በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ የስፖርት ልኡካን ቡድን ትናንት ማለዳ ወደ አገሩ ተመልሷል። ከኦሊምፒኩ ጉዞ አስቀድሞ በበርካታ አትሌቶች፣ የስፖርት ባለሙያዎችና ሌሎች ላይም የተፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች በሀገር ውጤት ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድሩ በማሰብ በወቅቱ በዝምታ የታለፉ ጉዳዮች ኦሊምፒኩ ከተጠናቀቀ በኋላ የግድ መነሳት አለባቸው።
በዚህ ረገድ አዲስ ዘመን ባለፉት ሁለት ቀናት ተከታታይ እትሞቹ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል በነበረው አለመግባባትና በግለሰቦች መቃቃር ምክንያት የሕዝብን አንገት ያስደፉ አሳፋሪ ስህተቶች፣ የሀገርን ጥቅም ያስቀሩ በቸልተኝነት የተላለፉ ውሳኔዎችና የአትሌቶችን ቅስም የሰበሩ በደሎችን ለመዳሰስ ሞክሯል። ዛሬ ደግሞ በሕዝብ ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ላይ የተፈፀሙ በደሎችን ለመዳሰስ ተሞክሯል።
በተጠናቀቀው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያና አትሌቶቿ የተበደሉትን ያህል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃንም ተበድለዋል። ከኦሊምፒክ ጨዋታዎችና ከኢትዮጵያውያን ድሎች ታሪክ ተነጥለው የማያውቁት አንጋፋው የሕትመት ሚዲያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ቀዳሚዎቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ የሚዲያ ልዑክ ቡድን ከልዩ ልዩ ብዙሃን መገናኛ መርጠው ሲወስዱ ታላላቆቹን የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ምንም አያመጡም ብለው ከታላቁ የስፖርት መድረክ እንዲቀሩ ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ አሳልፈዋል።
እነዚህ የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን በተለያየ ዘመን የተካሄዱ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተገኝተው በተለይ የአገሪቱ አትሌቶች ድሎች፣ ቃለመጠይቆች፣ በአትሌቶች መንደር የታዩ ክንውኖች፣ አቀባበሎች፣ ታላላቅ ሽልማቶች፣ አጠቃላይ የስፖርቱን ዘርፍ እንቅስቃሴ በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች፣ የምስልና የድምፅ ክምችት ታሪክን ሰንደው በማስቀመጥና ለሕዝብ መረጃዎችን በወቅቱ በማድረስ ትልቅ ሚና ነበራቸው። ዘንድሮ ግን እነዚህን መገናኛ ብዙሃን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ የኦሊምፒክ ታሪኮች በአንድነት ተሰንደው እንዳይገኙ የማድረግ ታሪካዊ ስህተት ተሰርቷል።
በሕዝብና በመንግስት በጀት የሕዝብ ታላላቅ መገናኛ ብዙሃንን ወደ ጎን ትቶ የግል መገናኛ ብዙሃንን ይዞ የተጓዘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህን ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ሲያሳልፍ ሕዝብና መንግስትን መናቅ መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቶ አይደለም። የግል መገናኛ ብዙሃን ወደ ኦሊምፒኩ መጓዛቸው ክፋት የለውም። ነገር ግን የግሎቹም መገናኛ ብዙሃን ቢሆኑ የተመረጡበት ምክንያት ግልፅ ካለመሆኑ በተጨማሪ ወደ ቶኪዮ የተጓዙ ጋዜጠኞች ሙያው የሚፈቅደው ስነ ምግባር ያላቸውና ነገሮችን ገለልተኛ ሆነው የሚመለከቱ ስለመሆናቸው ምክንያታዊ ሙግቶችን ማንሳት ይቻላል።
