የባቄላ ቆሎ፣ ከእንሰት እና ከጥቁር ጤፍ በዳቦ መልክ የተዘጋጀውን ምግብ፣ልሞ ከተፈጨ ነጭ ሽንኩርት፣ ማር፣ አይብ ከተለያየ ቅመማቅመም ከተሰናዳው ማባያ ጋር፣ ቡናውም ከእንጨት ውጤት በተሰራ ስኒ ቀረበልን። በወጣት የሙዚቃ ቡድን አባላት እየቀረበ ካለው የባህል ዘፈን ጋር ምግቡን እያጣጣምን ዘና አልን። በመካከላችንም በባህል አልባሳት የተዋቡም ስለነበሩ ታዳሚው በጨዋታውም ጭምር በባህል ድባብ ውስጥ ነበር ሰአታትን ያሳለፈው። በተለይም ከተማ ውስጥ የሚኖረው ቱባ ከሆነው ባህል የራቀ በመሆኑ እንዲህ ከአልባስ እስከ ምግብ ባህልን የተላበሰ አጋጣሚ ሲገኝ ልዩ ስሜት ይፈጥራል። አንዳንዶችም በሥራና በተለያየ ምክንያት ከትውልድ ቀያቸው ከራቁ ረጅም አመት ያስቆጠሩ ስለነበሩ ተወልደው ያደጉበትን አካባቢ የሚያስታውሳቸው ነገር በማግኘታቸው ልዩ ደስታ ተሰምቷቸው ነበር ያረፈዱት።
በተለመደው ኢትዮጵያዊ የባህል መስተንግዶ የአካባቢው ምድር ያፈራውንና በባለሙያ ሴቶች የተዘጋጀውን የባህል ምግብ ያቋደሰው፣በባህል ዘፈንና ጭፈራም እያዝናና አንዳንዶች የአካባቢያቸው ትዝታ እንዲኖራቸው አካባቢውንም ለማያውቁ ያስተዋወቀው የከፋ ዞን ነበር። እንዲህ ድንቅ የሆነውን የከፋን አካባቢ የባህል እሴት በአይነ ህሊናችን እንድንቃኝ ያደረገን መስተንግዶ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ በአየርመንገዱ ስካይላይት ሆቴል ውስጥ ሆነን ነበር። ያየነውም የቀመስነውም ጥቂቱን በመሆኑ ወደፊት በሰፊው ቱባውን የአካባቢውን ባህል አዲስ አበባ ከተማ ላይ የባህል ማዕከል በመገንባት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከመላው ዓለም ለሚመጣውም ጭምር ከፋን እንዲያውቃት ለማድረግ ሩቅ እንደማይሆን ያረጋገጠበትን ለባህል ማዕከል መገንቢያ የሚውል የመሬት ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅ ዞኑ ተረክቧል።
ዞኑ የባህል መገንቢያ ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ ማግኘቱና በዚህ አጋጣሚ ትውስታቸውንም ያጫወቱኝ፣ወይዘሮ ጽጌ ብርሃኑ በአካባቢው የሚለበሰውን አልባስ ለብሰው፣ፀጉራቸውንም በሻሽ አስረው አካባቢያቸውን መስለው ነበር በካርታ ርክክቡ ላይ የተገኙት። ተወልደው ያደጉት በከፋ ዞን አዴ ወረዳ፣አዴ አካካ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣የትውልድ ቦታቸው መለስተኛ የሚባል ከተማ ውስጥ በመሆኑ የገጠሩንም የከተማውንም አኗኗር ያውቁታል። በአካባቢው ከተለመደው የእንሰት ቅጠል እንደአሻንጉሊት በመጠቀም ነበር ህፃናት ሆነው ሲጫወቱ ያሳለፉት። እደዛሬው የእህል ወፍጮ ሳይለመድ እናቶች በምግብ የሚውለውን ሁሉ በእጃቸው ፈጭተው ነበር ቤተሰቡን የሚመግቡት። ህፃናቱም በጨዋታቸው ውስጥ ወላጆቻቸው እንደሚያደርጉት አፈር እየፈጩ አብኩተው እንጀራ በመጋገር ይጫወታሉ። ያኔ ለወይዘሮ ጽጌ ጨዋታ የነበረው ዛሬ ላይ ግን የቆየውን የማህበረሰቡን መገልገያ ለማወቅ አስችሏቸዋል።
ወይዘሮ ጽጌ ከአካባቢያቸው የባህል እሴቶች የሚወዱትና የሚያስታውሱት የመስቀል በዓል አከባበር ነው። በአካባቢው አሽቃሮ ይባላል። አዲስ አመት ወይንም የዘመን መለወጫ እንደማለት ነው። ለበዓሉ ከጤፍና ከማር የሚዘጋጅ ቦርዴ የተባለ የባህል መጠጥ፣እርድ ይከናወናል። ምግቡ ቁርጥ ሥጋ ነው። ለአመታት የተራራቀ ቤተሰብ ሁሉ በዚህ ወቅት ከያለበት ይሰባሰባል። ለቀናት በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም በባህላዊ ዘፈንና ጭፈራ ቤተሰቡ በአንድነት ሁሉም በየቤቱ የሚያዘጋጀውን ከቤተሰቡና ከጎረቤቱ ጋር በመጠራራት ለቀናት አብሮ ያሳልፋል። ወይዘሮ ጽጌ በአሁኑ ጊዜ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቢያደርጉም በየአመቱ የመስቀል በዓል በትውልድ አካባቢያቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው የሚያሳልፉት።
