ከትውልድ ቀያቸው ርቀው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ሁሉም እንግዳ ሆኖባቸው የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማቸው በርካቶች ናቸው። ታዲያ ይህን የባይተዋርነት ስሜት ለመግታት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የከተማዋ ነዋሪዎች ተማሪዎቹን ልጅ በማድረግ እንዲንከባከቧቸው የሚያስችል ‹‹የጎንደር ፕሮጀክት›› የተሰኘ መርሃግብር ነድፎ መተግበር ከጀመረ ሁለተኛ አመቱን አስቆጥሯል። ፕሮግራሙ ከተለያዩ ክልሎች በመጡ ተማሪዎች አማካኝነት የማይተዋወቁ የህብረተሰብ ክፍሎች በመተዋወቅ በኢትዮጵያዊ ፍቅር እንዲተሳሰሩ እያደረገ ነው።
‹‹ጎንደር በጠብ የመጣን ውርደትን፤በፍቅር የመጣን ፍቅር ታለብሳለች›› እንደሚባለው ባሳለፍነው ሳምንት ሁለተኛው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃልኪዳን ጥምረት ፕሮጀክት ሲጀመር የከተማዋ ነዋሪዎች በሀገረኛ ልብስ አጊጠው፣ በሳቅና በደስታ ታጅበው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ጐንደር ዩኒቨርስቲ የተመደቡ አዲስ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ በማድረግ አስተሳስሯል። ተማሪዎች በፈገግታ፣ ተስፋ በተሞላበት ራእይ ከወላጆቻቸው ጋር ተገናኝተዋል።
በሁለተኛው የተማሪዎች ወላጆች የቃልኪዳን ጥምረት መድረክ በቅርቡ ስለሀገር አንድነት ያዜመው በአጭር ጊዜ ውስጥ በህዝብ ልብ ውስጥ መግባት የቻለው “ዲሽታጊና” የሚል ሙዚቃ የሚጫወተው ታሪኩ ጋንካሲ (በቅጽል ስሙ ዲሽታጊና) ከተማሪዎች ፊት ደረሰ። ተማሪዎቹ ተነስተው ኢትዮጵያዊ ፍቀር በተሞላበት ድምጽ ተቀበሉበት። ታሪኩ ዲሽታጊና ባሳዩት ኢትዮጵያዊ ፍቅር በደስታ አነባ።
ከዚህ በፊት አሸባሪው ህወሓት ስለጐንደር የዘራውን የተዛባ አስተሳሰብን ጎንደር በፍቅር ሰብራዋለች። በዚህ ሁነት ‹‹በፍቅር የመጣን ፍቅር ታለብሳለች ለጠብ የመጣን ውርደትን ታከናንባለች›› የተባለውን ብሒል በተግባር አሳየች። “የሰላሙ ዩኒቨርሲቲ” ተብሎ የሚጠራው የጐንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የብቸኝነት ስሜት ሳይሰማቸው እንዲማሩ የሚያደርግ ቁልፍ የሆነ የሀገራዊ ስሜት የሚፈጥር የወላጆች ተማሪዎች ትስስር ላይ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ሁለተኛው ዩኒቨርስቲው ፕሮጀክት በተጀመረበት ወቅት ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ እየተሸረሸረ የመጣውን ሀገራዊ አንድነትን ለመጠገን ከመርዳቱም በላይ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል። ጐንደር በሀገራዊ አንድነት ኮትኩታ ያሳደገቻቸው ልጆቿ ከኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ሀረር፣ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል፣ ድሬዳዋና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን ተቀብለው ከአብራካቸው ከወጡት ልጆች ጋር በማዋሃድ ለመንከባከብ ቃል ገብተዋል። “የተማሪዎች እና የወላጆች የቃል ኪዳን ትስስር” የተሰኘው ፕሮጀክት በጐንደር ማህበረሰብና በጐንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ጥብቅ ቤተሰባዊ ትስስር በመመስረት በጐንደሬ የእንግዳ ወዳጅነትና አክባሪነት ኢትዮጵያውያዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃልኪዳን ትስስር ፕሮጀክት ሁለተኛ ልጃቸውን ለመቀበል የመጡት የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ወልደገብርኤል