በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱ ከአውቶቡስ ተራ – 18 ቁጥር ማዞሪያ ድረስ ያለው አካባቢ ነው። አካባቢው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት መሆኑ እና በአካባቢው ያሉ መንገዶች ጠባብ መሆናቸው ለመንገዱ መጨናነቅ ዋነኛው መንስኤ ነው። የአካባቢውን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ ከአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጥር 2012 ዓ.ም ነበር የተጀመረው።
መንገዱ ሦስት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር የጎን ስፋት፣ 75 ሜትር ርዝመት ያለው ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ፣ ወደ ዋናው መንገድ የሚያስገቡ 20 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ድልድዮች፣ አንድ ማሳለጫ ድልድይና የድጋፍ ግንቦች ያለው ነው። ለፕሮጀክቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን፤ መንገዱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ክፍት ይሆናል የሚል እቅድ ተይዞ ነበር ወደ ግንባታ ሥራው የተገባው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም የመንገድ ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሰረት እየሄደ አይደለም። እስከአሁን ድረስ ማጠናቀቅ የተቻለውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን እንደተናገሩት እስከአሁን ድረስ ማጠናቀቅ የተቻለው የመንገድ ግንባታውን 10 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። ይህም ማለት ፕሮጀክቱን በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘ ቢሆንም በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ውስጥ የፕሮጀክቱ 10 በመቶ ብቻ ነው የተገነባው ማለት ነው።
የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ አካል የሆነው ዋና የማሳለጫ ድልድይ ግንባታ የመሰረት ቁፋሮ፣ ድልድዩን የሚሸከሙ ምሰሶዎች የኮንክሪት ሙሌት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ በመንገዱ በስተግራ በኩል 800 ሜትር የሚሆን የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ተከናውኗል። ቀሪውን የግራ መስመርን ጨምሮ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ያለው የግንባታ ክፍል ልማቶች በጊዜው ባለመነሳታቸው ግንባታው በሚፈለገው ልክ አለመሄዱን አቶ ኢያሱ አብራርተዋል።
እንደ አብዛኞቹ የሀገራችን ፕሮጀክቶች የዚህ የመንገድ ፕሮጀክትም በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይከናወን እያደረገ ያለው የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑን የሚያብራሩት አቶ ኢያሱ፤ መንገዱ ተሻሽሎና ሰፍቶ የሚሠራ መሆኑ የወሰን ማስከበር ችግሩን ከባድ እንዳደረገ ይናገራሉ። በርካታ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶች እንዲሁም ቀድመው የተዘረጉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ማንሳት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የተወሰኑትን የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን ማስነሳት የተቻለ ቢሆንም አሁንም በርካታ ያልተነሱ ቤቶች እና መሰረተ ልማቶች ይገኛሉ። በተለይም ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ያለው የግንባታ ክፍል የውሃ መስመሮችና ቤቶች አለመነሳታቸው እንቅፋት ሆነው ቀጥለዋል።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ ከተማዋ አካባቢ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤቶች ችግር የሚስታዋል በመሆኑ ተለዋጭ ቤቶች እና መሬት ሳይዘጋጅ በርካታ የቀበሌ እና የግል የንግድ እና መኖሪያ ቤቶችን ማንሳት ከባድ ችግር ሆኖ ቆይቷል። ለእነዚህ ተነሺዎች ደግሞ ተለዋጭ ቤቶችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። ለቀበሌ ቤቶች ነዋሪዎች ተለዋጭ ቤት ለግል ነዋሪዎች ደግሞ ቦታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ደግሞ የራሱ ሂደት አለው። ቤትና መሬት ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው። በቀጣይ በጋ ወራት ቤቶችን እና መሰረተ ልማቶችን የማስነሳት ሥራው የሚፋጠን ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎን የመንገድ ግንባታውም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የመንገዱን ግንባታ ሥራ ቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ የተባለ የሥራ ተቋራጭ፣ የምህንድስና ቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ዩናይትድ ኮንሰልቲንግ እየተከናወነ ይገኛል። ግንባታው ሲጠናቀቅም ከአውቶቡስ ተራ – 18 ቁጥር ማዞሪያ ድረስ ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በተሻለ መልኩ ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ አሁን ካለበት መንፏቀቅ ተላቆ በፍጥነት መከናወን እንዲችል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል። የከተማ አስተዳደሩ ለቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ተለዋጭ ቤቶችን፣ ለግል ቤት ነዋሪዎች ደግሞ ተለዋጭ መሬት የማቅረብ ሥራውን ሊሠራ ይገባል። በአካባቢው ያሉ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ባለቤት አካላት ደግሞ መሰረተ ልማቶቹን በአፋጣኝ በማንሳትና ቦታ በመቀየር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ከሁሉም በላይ የልማቱ ባለቤት የሆነው የመንገድ ግንባታው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የግል እና የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ ለልማቱ መፋጠን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013