ሀገራት አንድ ሰው ማድረግ ያለበት ነገርና ማድረግ የሌለበት ነገር ምን እንደሆኑ በየሀገራቱ ህጎች ሰፍረው ይገኛሉ። በሀገራችን ኢትዮጵያም ዜጎች በህገ-መንግስቱም ሆነ በሌሎች ህጎች የተሰጣቸውን መብቶች ሲጠቀሙ በምን አግባብ እንደሆነ ዝርዝር ህጎች ተቀምጠው ይገኛሉ። ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያዊያን ዳብሮ እስካሁን ድረስ በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ የሞራል ልእልና ሲሆን ይህ ሞራል ወይም ስነምግባር በማህበረሰቡ ዘንድ ሊዳብር የቻለው ከሀይማኖትና ከባህል እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ማህበረሰቡ ለሃይማኖቱና ለባህሉ ተገዢ በመሆኑ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት ወይም ከስነምግባር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሲከሰቱ ህብረተሰቡ በስፋት ሲያወግዛቸው ይስተዋላል። ከዚህ በመነሳትም በኢትዮጵያ በወጡ የተለያዩ ህጎች በተለይም በወንጀል ህጉ ላይ ከስነምግባር ያፈነገጡ ተግባራት ሲከሰቱ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ ተደንግጎ ይገኛል። ስለሆነም በዚህ አጭር ጽሁፍ በወንጀል ህጉ ላይ የተቀመጡትን በመልካም ጠባይ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና ተያያዥነት ያላቸውን ከስነምግባር ያፈነገጡ ተግባራትን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ ዋና አላማው የህዝቦችን፣ የነዋሪዎችን፣ ሰላም፣ደህንነት፣ ስርአት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ሲሆን፤ ግቡም ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ነው። ይህ የሚሆነውም ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስንጠቀቂያ በመስጠት ወይም ማህበረሰቡን በማስተማር ነው። ማስጠንቀቂያው በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎች ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ ማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ማድረግ ነው።
ከዚህ አንጻር በወንጀል ህጉ አንቀጽ 639 ላይ እንደተደነገገው ሰው አስቦ ህዝብ በሚበዛበት ቦታ ወይም በህዝብ ፊት የግብረ ስጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ስነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ ጸያፍ ድርጊት የፈጸመ ወይም በአኳኋን ያሳየ አንደሆነ፤ ከሶስት ወር እስከ አንድ አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ተቀምጧል።
ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት አካለመጠን ባልደረሱ ልጆች ፊት ተፈጽሞ ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ማንም ሰው በአደባባይ ወይም በህዝብ ፊት ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ ተግባራትን መፈጸም ከሞራል ወይም ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ሲሆን፤ ይህ ድርጊት ፍጹም ከኢትዮጵያውያን ባህል ውጭ በመሆኑ በወንጀል እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።
እንዲሁም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 640 ስር ጸያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለህዝብ መግለጽ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን፤ ማንም ሰው ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ በጽሁፍ፣ ምስሎችን፣ ስዕላዊ መግለጫዎችን /ፖስተሮችን/፣ ፊልሞችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ያዘጋጀ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ ሀገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ የተቀበለ፣ የያዘ፣ ለህዝብ ያሳየ፣ ለሽያጭ ወይም ለኪራይ ያቀረበ፣ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከቦታ ቦታ ያዘዋወረ ወይም እነዚህን ነገሮች የነገደ እንደሆነ ነገሮቹ ተወርሰው ከመወገዳቸው በተጨማሪ ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራትና መቀጮ ይቀጣል።
ከዚህ አኳያ አሁን በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚስተዋለው በተለምዶ ሹገር ማሚ እና ሹገር ዳዲ እናገናኛለን እያሉ የሚያስተዋውቁ ግለሰቦች በርከት ያሉ ሲሆን፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ ደግሞ የሴት ተማሪዎችን ፎቶ ግራፍ በማሳየት ከወንዶች ጋር በተለይም ሹገር ዳዲ እየተባሉ ለሚጠሩ ግለሰቦች የሚያቀርቡ ሰዎች በስፋት ይታያሉ። አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ይህ ተግባር ፍጹም ከስነምግባር ያፈነገጠ መሆኑን ቢረዳም የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አብዛኛው ማህበረሰብ አያውቅም። ስለሆነም ህብረተሰቡ ይህን በመገንዘብ የዚህ አይነት ተግባር ሲፈጸም ባየና ባወቀ ሰአት ለፍትህ አካል ጥቆማ በማድረግ የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።
በሌላ በኩል በወንጀል ህግ አንቀጽ 641 ስር ማንም ሰው ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን በትያትር፣ በሲኒማ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልሞች፣ በሬዲዮ፣ በቪዲዮ፣ በቴሌቪዥን ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ እንዲተላለፍ ያደራገ፣ ለህዝብ ያሰማ ወይም እንዲታይ ያደረገ እንደሆነ በእስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል። አሁን ባለው ሁኔታ በተለይም በሶሻል ሚዲያ ኢትዮጵያዊያንን የማይወክል ከስነ ምግባር ያፈነገጡ ፍጹም ለሞራል ተቃራኒ የሆኑ ምስሎች ሲሰራጩ ይስተዋላል። በተለይ በየመንደሩ የሚገኙ አነስተኛ የፊልም ማከራያ ሱቆች የወሲብ ፊልሞችን በማከራየትና በመሸጥ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ወጣቱንም ላልተገባ ድርጊት የሚገፋፉ በመሆናቸው ህብረተሰቡ እነዚህን ሰዎች ለፍትህ አካል በማጋለጥ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ አለበት።
ከላይ የተመለከትናቸው የተከለከሉ ተግባራት እንዳሉ ሆነው በወንጀል ህጉ የደንብ መተላለፍ ክፍል ላይ ከአንቀጽ 845-847 ድረስ ባሉ ድንጋጌዎች፤ ማንም ሰው በአደባባይ ወይም ህዝብ በሚያየው ቦታ መልካም ስነምግባርን ወይም መልካም ጠባይን የሚነካ ድርጊት አስቦ የፈጸመ እንደሆነ፤ መልካም ስነ-ምግባርን ወይም መልካም ጠባይን በሚቃረን መንገድ ያልፈለገውን ሰው በድሪያ መልክ ያበሳጨው እንደሆነ፤ ተገቢ ባልሆነ ጥያቄ ሌላው ሰው ለስነ-ምግባር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ወይም በህብረተሰቡ የተወገዙ ማናቸውንም አይነት የብልሹነት ድርጊት እንዲፈጽም የገፋፋ፤ በዝሙት ወይም በህብረተሰቡ የተወገዙ ይህን መሰል ድርጊቶች በመሰማራት የጎረቤቶቹን ወይም የአካባቢውን ነዋሪዎች ያወከ እንደሆነ በመቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።
ከላይ በተመለከትናቸው አንቀጾች ለስነ-ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት ምን እንደሆኑ የተዘረዘሩ ሲሆን፤ በአንቀጽ 847 ስር በተለይም በሶሻል ሚዲያ ላይ ሹገር ማሚ እና ሹገር ዳዲ እናገናኛለን በማለት የሚያስተዋውቁ፤ እንዲሁም የሴቶችን ፎቶ ለወንዶች በማሳየት ለወሲብ የሚያደራድሩ ግለሰቦች በደንብ መተላለፍ የሚጠየቁ መሆኑን አስቀምጧል። የዚህን አንቀጽ ድንጋጌን ስንመለከት ማንም ሰው የብልግና ተግባርን ለማበረታታት ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ስጋ ለማርካት ሲል ዝሙት የፈለገ ሰው በእንደዚህ አይነት ቦታ ራሱን ሊያስደስት ይችላል ብሎ በማናቸውም ዘዴ በይፋ ያስታወቀ እንደሆነ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል በሚል ተቀምጧል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ የዳበረ ስነምግባርና ጥሩ የሆነ ስብዕና ያለው ስለሆነ፤ አሁን አሁን ግን በሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የግሎባላይዜሽን ጫና ምክንያት ጥቂት የማይባለውን የማህበረሰብ ክፍል ከስነ-ምግባር እንዲያፈነግጥ አድርጎታል። ነገር ግን ከማህበረሰቡ እሳቤ ወጣ ያሉ ወይም ከላይ የጠቀስናቸው ተግባራት በወንጀል የሚያስቀጡ እንደሆነ አብዛኛው ማህበረሰብ ግንዛቤ የለውም። ስለሆነም ከስብዕናና ስነ ምግባር ያፈነገጡ ተግባራት በወንጀል የሚያስቀጡ መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህን ተግባራት የሚፈጽሙ አካላትን በመጠቆም ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል።
ምንጭ:- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013