25ኛ ዓመት የምስረታ የብር እዩቤልዩ በዓሉን ከዓመት በፊት በተለያዩ ፕሮግራሞች ያከበረው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር በኮቪድ-19 ምክንያት ባለፈው የተቋረጠውን ዓመታዊ ውድድር ከነገ ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ ያካሂዳል። የውድድሩን መጀመር አስመልክቶ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈራ ደንበል በአራት ኪሎ ስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል በሰጡት መግለጫ፣ የወረርሽኙ ስጋት ባይለይለትም እንደ አገር የተቀመጡ የጥንቃቄ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ በማድረግ ውድድሩን ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ለዚህም የተለየ ትኩረት በመስጠት ውድድሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚካሄዱ የማህበሩ አባላት ተነጋግረውበት መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሃያ ሰባት ዓመታትን ባስቆጠረው ውድድር ማህበሩ ዓመታዊ ውድድሮችን በዚህ ዓመት ለማስቀጠል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እንደቆየ የገለጹት አቶ ተፈራ፣ ማህበሩ የሚያደርገው የስፖርት እንቅስቃሴ በመንግሥትም ጭምር ተቀባይነት ስላለው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ውድድሮቹ በዚህ ወቅት እንዲቀጥሉ መደረጉም ሌላው ማህበረሰብ ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲገባ ሊያነቃቃ እንደሚችልም አመልክተዋል።
ነገ በሚጀምረው ውድድር ሃያ ሁለት የማህበሩ አባላት የሆኑ የጤና ክለቦች በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ተከፍለው ውድድር ያደርጋሉ። በዚህም ከሃምሳ ዓመት በላይ አራት ክለቦች፣ ከአርባ ዓመት በላይ ዘጠኝ ክለቦች፣ ከሠላሳ አምስት ዓመት በላይ ዘጠኝ ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል። ከውድድሩ መክፈቻ አስቀድሞ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የአረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚኖርም ታውቋል።
አቶ ተፈራ ደንበል፣ ማህበሩ ባለፉት 27 ዓመታት በቢሾፍቱ ከተማ የጤና ስፖርት ማህበራትን በተለያዩ ስፖርቶች ሲያወዳድር እንደቆየ ገልጸው፣ በዚህም በርካታ ግቦችን ማሳካት እንደቻለ አብራርተዋል:: የማህበረሰቡን በተለይም ከ35 ዓመት በላይ የሚገኙና በብሔራዊ ፌዴሬሽን ደረጃ ተመዝግበው ውድድሮችን የማያደርጉ ሰዎች በዚህ የጤና ስፖርት ማህበር በኩል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማስቻል ማህበሩ ካሳካቸው ግቦች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዚህም በርካቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉና በየሳምንቱ ውድድሮችን በማሰብ ልምምድ እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል:: ማህበሩ የሚያካሂዳቸው ውድድሮች የማስ ስፖርት (ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት) ይዘት እንዲኖራቸው በማስቻል ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ እንዲሁም በኀዘንና በደስታ ጊዜ መተጋገዝ እንዲኖር በማድረግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብም ተችሏል::
ማህበሩ ባለፉት 27 ዓመታት እነዚህን ተግባራት ሲፈፅም የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ተፈራ፣ ዓመታዊ ውድድሮች ከከተማ ውጪ እንደመከናወናቸው የበጀት እጥረት ፈተና እንደነበር አስታውቀዋል:: ማህበሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ከሆኑ አካላት ድጋፍ ሳይሻ የማህበሩ አባላት ከኪሳቸው በሚያወጡት መዋጮ እስከአሁን መዝለቁን ተናግራዋል:: በማህበሩ 27 ዓመታት ጉዞ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር፣ ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪና ቢጂ አይ ኢትዮጵያ አጋር በመሆን ለማህበሩ እዚህ መድረስ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ከበደ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ለበርካታ ዓመታት ውድድሮችን በእግር ኳስ ስፖርት ብቻ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ አትሌቲክስና የተለያዩ የቤት ውስጥ ውድድሮች መካተታቸውን አስረድተዋል:: ውድድሮቹ ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባይካሄድም ወረርሽኙን ለመዋጋት አንዱ መንገድ ስፖርት መሆኑን በማመን የማህበሩ አባላት ተማክረው ዘንድሮ ውድድሩ እንዲቀጥል ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዘንድሮው ውድድር አስራ ስምንት የማህበሩ አባል የሆኑ የጤና ቡድኖች እንደማይሳተፉም አክለዋል።
በ1986 ዓ.ም ከሁለት የጤና ቡድኖች ተነስቶ ምስረታውን ያደረገው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር አሁን ላይ የማህበራቱ አባላት ቁጥር ከአርባ ሦስት በላይ ሆነዋል። እነዚህ ማህበራትም በተለይም በየዓመቱ ክረምት ወራት ላይ በቢሾፍቱ የሚያደርጉት ዓመታዊ ውድድር ትልቅ እውቅናን ማግኘት ችሏል::
የአዲስ አበባ የጤና ስፖርት ማህበር በኢትዮጵያ የተቋቋመ የመጀመሪያው የጤና ስፖርት ማህበር ሲሆን፤ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የስፖርት ፍቅርና ዝንባሌ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያየ ምድብ ከፍሎ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል:: ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ግለሰቦችን በማካተት፤ ለአገር መጥቀም የሚችሉ ዜጎችን ከአልባሌ ሱስና ከአላስፈላጊ ስብዕናዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ጭንቀት በመጠበቅ ረገድ ለህዝብና መንግሥት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013