በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው። መንግሥትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩ በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው። ይህም እንቅስቃሴ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው። የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል። በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከስሩ ለመፍታት ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት በመሰባሰብ አካባቢያቸው የሚገኙ ሰዎችን እየደገፉ ይገኛሉ። ወጣት በጎ አድራጊዎቹ አረጋውያንን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን እየረዱና እየደገፉ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ የፊንጫ አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ አምባ መረዳጃና በጎ አድራጎት ማህበር ይጠቀሳል። ማህበሩ ከተመሰረተ ቅርብ ጊዜ ቢሆነውም ተማሪዎችን በመርዳትና ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሁም አረጋውያንን በማገዝ ላይ ነው። ስለ ማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴ ከመስራቹ አቶ አብዱ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ላይ ህጋዊ ሆኖ የተመሰረተ ሲሆን ለማህበሩ መመስረት ዋነኛ ምክንያት የነበረው በአሶሳ ከተማ ውስጥ መስራቹ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የበጎ አድራጎት ክበባት ውስጥ ተሳትፎ ያደርግ በነበረበት ወቅት ያያቸው ሁኔታዎች ናቸው። ከዛም ውጪ በሚኖርበት አካባቢም በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያደርግ ነበር። በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የውሃ ምንጭ በመስራት፣ በፀረ ኤች አይ ቪ ክበባት ውስጥ እንዲሁም በቀይ መስቀል ክበባት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። በተጨማሪም አነስተኛ ድልድዮችን፣ መፀዳጃ ቤቶችንና አቅም የሌላቸውን አረጋውያን ቤት የማደስ ሥራ ያከናውን ነበር።
ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሚኖርበት አካባቢ ከሚገኙ ሰዎች ጋር በመሰባሰብ አቅም የሌላቸውን አረጋውያን የመደገፍ ሥራ ጀመረ። ይህን ሥራ ለማጠናከር መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት ወደ ሥራ ተገባ። በአሁኑ ወቅት 49 ቋሚ አባላት ያሉ ሲሆን ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እያከናወነም ይገኛል። ማህበሩ በዙ ሥራዎችን ካከናወነ በኋላ ህጋዊ ሰውነት እንዲገኝ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። ማህበሩ ሥራዎችን የሚያከናውነው ከአባላት ከሚያገኘው መዋጮ ሲሆን አቅም የሌላቸውን አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ለመደገፍ እየሠራ ይገኛል። በጎ ሥራ ማንኛውም ሰው ተባብሮ ሊሰራው የሚገባ ነገር ነው። የተሰሩ በጎ ሥራዎች ላይ ሌሎችም ሰዎች እንዲጨመሩ በመታሰቡ ማህበሩ አድማሱን አስፍቶ እንዲቋቋም ተደርጓል።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት 108 ለሚሆኑ ሕፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ነው። ወላጅ የሌላቸውንና ረዳት የሌላቸውን ልጆች በዓመት ሶስት ጊዜ አስፈላጊ እርዳታ እየተከናወነላቸው ነው። ሌላው ማህበሩ የሰራው የደም ልገሳ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ነው። ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ አስር ጊዜ የደም ልገሳዎች ተዘጋጅተዋል። ማህበሩ በሌሎች ሰብዓዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ ድንበር ሳይገድበው ድጋፍ የሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ላይ እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ ቀደም ብሎ አምባ ሁለት ይባል የነበረ ሲሆን ስሙን በመለወጥ የፊንጫ አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ አምባ መረዳጃና በጎ አድራጎት ማህበር በሚል ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲቋቋም ተደርጓል።
