በዘንድሮው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብና እንደ እንቁ አትሌቶቿ የተበደለ የለም።በራሳቸው ጥረት ነጭ ላብ አውጥተው ሜዳሊያ ያስመዘገቡት አትሌቶች የሚያፅናና ተጋድሎ ሳይዘነጋ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የፈሰሰበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጉዞ በብዙ መልኩ ቢሰላ ኪሳራው እንጂ ትርፉ አይታይም፡፡
የወጣው ከፍተኛ በጀት ይቅር።በግል ጥቅምና በአመራሩ ቡድንተኝነት የተነሳ ትልቅ በደል የተፈፀመባቸውና የምሬት እንባ ያነቡትን እንቁ አትሌቶች የፈሰሰ እንባ በየትኛው ዋጋ ማበስ ይቻላል?።ለበርካታ ወራት ብዙ ወጪ ወጥቶባቸውና ላባቸውን አፍስሰው ሲዘጋጁ የነበሩ አትሌቶችና የተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች ቤተሰብ ተሰናብተው በመጨረሻ ሰዓት ወደ ቶኪዮ ሊያቀኑ ካኮበኮቡበት አየር መንገድ በማያውቁት ምክንያት ጓዛቸውን ይዘው እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ኢትዮጵያውያን ከአገር እስከ ግለሰብ በዚህ ኦሊምፒክ የደረሰባቸውን ትልቅ በደል አንድ በአንድ መዘርዘር ሃጢያት ማብዛት ነውና የኦሊምፒኩ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት በእንቁ አትሌቶቻችን እንዲሁም በአገር ላይ የፈፀሙትን ታሪክ ይቅር የማይላቸውን ጥቂት በደሎች ብቻ መመልከት መጠየቅ ያለባቸውን ግለሰቦች ለመጠየቅም ስህተቶቹም ሌላ ጊዜ እንዳይደገሙ ይረዳል የሚል እምነት አለን።የቡድኑ ውጤት ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድር የነበረው ዝምታም መሰበር ግድ ይለዋል።
ቀነኒሳ በቀለና የማራቶን ውጤት
በማራቶን የዓለማችንን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት የያዘው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከዚህ ቀደም ባልነበረ የማራቶን ማጣሪያ ውድድር እንዲሳተፍ ተጠይቆ አሻፈረኝ በማለቱ ከቶኪዮ ቀርቷል።የቀነኒሳ መቅረት እሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም እንደ ጎዳ ከውድድሩ ውጤት የበለጠ ማስረጃ የለም።ይህ በተፎካካሪዎቹ ዘንድ የታፈረና የተፈራ ጀግና አትሌት ‹‹በጥሩ አቋም ላይ ነኝ፣ ለአገሬ ወርቅ እንደማመጣ እርግጠኛ ነኝ ልወዳደር›› ብሎ በግልፅ ከልመና ባልተናነሰ መልኩ ጠየቀ፣ ሰሚ አላገኘም።
ኦሊምፒክ ኮሚቴም ቀነኒሳን ወደ ቶኪዮ ይዞ እንደሚጓዝ ፎክሮ ቃሉን አልጠበቀም። ቀነኒሳን ለኦሊምፒክ ያልመረጠው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመርህ ላይ ተመስርቶ ነው።ያም ሆኖ ቀነኒሳ ተወዳድሮ ውጤት ባያመጣ እንኳን መኖሩ በራሱ ለበርካቶቹ አትሌቶች ትልቅ የስነ ልቦና ስንቅ ነውና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ወደ ቶኪዮ ይዞት ለመጓዝ ስልጣኑ ነበረው፣ አልተጠቀመበትም እንጂ።ለምን?
ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከፈለገ በመርህ ይመራል፣ ካልተመቸውም መርሆችን ይጥሳል።ይህ ማለት በአጭሩ ተቋሙ በግለሰቦች ስሜትና ይሁንታ እንጂ በህግና በመርህ አይመራም ማለት ነው።ይህ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በጀግናው አትሌት ላይ በመፈፀሙ ብቻ ሳይሆን በኦሊምፒኩ ላይ በተወዳደሩት አትሌቶች ላይ መከፋፈል ፈጥሮ አቅሙና ብቃቱ እያላቸው ውድድር እስከ ማቋረጥ እንደ ደረሱ ለመታዘብ ተችሏል።
ሙቀት፣ የአየር ሁኔታ፣ ወዘተ የሚሉትን ምክንያቶች እንዝለላቸው፡፡የአየር ንብረቱ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ የሚከብድበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም።ይህ ምክንያት ትክክል ነው ብሎ ማሰብ ቢቻል እንኳን የሚዋጥ አይደለም።የስፖርት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ልምምዳቸውን በከፍታማ ቦታ (በሀይ አልቲቲዩድ) የሚሰሩ አትሌቶች ብዙ ቀይ የደም ሴሎችን እንደሚያገኙ ሳይንሱ ያስረዳል።ይህም ደማቸው የበለጠ ኦክስጅንን እንዲሸከም ያስችለዋል። ዝቅተኛ ቦታ (በሎው አልቲቲዩድ) ሲወዳደሩም ተጨማሪ ኦክስጅን መኖሩ ለጡንቻዎቻቸው ተጨማሪ ተፈጥሯዊ ኃይልን ይሰጣቸዋል።
ውድድሩ ትንሽ ቀን ሲቀረው የሚሄዱበት ምክንያትም ይሄ ነው። ለአየር ሁኔታው የሚሆን ልምምድ ማድረጉ ላይ አተኩሮ ካልተሰራ ግን ዘግይቶ መሄዱ ብቻውን ውጤታማ ሊያደርግ አይችልም።በዚህ መሰረት ዝግጅት ባለመደረጉ በኦሊምፒኩ ከተጓዙት የማራቶን አትሌቶች ውስጥ አብዛኞቹ ውድድራቸውን እንደማይጨርሱ ጥርጣሬ እንደነበር ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች ቀደም ብለው ሲናገሩ ነበር።ይህ ማለት ወደ አማራጭ ለመሄድ፣ አሊያም እርምት ለመውሰድ ከተቻለ የተፈጠረውን የውጤት ቀውስ ማረም የሚቻልበት ትንፋሽና እድል ነበረ ማለት ነው።
ለአገር ውጤት ባለመጨነቅና በግል ስሜት በመመራት ግን ጉዳት ላይ ያሉ አትሌቶች ወደ ቶኪዮ የሄዱበት ዋነኛው ምክንያት በቀጣዮቹ ዓመታት ውድድር ላይ የሚሳተፉበትን ስም መገንባት ብቻ እንጂ ለውጤት እንዳልነበረ አመራሮቹ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡
የ5ሺ ሜትር አትሌቶች ኪሳራ
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ከኦሊምፒክ ሜዳሊያ አጥታበት በማታውቀው የ5ሺ ሜትር ወንዶች ውድድር አትሌቶቻችን ማጣሪያውን እንኳን ለማለፍ ሲቸገሩ ማየት ያማል። ወጣቱ አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ ብቻ ማጣሪያውን በ6ኛነት አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ፍፃሜውን ግን 10ኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው።
በማጣሪያው ውድድሮች የተሳተፉት ሌሎቹ አትሌቶች ጌትነት ዋለና ንብረት መላክ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባልተለመደ መልኩ 9ኛና 14ኛ ሆነው በማጠናቀቅ ወደ ፍፃሜ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህ ውጤት የተመዘገበው በአትሌቶቹ ድክመት ሳይሆን በግለሰቦች ስሜታዊ ውሳኔ በመሆኑ ኦሊምፒኩ ካለቀም በኋላ መጠየቅ ያለባቸው ሰዎች መጠየቅ አለባቸው።
