የእርጋታ ጊዜ ያስፈልገናል

በዓለም ላይ ያለ ሁሉም ነገር ከአንድና ከዛ በሚበልጡ የህልውና ድር የተደራ ነው። የሰው ልጅን ብትወስዱ ካለፍቅር ከንቱ እንደሆነ ከዘፍጥረት ተነግሮታል። እጽዋቶችን ብንወስድ ፍግና ኮንፖስት ያሻቸዋል። ጡቦች ያማረ ህንጻ ይሠራሉ። ያማሩ ህንጻዎች ጠንክረው እና አምረው እንዲታዩ ከጥበበኛ ሠራተኛ እኩል አሸዋና ሲሚንቶ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው። ሠራተኛው ህንጻውን ዲዛይን አድርጎ በአሸዋና ሲሚንቶ ሌሎች ግብዓቶችንም ተጠቅሞ ቤት ይሠራል። ወደሀገር ስንመጣ ደግሞ ሀገር ጸንታ እና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንድትኖር የሰላም ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ሰላም የጥያቄ አለመኖር ሳይሆን ጥያቄዎች ወደችግር ከመውሰዳቸው በፊት ቆም ብሎ በማሰብ ደህንነትን የማስቀጠል ስያሜ ነው። በአንድ ሀገር ላይ የሃሳብም ሆነ የፖለቲካ ልዩነት መኖሩ የማይቀር ነው። ይሄን ልዩነት የምናስተናግድበት መንገድ ግን እንደ አካዳሚክ ግሬድ ነጥብ የምናገኝበት እና የምንጥልበት በመሆን ይጠራል። በየትኛውም አንግል ውስጥ ያሉ የሃሳብ ልዩነቶች ወደጦርነት እንዳይወስዱን በንግግር ለመፍታት የምናደርገው ጥረት እሱ የደረጃ ምደባ ይሰጠናል።

ደረጃ አንድ ላይ ያሉ ሀገራት የችግር አፈታት ሥርዓታቸውን ብናየው ምክንያታዊ፣ ብዙሀነት፣ ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ዘመኑን የዋጀ ሆኖ እናገኘዋለን። እንደዚሁም በልዩነት ሀገር የገነቡ፣ በልዩነት የበለጸጉ፣ በልዩነት ጠቃሚ ሃሳቦችን የሚወልዱ ናቸው። ወደእኛ ሀገር ስንመጣ ይሄ ነገር ትርጉም አጥቶ ነው የምናገኘው። ሲጀመር በሃሳብ ልዩነት ተግባብተን አናውቅም። የሃሳብም ሆነ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን ዘረኝነትን ሲወልዱ እና ለእርስ በርስ ጦርነት ሲዳርጉን ኖረዋል።

ሀገር ግንባታ ሥርዓት ላይ ከሁሉም የተሻለው መንገድ ልዩነትን መጠቀም ነው። ልዩነት ከአንድ አይነትነት ወደልዩልዩነት መሸጋገር ነው። ይሄ ሽግግር ደግሞ በተለያዩ እውቀቶች፣ በተለያዩ ሃሳቦች፣ በተለያዩ ልምዶች እንዲሁም ዘዴዎች የዳበረ በመሆኑ ችግሮችን ከመቅረፍ እና ሰላማዊነትን ከመፍጠር አኳያ ሚናውን በበጎ መመልከት እንችላለን።

በመሠረቱ አንድነት ትርጉም የሚኖረው በልዩነት ውስጥ ነው። ልዩነት ውበት የሚባለው ለአንድነት ሲውል ነው። አንድነት በልዩልዩ እውቀቶች እና ሃሳቦች ካልተዋቀረ ልዩነት ሊባል አይችልም። ኢትዮጵያን ብንወስድ ከሰማንያ በላይ በሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ሥርዓቶች፣ አመለካከቶች ጸንታ በብርቱ አንድነት ትጠራለች። ከተዋቀርንበት የልዩልዩ አንድነት ተነስተን በፖለቲካው ምህዳር የሚፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶችንም ለሀገራዊ ግንባታ መጠቀም እንችላለን።

ዋጋቸው ከፍ ያለ የልእልና ልኬቶች በሰላማዊነት የሚጠሩ ናቸው። በጡብና በሲሚንቶ እንደጸናው ህንጻ የሀገር ሁለንተናዊ ብኩርና ያለው በሰላማዊ ትስስር ውስጥ ነው። ሰላማዊ ትስስር አብሮነትን በማግዘፍ የጋራ ዳና የሚያበጅ፣ ከቅርንጫፉ ይልቅ አበባና ፍሬ ላበቀለው ለግንዱ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።

በልዩነት ውስጥ ያለውን በረከት ለሀገር እድገት አውለን የተቀረውን ደግሞ በጠረጴዛ ዙሪያ ብንመክርበት የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን ኢትዮጵያ መፍጠር በቻልን ነበር። አሁን ባለው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ሀያላኖቹ ሀገራት ፊተኝነትን ያጸኑት በልዩነት ውስጥ ባለ ጸጋ እና በረከት ነው። እኛ ልዩነቶቻችንን ለጦርነት እና ለመለያየት ስንጠቀም ሌላው ለእድገት እና ለልማት እያዋለው ይገኛል።

እየተገዳደልን ሀገር ማጽናት አንችልም። የአንድ ሰው ሕይወት በሀገርኛ ሲመነዘር የሀገር ግማሽ ሞት ነው። ስንገልም ሆነ ስንሞት ሀገራችንን እየገደልን ነው። የሰው ልጅ ተነጋግሮ ከመግባባት የበለጠ ጥበብ አልተሰጠውም። በመኖር ውስጥ ካገኘነው ሁሉ የሚበልጠው ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም የመኖር ክህሎታችን ነው።

በልማቱም፣ በእድገቱም፣ በአብሮነቱም ለውጥ ለማምጣት በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ ኢላማ በማለም ላይ እንገኛለን። እኚህ ኢላማዎቻችን የምንፈልገውን እንዲመቱ ሰላም እና የሀገር ጡብ ምሰሶዎች አስፈላጊዎቻችን ናቸው። ሰላም በሌለበት፣ ምክክር እና እርቅ ባልጎለበተበት ማህበረሰብ ውስጥ ታልሞ የሚመታ ትልም የለም።

በመልካም ልብ ከተቀበልነው ሁሉም መልካም የሚሆን ነው። ወደፊት በተሰመረ ሕይወት በጥላቻ ወደኋላ እያየን ከጉዟችን መቆም የለብንም። ችግር ሊኖር ይችላል ችግሮቻችን የቱንም ያክል ይግዘፉ ስለአንድነት መሰባሰብ ከቻልን መፍትሄ ማምጣት እንችላለን። ሰፋፊ ጠረጴዛዎቻችንን ባማረ ስጋጃ ከመለበጥ አልፈን ለምክክር እና ለሀገራዊ እርቅ እንቀመጥባቸው። በውድ የተገዙ ወርቀዘቦ ወንበሮቻችንን በፍቅር ስለፍቅር እንነጋገርባቸው።

ሰላም እና የሕዝቦች የትስስር እሴቶች የሀገር ጡብ ምሰሶዎች ናቸው። ምሰሶው አቅፎ የያዘው ብዙ ነገር አለ። ሀገር፣ ታሪክ፣ ሉዓላዊነት፣ ህብረብሄራዊነት፣ ባህል፣ ሥርዓት፣ ወግ እና ልማድ እያልን የምንጠራቸው የማንነት ቀለሞች ከምሰሶው ስር ያረፉ የህብረብሄራዊነት መልኮቻችን ናቸው። እኚህ የክብር ዘውዶች አንዱን ከሌላው አያይዘው ኢትዮጵያ በሚል በወል ስም የተጠሩት በመቻቻል ነው።

ብዙሀነት በመቻቻል ካልሆነ በምንም አይደምቅም። የተጓዝናቸው እልፍ የአብሮነት ዓመታት ከየትኛውም እውነት በላይ መቻቻል በሚለው ስያሜ የሚገለጹ ናቸው። ቀለሞቻችን ሳይደበዝዙ ዘመን ተሻጋሪነትን የወረሱት በኢትዮጵያዊነት በተቧደኑ ነፍሶች አማካኝነት ነው። አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያዊነት መቧደን ነው ነጻ የሚያወጣን።

መቻቻል የጋራ እሴት ከመፍጠር አኳያ ከሀገር ጡብ ምሰሶዎች አንዱን ነው። ሰውነትን እንደሠራ እስትንፋስ ሀገርን የሚሠራ፣ ትውልድን የሚፈጥር ነው። ህንጻ እንዳቆመ ዋልታ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በመቻቻል ካልተፈጠሩ አስቸጋሪ ነው። የመጣንባቸው ሺህ ዘመናት በመቻቻል ሃዲድ ላይ እልፍ ትውልዶችን ያመላለሰ ነው። በውብ እጅ ሽመና እንደድር ተድረን ከብዙሀነት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ተብለናል ይሄ ሞገስ በመቻቻል ካልሆነ ከየት መጣ?