ድጋፍ ለሚፈልጉ አረጋውያንና ህፃናት አስፈላጊው የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ማህበሩ ለአረጋውያን የሚሆን ማእከል በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ ነው። ማህበሩ በአስር ሺህ ካሬ ሜትር ከከተማ ወጪ በሰራው ማእከል ለአረጋውያን ቤት ሰጥቶ እየተንከባከበ ይገኛል። ድጋፍ የሚደረገው በገጠርና በከተማ ለሚገኙ አረጋውያንና ህፃናት ነው። የኮሮና ወረርሽኝ ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች የምግብ ድጋፎች በስፋት ተደርገዋል። ሥራውን ለማከናወን በአካባቢው የሚገኙ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች በማስተባበር ሲሆን አባላቱ በወር የመቶ ብር መዋጮ በማድረግ ነው።
ሁሉንም ሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ በማድረግ ሌሎች ወጣቶች በበጎ ሥራ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እየታሰበ ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ትልቅ የአረጋውያን መርጃ ማእከል ለመክፈት ማህበሩ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ነው። ደጋፊና ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን በማሰባሰብ፣ በጎዳና የሚገኙ ልጆችን በመሰብሰብ እንዲሁም ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት ለመደገፍ ማህበሩ በቻለው አቅም እየሰራ ነው።
በማህበሩ 71 አረጋውያን ድጋፍ እያገኙ ሲሆን ለአረጋውያኑ በአልባሳትና በሌሎች መንገዶች ድጋፍ እየተደረገ ነው። በበዓላት ወቅት ደግሞ አብሮ የማሳለፍ ሥራ ይከናወናል። የሃይማኖት በዓላትን እንደየእምነታቸው እንዲያሳልፉ አስፈላጊው ነገር ይደረግላቸዋል። ለአረጋውያኑ በየሳምንቱ ሰውነታቸውን የማጠብ ሥራ የሚከናወን ሲሆን ሌሎችም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።
ሌላው ማህበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ወጣቱ በስፖርት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ነው። ቀደም ብሎ የተጀመሩ ሥራዎችን እንዲጠናቀቁ ለተተኪ ወጣት ማስተላለፍ ሥራ ማህበሩ እያከናወነ ነው። ወጣቱ ከአልባሌ ቦታ እራሱን እንዲያቅብና ሱስ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ለስፖርት ሥራ ትኩረት እየተሰጠው ነው። በሌላ በኩልም ወጣቱ የሚሳተፍባቸውን ሥራዎች ማህበሩ አቅዶ እየሰራ ነው። በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ማህበሩ ዘመናዊ የእጅ ማስታጠቢያዎችን በአሶሳ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ላይ አስቀምጧል። የእጅ ማስታጠቢያው ማህበሩ በራሱ ወጪ ያሰራው ሲሆን ውጤታማ ሥራ ተከናውኖበታል።
እነዚህ ሥራዎች ሲከናወኑ ሁሉም የማህበሩ አባላት ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት ለመርዳት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ቤት ለቤት በመሄድ በመለመንና ባለሀብቱን በመጠየቅ ነው። ህብረተሰቡ ለማህበሩ እያደረገ ያለው ድጋፍ መቀዛቀዝ እየታየባቸው ነው። የበጎ ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት ትኩረት ለማግኘት ከፍተኛ ሥራዎች መከናወን አለባቸው። በአካባቢው የሚገኙ ባለሀብቶች በቻሉት አቅም ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል። የማህበሩ አባላት በቻሉት አቅም እየተፍጨረጨሩ ናቸው።
በሌላ በኩል በከተማ ውስጥ ወላጅ የሌላቸው ህፃናት ስለሚገኙ እነሱን ለመርዳት፤ ወላጆቻቸው የሞቱ ልጆችን ለማሳደግ እንዲሁም ለሌሎች ሥራዎች የማህበሩ አባላት ግንባር ቀደም ሆነው እየሰሩ ናቸው። በጦርነትና በግጭት ምክንያት ቤተሰባቸውን ያጡ ልጆችን ለመደገፍ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ልጆቹም ወደ ቋሚ ተደጋፊነት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በቅርቡ በክልሉ በነበረው ጥቃት ቤተሰባቸውን ያጡ ልጆች ነበሩ። በወቅቱ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት ማህበሩ እየተንቀሳቀሰ ነው። በተጨማሪም ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች የተለያዩ ድጋፎች እየተሰባሰበላቸው ነው።
ደራሽ በሆኑ ችግሮች ለምሳሌ ደም በሚያስፈልግበት ጊዜ ማህበሩ የደም ልገሳ በማድረግ ተሳትፎ ያደርጋል። በበጎ ሥራ አላማውን ለማሳካት ማህበሩ ሲጥር ድጋፍ የሚያደርግ አመራር ያስፈልጋል። አመራሩ ክትትል እያደረገ ለውጥ እንዲመጣ እገዛ አያደርጉም። በትምህርት ቤቶች ውስጥ ወላጅ የሌላቸውንና አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ለዚህ ቁርጠኛ የሆነ አመራርና እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው።
የህብረተሰቡ አቀባበል
የማህበሩን ሥራ ህብረተሰቡ የተቀበለበት መንገድ ደስ በሚል ሁኔታ ነበር። የማህበሩ መስራች የአካባቢው ማህበረሰብ ተወላጅ ሲሆን ቀደም ብሎ ከክበባት ሥራ ጀምሮ ተሳትፎ ያደርግ ስለነበር ችግኝ በመትከል፣ አካባቢ በማፅዳት እንዲሁም የወጣት አደረጃጀቶች ላይ በመሳተፍ አካባቢውን ይደግፍ ነበር። ህብረተሰቡም በዚህ ማህበሩን እየደገፈ ይገኛል። ድጋፍ የሚደረግላቸው ወላጅ የሌላቸውና ችግረኛ አረጋውያን በመሆናቸው ህብረተሰቡ ማህበሩን እንዲደግፍ አስችሎታል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ያጋጠሙ ችግሮች ውስጥ የማህበሩን መልካም ሥራ ተመልክቶ የከተማው አመራር እውቅና አለመስጠቱ የሚጠቀስ ነው። ማህበሩ ለወጣቶች የተለያየ እውቅና እየሰጠ ቢሆንም ከአስተዳደሩ እያገኙ አይደለም። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የተመሰረቱ ማህበሮችን ወደ አንድ ቋት መግባት ይገባው ነበር። ማህበሩ ግን በራሱ መንቀሳቀሱን አላቋረጠም። አስተዳደሩ ትኩረት አለመስጠቱ የተሰሩ ሥራዎች እንዳይታወቁ አድርጓል። በተለይ ረዳት የሌላቸው ህፃናትና አረጋውያንን እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች ለማካሄድ የሞራል ድጋፍ ያስፈልጋል።
ድጋፍ የሚደረግላቸው ልጆች አስፈላጊ ነገር እየተደረገላቸው ቢሆንም በቂ ነው ማለት አይቻልም። ማህበሩን የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ብዙ ስለማያደርግለት ችግሮች ይስተዋላሉ። በማህበረሰቡ በኩል ግን ጥሩ ድጋፎች አሉ። በየትኛውም አካባቢ እንቅስቃሴ ሲደረግ ህብረተሰቡ ከማህበሩ ጎን ሆኖ ይሰራል። ነገር ግን ማህበሩ ብዙ ደረጃ መድረስ ሲገባው በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ስለተነፈገው ማሳካት አልቻለም። ሌላው ደግሞ ማህበሩ ወጪዎችን በአግባቡ እየመዘገበ የሚንቀሳቀስ ነው። ወርሃዊ ወጪዎች በአግባቡ እየተመዘገቡ የሚወጡ ሲሆን ገቢ ለማሰባሰብ ሁሉም በተሰጠው ኃላፊነት ሥራውን ያከናውናል። ግንባታ ለማከናወን ሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ የተዋቀረ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል እንቅስቃሴ አላደረገም። አብዛኛው አባል በራሱ ሥራ የተጠመደ በመሆኑ የታሰበውን ያህል መራመድ አልተቻለም።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ የመጀመሪያው የማህበሩን አላማና ሥራ ተረድተው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ግለሰቦችን ይዞ ወደ ሥራ መግባት ነው። ማህበሩ በሥሩ የሚገኘውን ቦታ ወደ ልማት በመመለስ ሀሳብ አለ። ማህበሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ልጆች ቁጥር ሲጨምር የሚማሩበት ትምህርት ቤት የመገንባት ሀሳብ አለው። በከተማው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት የለም። ለዚህም ማህበሩ በሚገነባው ትምህርት ቤት ውስጥ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መስጫ እንዲኖር ያደርጋል። ሌላው የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴው ድጋፍ ለማግኘት ሥራዎችን ጀምሯል። ለዚህ ደግሞ ማህበሩ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገበ መሆን አለበት በመባሉ በፌዴራል ደረጃ ለመመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው። እናቶች ላይና በጎዳና የሚገኙ ልጆችን የመደገፍ ሥራውን በማጠናከር የመስራት እቅድ አለ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013