ወይዘሮ ጽጌ አካባቢያቸውንም በደንብ ነበር ያስተዋወቁት። እርሳቸው እንዳሉት ከፋ የቡና መገኛ ናት። በዞኖ ዴቻ ወረዳ ውስጥ ነው ቡና የተገኘው። ኮፊ የሚለው የእንግሊዝኛው ቃል መጠሪያም ከከፋ ነው የመጣው ብለዋል። በማር፣በቅመማ ቅመም የታደለችው ከፋ የተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሆነ፣የሚያስደስቱ የሚጎበኙ ሌሎችም ሀብቶች መኖራቸውን፣የከፋ ህዝብ እንግዳ ወዳድና አክባሪ እንደሆነ ገልጸዋል። ለአካባቢያቸው እንዲህ የቱሪዝም አምባሳደር የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ ከባህል ጭቆናውም ያለውን ክፍተት አጫውተውኛል። ዛሬ ላይ መጠነኛ የሆነ ለውጥ እየታየ ቢሆንም፣በገጠሩ ላይ ሙሉ ለሙሉ ያልተወገደው በሴት ልጅ ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ነው። ሴት ልጅ በተፈጥሮ የምታየው የወር አበባ በምታይበት ቀን ከቤተሰቡ ተገልላ ከቤት ውጭ ትቆያለች።
ዞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ለባህል ማዕከል ግንባታ የሚውል መሬት ካርታ በማግኘቱ ያላቸውንም ስሜት እንደተናገሩት ማዕከል መገንባት ብቻውን በቂ አይደለም። ከፋ ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች፣የማህበረሰቡ መገልገያ የወግ ዕቃዎችና ታሪኮች ሁሉ ተሰብስበው ለቱሪስት መስህብነት መዘጋጀት አለባቸው። ከዚህ ደግሞ የዞኑ ማህበረሰብና ሀገርም ጥቅም ማግኘት ይኖርባቸዋል። ለባህል ማዕከሉ ግንባታ እርሳቸውም በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅና በሚችሉት ሁሉ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
የተጣላን ማስታረቅ፣የበደለ እንዲካስ ማድረግ፣በፍትህ ዕጦት የሚንገላታ ማህበረሰብ እምባው እንዲታበስ በማድረግ የኢትዮጵያውያን የሀገር ሽማግሌዎች የቆየ ተሞክሮ ነው። ይሁን እንጂ በሽምግልና ሥርአት ውስጥ አንዱ ከሌላው በተወሰነ ደረጃም ልዩነት ይኖራልና ለየት ያለ ነገር ካለ ብዬ ከዕለቱ ታዳሚዎች መካከል የቦንጋ ነዋሪ የሆኑትን የሀገር ሽማግሌ አቶ አድማሱ አተሞን ጠየኳቸው። እርሳቸው እንዳሉት በድንበር፣በትዳር አጋሮች መካከልና በአንዳንድ አለመግባባቶች ከሚፈጠር ፀብ ባለፈ የከረረና የሰው ህይወት እስከ ማጥፋት የደረሰ ነገር አያጋጥምም። በስህተት በሰው እጅ ነፍስ ከጠፋ ግን የእርድ ሥርአት በማከናወን ቂም በቀል እንዳይፈጠር የእርድ ሥነሥርአት በመፈጸም ቤተሰብ እንዲታረቅ ይደረጋል። የከፋ ዞን አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ ባህል ያዳበረ ማህበረሰብ እንደሆነም የሀገር ሽማግሌው አቶ አድማሱ ዞኑ ለግንባታ በተረከበው የባህል ማዕከል ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች ለዕርቅ ሥርአቱ ከሚለብሱት አለባበስ ጀምሮ የዕርቅ ሥርአቱን፣የማህበረሰቡን መልካም የሆነውን አብሮነቱን ጭምር ሌላው እንዲያውቀው በተለያየ መንገድ ሰንዶ እንዲተዋወቅ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
በዕለቱ ስለዞኑ አጠቃላይ ገጽታ ከቀረበው አጭር ዘጋቢ ፊልም በዞኑ ዋና ከተማ በሆነው ቦንጋ ውስጥ የቡና ሙዚየም ተገንብቷል። የአካባቢውን የቡና መገኛነት መሠረት በማድረግ በሙዝየሙ ውስጥ የአካባቢውን የቡና አፈላል ሥርአት የሚያሳይና ለቡና ማፍያ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች ጭምር ለእይታ እንዲቀርብ በማድረግ እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻነት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በዚሁ ሙዚየም ውስጥም በጥንት ጊዜ ከፋዎች አካባቢያቸውን ብሎም ሀገራቸውን በኃይል ሊደፍር የመጣን ጠላት ሲከላከሉበት የነበረ ጦርና ጋሻ እንዲሁም አልባሳት በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛል።
ከሀገር ውስጥ ፀሐፍት ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በግጥም ሥራው ከፋን አወድሷታል። ከውጭው ፀሐፍት ደግሞ ቤቢር የተባሉት ፀሐፍት ይጠቀሳሉ። ፀሐፍቱ ስለጥንቱ የዞኑ ነገሥታትና የእናት ቡና ችግኝ መገኛ ስለሆነቸው የዞኑ ማኪራ በብዕራቸው ጽፈው ለተደራሲው አስነብበዋል። ከፋ በዓለም የትምህርት፣የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)የተመዘገበ ጥቅጥቅ ደንም ባለቤት ናት። ከፋ የሚጎበኝ የተፈጥሮ ሀብቷ ብዙ እንደሆነ ከማሳያዎቹ ውስጥ ይጠቀሳል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ፤ዞኑ የአካባቢውን የባህል እሴቶች፣ታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ዞኑ ልማት ማህበር ሲቋቋም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቤት ኪራይ የተለያዩ ሥራዎችን ላለፉት 20 አመታት ሲሰራ ቆይቷል። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ጥረቶች ታሳቢ አድርጎ ለባህል ማዕከል መገንቢያ የመሬት ካርታ ማስረከቡ ከእገዛዎች አንዱ ማሳያ አድርገው ይወስዳሉ። ዞኑ በአሁኑ ጊዜ በአነስተኛ የኪራይ ቤት ውስጥ ጥረት ካደረገው በላይ ለመሥራት ተዘጋጅቷል። የተሰጠው ቦታ የዞኑን ነዋሪ በእጅጉ የሚያነቃቃና የሚያነሳሳ በመሆኑም ህዝቡ፣በገንዘቡ፣በጉልበቱና በሀሳብ ጭምር አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጎ ማዕከሉን በመገንባት እውን እንደሚያደርገውም አይጠራጠሩም።
በህዝቡ ላይ ትልቅ እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ በላይ‹‹ማዕከሉ ህዝቡ ከዚህ ቀደም የነበረውን አንድነትና አብሮነት ማዕከሉ መገንባቱ የበለጠ ያጠናክርልናል የሚል ግንዛቤ ነው የያዘው። ስለዚህ ያልተበረዘ የባህል እሴት ለሌላው የምናስተዋውቅበት ነው የሚሆነው›› በማለት አስረድተዋል። በዞኑ በኩልም ከ20 አመት በፊት በተቋቋመው የልማት ማህበሩ በኩል የገንዘብ መሰብሰቢያ ሰነድ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ሥራው በተቻለ ፍጥነት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት በመኖሩ የሚባክን ጊዜ አይኖርም።
ዞኑ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ፣ባህል ታሪ ክና ሌሎችንም ሀብቶች ለቱሪዝም መዳረሻነት በማልማት፣የአካባቢ ማህበረሰብም ከዘርፉ በሚያገኘው ገቢ እንዲጠቀምና ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይም አስተዋጽኦ በማበርከት እስከ ዛሬ ስለተሰሩ ሥራዎች አቶ በላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹እርግጥ ነው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያላቸው ሀብቶች በዞኑ ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያለው ትስስር አናሳ ነው። የእናት ቡና መገኛ የሆነችውን ማኪራን ለማየት የሚመጡ ቱሪስቶች አሉ ግን በበቂ ሁኔታ እንዲተዋወቅ ተደርጎ ከዘርፉ ጥቅም ለማግኘት ብዙ ሥራ ይቀራል። አሁን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ለመገንባት የታቀደው የባህል ማዕከል ሳንጠቀምበት የቆየነውን ሀብት እንድንጠቀም ያግዘናል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቆይታ የሚያደርገው የውጭ ቱሪስት በማዕከሉ ውስጥ መረጃ ማግኘት ሲችል ወደ ሥፍራው ለመሄድ ይነሳሳል። የሀገር ውስጥ ጎብኝም እንዲሁ›› በማለት ምልሻ ሰጥተዋል።
የከፋ ዞን በአዲስ አበባ ከተማ የባህል ማዕከል ገንብቶ ቱባ የሆነውን የባህል እሴቶቹን፣የተፈጥሮ ፀጋውንና ታሪኩን ለመላው ዓለም እንዲያስተዋውቅና ኢኮኖሚም እንዲያመነጭ የመሬት ካርታውን ለዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ ያስረኩበት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከፋ ተዝቆ የማያልቅ የባህል፣የታሪክና የተፈጥሮ ፀጋ እንዳለውም በአድናቆት በመግለጽ፣የሁሉም ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ላይ የከፋ ዞን ባህል ማዕከል መገንባት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ውበትና ድምቀት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ የባህል ማዕከሎች እንዲገነቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013