አባታቸው እንዳሉ በማሰብ እንዲማሩ ከማድረጉም በላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዝምድና በመፍጠር ሀገራዊ አንድነት እንዲጐለብት ያደርጋል። ይህም ለጽድቅ ሳይሆን ከአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ነው። ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ የቋንቋ ተናጋሪዎች የተወለድን ነን፣ አሁን ላይ የተከሰተውን የዘረኝነትና የጎጠኝነት በሽታ ለማከም ኃላፊነታችን ነው›› ስትል ገልፃለች።
በቋንቋ ሰበብ የተከሰተውን ሀገራዊ ችግር መቅረፊያ መንገዱ ኢትዮጵያዊ መሆንና በሰብአዊነት ማመን ነው። ስለሆነም ልጆቻቸው የመጡት ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልልች መሆኑን ጠቁመው፣ በሁለቱም የልጆች ቤተሰብ የሚፈጠረው ኢትዮጵያዊ የሆነ ቤተሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጅግጅጋ የመጣችው ተማሪ ሄርሜላ ተወልደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስትመደብ ስለጐንደር ዩኒቨርስቲ የሚወራው የሀሰት ወሬ አስጨንቋት ነበር። ትምህርቷን ማቋረጥ ስላልፈለገች ብቻ እየተጨነቀች እንደመጣች ገልጻ፣ ዩኒቨርሲቲው ስትደርስ ግን ሁሉም ስለጐንደር የተወራው ሁሉ ሀሰት ሆኖ አግኝታዋለች። ‹‹ወላጅ በማግኘቴ ሁለተኛ ጐንደር እንደተወለድኩ ተሰምቶኛል›› ስትል ስሜቷን ገልጻለች።
ሌላኛው ከኦሮሚያ ክልል፣ ጉጂ ዞን የመጣው ተማሪ ቢሽን አየለ የሄርሜላ አይነት ስሜት ፈጥሮበት እንደነበር አስታውሶ፣ ‹‹በሀሰት ወሬ ሰው መሸበርና መጥላት የለበትም። ቤተሰቦቼ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እናንተን ተክቶ የሚንከባከበኝ ወላጅ፣ እህት፣ ጓደኛ አግኝቻለሁ›› ይላል። ሁሉም ከጐንደር ዩኒቨርስቲ እና ማህበረሰብ ቢማር ሀገራችን አንድ እንድትሆን የሚያደርግ ትልቅ እድል ነው።
የክረምት ወቅትን ተከትለው ከሚመጡ ህመሞች መካከል በጉንፋንና በሌሎች ምክንያቶች የሚመጣው የቶንሲል ህመም ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ የህክምና ቤት ደጃፍን አንኳኩተናል። ስለ ቶንሲል የምናውቀው እና የምንሳሳተው ምንድን ነው የሚለውን ሀሳብ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ንጉሴ ጫኔ በዚህ መልኩ አብራርተውልናል።
ቶንሲል ለብዙዎቻችን እንደሚመስለን በሽታ አይደለም። ቶንሲል ማለት ትንንሽ አበጥ ያሉ የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ አካላት ስብስብ ነው። ይህም በክብ ቀለበት ከምላስ ጀርባ የላንቃን የጎን ግድግዳ እና የላንቃን ክዳንና የአፍንጫን የውስጠኛ ክፍሎች ያስተሳስራል። ቶንሲል ጥቅሙ በአፍም በአፍንጫም የሚገቡ ተህዋስያንን መዋጋት ነው። የሰውነትን በር ከጠላት መከላከያ ነው።
ቶንሲል እና እንጥል ሁለቱም በላንቃ አካባቢ ይገኛሉ። ግንኙነታቸው ግን ጉርብትና እንጅ በአገልግሎት አይገናኙም። እንጥል ማለት ከላንቃ ላይ የተንጠለጠለ ማለት ነው። ከቶንሲል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።
የቶንሲል ህመም /tonsialiophayngitis ማለት የቶንሲል እና የላንቃ አካባቢ በተህዋስያን መወረር ነው።
