በተለያዩ ጊዜያት ስለንባብ ሲነገሩ የተለያዩ አባባሎች እንሰማለን። የማያነብ እንደ እንስሳ ነው ከሚለው አንስቶ ማንበብ የነፍስ ምግብ ነው፣ መጻፍ ግን የነፍስ ትግል፤ እስከሚሉት ድረስ ማለት ነው፡፡ ሰው በንባብ የብርሃንና የጨለማ፣ የሞትና የሕይወት ያህል ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እንዲያውም ምግብ እያለ የማይበላ፣ መጽሐፍ እያለ የማያነብ ሰውን ያህል የከሰረ የለም የሚል አባባልም አለ።
ስለ ንባብ ይህን ካልን ዘንዳ አለማንበብ ወንጀል ነው ከሚሉት በዛሬው የህይወት ገፃችን እንግዳ አቶ አህመዲን መሀመድ ናስር ጋር እናስተዋውቃችሁ፡፡ ማንበብ እንደ ነፍሳቸው የሚወዱት ነገር መሆኑን ነው ሰሞኑን በተካሄደ አንድ የመፅሃፍት ኤግዚቢሽን ላይ ተገናኝተን የነገሩኝ። ሳያነቡ መኖር ጨለማ ውስጥ እንደ መኖር ነው። ይህን ጨለማ ደግሞ ለመግፈፍ ጊዜው ዛሬ ነው ብለው ከ23 አመታት በፊት በጀመሩት እንቅስቃሴ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ የእንግሊዘኛ መፅሀፍትን ወደ ሀገር በማስገባት አለማዊ እውቀቶች ለኢትዮዽያ ተማሪዎች እንዲያደርሱ አድርጓቸዋል።
ማንበብ ያባንናል፣ ከእንቅልፍም ይቀሰቅሳል የሚሉት አቶ አህመዲን ሰው የማያነብ ከሆነ፣ ማር-የለሽ ቀፎ ነው፤ ያልተላገ እንጨትና የማያነብ ሰው አንድ ናቸው፤ ኰረኰንች መንገድና የማያነብ ሰው አንድ ናቸው፤ መጽሐፍ እውነተኛ ጓደኛ ነው፤ እና የመሳሰሉትን ጥቅሶች ካነበቡት ውስጥ እየጠቃቀሱ እየተጨዋወትን ቆይተን ስለማንነታቸው እስከዚህ እድሜያቸው ድረስ የሰሯቸውን ስራዎች ለመነጋገር ተቀጣጠርን። በእለተ ቀጠሯችን ያካፈሉንን እነሆ ብለናል። መልካም ንባብ።
ከውልደት እስከ ስደት
ገባ ያለ ፀጉር፤ አጠር ያለ ቁመት ያላቸው አንደበተ ርቱእ አባት ናቸው አቶ አህመዲን መሀመድ ናስር። በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ ነው የተወለዱት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተስፋ ኮኮብ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በንፋስ ስልክ እና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። 1966 ዓ.ም ነበር መጨረሻዎቹ የሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ማትሪክ ወሳጆች ሆነው እሳቸውና ጓደኞቻቸው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። ወቅቱ የንጉሱ ዘመን አልፎ ደርግ ወደ ስልጣን እየመጣ የነበረበት በመሆኑ ለወጣቶች ያልተመቸ ዘመን እንደነበረ ያስታውሳሉ።
በ 1966 ዓ.ም ብሄራዊ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ወዲያው ስራ አግኝተው እንደ ነበር ይናገራሉ። በዘመኑ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ የተሻለ እውቀት አለው ተብሎ ስለሚገመት በፊት አዲስ ባንክ የሚባል አሁን ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጋር የተቀላቀለ ባንክ ውስጥ በወጣው ክፍት የስራ ቦታ በሂሳብ ሰራተኝነት ተወዳድረው ተቀጠሩ፤ በባንኩ ውስጥም ለአራት ዓመታት ሰርተዋል።
ቀን ቀን በባንክ ቤቱ እየሰሩ ማታ ማታ ደግሞ በንግድ ስራ ትምህርት ቤት የሂሳብ ስራ ትምህርት ወይም በአካውንቲንግ ዲፕሎማ አገኙ። በትምህርት ላይ እያሉ ቀይ ሽብር እየተጋጋለ መጣ። እሳቸው ደግሞ በመስሪያ ቤታቸው የሰራተኛ ማህበር መሪ በዛ ላይ በእግር ኳስ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያደርጉ ስለነበር በወቅቱ በነበረው ስርአት በጥሩ አይን አይታዩም ነበር። በወቅቱ ወጣቶች የፖለቲካ ሙቀቶች ነበሩ። የሚፋጀው ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት የማይፈሩበት ብዙዎቹም ለአለማቸው ሲሉ የተማገዱበት ወቅት ነበር።
በጊዜው አቶ አህመዲንም የኢህአፓ አባል ነበሩ። የሰራተኛ ማህበርም ፀሃፊ ነበሩ። የእያንዳንዱ እንቅስቃሴ መሪ የነበሩት የዛኔው ወጣት ወጣቶች በባትሪ እየተፈለጉ የሚታሰሩና የሚረሸኑበት ጊዜ ላይ በነፃነት መንቀሳቀስ ቀርቶ ተኝቶ ማደር አስጊ ሆኖባቸው እንደ ነበር ይገልፃሉ። አስቸጋሪውን ጊዜም ለማለፍ አብዛኞቹ የወቅቱ ወጣቶች ከሀገር መውጣት ምርጫቸው የሆነበት ጊዜም እንደነበረ ያስታውሳሉ። በወቅቱ በራሺያ የነፃ የትምህርት እድሎች የተመቻቹበት ወቅት ስለነበር ተወዳድረው ለራሺያው የነፃ ትምህርት እድል አለፉ።
የፓስፖርትና የተለያዩ ቅደመ ሁኔታዎችን ካጠናቀቁ በኋላ ያንን የትምህርት እድል በመተው በሌላ መንገድ አቆራርጠው ከሀገር በመውጣት ሳውዲ አረቢያ ገቡ። ይህ በሆነ በአመቱ ካሉበት ሀገር የስደተኛ ወረቀት በማውጣት ወደ ጣሊያን ሄዱ። ይህ ቢሆንም ጣሊያንን በድልድይነት ተጠቅሜ ወዳአሰብኳት አሜሪካ እደርሳለሁ ያሉት እቅድ ሳይሳካ በመቅረቱ ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ሳውዲ አረቢያ ተመለሱ። በሳውዲ አረቢያ እዚህ ሲያገለግሉበት በነበረ በባንክ ባለሙያነት እየሰሩ ዓመታትን አስቆጠሩ።
ሰው አላማው ከግብ እስኪደርስ ያለበትን ተለማምዶ ተዋህዶ መኖር ግዴታ ነውና አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት እግር ኳስ ይወዱና ይጫወቱ ስለነበር ነበር፤ ለባንክ ቡድንም ተሰልፈው ይጫወቱም ስለነበር፤ ሳውድ አረቢያ ላይም ባንክ ቡድን ውስጥ እየተጫወቱ እዛው እየሰሩም ዓመታት ካሳለፉ በኋላ በ1977 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ መዳረሻዬ ትሆናለች ብለው ከሀገራቸው የወጡባት አላማቸው ወደ አሜሪካ ገቡ።
