኔ ትግል የጀመረው የኦሮሞ ህዝብ ከወንድሞቹ ጋር ተባብሮ ህወሓትን ከገረሰሰ በኋላ ነው ትግል ታይቶት የጀመረው። መቼ ካልን 2010 ዓ.ም ከለውጡ በኋላ ነው። ሸኔ ከመጣ በኋላስ ማን ላይ ነው የተኮሰው ካልን የኦሮሞ አባቶች ላይ፤ የኦሮሞ አመራሮች እና ህዝብ ላይ ነው።
ሸኔም እንደህወሓት የህዝብን ንብረት ማቃጠል እና ነብስ ማጥፋት ነው ሲያከናውን የቆየው። ሸኔ ማለት ኦሮምኛ የሚናገር ህወሓት ማለት ነው። ስለዚህ የህወሓትን ዓላማና ሂደት ይከተላል፤ እንደነሱ በግጭትና ጥፋት ላይ የሚያተኩር ነው። አሁን ድብቅ የነበረው የህወሓትና የሸኔ ግንኙነት በሰነድ በግላጭ በመገናኛ ብዙሃን መውጣቱ ነው እንጂ አይለያዩም።
ኦሮሞ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ትቶ ሸኔ አሁን ከህወሓት ጋር አብረን ነን ማለቱ ህወሓት የፈጸመውን ወንጀል ሸኔም እንደሚጋራው ያረጋገጠ ነው። ወያኔ ሲፈጽማቸው የነበሩ ወንጀሎች የእኔም ናቸው ማለቱን ያመላክታል። ኢትዮጵያ ላይ ወንጀል ስንፈጽም የነበረው እና ህዝብ ስናሰቃይ የነበረው በጋራ ነው ለማለት ያክል ካልሆነ ቀድሞም አንድ መሆናቸውን እናውቃለን።
ይህንን ህዝብ በይበልጥ እንዲረዳው ግልጽ ማድረጋቸው ጥሩ ነው። አሁን ህዝብ እራሱ የዚህን ከሃዲ ቡድን ዓላማ የበለጠ ተረድቷል። አንዳንድ ጥርጣሬ የነበራቸው ዜጎችም ግልጽ ሆኖላቸዋል። በፊት ሸኔን ከህወሓት ጋር አንድ ነው ለማለት ብዙ ማስረዳት ይጠይቅ ነበር። አሁን ግን አሸባሪው ሸኔም ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አንድ ነን ብለው ስለመጡ እና ብዥታውንም ስላጠሩ ትግሉንም መስመር ያስይዘዋል ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ቀደም ሲገርፈውና ቤተሰቦቹን ሲገድል ከኖረው ህወሓት ጋር አብሬ ልሠራ ነው ማለት ቢያዋርድ እንጂ የሚያስከብር አይደለም። አሁን በግልጽ ማውጣታቸው ጥሩ ነው ምክንያቱም አንዳንድ የኦሮሞ ልጆች ሸኔ የሆነ ነገር ያመጣልን ይሆን እንዴ? የእኛን ቋንቋ ይናገራሉ እያሉ ከሚዘናጉ ጉዳዩን ያጠራዋል።
ሸኔ በቀላሉ ህወሓትን መጣል ሲችል ህወሓት እንዲነግስ ሲሠራ የቆየ ድርጅት ሆኖ የተፈጠረ ነው። ኦሮሞ ላይ የተጫነና የነገደ ስለሆነ አሁን ህዝብ በአግባቡ እንዲለየው ይበልጥ ጠርቶ ተቀምጧል። በወያኔ ላይ የሚደረገው ትግል በሸኔም ላይ መደረግ አለበት። ይህንን ህዝባችን መገንዘብ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ የሁለቱ ጥምረት እስከምን ይወስዳቸዋል?