የህመሙ ምልክቶች ትኩሳት፣ ለመዋጥ መቸገር፣ ራስ ምታት፣ የአፍ መሽተት፣ የአንገት ንፍፊት እብጠት፣ ማንኮራፋት፣ ሳል ናቸው።
የቶንሲል ህመም መተላለፊያ መንገዶች በትንፋሽ ጠብታና በንክኪ ነው። የባክቴሪያ ቶንሲል ከሁለት አመት በላይ የሆኑ ህጻናትን የሚያጠቃ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከ5 እስከ 15 እድሜ ያሉት ይጠቃሉ። የቫይረስ ሲሆን ደግሞ ለጋ ህጻናትም ይጠቃሉ።
የቶንሲል ህመም ተያያዥ ችግሮች መግል መቋጠር tonsiar, peritosilar or retropharyngeal abscess
የሳንባ ምች / የማጅራት ገትር የልብ ህመም rheumatic heart disease የኩላሊት ህመም PS glomerulonephritis የቶንሲል መፋፋት adenotonsilar hyperthrophy ሲሆኑ ይህን ለመከላከል ቶንሲል እንዳመመን ወደ ጤና ተቋም መሄድ የሚገባ መሆኑን አስረድተዋል።
የቶንሲል ህመም ህክምና ለመስጠት መጀመሪያ የባክቴሪያ ወይስ የቫይረስ ነው የሚለውን መለየት
ያስፈልጋል። ይህንንም መለያ መንገዶች፤
1. የቫይረስ ከሆነ የጉንፋን ምልክት አብሮ ይኖራል ግን አንዳንድ ጊዜ እንደ ቫይረስ ጀምሮ ወደ ባክቴሪያ ሊቀየር ስለሚችል ጥንቃቄ ይፈልጋል።
2. መግል የያዘ ከሆነ የባክቴሪያ ምልክት ነው ግን ይህን በደንብ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል።
3. ድድ፣ ከንፈር ወይም ምላስ የቆሰሉ ከሆነ የቫይረስ ምልክት ነው።
4. የነጭ የደም ሴል እና ተያያዥ ምርመራ ይለያል።
ለቶንሲል ህመም የተዘጋጁት መድሃኒቶች፤ የህመም
ማስታገሻ፤ እንደ ቶንሲሉ ህመም መነሻ የተለያዩ ጸረ ባክቴሪያ አለበለዚያም ፀረ ቫይረስ መድሃኒት፤ በቂ ፈሳሽ መውሰድ ዕረፍት ማድረግ፤ ማር እና የውሃ እንፋሎት መታጠን፤ የብርቱካን ወይም ሎሚ ጭማቂ መጠቀም ፈውስ ከሚሰጡት መካከል ናቸው።
ሌላው የቶንሲልና/የአዴኖይድ ማደግ (adenotonsillar hypertrophy) የእንቅልፍ ጊዜ አየር ማጠር (Obstructive sleep apnea s.) አንዱ መንስኤ ሲሆን፤ ይህም ያደገው ቶንሲል/አዴኖይድ በእንቅልፍ ሰዓት የአየር ቧንቧን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሲዘጋ የሚከሰት በሽታ ነው።
በሽታው ቶንሲል በተደጋጋሚ በሚታመሙና አለርጂ ባለባቸው ልጆች ላይ የበለጠ ይታያል። ምልክቶቹም በሁለት ይከፈላሉ፤ ማታ ሊኖራቸው የሚችሉ የህመሙ ምልክቶች፤ ማንኮራፋት፤ እያረፉ መተንፈስ፤ ተረጋግቶ አለመተኛት (ከመጠን በላይ መገላበጥ) restless sleep፤ አፍ ከፍቶ መተኛት/በአፍ መተንፈስ፤ አልጋ ላይ መሽናት (bedwetting) ሲሆን ቀን ሊኖራቸው የሚችሉ የህመሙ ምልክቶች፤ ክብደት አለመጨመር፤ ትምህርት ቤት በንቃት አለመከታተል፤ ትኩረት ማጣት፤ የልብ ችግር፤ ተደጋጋሚ የጆሮ ኢንፌክሽን ናቸው።
የዚህኛው የቶንሲል አይነት ህክምናው፤ ከመጠን በላይ ያደገውን ቶንሲልና አዴኖይድ በኦፕሬሽን ማስወጣት ነው። ይህም ልጁ የተረጋጋ እንቅልፍ እንዲኖረውና ወደ ጤናው እንዲመለስ ያደርገዋል።
ለእያንዳንዱ ህመም መፍትሄ ለማግኘት በጊዜ ወደ ህክምና ተቋማት መምጣት አስፈላጊ በመሆኑ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚለው መርህ በሁሉም ማህበረሰብ ሊተገበር የሚገባው መሆኑን አስረድተውናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013