አሜሪካን ሀገር እንደሄዱ በእንጥልጥል የቀረውን ትምህርት የማስቀጠል ሀሳባቸውን ጥግ ለማድረስ ተጉ። በዚህም ጥረት በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከካሊፎርኒያ ካሊስት ሄዋርድ ዩኒቨርሲቲ ወሰዱ። የትምህርት ጉዟቸውን በዚህ ካስቀጠሉ በኋላ ነበር ወትሮም በሀገራቸው የሚያውቁትን የባንክ ስራ በማግኘት ባንክ ኦፍ አሜሪካ የተባለ የቢዝነስ ተቋም ውስጥ ተቀጥረው መስራት የጀመሩት።
መፅሀፍትን የማሰባሰብ ጥንስስ
በ1991 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከካሊፎርኒያ ካሊስት ሄዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከወሰዱ በኋላ ለአራት ዓመታት ዩኒቨርሲቲ የተማሩበት መፅሃፍ መደርደሪያው ሞልቶት ተመለከቱ። ይሄን ሁሉ መፅሀፍ ምን ላድርገው በሚል ጭንቀት ውስጥ ወደቁ። ̋ያን ጊዜ ለኔና ለጓደኞቼ ከባድ ሸከም ሊሆን የሚችልን መፅሀፍ ወደ ሀገር ቤት ቢላክ ደግሞ ለኢትዮዽያዊያን ልጆች በተለይም እንደልብ የማጣቀሻ መፅሃፍት በማይገኙበት በዛ ጊዜ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ መፅሃፍትን የማሰባሰብ እቅድ በልቤ እንዲፀነስ ምክንያት ሆነ” ይላሉ።
በወቅቱ እሳቸውና ጓደኞቻቸው ገና አዲስ ተመራቂ ተማሪ ስለነበሩ እያንዳንዳቸው የተማሩበትን መፅሀፍ ወደ ኢትዮዽያ ለመላክ የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም ነበር። ከዛም በኋላ አንድ ወዳጃቸው የሆነ ጥቁር አሜሪካዊ ለመላክ የሚሆን እርዳታ የሚያደርግ ሰው በመፈለግ የሚያግዛቸው መሆኑን ቃል ከገባ በኋላ በእጃቸው ያሉትን ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ መፅሃፍት አሰባሰቡ። መፅሃፍቱን ለመሰብሰብ ሶስት ወራት ቢፈጅም እንኳን ቃል የተገባው ለመላክ የሚያግዘው አካል ሊገኝ ባለመቻሉ እሱን ማስቀመጫ ቦታ ማግኘትም ከባድ ሆነ።
̋አሁን በህይወት የሌለው አንድ ጓደኛዬ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ሺህ መፅሀፍቶች በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በኩል መላክ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ አመቻቸልኝ።” የሚሉት አቶ አህመዲን ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም በጣም የተሻለ ይዘት ያላቸውን አምስት ሺ መፅሀፍት ለመምረጥ ሊያውም ከመቶ ሺህ መፅሃፍት ውስጥ እጅግ ከባድ ራስ ምታት ሆኖባቸው እንደነበረ ይናገራሉ። ከዛም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያሉ የሚጫወቱበትን የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ የሚሳተፉ ልጆችን በማስተባበር መርጠው በ1986 ዓ.ም ወደ ኢትዮዽያ ተላከ። በወቅቱ ዶክተር ታዬ የተባሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የላይብረሪ ኃላፊ የምስጋና ደብዳቤ ልከውላቸው እንደ ነበር ነግረውናል።
