ባደጉት ሀገራት የንግድ ፈጣራ ሀሳብ ከገንዘብ በላይ ነው። በነዚህ ሀገራት የንግድ ፈጠራ ሀሳብ በእጅጉ ይከበራል፤ ይሸጣል ይለወጣልም። በተለይ ደግሞ ሀሳቡ ከሀሳብነት አልፎ ወደተግባር ቢለወጥ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ሆኖ ከተገኘ ብዙዎች ሀሳቡን የራሳቸው ለማድረግ ይሽቀዳደማሉ።
የነዚሁ ሀገራት መንግስታት ለንግድ ፈጠራ ሀሳብ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ዜጎች የንግድ ፈጠራ ሃሳቦችን ያለገደብ እንዲያፈልቁ የሚያስችሉ ትላልቅ ተቋማትን እስከመገንባት ደርሰዋል። በነዚሁ ተቋማት አማካኝነት አዳዲስ የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች እንዲፈልቁም አድርገዋል።
ሀገራቱ አያንዳንዱ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ከሌላው ልቆ እንዲገኝና ሃሳቡ ወደተግባር ተቀይሮ ውጤት እንዲያመጣ ያልተቆጠበ ድጋፍም የሚያደርጉ ሲሆን ሁሌም አዳዲስ የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች በሰዎች እንዲፈልቁ በማድረግና ሃሳቡን ወደ ተግባር በመቀየር በሀገራቸው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መሻሻል እንዲኖርም ያለመታከት ይሰራሉ። በዚህም ተሳክቶላቸው አብዛኞቹ ሀገራት የአለም የኢኮኖሚ የበላይነትን አስከመቆጣጠር ደርሰዋል።
ሀብት ውስን፤ ፈጠራ ግን ያልተገደበ መሆኑን በቅጡ የተረዱት እነዚሁ በእድገት የገሰገሱ ሀገራት በተለይ ለንግድ ፈጠራ ሃሳብ ትልቅ ትኩረት በመስጠት አሁንም ሀገራቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከሀገራቸው ውጪ የተለያዩ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች የሚሳተፉባቸው ውድድሮችን ጭምር በማካሄድ ሃሳባቸውን የመጠቀም ስልት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በኢትዮጵያም በአንድ ወቅት የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ግዜ ግን ውድድሩ ቆሟል። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ሊዘልቅ ግን አልቻለም። በቅርቡ ግን በፌዴራል ስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን አዘጋጅነትና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ‹‹ብሩህ›› የተሰኘ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ተካሂዷል።
የውድድሩ ዋነኛ አላማም በሀገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የስራ አድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ያሏቸው ወጣቶችን ለማበረታት መሆኑ ታውቋል። የሶስት ዓመት መርሃግብር መሆኑም ተነግሯል።
በተለያዩ ዘርፎች ለውድድሩ ከቀረቡ 356 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ሰባዎቹ ለመጨረሻው የማጣሪያ ዙር አልፈው ከሰባዎቹ ሃያዎቹ በማሸነፋቸው እያንዳንዳቸው 200 ሺ ብር ተሸልመዋል። ከውድድሩ አሸናፊዎች ውስጥም ከወላይታ ሶዶ አንድ፣ ከአዲስ አበባ አስራ ስድስት፣ ከዱራሜ አንድ እንዲሁም ከደብረ ማርቆስ ሁለት ይገኙበታል።
ከነዚሁ አሸናፊዎች መካከል ደግሞ አምስቱ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመሩ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ውድድሮች እንደሆኑና አስራ አራቱ ሴቶች በከፊል የሚገኙበት መሆኑም ተረጋግጧል። ሙሉ በሙሉ በሴቶች እየተመሩ በውድድሩ ተካፍለው ሽልማቱን ካገኙት አምስት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ታዲያ ‹‹አይ ጤና ዲጂታል ሜዲሲን›› የተሰኘው የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ይገኝበታል።