ኢትዮጵያ በዚህ ርቀት በትልቁ ወርቅ ባይሳካ ብር ካልሆነም በትንሹ የነሐስ ሜዳሊያ የማስመዝገብ አቅሙ ያላቸው በርካታ አትሌቶች እንዳላት ለማንም ግልፅ ነው።ያምሆኖ ግለሰቦች አንዱ ባንዱ ላይ ነጥብ ለማስቆጠር በርቀቱ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የተደረጉ አትሌቶች ራሳቸውን እንዲያባክኑና ኢትዮጵያም ሜዳሊያ እንድታጣ አድርጓል።
ስህተቱ የ5ሺ ሜትር ማጣሪያ ውድድርን የ3ሺ ሜትር መሰናክል ማጣሪያና ፍፃሜ ውድድር ያደረገውን አትሌት ጌትነት ዋለን ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲወዳደር ከማድረግ ይጀምራል። አትሌት ጌትነት በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት ባላሳየበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል ያውም የተመረጡ አትሌቶች ከቦሌ አየር መንገድ እንዲቀሩ ተደርገው ጌትነት ባልተዘጋጀበት ርቀት እንዲወዳደር ተደርጓል።ይህም በርቀቱ የተዘጋጁትን አትሌቶች ተስፋ ያጨለመና ሞራላቸውን የከሰከሰ ይቅር የማይባል ስህተት ነው። ይህ ስህተት አትሌቱ ድንቅ ብቃት አሳይቶ ሲዘጋጅበት የቆየውን የ5ሺ ሜትር ተስፋም ገደል ከትቷል። ምናልባትም ጌትነት በተዘጋጀበት 5ሺ ሜትር ብቻ ቢሮጥ ወርቁ ቢቀር ብርና ነሐስ ማጥለቅ የሚችል አቅም እንዳለው ማንም መመስከር ይችላል።
የግለሰቦች ስሜትና የእልህ ውሳኔ ግን አትሌቱንም አገርንም በትልቁ በድሏል። ከጌትነት ይልቅ በርቀቱ ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘውና 10ሺ ሜትርን አሸንፎ አራት ቀናትን በቂ እረፍት ያደረገው ሰለሞን ባረጋ እንዲወዳደር አለመደረጉ በርካቶችን ያንገበገበ ስህተት ነው። ሰለሞን በ10 ሺ ሜትር ያሸነፋቸው በርካቶቹ አትሌቶች በ5ሺው ማጣሪያ አልፈው የሜዳሊያ ተፎካካሪ ሲሆኑ ሰለሞን አስደናቂ ብቃት ይዞ የምሩፅ ይፍጠርና የቀነኒሳ በቀለን ታሪክ እንዳይደግም ተፈርዶበታል፡፡
የርቀቱን ወርቅ ያጠለቀው ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጌም እነሰለሞን ቢኖሩ ወርቁን ላያገኝ እንደሚችል ከውድድሩ በኋላ ተናግሯል።ወደ ቶኪዮ ያቀናው የልዑካን ቡድን አመራርም በዚህ ይቅር የማይባል ስህተት የኢትዮጵያን ወርቅ ለዩጋንዳ አጥልቋል።
በሄንግሎ የኢትዮጵያውያን ማጣሪያ ውድድር አምስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ተጠባባቂ ተደርጎ የተያዘው አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ቶኪዮ ቢገኝም የመወዳደር እድል አላገኘም። ሙክታር ማጣሪያው ላይ ቀዳሚ ሆኖ ባይመረጥም ታላላቅ ውድድሮች ላይ በመጨረሻ ሰዓት መጥቶ የማሸነፍ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ ያሳየ አትሌት ነው። ለዚህም ባለፈው የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና ዓመቱን ሙሉ በሌሎች ውድድሮች ላይ ሳይታይ ከነ ጉዳቱ መጨረሻ ላይ ብቅ ብሎ ማሸነፉን መጥቀስ በቂ ነው።
ጉዳዩ የመርህ ከሆነ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ለሜቻ ግርማ ለትልቅ ውጤት የበቃው በርቀቱ ቀደም ሲል የተመረጡ አትሌቶች ቀርተው መጨረሻ ሰዓት ላይ በመወዳደሩ ነው። ይህ ለሜቻ ላይ የሰራው ውሳኔ ለምን ለሰለሞንና ሙክታር እንዲሁም ቀነኒሳ ላይ አልሰራም? የበርካቶች ጥያቄ ቢሆንም ከህግና ስርዓት ውጪ ግለሰቦች የገዛ ስሜትና ጥቅማቸውን ስላስቀደሙ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