መፅሀፍት ቤቶችን የማደራጀት ሀሳብ
̋መፅሀፍት ቤቶችን የማደራጀት ሀሳብ የተነሳው በአንድ ቀላል የምትመሰል ገጠመኝ ነበር። እኔ በህይወት ዘመኔ ሁሉ አንድ ቀን ቡና ጠጥቼ አላውቅም ነበር።” ብለው ጨዋታቸውን የጀመሩት አቶ አህመዲን ̋ይህንንም ጓደኞቻቸው ያውቁ እንደነበር አጫውተውናል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ከጓደኞቻቸው ጋር እሳቸው ሻይ ጓደኞቻቸው ደግሞ ቡና አዘው በአንድ ካፍቴሪያ ውስጥ እየተጨዋወቱ ነበር። እሳቸው ወደ መታጠቢያ ቤት ደርሰው እስኪመለሱ ድረስ ሻይ ውስጥ ቡና ጨምረው ጠበቋቸው። ጣእሙ ግራ ቢገባቸውም ምን ምን እንደሚል ሊቀምሱት ወስነው ጠጡት። ያችን በቡና የተቀላቀለች ሻይ የጠጡባት ሌሊት አንድም እንቅልፍ ባይናቸው ሳይዞር አደረ። ያቺ እንቅልፍ አልባ ሌሊት በአምስት ሺ መፅሃፍት የተጀመረውን ለሀገር ልጆች የአጋዥ መፅሃፍቶች የመላክ ሀሳብ በብዛት በተቀናጀ መልኩ መስራት የሚገባው መሆኑን ከልባቸው ጋር ተማክረው ወስነው ያደሩባት ሌሊት እንደነበረች ያስታውሳሉ። ይህ ውሳኔ ላይ ያደረሳቸው ሌሊት የመጀመሪያዎቹ መፅሃፍት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተላከ ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ በ1999 ዓ.ም ነበር። ይህ ሀሳብ መፅሀፍትን ለመላክ የሚያስችል ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቋሙ። ድርጅቱ ውስጥ የተለያዩ ተልእኮችን የሚያስፈፅሙ አስራ ሁለት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ። ከኮሚቴው አባላት ውስጥ ስምንቱ ፈረንጆች ነበሩ።
̋እዚህ ላይ አንድ መናገር የምፈልገው ህዝብና መንግስት በየትኛውም ዓለም አንድ አይደለም። እንደ መንግስት ከሆነ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ፖሊሲ በጣም የሚጠላ ነው። ከነጭ ውጪ በአፍሪካዊያን ላይ ያላቸው የበላይነት ስሜት በጣም ከባድ ነው። እንኳን ስደተኛውን ይቅርና ለራሳቸው ጥቁር ዜጎችም የሚመች ፖሊሲ የላቸውም። ለአሜሪካን ህዝቦች ግን ትልቅ አክብሮትና አድናቆት አለኝ። ማድነቅ፤ መርዳት፤ ማመስገን ይችሉበታል።
የተዋቀረው ኮሚቴው የመጀመሪያውን ስብሰባ ባደረገበት ወቅት መፅሀፍት እናሰባስብ ብለን ከተነሳን ያልተመረጡ፤ ይዘታቸው በአግባቡ ያልተለዩ፤ በመላኩ ከገንዘብ ውጪ በስተቀር ምንም ትርፍ የሌላቸው፤ ሰው የማይፈልጋቸውን መፅሃፍት ሊሰጥ ስለሚችል፤ መሰብሰቡን በማቆም ፈንድ በማሰባሰብ ውሳኔ ላይ ደርሶ ተበተነ። ወረቀት ላይ የሰፈረውን ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት የኮሚቴ አባላት 15 ሺ ዶላር ለማሰባሰብቻሉ። በተሰበሰበው አስራ አምስት ሺ ዶላር 33 ሺ በሁሉም የትምህርት አይነቶች ላይ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ መፅሀፍቶች ተገዙ። ከዚህም በተጨማሪም አስራ አንድ ኮምፒውተሮችንና አራት ፕሪንተሮችን ከመግዛት አልፎ እስከ ጅቡቲ ድረስ ለማድረስ የሚያስችል ሆነ ማለት ነው።
