
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተካሄዱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በድል ደምቀው አሳልፈዋል። ከነዚህ ውድድሮች መካከል ተጠባቂ በነበረው የቅዳሜ ዕለቱ የለንደን ዳይመንድሊግ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አሸናፊ መሆን ችለዋል።
ባለፉት ሦስት የዳይመንድሊግ ውድድሮች በ3 እና 5 ሺ ሜትር ፉክክሮች ከድል ርቃ የነበረችው ኮከብ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በክብረወሰን ታጅባ ወደ ድል የተመለሰችበት ውድድር ቀዳሚ ነው።
ጉዳፍ በለንደን ዳይመንድሊግ የአንድ ማይል ውድድር በአስደናቂ ብቃት 4:11.88 ሰዓት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ያስመዘገበችውም ሰዓት በርቀቱ የቦታውና የኢትዮጵያ ክብረወሰን ሆኗል። በርቀቱ ሁለተኛው የዓለም ፈጣን ሰዓትም ነው። በውድድሩ ከባድ ተፎካካሪ ትሆናለች የሚል ግምት የተሰጣት አውስትራሊያዊቷ አትሌት ጄሲካ ሀል የኦሽኒያን ክብረወሰን በማሻሻል በ4:13.68 ሰዓት ሁለተኛ፣ አየርላንዳዊቷ ሣራ ሂለይ የግሏን ምርጥ ሰዓት በ4:16.26 በማስመዝገብ ሦስተኛ ሆናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ብርቄ ኃየሎም 10ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
የ10 ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኗ ኮከብ ጉዳፍ ከዚህ በፊት በማይል ውድድር 4:16.14 የሆነ የራሷ ምርጥ ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል። ጉዳፍ ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ በለንደን ዳይመንድሊግ በ5ሺ ሜትር 14:12:29 በሆነ የራሷ ምርጥ ሰዓት ማሸነፏ አይዘነጋም።
የ2025 ዳይመንድሊግ ውድድሮች አስራ አንደኛ መዳረሻ ከተማ በሆነችው ለንደን ተጠባቂ የነበረው የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር በመዲና ኢሳ አሸናፊነት ተደምድሟል። መዲና ሌላኛዋን ኢትዮጵያዊት አትሌት ፋንታዬ በላይነህን አስከትላ በመግባት 14:30.57 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ፣ አውስትራሊያዊቷ ሮስ ዴቪስ 14:31.45 ሰዓት ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች። ይህም የኦሽኒያን ክብረወሰን አስጨብጧታል።
ከአምስት ወር በፊት በሲቪያ ማራቶን በርቀቱ የመጀመሪያ ውድድሩን አድርጎ በ2፡05፡15 ሰዓት ያሸነፈው ሰለሞን ባረጋ የወንዶች 1500 ሜትር ውድድር ላይ የራሱን ምርጥ ሰዓት ባሻሻለበት 3:32.93 ሰዓት ዘጠነኛ ሆኖ ጨርሷል። ሰለሞን ከቶኪዮ 2025 የዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ትኩረቱ በ10 ሺ ሜትር ላይ መወዳደር እንደሆነ ይታወቃል። የለንደኑ የዳይመንድ ሊግ 1500 ሜትር ውድድር ተሳትፎውም ከማራቶን ወደ 10 ሺ ሜትር ሲመለስ ፍጥነቱን ለማሻሻል እንዲረዳው የሚያደርገው ዝግጅት አካል መሆኑ ተነግሯል።
ሰለሞን በለንደን ዳይመንድ ሊግ የወንዶች 1500 ሜትር ውድድር ላይ የጨረሰበት ደረጃ ለዜናነት ባይበቃም ያስመዘገበው የግል ምርጥ እና የቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮናን ሚኒማ ያሟላ ሰዓት ትኩረትን የሚስብ ነው። ምንም እንኳን በሁሉም ርቀቶች ተመርጦ እንደማይወዳደር ቢታወቅም ከለንደኑ ውጤቱ በኋላ ሰለሞን ለቶኪዮ 2025 የዓለም ሻምፒዮና በአራት ርቀቶች (በ1500ሜ፣ 5000ሜ፣ 10,000ሜ እና ማራቶን) ሚኒማውን ያሟላ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል። ከአራቱ መካከልም በወንዶች 1500 ሜትር እስካሁን ከኢትዮጵያ የሚጠበቀውን ዝቅተኛ የመመረጫ ሰዓት (ሚኒማ) ያሟላ ብቸኛው አትሌት ነው።
ከትናንት በስቲያ በስፔን ማድሪድ ከተማ በተካሄደው የብር ደረጃ ያለው የዓለም አትሌቲክስ ኮንቲኔንታል ቱር ውድድር (ሚቲንግ ማድሪድ 2025) ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አብዲሳ ፈይሳ 3፡ 34.63 በሆነ ሰዓት የወንዶች 1500 ሜትር አሸናፊ ሆኗል። በማድሪዱ የወንዶች 1500 ሜትር ፉክክር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሞሲሳ ስዩም (3፡35.98) እና ወገኔ አዲሱ (3፡ 36.36) በቅደም ተከተል ሰባተኛ እና ስምንተኛ ሆነው ጨርሰዋል።
በማድሪድ የሴቶች 1500 ሜትር ውድድር ላይም ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ነፃነት ደስታ በ4፡08.79 እና ትግስት ግርማ በ4፡09.50 ሰዓት በቅደም ተከተል ሦስተኛ እና አራተኛ ሲወጡ ባዪሴ ቶለሳ በ4፡15.90 ሰዓት አስራ ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።
በቤልጂየም በተካሄደው የነሐስ ደረጃ ያለው የዓለም አትሌቲክስ ኮንቲኔንታል ቱር የሴቶች 800 ሜትር ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረችው ንግስት ጌታቸው የራሷን ምርጥ ባሻሻለችበት 1፡57.01 የሆነ ሰዓት አሸንፋለች።
በሂዩስደን በወንዶች 1500 ሜትር ውድድር ላይ የተሳተፈው መልኬነህ አዘዘ 3፡36.17 በሆነ ሰዓት አምስተኛ ሲወጣ በወንዶች 5000 ሜትር የተወዳደረው ኃይለማርያም አማረ በ13፡19.65 ሰዓት አስረኛ ሆኖ ጨርሷል።
ኢትዮጵያውያኑ ወንድ አትሌቶች በማድሪድ እና ሂዩስደን ያደረጉት የ1500 ሜትር የቶኪዮ 2025 የዓለም ሻምፒዮናን ሚኒማ (ዝቅተኛ የሰዓት መስፈርት) የማሟላት ሙከራ ስኬታማ አልነበረም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም