ከተማ ሰፊና ቋሚ ህዝብ የሰፈረበት፣ የራሱ የሆነ አስተዳደር ያለውና በህግም እንደሚመራ መረጃዎች ያመለክታሉ። እንዲህ ባለው ሥርዓት ውስጥ የተመሰረተ ከተማ በውስጡ ለሚኖረው ሰው የተለያዩ አገልግሎቶችን፣እንዲሁም የሁሉንም ዕድሜ ባማከለ የመዝናኛ ማሟላት ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል። በከተሞች ከሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍል ደግሞ ወጣቶች በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል። በሥነምግባር የታነፀ፣ በዕውቀት የዳበረ፣ ሀገርን ወደ ተሻለ የሚያሻግር ትውልድ ለማፍራት ወጣቱ ነፃ አዕምሮ እንዲኖረው የሚያደርጉ ሥራዎች ያስፈልጋሉ። በተለይም በከተሞች ለወጣቱ ትልቅ ፈተና ከሆኑት መካከል አንዱ ለደባል ሱስ የሚያጋልጥ እንደ ጫትና ሺሻ ያሉ አደንዛዥ ዕፅ ይጠቀሳል። ወጣቱን ከዚህ ለመታደግ ደግሞ በተሻለ የሚታነጽበትንና አዕምሮውንም ዘና የሚያደርግበትን እንደ ስፖርት ማዘወተሪያ ማዕከል፣ በንብባ ክህሎቱን የሚያዳብርበት ቤተመጽሐፍት፣አረንጓዴ ሥፍራዎች ማመቻቸት ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር ምን እየተሠራ ነው የሚለውን በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ለወጣቶች የፈጠረችውን ምቹ ሁኔታ ለመዳሰስ ሞከረናል። እኛም እንዳስተዋልነው ለከተማዋ ውበት፣ ለነዋሪዎቿ ደግሞ ጥሩ የጊዜ ማሳለፊያ የሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኮች ተሠርተዋል። ለአብነትም በቅርቡ የተሠሩትን የወዳጅነት፣አንድነትና እንጦጦ ፓርኮችን መጥቀስ ይቻላል። የቅርቡን አነሳን እንጂ በከተማዋ አስሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ነዋሪው ከአካባቢው ሳይርቅ ጊዜ የሚያሳልፍባቸው መናፈሻዎች ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም ለወጣቶች ተብለው የተገነቡ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከሎችም እንደነበሩ ይታወሳል። ማዕከላቱ የታለመላቸውን ዓላማ ስለማሳካታቸው እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ጥረቶች ግን ተደርገዋል።
አንዳንድ ያነጋገርናቸው ወጣቶችም በከተማዋ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ግን በቂ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። በከተማዋ የተሠሩት የወጣት ማዕከላትና የስፖርት ማዝወተሪያ ሥፍራዎች በከተማዋ ካለው የወጣት ቁጥር ጋር አይመጣጠንም። ማዕከላቱም በሚሰጡት አገልግሎት ሳቢነት ይጎላቸዋል። በመሆኑም ማዕከላቱ ወጣቱን ከአልባሌ ቦታ ለማስቀረትና ከደባል ሱስ ሊታደጉት እንዳልቻሉ ነው ከአስተያየት ሰጭዎቹ መረዳት የተቻለው።
የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ወጣት ከማል ከድር እንደሚለው ማዕከላቱ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ላለመዋላቸው ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ዋናው ጉዳይ ግን የስፖርት ማዝወተርያ ሥፍራዎች ለሌላ አገልግሎት መዋላቸው ነው። እርሱ በሚኖርበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አካባቢ የነበረው ኳስ ሜዳ ፈርሶ ሕንፃ ተገንብቶበታል። የማዕከሉ አለመኖር የአካባቢውን ወጣቶች በእጅጉ ጎድቷል። ወጣቱ አዕምሮው ሌላ ነገር እንዳያስብ የሚያደርግ ሥራ ባለመሠራቱ ጉዳቱን ተደራራቢ ያደርገዋል ብሏል ወጣት ከማል። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ክፍተቱን መልሰው እንዲያጤኑም ሃሳብ አቅርቧል።
ሌላው ሃሳቡን ያካፈለን ወጣት ካሳሁን ተበጀ ሲሆን፣ በኢንጂነሪንግ ዕጩ ተመራቂ ነው። ልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 27 ነው የሚኖረው። እርሱ እንዳለው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ወጣቱ ዕውቀት እየጨበጠ፤ ሊዝናና የዕረፍት ጊዜውን ሊያሳልፍባቸው የሚችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው። አራት ኪሎ አካባቢ የሚገነባው ትልቅ ቤተ መጽሐፍት፣ ፒያስ አካባቢ እየተገነባ ያለው ዓደዋን የሚዘክር ግንባታ ማሳያ ነው። ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የዋሉት ሸገርና እንጦጦ ፓርኮችም ይጠቀሳሉ። ወጣቱ የሚዝናናባቸውና ጊዜ የሚያሳልፍባቸው በየአካባቢው መገንባት አለባቸው። በግንባታ ላይ ያሉት ሲጠናቀቁ ችግሩ ሊፈታ ቢችልም ችግር አለ። እሱ በሚኖርባቸው በልደታ ክፍለ ከተማ ወጣቱ ጊዜውን የሚያሳልፍባቸውና የሚዝናናባቸው ስፍራዎች የሉም። አካባቢው በአልኮል መሸጫዎች የተከበበ ነው። ወጣቱ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ የሚያነብባቸው አረንጓዴ ቦታዎች የሉም። ቤርሞ ሜዳ የሚባል ቢኖርም ብዙ ጊዜ በበርካታ ሰዎች ስለሚያዝ በቂ አይደለም። ክረምት ላይ ደግሞ ጭቃ በመሆኑ ለጨዋታ አያመችም። በመሆኑም ወጣቱ በአካባቢው ባሉ አልኮል፣ ጫት ቤቶችና አልባሌ ሥፍራዎች ጊዜውን የሚያሳልፍበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም ከተሞች ለወጣቶች ምቹ መሆን አለባቸው። ምቹነታቸው ወጣቶች እንደዚህ ላሉ አስከፊ ችግሮች እንዳይጋለጡ ይረዳል።
የወጣት ካሳሁንን ሃሳብ የምትጋራው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ወደሬ ገብረፃድቅ፤ እንደ ማህበር ችግሩን ለመቅረፍ በቅርቡ ለከተማዋ 11ኛ ክፍለከተማ የሆነውን ለሚ ኩራን ጨምሮ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የወጣት ማዕከላትና ስፖርት ማዘወተሪያዎችን የመገንባትና በግብዓት የማሟላት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን፣ በዚህ የክረምት ወቅት በዕረፍት ላይ ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ስፖርት ማዝወተሪያዎች አስፈላጊ መሆናቸው እንደታመነበት ገልጻለች። እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ የካ ወረዳ አንድ ጨፌ የሚባለው አካባቢ ለእረጅም ዓመታት በወጣቶች እየተጠየቀ የነበረ ስቴዲዮም ተሠርቶ ለአገልግሎት ውሏል። አምናና ዘንድሮ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ምክንያት ማህበሩ ተማሪዎችን አልሰበሰበም። በዚህ ምክንያት ለዕረፍት የሚመጡ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ከአምስተኛ ክፍል በላይ ያሉ ተማሪዎችን ማብቃት ሥራ በስፋት ባይካሄድም ቤት ለቤት በሚደረግ እንቅስቃሴ በወጣቱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የማህበሩ አመራሮችና አባላቶች ትምህርት በቴሌግራም ፣በሲዲ እያሳተሙ እያሰራጩ ነው። ተከፋፍሎ በ11ዱ ክፍለ ከተማ እየተሠራ ይገኛል። በመንገድ ላይ ትራፊክ የአራዳ፣ በደም ልገሳ ቂርቆስ፣ የአረጋዊያንን ቤት በመጠገን ልደታ፣በችግኝ ተከላ የየካ ክፍለ ከተማ ወጣቶች በስፋት እየተሳተፉ ነው። ዲሾች (የውሃ መውረጃ ቱቦዎች) በቆሻሻ እንዳይደፈኑ የማፅዳት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ወጣቱ እንዲህ ባለው በጎ ተግባር ከተሰማራ በኋላ ጊዜውን የሚያሳልፍበት የመዝናኛ ሥፍራ ያስፈልገዋል። መዝናኛዎቹ በቂ ባይሆኑም ሙሉ ለሙሉ የለም ማለት አይቻልም።
በከተማዋ ያሉት ስፖርት ማዕከላቶች አንዳንዶቹ ለወጣቱ ሳቢና ማራኪ አይደሉም። የወጣት ማዕከል ተብለው ወጣቱ ከሚዝናናባቸው ይልቅ ለቢሮና ለመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚሆኑበት ይስተዋላል። በቀላሉ ዋይፋይ ተገጥሞ በክረምት የዕረፍት ጊዜ ማዕከላቱ ላይ ከኤች አይቪ ጋር ተያይዞ ምክር የሚሰጥበት ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻልም ሲደረግ አይስተዋልም። ወጣት ማዕከላትና ስፖርት ማዝወተርያ ሥፍራዎች በዚህ መልኩ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ወጣቱ አልባሌ ሥፍራዎች ለሚውልበት ሁኔታ እንዲጋለጥ እያደረጉ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጫት አትቃሙ እየተባለ በርካታ ጫት ቤቶች የሚከፈቱበት ሁኔታ ይስተዋላል። አሁንም በየአካባቢው በድብቅም ቢሆን ገዳም ሰፈር፣ ጃልሜዳ አካባቢ ሺሻ ቤቶች አሉ። ብዙ ወጣት ይቅሙባቸዋል።
የአዲስ አበባ ቦሊቦል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ በላይነህ ተካ እንደሚሉት የስፖርት ማዝወተሪያ ሥፍራዎችን ማስፋት ወጣቶችን ከእነዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ይጠብቃል። ሆኖም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተወዳጁ የቦሊቦል ጨዋታ ሜዳ ለመኪና ማቆሚያ(ፓርኪንግ) ለተለያዩ አገልግሎቶች በመዋሉ በወጣቱ ተዘንግቶ ለመቆየት ተገድዷል። ሦስት መጫወቻ ቦታዎች ለፓርኪንግና ለሌሎች አገልግሎቶች ውለዋል። ብዙ ገንዘብ ፈሶባቸው በሲሚንቶ ቢሠሩም በታኬታና በቆዳ ጫማ ተጫዋቾች እንዲሁም በሚወጣ በሚገባ መኪና ተፈርፍረው ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዚሁ ጋር ቀድሞ በጨዋታው ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በመሳተፍ አርያ የሆነችው የአፍሪካ እና ሀገራችን መዲና እና የበርካታ ዲፕሎማት መኖርያ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ለራሷም ሆነ ለሀገርና ለዓለም አቀፍ ጨዋታ ዜጎች ማፍራት ሳትችል እንድትቆይም ዳርገዋታል። በተለያየ ምክንያት ሀገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ ዜጎች በስፖርቱ መሳተፍና ጤናቸውን እየጠበቁ መዝናናት ቢፈለጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በዚህ የተነሳ በርካታ የከተማዋ ወጣትም ለሱሰኝነት ተጋልጧል። ስፖርት ማዝወተርያና መዝናኛ ቦታዎች ተስፋፍተው ቢሆን ግን ወጣቱ ለእንዲህ ዓይነት ድርጊት አይዳረግም ነበር። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ችግሩን ለመቅረፍ ከክፍለ ከተሞች ጋር በጋራ በመሆን በአምስት የወንድና በአምስት የሴት ቡድን ውድድር ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ ፀጋዬ ክፍተቶቹን እየሞሉ ከመሄድ ባሻገር አዲስ አበባ ከተማን ለወጣቶች ምቹ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ይናገራሉ። 113 ወጣት ማዕከላት ፣840 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 1 ሚሊዮን 571 ሺህ 294 ወጣቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከልም ለ274 ሺ 894 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በተለያዩ ጊዜ ህገ ወጥ የጫት ማስቃሚያና የሺሻ ቤቶች ላይም ህጋዊ ዕርምጃ ተወስዷል። በድብቅ የሚሠሩ ከመሆናቸው አንፃር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አልተቻለም ለዚህም የማህበረሰቡ ተባባሪነት ያስፈልጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013