̋ይህ ለኔ ትልቅ ድል ነበር።” የሚሉት አቶ አህመዲን ̋የተዘጋጀው መፅሀፍ ወደሀገሬ ይላክ እንጂ አንድም ቀን አሜሪካ ውስጥ አላድርም።” እያሉ ሲፎክሩ የሰሟቸው ጓደኞቻቸው የምሳ ግብዣ ያደርጉላቸዋል። የመፅሃፍት አሰባሳቢው ማህበር ፀሀፊ ልክ ምሳው እንደተጠናቀቀ ̋መፅሀፉ ወደ ሀገሬ ከተላከ አንድ ቀን አላድርም እያልክ ትፎክር ነበር” አሏቸው፤ እሳቸውን ̋የማወራውን የምተገብር ሰው ነኝ ” በማለት በፍፁም በኢትዮዽያዊ ኩራት ተናገሩ። ይህን ጥያቄ ያነሱት አባላት መፅሃፉ የተላከበትን ወረቀት እጃቸው ላይ አስቀምጠው ቃላቸውን ያከብሩ እንደሆነ ለመመልከት መጠባበቅ ጀመሩ።
ይህ በሆነ በአስር ቀን ውስጥ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ጉዟቸውን ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ገቡ። ̋ ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ አይደል የሚባለው በሀገሬ ማንበብ ለሚፈልጉ ሰዎች የጠብታ ያህልም ቢሆን ፍላጎታቸውን ለመሙላት የሚያስችለኝን በጎ ስራ ለመስራት አስፈላጊውን መረጃ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው የኢትየዽያ ኤንባሲ በማውጣት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ያረጋገጠውን መረጃ ይዘው እነዛ ጅቡቲ የደረሱ መፅሀፍትን ለማስለቀቅ ሩጫ ጀመርኩ” የሚሉት አቶ አህመዲን በወቅቱ ወደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሄዱበት ወቅት በተለያዩ ቢሮክራሲዎች እጅግ በጣም ተቸግረው እንደነበረ ያስታውሳሉ።
መፅሀፍቱ ይግቡ አይግቡ ትንቅንቅ
ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄደው ጉዳያቸውን የሚያስፈፅምላቸው ሰው በማጣታቸው መፍትሄ ለማግኘት የፍትህ ሚኒስቴርን ደጃፍ መርገጥ ጀመሩ። እዛም ግን ቀድመው ከሄዱበት የተለየ ነገር ባለ ማግኘታቸው መፅሀፉን የያዘው ኮንቴነር ጅቡቲ ላይ የቆየበት ሂሳብ እየጨመረ፤ መፅሀፍቱም ሳይለቀቁ በጣም ከመቆየታቸውም በላይ በየእለቱ የሚረግጣቸው የመንግስት ቢሮዎች ቤተኛ ሆኑ። በየእለቱ እየተመላለሱ የሚመለከቷቸው ሴቶች የመፍትሄ ሀሳብ አመጡ። ̋በነገራችን ላይ” ይላሉ አቶ አህመዲን ” በነገራችን ላይ ሴቶች ለመልካም ነገር ቀዳሚ ተሰላፊ ናቸው። ለያዙት ስራም ጠንካራ ሰራተኛ መሆናቸውን ሳልመሰክር ባልፍ ንፉግ መሆን ነው።” የሚሉት አቶ አህመዲን በወቅቱ በፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ጋ ጉዳያቸውን ይዘው ቀረቡ። በጊዜው በጣም አዝነው የነበሩትን ሰው አፅናንተው ጉዳያቸውን በቀላሉ አስጨርሰውላቸው ሀገራቸው ከገቡ ለሁለት ዓመት ጊዜ ጉዳዩ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላው ሲንከባለል ቆይቶ ተፈፀመላቸው። እቃው ወደብ የቆየበት የክራይ ገንዘብ 9 ሺ ዶላር ሆኖ ነበር።
̋አሸናፊዎች ተስፋ አይቆርጡም፤ ተሸናፊዎች አያሸንፉም” የሚል አባባልን በውስጣቸው የሰነቁት የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች የመሸነፍም፣ የማሸነፍም ልምድ ስላላቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ጉዳያቸውን ዳር አድርሰዋል። ̋ በየቦታው በሚገጥመኝ እንቅፋት ተሸንፌ ምንም ነገር ሳላደርግ ወደ መጣሁበት ብመለስ እንደሞትኩ ነበር የምቆጥረው፤ ግን ህልሜን አሳክቼ ከዛ በኋላ ሀገሬ ውስጥ ለስድስት ዓመታት ቆየሁ።” ያሉት አቶ አህመዲን ከዛ በኋላ ድካማቸውን የተረዱት የወደቡ ሀላፊዎች የተጠራቀመውን የኪራይ እዳ ሰርዘውላቸው በመኪና አዲስ አበባ ቃሊቲ መፅሀፍቱ ደረሱ፤ መፅሀፍቱም ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ፍላጎታቸውን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ከመሰራጨቱም በላይ በአዲስ አበባ አስር ለሚሆኑ ቤተ መፅሀፍቶችና ለክልልች ተሰራጨ።
ከዚህም በተጨማሪ የመፅሀፍት ቤት የማቋቋም ሀሳቡን የጀመሩበት ምክንያትን ሲናገሩ ̋ አንደኛው ምክንያት በእስልምና ሀይማኖት መመሪያ ቁርአን ላይ እንዲህ የሚል ነገር ተፅፏል። “ለራስህ የምትፈልገውን ለወንድምህ ለጓደኛህ ለዘመድህ አድርግ”። ሁለተኛ እኔ መፅሃፍትን ማንበብ በጣም ስለምወድ ነው። ሶስተኛው ነብዩ መሀመድ በገብርኤል በኩል የመጀመሪያ የደረሳቸው ትእዛዝ ኤክራ የሚል ነው። አንብብ ማለት ነው። እሳቸውም እኔ አላነብም አሉ። አሁንም አንብብ ሲባሉ፤ እኔ መሀይም ነኝ አሉ። በመጨረሻም ቁርአን በረመዳን ወር ወረደላቸው የሚለው ሀሳብ አንብቦም አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ያነሳሳኝ ሀሳብ ነው።” ይላሉ።
̋ሌላው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሀገሬ ምን ሰራችልኝ አትበል ለሀገሬ ምን ሰራሁ እንጂ ብለው ነበር፤ እኔ ፤ አንቺም እሱም ምን ሰራን ብለን መጠየቅ አለብን።” ያሉት አቶ አህመዲን ገበሬው ለሀገሩ ተገቢውን ግብር በአግባቡ እየከፈለ እሱ በከፈለው ገንዘብ እሱ ሳይማር በርካቶችን ከእውቀት ብርሃን ጋር በማገናኘቱ ውለታ እንዴት ልንከፍል እንችላለን ይላሉ። ገበሬውን ባናገኘውም እንኳን ለልጁና ለልጅ ልጆቹ የእውቀትን ደጃፍ ለማሳየት መፅሃፍትን ለማዳረስ እየሞከሩ መሆኑን ይናገራሉ።
በሀገራችን የንባብ ባሕል ማደግ ይኖርበታል። ትውልድ ራሱን እንዲያውቅ፣ ራሱን እንዲሆን፣ የፈጠራ አቅሙን እንዲያዳብር፣ በዕውቀት እንዲበለጽግ፣ ውጤታማነትና ስኬታማነት ባሕል እንዲኖረን፣ የዕቅድ አቀራረጽ አፈጻጸምና አገማገም እንዲጎለብት፣ የውይይት ባሕል እንዲስፋፋ፣ የዕውቀት ሽግግርና የትውልዶች ግንኙነት እንዲጠናከር፣ እርስ በራስ የመተዋወቅ ብሎም ሌላውን የማወቅና የመረዳት አቅምን ከፍ በማድረግ ጠያቂ፣ ተመራማሪና ምክንያታዊ ሕብረተሰብን ለመፍጠር አንባቢ መሆን ያግዛል።
የአንድ ሀገር ሀብት ምድሯ ውስጥ ያለው ማእድን፤ አልማዝ፤ ወርቅ፤ ነዳጅ፤ አይደለም፤ የሰለጠነ የሰው ሀይል እንጂ፤ በእውቀት የሚመራ የሰው ልቦና እንጂ። ዛሬ ሀገራችን ምንም አይነት አልማዝ ቢኖራት ያንን የሚያወጣ የሰው ሀይል ከሌላት ሁልጊዜም ድህነት ላይ ነን። አሁን ኢትዮዽያ ውስጥ እየተቀየረ ያለ ነገር አለ እንጂ መንገድ የሚሰሩትም እኮ ቻይናዎች ናቸው።
በሀገራችን ህዝብ መካከል ከሰላሳ አምስት አመት በታች የሆኑት ከሀገሪቱ ህዝብ ሰባ በመቶ እንደሆነ እየታወቀ እውቀትን በመፅሃፍት መልክ ብንሰጠው እንዴት ታሪክ አይቀየር የሚል ሀሳብ ውስጤ ይመጣል። ወጣቱ 24 ሰአት ኳስ ቢመለከቱ ለውጥ አይመጣም፤ መጫወት ነው ያለበት።
ለሰው ልጆች በሙሉ እኩል የተሰጡን ነገሮች መካከል ጊዜ አንደኛው ነው። ለኛም ለአለም ሀብታሙ ቢልጌትስም የተሰጠው እኩል 24 ሰአት ነው። ሰው በ24 ሰአት ውስጥ ምን ይሰራል። የጊዜ አጠቃቀም ላይ ችግር አለብን፤ በእውቀት መታረቅ አለበት።
ወጣቶች ስምንት አስር ሰአት ስለማይረቡ ነገሮች እያወሩ ይውላሉ። እኔ የሚያስደንቀኝ ዘመናዊነት ብለን ከፈረንጆቹ የምንወስደው የማይጠቅሙ መጥፎ መጥፎ ነገሮችን ብቻ ነው። የኛን ጥሩ ትተን የሰው መጥፎ ለቅመን እንዴት እንችለዋለን? ብለው ይጠይቃሉ።
መገናኛ ብዙሃን ስለማይረባ ነገር የሚያወሩበት ወጣቱ የማያውቀውን አለም ናፋቂ መሆኑን ትቶ ሀገር ወዳድ የሚሆንበት ለውጥ አምጪ ሀሳቦችን እንዲያስቡ ቢደረግ ጥሩ ነው። ለምሳሌ የእስፔሊንግ ውድድሮች ቢደረግ፤ ወጣቶች ሀሳብ የሚለዋወጡባቸው የሚከራከሩባቸው አይነት መድረኮች ቢፈጠሩ፤ ስለ ቋንቋ አጠቃቀማችን ስለ ግብረ ገብ ያለው የቀደም እውቀት መመለስ አለበት።
መሰልጠን ማለት የራስን መተው አይደለም። ጃፓን ይሄ ነው የሚባል ሀብት ሳይኖራት ህዝቧ ብቻ ሀብቷ ሆኖ በራሷ ቋንቋ አለምን በሙሉ እየተቆጣጠረች ያለች ሀገር ናት። ለመሰልጠን የግድ ምዕራባዊ መሆን የለበትም የሚል አባባል አላቸው። እኛም የጃፓንን ልምደ መውሰድ አለብን።
መናደድ መቆጨት ይገባናል፤ እንዴት እንደዚህ ሆንን ከማን እናንሳለን በማለት መነሳት ይኖርበታል፤ የተወሰነው ሰው ስለ ቤተ መፅሀፍት ከተጨነቀ፤ የተወሰነው ደግሞ ስለ መድሀኒት ፤ ሌላው ስለ ሀገሩ፤ ሁሉም በየመክሊቱ ከተሰማራ የሰው የማይረባ የማይሰራ ጭንቅላት የለም። በመክሊቱ በሚወደው ነገር ከተሰማራ መሳካቱ ሀገር በሚፈለገው ልክ ማደጓ አይቀርም። እኔም በዚህ ነው ለመፅሀፍት ቤቶች መፅሀፍት ማበርከት የጀመርኩት።