ፍሬይ አብርሃ ትውልዳቸው ኤርትራዊ እንደሆነ ገልጸው፣ በመምህርነት አገልግለው አሁን ላይ ጡረታ ላይ ናቸው። ጐንደር ዩኒቨርስቲ የሰጣቸው ልጅ ተመስገን ስባቱ ሲባል ለልጆቻቸው ወንድም ነው። በትምህርቱ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ወላጆችንና ተማሪዎችን የማስተሳሰር ፕሮግራም ለሀገር አንድነት መጎልበት ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው። ‹‹ልጁ ከየት እንደመጣ፣ ምን እንደሆነ ማወቅ አልፈልግም። ማወቅ እምፈልገው ሰው በመሆኑ እና ሰው በመሆኔ መገናኘታችን ነው›› ይላሉ። ‹‹ቤተሰቦቹን በመተዋወቅ ኢትዮጵያዊ ዝምድናን ለማጠናከርና ለመንከባከብ ከዩኒቨርሲቲው መረከባቸውን ጠቁመዋል። የሚያገናኘን ኢትዮጵያዊ ደም ነው እንጂ በህወሃት የተጀመረው አፍራሽ የሆነው ጐጠኝነት አይደለም›› ሲሉም ይናገራሉ።
ተማሪ ተመስገን ስባቱ ከምዕራብ ወለጋ መምጣቱን ገልጾ፣ አባቱ በህይወት እንደሌለና አሁን አባት በማግኘቱ በደስታ አቅፎ አንብቷል። ‹‹አማራ፣ ኦሮሞ እያሉ ከፋፍለውን ነበር። አሁን አንድ ሁነናል፤ አንድነታችን ጠንክሮ እንዲቀጥል አምባሳደር ሆኜ እሰራለሁ›› በማለት ተናግሯል።
ወይዘሮ አክሱማዊት አብረሃ በበኩሏ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ከቤተሰብ ርቃ ስትማር የተሰማትን የብቸኝነት ስሜት በማስታወስ፣ እርሳቸው ያሳለፉት ብቸኝነት አሁን ላይ ተማሪዎች እንዳይሰማቸው ፍቅር በመስጠት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል ሁለት ልጆችን ተቀብለዋል። ‹‹ይህ ተግባር ምንም አይነት ችግር ቢፈጠር ሳይሳቀቁ እናትና
አባታቸው እንዳሉ በማሰብ እንዲማሩ ከማድረጉም በላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዝምድና በመፍጠር ሀገራዊ አንድነት እንዲጐለብት ያደርጋል። ይህም ለጽድቅ ሳይሆን ከአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ነው። ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ የቋንቋ ተናጋሪዎች የተወለድን ነን፣ አሁን ላይ የተከሰተውን የዘረኝነትና የጎጠኝነት በሽታ ለማከም ኃላፊነታችን ነው›› ስትል ገልፃለች።
በቋንቋ ሰበብ የተከሰተውን ሀገራዊ ችግር መቅረፊያ መንገዱ ኢትዮጵያዊ መሆንና በሰብአዊነት ማመን ነው። ስለሆነም ልጆቻቸው የመጡት ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልልች መሆኑን ጠቁመው፣ በሁለቱም የልጆች ቤተሰብ የሚፈጠረው ኢትዮጵያዊ የሆነ ቤተሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጅግጅጋ የመጣችው ተማሪ ሄርሜላ ተወልደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስትመደብ ስለጐንደር ዩኒቨርስቲ የሚወራው የሀሰት ወሬ አስጨንቋት ነበር። ትምህርቷን ማቋረጥ ስላልፈለገች ብቻ እየተጨነቀች እንደመጣች ገልጻ፣ ዩኒቨርሲቲው ስትደርስ ግን ሁሉም ስለጐንደር የተወራው ሁሉ ሀሰት ሆኖ አግኝታዋለች። ‹‹ወላጅ በማግኘቴ ሁለተኛ ጐንደር እንደተወለድኩ ተሰምቶኛል›› ስትል ስሜቷን ገልጻለች።
ሌላኛው ከኦሮሚያ ክልል፣ ጉጂ ዞን የመጣው ተማሪ ቢሽን አየለ የሄርሜላ አይነት ስሜት ፈጥሮበት እንደነበር አስታውሶ፣ ‹‹በሀሰት ወሬ ሰው መሸበርና መጥላት የለበትም። ቤተሰቦቼ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እናንተን ተክቶ የሚንከባከበኝ ወላጅ፣ እህት፣ ጓደኛ አግኝቻለሁ›› ይላል። ሁሉም ከጐንደር ዩኒቨርስቲ እና ማህበረሰብ ቢማር ሀገራችን አንድ እንድትሆን የሚያደርግ ትልቅ እድል ነው።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013