የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ‹‹ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና የገጠሟትን የክፋት ኃይላት ሁሉ ድል በመንሣት ታፍራና ተከብራ ነጻነቷን አስጠብቃ ኖራለች። ጀግኖች እናቶችና አባቶች የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎችን በማንበርከክ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በነፍሳቸው ተወራርደው አቆይተዋታል። በታሪክ አጋጣሚ ዛሬም ኢትዮጵያ የአጠባ ጡቷን፣ የአጎረሰ እጇን የሚነክሱ ከሐዲዎች፣ ሊያዳክሟትና ሊበትኗት ከቅርብና ከሩቅ ከተነሡ ኃይላት ጋር በመመሳጠር አቆብቁበው ተነሥተዋል።›› ሲል ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የነበረበትን ችግር እያወቀ እንኳን ብዙ ዕድሎችንና ሃያ ሰባት የመታረሚያ ዓመታትን ሰጥቶታል። አሸባሪ ቡድኑ ግን በሤራ ተጠንስሶ በጥፋት ያደገ ነውና፣ የሚብስበት እንጂ የሚታረም አልሆነም። ይህ የጥፋት ኃይል በሕዝብ ቁጣ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም ቢሆን፣ የተሰጠውን ተደጋጋሚ የመታረም ዕድል ለመጠቀም አልፈለገም። ይልቁንም መቀሌ ላይ መሽጎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር በማሤር ጊዜውንና የዘረፈውን ገንዘብ ሲረጭ ከርሟል። በዚህም የተነሣ ግጭት፣ መፈናቀልና አሰቃቂ ግድያን በመላ ሀገራችን መለኮስና ማስፋፋት የዕለት ተግባሮቹ አድርጎ ቆይቷል። የትግራይ ሕዝብ በዚህ ለጥፋት ተጸንሶ ለአፍራሽነት በተወለደ አሸባሪ ቡድን የተነሣ እንዳይጎዳ በማለት፣ መንግሥታችን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያልሞከረው መንገድ አልነበረም። ስድብና መንጓጠጡ ሳያስቆጣው እስከ መጨረሻው ሰዓት መንግሥት ሁሉንም የሰላምና የሽምግልና መንገድ ተግባራዊ መደረጉን መግለጫው ይጠቅሳል።
መግለጫው እንደሚያትተው፤ በተቃራኒው ይኽ የጥፋት ኃይል የፈጸማቸው ልዩ ልዩ ግፎች አልበቃ ብሎት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው በታሪካችን የማይረሳ አሰቃቂ ጥፋት ነገሩን ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ አደረገው። ጀግናው የመከላከያ ኃይላችንም ከአማራ እና ከአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ይሄንን የጥፋት ኃይል መትቶ አከርካሪውን በመስበር፣ የቡድኑ አባላት በተንቤን ጉድጓዶች እንዲወሸቁ ተገድደዋል። ከአመራሮቹ ብዙዎቹ ተደመሰሱ፤ ከፊሎቹ ተማረኩ፤ ጥቂቶቹም በየዋሻውና በሰላማዊ ሕዝቡ ጉያ ውስጥ ገብተው ተሸጎጡ። ሕግን ከማስከበሩ ተግባር ጎን ለጎን፣ መንግሥት የትግራይ ክልልን ከዚህ የጥፋት ኃይል ነጻ ለማድረግ፣ ያፈረሱትን መሠረተ ልማቶች ለመገንባት፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለማስቻል፣ ሰብአዊ ርዳታ ለሕዝቡ ለማድረስ፣ በሂደቱ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ለማረምና፣ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ ባለፉት ስምንት ወራት በሙሉ ጉልበቱ ተግቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የጁንታው ርዝራዦች በሕዝቡ ውስጥ ተሠግሥገው ሕዝቡን ለጥፋት እየቀሰቀሱ በሚፈጥሩት ቀውስ የትግራይ ሕዝብ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አልቻለም። የርዳታ ሥርጭትን በማስተጓጎል፣ መሠረተ ልማቶች እንደገና ሥራ እንዳይጀመሩ በማደናቀፍ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን በማውደም፣ የአካባቢ አመራሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ገበሬው