ዶክተር እየሩሳሌም ማሞ የአይ ጤና ዲጂታል ሜዲስን የንግድ ፈጠራ ሀሳብ አመንጪና ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ በጤናው ዘርፍ ተወዳድረው ለሽልማት ከበቁት ውስጥ አንዱ ሲሆን በዋናነት ድርጅቱ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ሀገሪቷ ካፈራቻቸው የጤና ባለሞያዎች ጋር አዳዲስ በሆኑና የፈጠራ ስራ በታከለባቸው መንገዶች ማገናኘት ላይ አተኩሮ ይሰራል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም ቨርችዋልና ተቋማዊ የጤና እንክብካቤ ፕሮጀክቶችን ይዞ በውድድሩ ላይ ቀርቧል።
በቨርችዋል ጤና እንክብካቤ ድርጅቱ ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ሲም ካርድና የሞባይል ቀፎ ያለው ሰው በአጭር የስልክ ቁጥር ማለትም በ7272 ላይ በመደወል በሚናገረው ቋንቋና በሚፈልገው የህክምና ባለሞያ ዓይነት የጤና ምክር አገልግሎት ማግኘት የሚችልበትን መንገድ ዘርግቷል። በተቋማዊ የጤና እንክብካቤ ደግሞ ህብረተሰቡን በሰፊው ቀጥረው ይዘው ያሉና እንደትምህርት ቤት፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመሰሉ ተቋማት ላይ የሚገኙ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰራተኞች እንዳይታመሙ አስቀድሞ ቋሚ የሆነ የህክምና ባለሞያዎችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ከጤና ትምህርት ጋር ቦታው ላይ መድቦ በሙሉ ግዜው የሚሰራበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ድርጅቱ ይህን ሲያደርግ ጤናማና ደስተኛ የሰው ሃይል እገነባለው ብሎ ያስባል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጇ ገለፃ ይህ ‹‹አይ ጤና ዲጂታል ሜዲስን›› የተሰኘ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ የመነጨው እርሳቸውን ጨምሮ በአራት የህክምና ጓደኞቻቸው አማካኝነት ሲሆን በተለይ እናታቸው ወደ እርሳቸው ስልክ ደውለው የህክምና ምክር መጠየቃቸው ሀሳቡን ለማመንጨት በር ከፍቷል። በተመሳሳይ ጓደኞቻቸውም ከዘመዶቻቸው በስልክ እየተደወለ የህክምና ምክር በመጠየቃቸው የዲጂታል ጤና ምክር አገልግሎት የንግድ ፈጠራ ሃሳቡን ለማጎልበት አጋጣሚ ፈጥሯል።
በዚህ መነሻነትም አራቱም የህክምና ባለሞያ ጓደኛሞች የግል ሀኪምና ዘመድ የሌለውስ እንዴት ይህን የጤና ምክር አገልግሎት ሊያገኝ ይችላል? አገልግሎቱን ካላገኘስ ምን ያጋጥመዋል? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣቸው ተፈጠረ። ሃሳቡን በጋራ ሲያብላሉ ከቆዩ በኋላም የኢትዮጵያ ህዝብ የህክምና ባለሞያ ዘመድ ያስፈልገዋል ከሚል እሳቤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ህብረተሰቡን ከህክምና ባለሞያዎች ጋር ለማገናኘት በሚል የንግድ ፈጠራ ሀሳቡ ተጀምሯል።
ድርጅቱ የንግድ ፈጠራ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለውጦ መስራት ከጀመረ ወዲህ በኢፌዴሪ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን አማካኝነት በተዘጋጀው የብሩህ የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ላይ ቀርቦ በጤናው ዘርፍ ከቀረቡ የንግድ ፈጠራ ሀሳቦች መካከል አሸናፊ በመሆኑ የ200 ሺ ብር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
ማንኛውም ሰው በድርጅቱ በኩል የጤና ምክር አገልግሎት ሲፈልግ በቅድሚያ በ7272 የስልክ መስመር ላይ ደውሎ ቋንቋና ምን አይነት የህክምና ባለሞያ እንደሚፈልግ ይመርጣል። በመቀጠልም ከህክምና ባለሞያው ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ የሚሰማውን የጤና እክል ይናገራል። ታማሚው ከሚሰጠው መረጃ በመነሳትም የህክምና ባለሞያው ተገቢውን የጤና ምክር አገልግሎት ይሰጠዋል። የህክምና ባለሞያዎችም የጤና ምክር አገልግሎት ለመስጠት መስመር ላይ ስለመሆናቸው የሚያሳውቁበት መተግበሪያ አላቸው። ይህም ለየክልሉና ለሁሉም ሰው ሊሆን የሚችል አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል።