አቶ ታዬ፡– በእኔ እይታ ሁለቱም ጠፊዎች ናቸው። ለምን ካልን የያዙት አጀንዳ ግልጽ ፤ በአንድ በኩል አረመኔዎች መሆናቸውን ዓለምም ያውቀዋል። በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ግፍን ፈጽመዋል። ወያኔ ሰው አኮላሽቷል፣ ጥፍር ነቅሏል ስንል ሸኔም ፕላስቲክ እያቀለጠ ሰው መግደሉን የኢትዮጵያ ህዝብ አይረሳውም።
ሸኔ የሦስት ወር ሕፃናትን ያረደ ቡድን ነው። ልጆች ፊት አባትን ረሽኗል። ህወሓትም የፈጠመው ግፍ ከዚህ የተለየ አይደለም ስለዚህ ይህ ከልክ ያለፈ ጥፋታቸው የተደበቀ አይደለም። በሌላ በኩል በህዝብ ስም ነው የሚነግዱት። አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም ለረጅም ጊዜ ነግዷል። ሸኔም እንደዚሁ በኦሮሞ ስም እየነገደ ነው።
ሁለቱም ለሚነግዱበት ህዝብ ይዘው የሚሄዱት እሳት ነው፤ አፈሙዝ ነው። ሕፃናትና ወጣቶችን በጦርነት መማገድ ነው ዓላማቸው። ይህን ዓይነት አመለካከት የያዘ ደግሞ ዕድሜው አጭር ነው። ይህን ሁሉ ዓላማህንና ግፍ ህዝብ በቃኝ የሚል ከሆነ ደግሞ መጨረሻህ አያምርም።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተቀበላቸው እና በቃችሁኝ ያላቸው በመሆናቸው መጥፋታቸው አይቀሬ ነው። አሸባሪ ከአሸባሪው ጋር ቢተባበር ለጥፋት ካልሆነ በቀል ለበጎ ነገር እንደማይሆን ይታወቃል። መንግሥትም ከህዝብ ጋር በመሆን አሸባሪዎቹን ከሀገራችን ለማጥፋት ቆርጧል። ስለዚህ ጥምረትም ብንለው በጋራ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የትም የሚያደርሳቸው አይደለም።
ህዝብ የእራሱን መንግስት መርጧል። ስለዚህ ህዝብ ከመንግሥት ጋር ሆኖ ይታገላቸዋል። ህወሓትና ሸኔ ዝምድናቸው እስኪሞቱ ድረስ ነው የሚቆየው። ወደገደል እየሄዱ ስለሆነ አሁን የሚለያዩበት ጊዜም አያገኙም።
ህወሓት እራሱ ይሞታል፤ ሸኔም ይሞታል የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በአንድነቱና በወንድማማችነቱ የበለጸገች ሀገር ይገነባል። እነዚህን እኩይ ቡድኖች ምንም ዓይነት ድጋፍ ከተለያዩ አካላት ቢያገኙ የኢትዮጵያ ህዝብ እስካልፈቀደ ድረስ ቢጣመሩም ባይጣመሩም በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ኃይል ሆነው አይቀጥሉም።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ህወሓት ችግሬ ከአማራ ጋር ነው ሲል ቆየ፤ ከዚያም አልፎ የአፋር ክልል ላይ ጥቃት በማድረስ እንዲሁም አዲስ አበባ ድረስ ነው መምጣት የምፈልገው በማለት የተለያዩ የሽብር ተግባራን ሲነዛ ቆየ፤ ይህ የሚያመላክተው ጉዳይ አለ?
አቶ ታዬ፡– አሸባሪው ህወሓት እኮ ችግሩ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሓት ቁስል የሌለበት ማን ነው? አይደለም በብሔር ደረጃ በግለሰብ ደረጃ በርካታስ በህወሓት ምክንያት ቆስሏል። ጓደኛው አሊያም ዘመዱ ያልተጎዳበት የለም።
የህወሓት ጉዳይ ከአማራ ጋር ብቻ አይደለም። በዚያ ረገድ የህወሓትን አጀንዳ ተቀብለው የህወሓት አጀንዳ የእኛ ብቻ ነው የሚሉትም ወይ አልገባቸውም፤ አሊያም ህወሓትን እያገዙት ነው። የአሸባሪው ቡድን ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካም ጉዳይ ሆኗል። ከዚህም አልፎ ኢሰብዓዊ እና አረመኔያዌ ድርጊቶችን መቃወም ያለባቸው የሰው ልጆችን ሁሉ የሚነካ ችግር ነው ህወሓት እየፈጠረ ያለው።
ህወሓት አፋርን አልነካም ብሎ በጎን ሕፃናትን ይገድላል። ይህ አካሄዱ ከፋፍሎ ለመግዛት ከማሰብ የመጣ ነው። የህወሓት ጉልበት ያለው በመከፋፈል ውስጥ ስለሆነ ነው ችግሬ ከዚህ ነው ከዚያ ነው እያለ ወሬ የሚነዛው። አይደለም ብሔር ከብሔር አርሶአደሩንና ምሁራንን ለመለያየትም የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለዚህም ነው የአማራ ምሁራኖች አንዳንዶቹ ከእኛ ጋር ናቸው በማለት ሲያስወራ የነበረው።
በ1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርጫውን ተከትሎ በጋራ ያመጸበትን ወቅት ማንሳት ይቻላል። በወቅቱ ተማሪዎችን ለመከፋፈል ቅዱስ ቁርአንን በመቀዳደድ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነው የጣለው። በጎን ደግሞ እንዴት ቁርአን ይነካል የሚሉ የእራሱን ቀስቃሾች አስነሳ። ያንን የተጠናከረ የተማሪዎች ትግልም አዳከመ።
ይህንን አካሄድ ስታይ አሸባሪው ህወሓት ሁልጊዜም ብሔርን ከብሔር ሐይማኖትን ከሐይማኖት እየነጣጠለ ለማጥቃትና የእራሱን ዓላማ ብቻ ለማስፈፀም እንደሚጠቀምበት መገንዘብ ይቸላል። ስለዚህ እኛ ደግሞ ጁንታው በሚያወራው ነገር አንደናገጥም። የወያኔ አጀንዳ የአማራ ብቻ ፤ የኦሮሞም ብቻ፤ የሲዳማ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነው። ለዚህም ነው ሁሉም ሊታገለው የወጣው።
ኢትዮጵያ ወደፊት መሄድ አለባት፤ ልጄ ነገ የተሻለ ሀገር እንዲኖረው እፈልጋለሁ። ይህ እንዳይሳካ ትልቁ ሳንካ አሸባሪው ቡድን ነው። ለዚህም ነው አንድነትን የሚያሻክር ስልት የሚከተለው። ለዚህ አይነት አካሄድ ደግሞ የሚንበረከክ የለም አሁን። በተባበረ ክንድ ህወሓት ከእነአረመኔ ባህሪው ይጠፋል።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በድርድር ስም ሌሎችን እያጠፋ በአምባገነንነት የመጣ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በሌላ በኩል ቡድኑ አሁን ላይ ከመንግሥት ጋር ድርድር እፈልጋለሁ ማለቱ ምን አንድምታ አለው?
አቶ ታዬ፡– አሸባሪው ህወሓት ከመነሻው ታላቋን ትግራይን መመስረት የሚል ግልጽ ዓላማ ነበረው። መሃል ላይ በኢትዮጵያ የነበረው መንግሥት መዳከሙን ሲያይ ልዝረፋት የሚል ሃሳብ ጨመረበት።
በኋላም እስከቻልን ድረስ ኢትዮጵያን እየዘረፍን እየገዛን እንቆይ፣ በቃ ስንባል ደግሞ ኢትዮጵያን በታትነን ወደመጀመሪያው ዓላማችን እንመለስ የሚል ስምምነት አደረጉ። ማንኛውንም ድርድር ሲያደርጉ ደግሞ ከዚህ ዓላማቸው ጋር ነው የሚያያይዙት። ሰጥቶ መቀበል የሚባል ነገር በእነሱ ቤት የለም።
ድርድር ሲሉ አሸባሪዎቹ ህወሓቶች ያስቀመጧቸው ነገሮች መሟላት አለባቸው፤ አንተ የምትለውን አይቀበሉትም። ስለዚህ ድርድር የሚባለው በስም ካልሆነ አያውቁትም ማለት ነው። ቀደም ካለው ታሪካቸው ብናይ ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አንድ ፓርቲን አብረን እንሥራ ወንድማማቾች ነን ብለው ከተወያዩ በኋላ ድግስ ተደግሶ ከተጫወቱ በኋላ ሌሊት ላይ በሙሉ ነው የገደሏቸው።
በ1998 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ ፓርቲዎች ቤት የመዋል ተቃውሞን ሊጠሩ ሲሉ እንደራደር ብለው ነው ያስቆሟቸው። ከዚያም በድርድር ስም ሁሉንም በማሰር ነው ድርድርን ያፈረሱት። ከኦነግ ጋርም ከዚህ በፊት ስምምነት አድርገው ነበር። ኦነጎች ሲገቡ ግን ትጥቅ ፍቱና ስልጣንም ለመጋራት እንደራደር አሉ።
ይሁንና 1985 ዓ.ም አካባቢ የኦነግን ሠራዊት ልክ ትግራይ ላይ በሰሜን እዝ እንደፈጸሙት ጥቃት ድንገት ተነስተው ነው ከበው የፈጇቸው። ስለዚህ የህወሓት ዓላማና ዓላማ ብቻ መሳካት አለበት እንጂ ድርድር ብለው የሚመጡበት አካሄድ ግቡ ለመሸወድ ብቻ ነው።
አይሳካላቸውም እንጂ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ አሁን ደግሞ አብረን መንግሥት እንሆናለን የሚል ስምምነቶች እንዳደረጉ በመረጃ ደረጃ ያገኘነው አለ። እኛ ሪፐብሊክ መሆን እንፈልጋለን፣ ይሁንና እስከአዲስ አበባ ድረስ መጥተን መንግሥትን ካጠፋን በኋላ ከተማዋን ለእናንተ ሰጥተን ወደትግራይ ነው መመለስ የምንፈልገው የሚል የሞኝ ስምምነት አላቸው።
አሸባሪው ሸኔ ኦሮሚያን ሲመሰርት አሸባሪው ህወሓት ትልቋን ትግራይ እንጂ ኢትዮጵያን አንፈልግም የሚል ስምምነት አድርገዋል። አይሆንም እንጂ ቢመጡ እንኳን ሸኔን በመጨረሻ ድራሹ እንደሚጠፋ አያጠያይቅም። እስከጠቀማቸው ድረስ ከሸኔ ጋር ይስማማሉ በኋላ ግን ዘወር በል እንደሚሉት ይታወቃል። ያም ሆነ ይህ ግን ቀድሞውኑም የሁለቱም የድርድር እቅድም ሆነ ዓላማቸው ሊሳካ የማይችል ምኞት ነው።
በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሓት አሁን ላይ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ቢፈልግም የማይሆን ነው፤ ከአሸባሪ ጋር የሚደራደር መንግሥት የለም። በእርግጥ ቀደም ብሎ ፌዴራል መንግሥት ነገሮችን በሰላም ለመጨረስ ብሎ ብዙ ጥረት አድርጓል ግን አልሠራም።
ከዚህ በኋላ ሰሜን እዝ ላይ የሠሩት ግፍ እያለ፣ ብሔርን ከብሔር ለማባላት የሰሩት እያለ፤ ወረራ ፈጽመው ክልሎችን በመጉዳታቸው፣ ሀገርን ለመበታተን በግልጽ በመንቀሳቀሳቸው ድርድር ብሎ ነገር ከእነሱ ጋር የማይታሰብ እንዲሆን አድርጎታል።
ቀድሞውንም በድርድር ስም የሚያጭጥበረብሩ ሆነው ሳለ ይባስ ብሎ ጥፋተኝነታቸው እና ሽብርተኝነታቸው እየከፋ ከመጣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የህልውና ዘመቻውን በብቃት መወጣት እንጂ ከጁንታው ቡድን ጋር የመደራደርም ፍላጎት አይኖርም። አሁን ያለው አማራጭ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር መደራደር ሳይሆን ታግሎ ማሸነፍ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ሀገራትም ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ያስፈልጋል እያሉ ነው በዚህ ላይ ምን የሚሉት ነገር አለ?
አቶ ታዬ፡– ህወሓት አሸባሪ ቡድን ነው፤ ከህወሓት ጋር የሚደረግ ውይይት አይኖርም። መንግሥትም ለዚህ ፍላጎት የለውም። ሁሉን አቀፍ ውይይት እያሉ ለሚያነሱት ግን መንግሥት በትግራይ ከሚገኙ ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ቀድሞም የሄደበት መንገድ አለ።
አሸባሪው ሸኔም የዚሁ አካል ነውና ከእነሱም ጋር መንግሥት ለውይይት አይቀርብም። ህዝብ ያልተቀበላቸውንና ትልቅ ጥፋት ያደረሱትን በድርድር ስም ማቅረብ አይገባም። ህዝብም በነቂስ ወጥቶ እየታገላቸው ባለበት ወቅት ሌላ ሥራ አይሠራም።
የኢትዮጵያ ህዝብም ጠላቱን በአንድነት በመታገል ረገድ ታሪክ አለው። አሁንም ከሁሉም ጫፎች የሚገኙ ወጣቶች ባንዲራ ይዘው እያለቀሱ የሚነሱበት ምክንያት ሌላ ምስጢር የለውም። ስለተመቻቸውም አይደለም፤ ዋናው ጉዳይ ሀገር ነው የሚለውን በመገንዝብ ነው። ሀገር ከሌለ ምንም አይኖርም።
ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ደግሞ ውድ ሊሆን አይችልም። ማንኛውም አይነት መስዋዕትነት እንከፍላለን በሚል ነው እየዘመቱ የሚገኘው። ህዝቡም ከራሱ ቀንሶ ሰንጋ እና በግ እየሰጠ ነው። ይህ የሚያሳየው ለሀገሩ ነፃነት፤ ለእራሱ ክብር ምን ያክል ቆራጥ አቋም እንዳለው ነው። ይህንን ቆራጥና የተባበረ ህዝብ ደግሞ ማንም ሊያሸንፈው አይችልም።
ስለዚህ በኃይል የሚጠፉት ይጠፋሉ፤ ሁሉን አቀፍ ውይይት በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ አካላትና፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በአጠቃለለ መልኩ የሚደረጉ ውይይትች ግን ይቀጥላሉ።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ኃይሎች በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት እንዲያንሰራራ የመፈለጋቸው ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ታዬ፡- የውጭ ኃይሎች የእራሳቸው ፍላጎት አላቸው። አሸባሪውን ህወሓትንም ወደውት አይደለም የሚደግፉት። እነዚህ ዓይነት ቡድን ተስፋ ስለሌለው ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚጥረው ለውጭ ሀገራት እየታዘዘ እና እየተላላከ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ የኃያላን ሀገራት ተወካይ እንጂ የኢትዮጵያ አመራር አልነበረም። ለዚህ ነው አሁንም እንዲያንሰራራላቸው የሚፈልጉት። ቀደም ባለው ጊዜ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ ሳለኮ የውጭ ሀገራትን አጀንዳ ያላስፈጸመበት ጊዜ የለም።
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት ሲፈርሱ፤ አገልግሎት ሲላሽቅ ታይቷል፤ ፍትህ ሲዛባ ታይቷል። ህወሓት ግን የሌሎች ሀገራት መሞከሪያ እና ጉዳይ አስፈጻሚ ስለነበር የሀገሩ ጉዳይ አያሳስበውም ነበር። ይሄን እያዩ የውጭ ሀገራት ምንም አይሉትም፤ ሰው ሲያኮላሽና በጅምላ ሲገድልም ዝም ነበር የሚሉት። ምክንያቱን የእነሱን አጀንዳ ስለሚያስፈጽም ነው።