ኢትዮጵያ የነጻነት ምድር፣ የሠብዓዊነት አልፋ ወደብ ስንባል ከጀግንነታችን እና ከአትንኩኝ ባይነታችን እኩል ማህበራዊ ሥርዓቶቻችንም ተቆጥረው ነው። ማህበራዊ ሥርዓታችን ሠብዓዊነት እና ነጻነት የበቀለበት ሰውነታችን ነው። ይሄ ማህበራዊ ሥርዓት ብዙ የክብር ስሞችን አሰጥቶን ለእልፍ ዘመናት በከፍታ አኑሮናል። አሁን ላይ እየተስተዋሉ የሚገኙ አንዳንድ ልክ ያልሆኑ ሁኔታዎች ከእኛ መልክና ማንነት አኳያ ያልተገቡ በመሆናቸው ከተቻለ በፍቅር ካልተቻለ ደግሞ በእርቅ መታለፍ የሚገባቸው እንደሆኑ አምናለሁ።

ዘመኑ ተለያይቶ ለመሄድ የሚመች አይደለም። ተሳስረን፣ ተቧድነን እና ተጠላልፈን አንድ ጠንካራ ሃይለኝነትን ካልፈጠርን ወደአስቸጋሪ ነገ እየሄድን እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች ላይ ለብቻ የተሠራ ጀብድ የለም። ታሪኮቻችን ሁላችንም የተሳተፍንበት የጋራ ታሪካችን ነው። ተከባብረን በአንድ ወንዝ ፈሰን ውቅያኖስ የመሆናችን ምስጢርም ከዚህ የተነሳ ነው። ተለያይተን በየፊናችን መሄድን ከመረጥን ትናንት ላይ በአብሮነት የገነባንውን አስፈሪነት ከማኮሰስ እና ከባህርነት ወደምንጭነት ከማነስ በስተቀር ክብር የለንም።

አሁን ላይ ሀገራት ፈርጣማነታቸውን በጦር መሣሪያ ብዛት እና በሠራዊታቸው ቁጥር እየመዘኑ ያለንበት ዘመን ላይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድነቱ እንደደረጀ ሀገርና ሕዝብ አስፈሪ እንደሌለም እየሰማን እንገኛለን። እንደኢትዮጵያ ያሉ በነጻነት እና በቀደምትነት የሚታወቁ ሀገራት ይዘውት የመጡትን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና መልካም የጉርብትና እሴት አሳድጎ ከመቀጠል የበለጠ የሉዓላዊነት ልኬት እንደሌላቸው እንረዳለን። ከዚህ በመነሳት እኛ ኢትዮጵያውያን ካለንበት የድህነት እና የኋላ ቀርነት ጉዞ ተላቀን ወደምንፈልገው የከፍታ ስፍራ ለመድረስ ከምንም በላይ ያልተዛነፉ የአብሮነት ጎዳናዎች ያስፈልጉናል።

የአብሮነት ጎዳናዎች መዳረሻቸው አንድ ነው። በዘርና በብሄር ተቧድነን የምንሄደው አካሄድ ጠልፎ ከመጣል እና ከመንገድ ከማስቀረት ባለፈ መዳረሻ የለውም።

ብንደርስ እስካሁን እንደርስ ነበር። ግን አልደረስንም። ዘረኝነት እንደዛር በስሜት ያስጨፍራል እንጂ በስክነት እና በብስለት ነገሮችን ለማጤን እድል አይሰጥም። ትናንሽ ችግሮቻችን በዘረኝነት ዓይን ተቃኝተው በጊዜ መፈታት እየቻሉ ጦር ሲያማዝዙን አይተናል። እዚህ ግቡ የማይባሉ የሰፈር አሉባልታዎች በጎጠኝነት ተመንዝረው ብሄራዊ እዳ ሆነውን ያውቃሉ።

ነገሮችን በእርጋታ እና በስክነት መመልከት ካልቻልን በሰማንው እና በተነገረን ሀገር ማጽናት የማይሞከር ነው። ጊዜው እንደቁልቁለት መንገድ ማንም ካሻው ጋር ተጣድፎ የሚሮጥበት ነው። ከሩጫችን ዝግ ብለን ችግሮቻችንን የምንቃኝበት የእርጋታ ጊዜ ያስፈልገናል። እንደሀገር የእርጋታ እና የጽሞና ጊዜ ወስደን ስለችግሮቻችን፣ ስለሕዝብ ጥያቄ፣ ስለፖለቲካ ምህዳሩ ማውራት መቻል አለብን።

መነጋገር አቅቶን ዋጋ እየከፈልን ያለነው ስክነት በሌለው የቁልቁለት መንገድ ላይ ስለቆምን ነው። ምንም እንኳን አታካች እና ዳገታማ ቢሆንም ከወደታች ወጥተን ከወደላይ ማሻቀብ አለብን። ላይና ታች ሁለት አቅጣጫዎቻችንን የችግርና የመፍትሄ ስፍራ ብለን ልንፈርጃቸው እንችላለን። ታቹ በቁልቁለት ሲመሰል እርጋታና ስክነት የለውም። ላይኛው አድካሚ ቢሆንም ለየትኛውም ችግር መፍትሄ የሚሆን ግብረ መልስ ያለው ነው። ስለሆነም አብዛኛው የሰው ልጅ ችግሮች ከወደላይ በኩል ባለው አቅጣጫ በኩል ስለሆነ ከቁልቁለቱ ወጥተን ወደላይ ማቅናት ይኖርብናል።

በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ስለሀገር ያላቡ እና ስለብሄር ያላቡ ግለሰቦችን እያስተናገደች የምትገኝበት ጊዜ ላይ ነን። ዓላማቸው ግን የተራራቀ ነው። ስለሀገር ያላቡ ስለብሄር ካላቡ ጋር በአንድ ወንበር በነጻነት ሲቀመጡ ማየት ከግራ አጋቢነቱ በላይ ምን ነካን የሚያስብል ነው። በእኔ አተያይ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ለብሄር ያላቡ ዘረኞች አያስፈልጋትም። ሀገርና ሕዝብን ከፊት አድርገው ስለብዙሀነት ያላቡት ናቸው የሚያስፈልጓት።

በእኩል ስፍራ፣ በእኩል ተከታይ፣ በእኩል ነጻነት አንዱ ሀገርን አንዱ ነጣጣይ ትርክትን ይዞ በሁለት ጎራ ለሁለት አላማ የተሰለፉባት ኢትዮጵያ አታስፈልገንም። እያወራን ያለንው ስለጋራ ርስት፣ ስለብዙሀነት ውርስ ነው። ብዙሀነት ደግሞ ለአንድ አላማ ከመሰለፍ፣ ለአንድ ተልዕኮ ከመቅናት የሚነሳ እንጂ የተለያየ ሃሳብ እና ግብን ይዞ ከማላብ የሚነሳ አይደለም። ጉዳያችን ሰላም ከሆነ፣ ጉዳያችን አብሮነት እና ብዙሀነት ከሆነ የጋራ ትርክት ነው የሚያስፈልገን።

ግንባራችሁ ላይ ያቸፈቸፉ ላቦቻችሁን እስኪ እዩዋቸው.. ስለማን ነው ያላቡት? ስለሀገር ወይስ ስለብሄር? ስለትውልድ ወይስ ስለመንደር? ስለብዙሀነት ወይስ ስለነጠላነት? ስለእኛነት ወይስ ስለእኔነት? ላቦቻችን ፈር ስተው ስለግለሰብ ያላቡ ከሆነ ድካሞቻችን ከውድመት ባለፈ ትርፎቻችን አይሆኑም። ስለሀገር ከሆነ ያላብነው ሀገር ለማቆም የሄድንበት ረጅም መንገድ ጥሩ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

ዘመን እና ሃላፊነት ወሳጅ በሌላቸው የአንድ ወገን ትርክሮች የወርቅ ስጋጃዎቻችንን አቆሽሸናል። የክብር ደፎቻችን ንደናል። ስለሀገር ካልሆነ ስለሌላ የምናልባቸው ላቦች አይጠቅሙንም። የብቻ ትርክት በመፍጠር ከመሄድ የሚያስቀሩን ናቸው። አሁን የፈረሱብንን የምንክብበት፣ የተበላሹብንን የምናስተካክልበት እንጂ በድካም ላይ ድካምን ፈጥረን ከጉዟችን የምንገታበት አይደለም።

የሰለጠነ ዓለም ላይ ነን። መሰልጠን ቢያቅተን እንኳን በራሳችን ላይ መሰይጠን የለብንም። ዘረኝነት የገባንበት የፖለቲካ ምህዳር ጠልፎ ጣይ የደም መሬት ከመሆን ባለፈ ርስት የለውም። በብሄር ተቧድኖ ሀገር ያፈረሰ እንጂ ሀገር የገነባ ፖለቲከኛ አላውቅም። በዘረኝነት በኩል የዓለም ሥርዓት ከትናንት እስከዛሬ ገሎ ሟች አንድ አይነት ነው። የሀገር ጡብ ምሰሶዎች ሀገር ማጽኛ ካስማዎች እንደሆኑ በማመን ነውርን እና ነውረኞችን በመጸየፍ ሁሉን አስተሳስረን እንደደወሩ ጥንተ መልኮቻችን በአብሮነት ወደፊት ከመሄድ ውጪ ምርጫ የለንም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You