ወርቅውሃ ላይ የተፈፀመው ክህደት
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር ማጣሪያ ለመወዳደር ተዘጋጅታ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው ድንገት መታገዷ በወቅቱ መነጋገሪያ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። ውድድሩን ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማከናወን ከስፍራው የተገኘችው ወርቅውሃ እንደማትወዳደር ሲገለጽላት በተፈጠረው ድንገተኛ ነገር ስሜቷ መነካቱ ተገልጿል።
በተለይ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል መረጃ የማድረስ ክፍተቶች መኖራቸው የችግሩ መንስዔ እንደሆነ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ችግሩ የተፈጠረው ከዚሁ ከአዲስ አበባ የአትሌቷን ሚስጢር የሚያጋልጥ መረጃ በመውጣቱና ክህደት ስለተፈፀመባት መሆኑን ሲገልፁ መሰማቱን መረጃዎች ጠቁመዋል።
አትሌቷም በተፈፀመባት ክህደት ክስ መስርታ ጉዳዩን ወደ ህግ እንደምትወስደው በተሰበረ ድምፅ ስታስረዳ ተሰምቷል። የመከላከያ ስፖርት ክለብ አትሌት የሆነችው ወርቅውሃ፣ በአዲስ አበባ በተከናወነው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይ ተሳትፋ በበላይነት ማጠናቀቋን ተከትሎ፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ መመረጧ ይታወሳል።ሆኖም ቶኪዮ ከደረሰች በኋላ የቴስቶስትሮን መጠኗ የውድድሩ ህግ ከሚፈቅደው በላይ በመሆኑ፣ መወዳደር እንደማትችል የዓለም አትሌቲክስ መወሰኑ ተገልጿል።
ከስምንት ወራት በላይ በቆየው የኦሊምፒክ ዝግጅት ከስድስት ጊዜ በላይ የተለያዩ ምርመራዎችና ክትትል የተደረገላቸው አትሌቶቹ፣ ውጤታቸው ለዓለም አትሌቲክስ ሪፖርት ሲደረግ እንደቆየ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አትሌቷ ወደ ቶኪዮ ከማምራቷ ቀደም ብሎ ስለ ጉዳዩ ለማማከር ሲሞከር አትሌቷን ማግኘት ስለአለመቻሉ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ ሲሰጥ ነበር።
አትሌቷም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል በነበረው እሰጣ አገባ ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ወደ ስፍራው ማቅናቷን መግለፅም የንቀት መልስ ይመስላል። ሆኖም በአትሌቷ ተፈጠረ በተባለው እክል ምክንያት ከውድድር ወጪ ብትሆንም በቶኪዮ ያለው የልዑካን ቡድን ጉዳዩ በአግባቡና የሥነ ልቦና ጉዳት በማያደርስ መልኩ ለአትሌቷ አለማሳወቁ የበለጠ የአትሌቷን ሞራል እንደከሰከሰው በግልፅ ታይቷል።
የውሃ ዋና አትሌቶች እንባ
ገና ከጅምሩ በርካታ ውዝግቦችን ያስነሳው የውሃ ዋና ተወዳዳሪዎች ምርጫ ጉዳይ አንዱን አስደስቶ አንዱን ያስነባ ነበር። ይህ መዘዝ ቶኪዮም ድረስ ዘልቋል። የውሃ ዋና ተወዳዳሪዋ ሊና አለማየሁ ቶኪዮ ደርሳ ሌሎቹ ስፖርተኞች ኦሊምፒክ መንደር ሲገቡ እሷና የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኟ ምህረት ከድር መግባት አልቻሉም ፤ ሆቴል አረፉ፤ ሊና የያዘችው ገንዘብ አሰልጣኟ ጋር ስለነበረና ኦሊምፒክ መንደር ውስጥ ስለሆነ ሆቴል አብረዋት ከነበሩ የቡድን አባላት ጋር ተካፍላ እየተመገበች ለሁለት ቀናት አሳለፈች፤ ጥያቄ ሲበዛ የመክፈቻው እለት ወደ ኦሊምፒክ መንደሩ ገባች። ሆኖም አትወዳደርም፤ ስሟ አልተላለፈም፤ ለምን እንደሄደችም አይታወቅም። የ20 ዓመቷ ወጣት ሊና ያለምንም ፋይዳ ቶኪዮ ተቀመጠች፣ አገሯን በታላቁ መድረክ የመወከል ህልሟም መከነ።