አሸባሪው ህወሓት ለውጭ ኃይሎች ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ቡድን ነው። አሁን በኢትዮጵያ ያለው አመራር ይህንን ነው የቀየረው። ኢትዮጵያዊነትን ለማንገስ ነው መንግሥት የሚሠራው። ውስንነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመርህ ደረጃ ግን የበለጸገች እና የተከበረች ኢትዮጵያ እንድትኖር ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ አመራር ነው ያለው። ይህ ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብ ሀገራት አይመቻቸውም።
አሁን ያለው መንግሥት የስልጣን መሰረቱን ህዝብ ማድረግ ይፈልጋል። ይህ ከሆነ ደግሞ ተላላኪነት ይቀራል። በዚህ አካሄድ መንግሥት ቢቀየርም የሚመጣውም መንግሥት የህዝብን አጀንዳ ነው የሚከተለው። ይህ ከሆነ የመበልጸግም የማደግ ዕድል አለ። የውጭ ኃይሎች ደግሞ እንድንበለጽግ አይፈልጉም።
ኒዮ ኮሎኒያሊዝም አሁንም አለ፤ አፍሪካ ነፃ አልወጣም ከውጭ ኃይሎች። ፈረንጆቹ በግልጽ እንደተናገሩትም አፍሪካውያን ከድህነታቸው ከወጡ የእነሱ የህይወት ደረጃ ይቀንሳል። ዕርዳታ እና ብድር የሚሉት የእነሱ ሰንሰለት ነው። ስንዴ እየተሰፈረልን እንዳንሞት በሌላ በኩል ደግሞ እንዳናድግ ያደርጋሉ። በሂደቱም የእነሱን ዕርዳታ እየተቀበልን ጉዳያቸውን የምናስፈጽምላቸው እንድንሆን ነው ምኞታቸው።
ስንት ዓመት ተረድተናል፤ ጠብ ያለ ነገር የለም። በዕርዳታ ስም የዓላማቸው ማስፈጸሚያ መንግሥት ይሻሉ። ስለዚህ ለእነሱ የሚመቻቸውንና የሚላላክላቸውን መንግሥት ነው መትከል የሚገፈልጉት። አምባገነን ብትሆንም ዓላማቸውን ካስፈጸምክ እንደነሆስኒ ሙባረክ 30 ዓመት ትገዛለህ፤ በዴሞክራሲ ስም ትሞሸራለህ። በዚህ አግባብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ይልቅ አሸባሪው ህወሓት ይመቻቸዋል።
ስለዚህ የደከመች ኢትዮጵያን የሚፈጥርላቸው እና አላማቸውን የሚያሳካላቸውን አሸባሪውን ህወሓት ቢደግፉ አይገርምም። አሁን ያለው የኢትዮጵያ አመራር ደግሞ የእራሳችንን ችግር በእራሳችን መነጸር አይተን በእራሳችን መድሐኒት ማከም አለብን የሚል አቅጣጫ አለው። ይህ አይመቻቸውም ችግራችሁን እኛ እናውቃለን የሚመቻችሁን እኛ እንሰጣችኋለን ነውና አካሄዳቸው ከመንግሽት ይልቅ ህወሓትን መደገፍ መርጠዋል።
ኢትዮጵያ ደግሞ ሉአላዊነቴን አስከብሬ የመልማት መብቴ ይከበር ስላለች ቅር ያላቸው የውጭ ኃይሎች አሉ። በዚያው ልክ ደግሞ የምናመሰግናቸው፤ የኢትዮጵያን መብት ያከበሩና በችግር ጊዜ አብረው የቆሙም ሀገራት አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በህልውናው ዘመቻ መንግሥት በሚወስደው እርምጃ ልክ መንግሥት ያለው አቅም ምን ያክል ነው?
አቶ ታዬ፡– የመንግሥት አቅም የመቶ ሚሊዮን ህዝብ አቅም ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ሉአላዊነቱን ማስከበር ይፈልጋል። አሸባሪዎቹ ወያኔም ሆነ ሸኔ የሚያራምዷቸው ሃሳቦች ኢተዮጵያን የማዳከምና የማደሕየት ነው። ይህንን የማስተካከል አቅም የህዝብ ነው።
መንግሥት በቂ የመከላከያ ኃይል አደራጅቷል። ተጨማሪ ወጣቶችም ወደማሰልጠኛ ገብተዋል። ህዝብ ደግሞ በሁሉም ረገድ ከመንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆሙን በሚሰጠው ድጋፍ እያሳየ ነው። የህዝብ ድጋፍ ይዞ ደግሞ መንግሥት እያስተባበረ እና ውሳኔ እየተሰጠ የህልውናውን ዘመቻ በብቃት የሚወጣበት ቁመና ላይ ይገኛል።
አሸባሪው ህወሓት የ15 እና የ16 ዓመት ወጣቶችን ለቀናት እያሰለጠነ በጦርነት ያሰልፋል። ሕፃናትንም ያስገድላል። ከዚህ ባለፈ ግን በፕሮፓጋንዳው ይህንን ከተማ ተቆጣጠርኩ ይህንን ያዝኩ እያለ የሚዋሽበት ሁኔታ ነበር። አሁን ላይ ተደብቆም ቢሆን አንዳንድ ከተማ የሚገባበት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በጥቃት ቦታ የሚይዝበት ሁኔታ የለም። ያሰለፋቸው ወጣቶችም እጃቸውን ለመከላከያ እየሰጡ ይገኛል።
አሸባሪው ህወሓት አሁን አቅም የለውም፤ መንግሥትም በአንጻሩ የተደራጀ አቅም አለው። አንዳንድ ሰዎች ግር የሚላቸውና ሊስተካከል የሚገባውም። አሸባሪው ህወሓት ከሦስት ዓመት በፊት መከላከያውን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥሮ፣ የደህንነት መዋቅሩን 92 በመቶ ይዞ፣ ኢኮኖሚውንም እየተቆጣጠረ ሳለ እንኳን በህዝብ ኃይል ነው የወደቀው።
አሁን ደግሞ ዋና ዋና የሚባሉ አመራሮቹ ተገድለው፤ የመከላከያ እና ደህንነት አቅሙ ሳይኖረው በየጉድጓዱ እየተሽሎከሎከ በእነዚህ ሕፃናት ያሸንፋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ህወሓት አሁን ላሊበላን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በግድ እንዲለቅ ተደርጓል።
አሁን አሸባሪው ህወሓት በምንም አይነት መልኩ ወደፊት የሚሄድበት አቅም የለውም፤ መንግሥትም እያንዳንዱን እቅስቃሴ እየተከታተለ ነው። አስፈላጊው ድጋፍም እየቀረበ ነው። መከላከያ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችም አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰዱ በመሆኑ አሸባሪው ህወሓት ህልውና የሚጠናቀቅበት ወቅት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን አያጠያይቅም።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ታዬ፡- እኔም እጅግ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013