ዋና ስራ አስኪያጇ እንደሚሉት እንዲህ አይነቱ የጤና ምክር አግልግሎት አሰጣጥ ዘዴ ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ነበር። ይሁንና በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ ዘዴውን ለመተግበር የግድ ብሏል። በተለይ ወረርሽኙ ማህበራዊ ርቀትን የሚጠይቅ በመሆኑና አብዛኛው ማህበረሰብም እቤት ለመቆየት በመገደዱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጤና ምክር አገልግሎቶችን ሲጠቀም ቆይቷል።
ይኸው ክስተትም በኢትዮጵያም በመታየቱ በዚሁ ዘዴ አማካኝነት የህክምና ምክር አገልግሎት ፍላጎት በህበረተሰቡ በኩል እንደሚጨምር ይጠበቃል። ቀጣዩ ግዜ የቴክኖሎጂ ከመሆኑ አኳያም ይህንኑ ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችም የተሟሉ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል።
በአሁኑ ግዜ አይ ጤና ዲጂታል ሜዲስን በ7272 የስልክ መስመር የቨርችዋል የጤና ምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ድርጅቱ በሁለተኛው ፕሮጀክቱ ማለትም ተቋማዊ የጤና እንክብካቤ ስራው መሬት ላይ እንዲወርድ ከጤና ሚንስቴር ጋር በመሆን የአሰራር ደረጃዎችን እያወጣ ይገኛል።
ሁሉም ህብረተሰብ እንዲህ አይነቱ የዲጂታል የጤና ምክር አገልግሎት እንዳለ ያውቃል ተብሎ የሚገመት ባለመሆኑ በቀጣይ ድርጅቱ አገልግሎቱን በተመለከተ ለማህረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን የመስጠትና የገበያ ተደራሽነት ስራዎችን ለማከናወን እቅድ ነድፏል። ተቋማት ተኮር የሆነው የጤና አገልግሎት አቅርቦት ወደ ዲጂታል የጤና ምክር አገልግሎት እንዲቀየርና ጥቅሙም የጎላ ስለመሆኑም አበክሮ የመስራት ሀሳብም አለው።
በስራ ሂደት አስካሁን ድረስ ድርጅቱ በርካታ ነገሮችንም የተረዳ ሲሆን በተለይ ወደ ድርጅቱ ደውለው የጤና ምክር አገልግሎት የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ሚስጥራቸው እንዲጠበቅላቸው እንደሚፈልጉና በህብረተሰቡም ሆነ በጤና ሚኒስቴር በኩል አሉ ተብለው የማይታሰቡ የጤና ችግሮች እንዳሉም ለመረዳት ችሏል። እነዚህ መረጃዎችም የማህበረሰብ ጤና ፖሊሲዎች ሲቀረፁ በግብአትነት ያገለግላሉ።
ማህበረሰቡ በጤና ላይ ያለውን ትኩረት እንዲጨምር ለማድረግ ከመንግስት ብዙ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ስራ አስኪያጇ፤ እነርሱ ባመነጩት በዚሁ የዲጂታል ጤና ምክር አገልግሎት የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ማረጋገጣቸውንም ይጠቁማሉ። ይህም ህብረተሰቡ ለማይወጣው ህመምና የህክምና አገልግሎት ወጪ የሚዳርገው ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ። ከዚህ አኳያ መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ምክር አገልግሎት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ያሳስባሉ። ከዚህ አኳያ በተለይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት ረገድ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ያመለክታሉ።
የኢፌዴሪ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ባዘጋጀው የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ላይ ቀርበው ካሸነፉ ሀያዎቹ ውስጥ ‹‹አይ ጤና ዲጂታል ሜዲስን›› አንዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አስሩ አሸናፊዎች ለስድስት ወራት ያህል ወደ ንግድ ማበልፀጊያ እንደሚገቡ የተነገረ ሲሆን የእነ ዶክተር እየሩሳሌም የንግድ ፈጠራ ሃሳብን ጨምሮ ቀሪዎቹ አስሮቹ ቀድመው ወደ ንግድ ስራ የመግባት ሂደት ውስጥ በመሆናቸው የፋይናንስ ድጋፍ በኮሚሽኑ በኩል ይደረግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013