ተረጋግቶ እንዳያርስ የእርሻ ሥራውን በማስተጓጎል፣ የመልሶ ግንባታ ተግባራትን ማደናቀፉን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አደረጉት። ችግሩን ለማባባስ በሚፈልጉ ኃይላት ጆሮውን የተጠመዘዘው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሂደቱን ውስብስብ ጠባይና የአሸባሪውን የጥፋት ባሕርይ ለመገንዘብ ባለመፈለግ፣ እውነትን ትቶ የአጥፊውን አካል ጩኸት አስተጋባ። ቡድኑ በረጅም የሥልጣን ዘመኑ የፈጸመውን አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሚልዮኖችን ህልውና የማጥፋት ሥራ በዝምታ የተመለከቱ ዓለም አቀፍ አካላት፣ ዛሬ አጥፊውን ኃይል ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ስለሚፈልጉት፣ እርሱን ለማዳን ሲሉ የመንግሥትን መልካም ጥረት እንዳላዩ ማለፍን መምረጣቸውን መግለጫው ይጠቁማል።
ሕዝቡ ከአሸባሪው ጁንታ እስከ ዘለዓለሙ ካልተለያየ በቀር፣ ገበሬው ተረጋግቶ ማረስ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል። እንኳንስ የትግራይ ገበሬ ወደ እርሻው ሊመለስ ቀርቶ፣ አሸባሪው ጁንታ በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች እንዳያርሱ ማወክ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊ ርዳታ እንዳይደርስና ሰብአዊ መብቶች እንዳይከበሩ አድርጓል። አሁን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የተኩስ አቁም አድርጎ ከወጣ በኋላ ግን ሕጻናት ለጦርነት ሲሰለፉ፤ ርዳታ የጦርነት መሣሪያ ሲሆን፣ እናቶችና ወጣት ሴቶች ሲደፈሩ፣ የእምነት ተቋማት የጦር መለማመጃዎችና የጦር መሣሪያ መጋዘን ሲደረጉ፣ የርዳታ እህል የጫኑ መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ በጁንታው የጥፋት ተግባር ሲስተጓጎሉ፣ በአፋር ክልል በአንድ የሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችን ሲያርድ፣ ከ300 ሺህ በላይ ዜጋ ሲያፈናቅል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እውነታው ምን እንደሆነ ለማወቅ ፍላጎት ያለው አካል ሁሉ ለመታዘብ መቻሉን በመግለጫው ተመልክቷል።
የሽብርተኛ ቡድኑ ግን ኢትዮጵያን ለመበተን ከተነሳበት የአሸባሪነት ባህሪው ሊላቀቅ አልቻለም። የአማራንና የአፋር ክልሎች አጎራባች ሕዝቦችን መግደልና መዝረፍ ቀጥሏል። ገበሬዎችን እንዳያርሱ አስተጓጉሏል። ገዳማትን ሳይቀር ዘርፏል። የርዳታ መኪኖችን ወደ ትግራይ ከመግባት አግዷል። መንግሥት መቀሌ ውስጥ ያከማቸውን እህልም ጁንታው አይዘምቱልኝም ላላቸው ሰዎች እንዳይታደል ከልክሏል። የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንና የክልል ልዩ ኃይሎች መንግሥት የወሰነውን የተኩስ አቁም በማክበር ርምጃ ከመውሰድ ቢቆጠቡም፣ አሸባሪው ጁንታ ግን የድፍረት ድፍረት ተሰምቶት የጥፋት ሥራውን ቀጥሎበታል። የሕወሐት ዓላማና ግብ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደሆነ አመራሮቹ በእብሪት መናገራቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
ለዓላማው መሳካትም በብዙ የውጭ ኃይሎች በመታገዝ ለበለጠ ጥፋት ምላጭ መሳብን መርጧል። ወጣቶችን በእኩይ ፕሮፓጋንዳ በመደለልና ሕጻናትን በሐሽሽ እንዲናውዙ በማድረግ ለጦርነት እየመለመለ፣ በአፈሙዝ የሚነዱ አዛውንቶችን ጭምር እያሰለፈ ይገኛል። የአሸባሪው ጁንታ አካሄድ ሕዝብ አስጨራሽ የሆነ የሽፍትነት አካሄድ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ ተናግረናል፤ አስጠንቅቀናል። ጁንታው እየከፈተ ያለው ጥቃት ሕዝባዊ መልክ እንዲይዝ በማድረግ ስለሆነ መመከት የሚገባውም በዚያ አግባብ ነው፤ የመላው ሕዝባችንን የማያዳግም ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲል መግለጫው ሰጥቷል። ይህን ሁኔታ በማስመልከት በአገሪቱ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ዙሪያ የወጣቱ ተሳትፎ ምን መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ አመራር አቶ ግዛው አመራ እንደሚናገሩት፤ አገሪቱ የወጣቶች እንደመሆኗ በአገር ጉዳይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። አባቶች በወጣትነት እድሜያቸው ተዋድቀው ያቆዩትን አገር የአሁኑ ወጣት መረከብ አለበት። ወጣቶች በአገር ጉዳይ ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል። በአገሪቱ በሚከሰቱ ጉዳዮች የሚኖራቸው ተሳትፎ ያልተገደበና ቁርጠኝነት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። አላስፈላጊ ከሆኑ እኩይ ተግባራትና አፍራሽ ስራ መታቀብና መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል። በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ ከሚገኙ የጥፋት ሃይሎች አገሪቱን ተግተው በመጠበቅ መንቀሳቀስ አለባቸው።
ወጣቱ ኃላፊነቱን በአግባቡና በስርዓቱ መወጣት ካልቻለ ህጋዊ በሆነ መንገድ አገሪቱን ከሚያፈርሱ እኩይ ተግባራት መታገልና ማፈራረስ ይጠበቅባቸዋል። ወጣቱ ለአገሩ መቆሙን በተግባር ማሳየት የሚጠበቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን። አገሪቱ በምታቀርብ ማንኛውም ጥሪ ወጣቱ በግንባር ቀደምነት ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል። አገሪቱን ከማንኛውም አደጋዎች የመታደግ ኃላፊነት ያለበት ወጣቱ ክፍል ነው። አሁን ያለው ሁኔታ አስጊ በመሆኑ የወጣቱን ትኩረት የሚፈልግበት ወቅት መሆኑን አቶ ግዛው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግዛው አባባል፤ አገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ትውልዱ ኃላፊነት ወስዶ በውጪም በውስጥም የሚመጡ ችግሮችን ሊፈታና ሊበታትን ይገባል። አገር ለማፍረስ የሚጥሩ ወገኖችን አላማ ለማክሸፍ በአንድነትና በቁርጠኝነት ተባብሮ አገር የማስቀጠል ስራው በወጣቱ ጫንቃ ላይ ያረፈ ነው። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ላይ ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅበታል። ከምንግዜውም በላይ ከማንም ይልቅ አገር የማዳን ስራ የወጣቱ ኃላፊነት ነው። በአሁን ወቅት ይህ ስራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ወታደሩም፣ ጄኔራሉም፣ መንግስትም ሁሉም ሰው መተባበር መቻል አለበት።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይበቃል ደሳለኝ፤ በአሁን ወቅት ያለውን የአገሪቱን ሁኔታ ሁሉም ሰው የሚረዳው ነው። አገሪቱ ከውስጥም ከውጪም ትልቅ አጣብቂኝ ውስጥ ያለችበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። ይህንንም ሁሉም ሰው በየእለት እንቅስቃሴው የሚያየውና እየተሳተፈበት የሚገኝ ነው። ይህን ችግር በደንብ በመጋፈጥና አገሪቱ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንድትመጣ የሁሉም ሰው ድርሻ ያስፈልጋል። ወጣቱን ብቻ ለይቶ ሚናው ይህ መሆን አለበት የሚባልበት ጊዜ ላይ አይደለንም። በአብዛኛው ወጣቱ በዚህ ሁኔታ የበለጠ መስራትና ኃላፊነቱን ሊወጣ የሚገባት ጊዜ መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹ወጣቱ በተሻለ መንገድ ስራዎችን ይሰራበታል ተብሎ የሚጠበቅበት ጊዜ አሁን ነው። ›› የሚሉት አቶ ይበቃል፤ ከዚህ አንፃር በየትኛውም መንገድ አገሪቱ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የወጣቱን አስተዋፅኦ የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ነች። ሁሉም በያለበት አካባቢ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሴቶችና የወጣት አደረጃጀት አለው። ይህን በመጠቀም የተለያዩ የድጋፍ ስራዎች ለአገር መከላከያው እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ ውጪ በየአካባቢው እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት፣ የክልል ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ድጋፍ እየተደረገ ነው። ፓርቲው የተወሰኑ አመራሮችን ወደ ግንባርም መላኩን ያስረዳሉ።
ሁሉም ወጣት ከቻለ በመዝመት ካልቻለ ደግሞ ከኋላ ሆኖ በደጀንነት አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል። ለመከላከያው በተቻለ አቅም ድጋፎች እየተደረጉ ሲሆን በገንዘብና በተለያዩ ቁሳቁሶች እየተሰጡ ነው። ወጣቱ ግን መዝመት በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚገኝ ከሆነ በግንባር ሄዶ ከሽብርተኛው ቡድን ጋር መዋጋት አለበት። በክልሎች የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ግንባር ድረስ በመሄድ እየተፋለሙ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ወጣቱ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅበት አቶ ይበቃል ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ይበቃል አባባል፤ የውጪ ጫናዎችን ለመቋቋም ወጣቱ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል። የተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ናቸው። ይህን ለማድረግ ወጣቱ በተለያየ መንገድ አገሪቱን ሊጠብቅ ይገባል። ይህ ሲባል በአገር መከላከያ ሰራዊትና በክልል የፀጥታ ተቋማት ውስጥ በመሳተፍ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ ደግሞ አገር ሊገነባ የሚችለውንና አሁን ከተፈጠረው አይነት ችግር ልትወጣ የምትችለው፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትና የመፍረስ አደጋ የሚቆመው የውስጥ አንድነት ሲኖር ነው። ከዚህ አንፃር ወጣቱ አንድነቱን ጠብቆ የሚመጡ አደጋዎችን መጋፈጥ ይጠበቅበታል።
ሌላው በማህበራዊ ሚድያ የሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ሲታይ የአገሪቱ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ሲታይ ደካማ ነው። ባደጉት አገራት የፊት ለፊት ጦርነት ከሚካሄደው በላይ የሳይበር ጦርነቱ የስነልቦና ጫና ፈጥሮ አሸናፊ ለመሆን የሚደረጉ ግብግቦች አሉ። ይህ የሳይበር ጦርነት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ነገር ነው። ስለዚህ የትኛውም ወጣት የማህበራዊ ሚድያ ፕሮፓጋንዳ በተመለከተ ማድረግ ያለበትን ነገር ማከናወን አለበት። ይህ ሲባል በማህበራዊ ሚዲያን አወንታዊ ለሆነ ነገር ሊጠቀመው ይችላል። ሌሎች ሰዎችን በስነልቦና ሆነ በሌሎች ነገሮች ለመጉዳት የተሳሳቱ ነገሮችን ሊያሰራጭ ይችላል። ይህን ለመግታት የተጣራ መረጃ የሚባሉትን ከህጋዊ ተቋማት መውሰድ መቻል አለበት። ከዚህ ውጪ ወገንን ሊደግፍ በሚችል መልኩና አንድነትን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ የሳይበር ጦርነቱን መቀላቀል መቻል እንዳለበት አቶ ይበቃል ያመለክታሉ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013