ለዚህም በኦሊምፒኩ ወቅት የተለያዩ የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን አባላት ላይ የተፈፀሙ በደሎች፣ የተሳሳቱ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና ምክንያታቸው ከስፍራው ሲዘገቡ እንዳልነበረ ማስተዋል ይቻላል። ይህም ሕዝብ በስፍራው ላይ በትክክል ምን እንደተፈጠረ እንዳያውቅና ስህተቶችን የትኛው አካል እንደፈፀመ እንዳያውቅ አድርጓል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት በሕዝብና በሀገር ጥቅም ላይ እንደፈለጋቸው የፈነጩ ግለሰቦችን ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ የሚያግዝና መረጃን የማፈን ተግባር እንደሆነ ግልፅ ነው።
በዚህ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ልኡክ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞችን ይዞ አልተጓዘም። አመራሩ ጉዳዩን የሚያስፈፅምለት ቃል አቀባይ ወይም ፕሮፓጋንዲስቶችን ወጪያቸው ተችሎ ሶስት ሺ ሁለት መቶ ዶላር አበል እየከፈለ ይዞ እንደተጓዘ ለማንም ግልፅ ነው። ምክንያቱም አመራሩ ገና ወደ ኦሎምፒኩ ከመጓዙ በፊት ምን እንደሰራና እዚያም ምን እንደሚሰራ ቀድሞ ያውቀዋል።
ታላላቆቹን የሕዝብ መገናኛ ብዙሃንን ማግለል የኦሎምፒክ ውድድሮችን የሚከታተሉ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን መብት መጋፋት ወይም መንፈግ ነው። በተለይ በክልል የሚኖሩ ሬዴዮና ጋዜጣ ዋና የመረጃ ምንጫቸው የሆኑ ብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን መናቅ ነው። እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ከተደራሽነት አኳያ ከግሎቹ የተሻሉ መሆኑን እየተናነቃቸውም ቢሆን የኦሊምፒክ አመራሮች እንደሚቀበሉት ግልፅ ነው።
በተለይም በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎች እንዲሁም በዘመናዊው የድረ ገፅና ማህበራዊ ሚዲያም ዘገባዎችን የሚሰሩ በመሆኑ ከኦሊምፒክ ለመቅረታቸው ምንም አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ከባድ ነው። ለምሳሌ ያህል ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር ዘወትር በቅርበት እየሰራ የነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኦሎምፒኩ በኮቪድ-19 ምክንያት ከመራዘሙ በፊት የቶኪዮ ኦሎምፒክን በየእለቱ በሚወጡ የሕትመት ውጤቶቹ ሰፊ ሽፋን ለመስጠት ከዝግጅት አንስቶ እስከ ውድድርና አቀባበል ድረስ በምን መልኩ እንደሚዘግብ በአስር ገፅ ዝርዝር የስራ እቅድ አቅርቦ የተሰጠው ምላሽ አልነበረም።
እነዚህን መገናኛ ብዙሃን በኦሊምፒክ ዘገባ አለማሳተፍ ለብዙሃኑ ህዝብ በሚረዳው ቋንቋ ስለገዛ ሀገሩ ኦሎምፒክ ውድድር እንዳይሰማ መከላከል ማለት ነው፡፡ ከተለያየ የቋንቋ ቤተሰብ የመጡ የኦሎምፒክ ተወዳዳሪዎች ገድል በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ፣ በሱማልኛ ወዘተ በሬዴዮና በቴሌቨዥን እንዲሁም በጋዜጣ በተከታታይ እንዳይቀርብ ማገድ ማለት ነው።
ኦሎምፒክ የሀገሮች ውድድር ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኖች ፉክክር የሚታይበት ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት ውድድሮች ብሄራዊ ሚዲያዎችን መዘንጋት” መብታችን ስለሆነ” ተብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም። ታላላቆቹን የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ከአንድ ነጠላ ሬዴዮ ወይም ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በኩል ለማወዳደር የሚደረገው የተሳሳተ ምልከታ መንግስትንም መናቅ ነው። የተወዳዳሪነት ደረጃቸው በጥናት የሚወራረድ ቢሆንም፤ እነዚህን መገናኛ ብዙሃን ማግለል መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማግለል ተለይቶ አይታይምና ስህተቱን የፈፀመው ተቋምም ይሁን ግለሰቦች ሊጠየቁበት ይገባል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013