የንባብ ባህልን ያዳበረ ማህበረሰብ መፍጠር ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ የሚያሳካ ትውልድን ለመፍጠር የሚያነሳሳ ሲሆን ከመነሻችን ጀምሮ ማንነትን አስለይቶ ወደ ታላቅነት የሚያመራ አቅም ይፈጥራል። ይህ እንዲሆን ትልቁ መሳሪያ ንባብና የንባብ ባሕልን ማዳበርና ማበልጸግ ከዋነኞቹ የሀገር ግንባታ (Nation Building) ና ሕብረተሰብን የማነጽ (Reshaping Society) መሣሪያዎች መሐከል አንዱና ዋነኛው ነው። የንባብ ባሕልን በሕብረተሰብ በሁለንተናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ግንኙነት ውስጥ አካል ማድረግ ከላይ ለተጠቀሱ ሁለንተናዊ ተግባራት ወሳኝ ነው።
መፅሀፍቶቹ የተዳረሱባቸው ቤተ መፅሃፍት ከአዲስ አበባ ቢጀመር ላፍቶ ክፍለ ከተማ፤ ሉሱሉልታ፤ ማረሚያ ቤት፤ አባድር፤ አወሊያ፤ ዲያሊያ፤ ደብረ ዘይት ሁለት ቦታዎች ላይ፤ ጎጃም፤ ጎንደር፤ ጉራጌ ላይ ወልቂጤና እንድብር ገወዲዮ ላይ፤ ወሎ ወሊዲያ፤ ጃልሜዳና የመሳሰሉት ቦታ መፅሀፍት ከአስራ ሁለተኛ እስከ ኮሌጅ ላሉ ልጆች የሚጠቅሙ መፅሃፍት የተሟሉላቸው ናቸው።
መፅሀፍቱ ወደ ሀገር ማስገባት ከጀመሩ በኋላ ዜናው በመገናኛ ብዙሀን መነገር ጀመረ፤ በብዛት ሀሳቡን የሚደገፉት ሰዎች ሲመጡ ከነዚህ ሰዎች ጋር በጋራ ምን መስራት እንደሚቻል መናገር ተጀመረ። ያኔ አቶ አህመዲን መፅሀፍትና ኮምፒውተሮችን ለማምጣት እነሱ ደግሞ ቦታዎችን ሊያመቻቹ ተስማሙ። በዚህ መንገድ ነው እንግዲህ 22 መፅሃፍት ቤቶች ተቋቁመው ለሀገሪቱ አንባቢያን ክፍት የሆኑት። ለሀያ ሶስት ዓመታት የቀጠለው ይህ የመፅሃፍት ንቅናቄ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመድረስ 33 ሺ መፅሃፍቶች ወደሀገር ሊገቡ ችለዋል።
በመጨረሻም
በውጭ ያሉ ዲያስፖራ ኢትዮዽያዊን ሀገራቸው ገብተው በሚያውቁት፤ በተሰማሩበት ሰው ሀገር ሲያገለግሉ በኖሩበት ሞያ ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው። ይህ ማለት ኢንጅነሩ መጥቶ ሹመትን ወንበርን ለማግኘት ከሚታገል ወይም አማካሪነትን ከሚሻ እታች ወርዶ እጁ አፈር ነክቶት መስራት ይኖርበታል።
የሀገራችንን አረም እኛ ካልነቀልን ማን ይነቅለዋል። ዛሬ ካልሆነ መቼ ሊፀዳ ነው። መጀመሪያ አመለካከታችን መቀየር አለበት ። ውጭ የኖሩ ሰዎች ይዘው የመጡትን የስራ ባህል ከታች ሆነው ለሁሉም የተቋም ሰራተኛ ማጋባት ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል አንድ ትምህርት ሚኒስቴር ከሀገር ውስጥ ምሁር ቢሾም ምክትሉ ከውጭ ሆኖ የጋራ መሞራረድ ላይ በመድረስ አብሮ በመስራት ለውጥ የሚያመጡ ስራ መስራት ይኖርበታል።
በየትም ሀገር የሚኖሩ ኢትዮዽያዊያን በታማኝነታ ቸው የሚጠቀሱ ናቸው። በጣም ብዙ የተለያዩ ቦታዎች ታላላቅ ሰዎች ኢትዮዽያዊያን ናቸው የመስራት የማወቅ ምንም ችግር የሌለባቸው፤ ለማደግ ምንም ቅድመ ሁኔታ አያስፈልገውም። በልጅነት የተያዘ እውቀት ድንጋይ ላይ እንደተቀረፀ ፅሁፍ ነው የሚባል አባባል አለ። ልጆች ላይ መሰራት አለበት። የሰለጠነ ህዝብ ለመረገጥ አይመችም፤ ስኬት የሚካፈለው ሰው ከሌለ መደንቆር ነው፤ በማለት በምክር ጨዋታችንን ጨርሰናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013