በውሃ ዋና ስፖርት ራሄል ፍስሀ ተስፋ የተጣለባት የ25 ዓመት አትሌት ናት። በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ50 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ተሳትፋ በመጀመሪያው ዙር 4ኛ ሆና በማጠናቀቅ ተስፋ የተጣለባት ነበረች። እድሜና ልምድ ያበሰላት ራሄል ከአምስት ዓመት በኋላም በቶኪዮ የምትጠበቅ ለዚህም ዝግጅት ስታደርግ የቆየች ዓለም አቀፉ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንም ለተሳትፎዋ እውቅና የሰጣት ስፖርተኛ ሆነች፤ ቶኪዮ ግን እንድትሄድ አልተደረገም። በዚህ የተነሳም ውስጧ ቆስሎ እንባዋ ፈሶ ቤቷ ለመቆየት ተገደደች።
ራሄል ለምን ቀረች? ሊናስ ከሄደች በኋላ ለምን አትወዳደርም? የተፈጠረው ምንድነው? የሚመለከታቸው ሁሉ ይጠየቁበት። የሆነው ሆኖ ግን በአመራሩ መካከል በተሰራው ሴራው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ራሄል ፍስሀን በሊና አለማየሁ በመተካት ሊናን ይዞ የሄደው ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቷንም የአገርንም ሃብት ካለምንም ምክንያት በከንቱ አባክኗል። የቀረችው ራሄልም በከፍተኛ ኀዘን ተጎዳች፤ ሊና ብትሄድም ስሟ ስላልተላለፈ አትወዳደርም ተባለ ይህም የሴቶቹን የውሃ ዋና እድል ባክኖ የቀረ ሌላ ድራማ ሆነ።
በመጨረሻም
የኦሊምፒክም ይሁኑ የአትሌቲክስ የሥራ ኃላፊዎች እልህ መወጣጫ ባደረጉት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያና አትሌቶቿ አልተጠቀሙም። የጠፋው ይጥፋና የወደፊቱ አሳሳቢ ጉዳይ ነገም ይህን ሁሉ በደል በአትሌቶችና በአገር ላይ የፈፀሙ ግለሰቦች ስፖርቱን እንዲመሩ መፍቀድ የበለጠ ያቆስላል። ከዚህም በላይ አሁን የተፈፀሙ በደሎች በነገው የአገሪቱ ስፖርት ላይ ያላቸው ተፅእኖ የበለጠ ኪሳራ እንደሚያስከትል ማሰቡ ተገቢ ነው።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌላ አገር በመሮጥ በርካታ ሜዳሊያዎችን የሰበሰቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከ35 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዜግነታቸውን በመቀየር ለ14 የተለያዩ አገራት እየሮጡ ናቸው። 7 ለባህሬን ፤ 7 ለእስራኤል ፤ 5 ለቱርክ ፤ 3 ለኳታር ፤ 2 ለታላቋ ብሪታኒያ ፤ 2 ለዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፤ 2 ለሆላንድ ፤ ለአሜሪካ ፤ ለቤልጅየም፤ ለጀርመን ፤ ለስፔን ፤ ለስዊድን፤ ለአውስትራሊያ ይሮጣሉ።
የትውልድ ዜግነትን በመቀየር ለሌላ አገር የመወዳደር ሁኔታ በዓለም ስፖርት አመኔታ አግኝቶ እየተስፋፋ መጥቷል።የኦሊምፒክ መድረክ ኦሊምፒያኖች ለሚወክሏቸው አገሮች ብሔራዊ ኩራትን የሚያመጡበት ቢሆንም፣ ለአንዳንዶች የውድድር ዕድል ብቻ ሆኖ መታየት ጀምሯል። ኦሊምፒያኖች ዜግነት እንዲቀይሩ ወይም እንደ ግለሰብ እንዲወዳደሩ የሚያስችሉ ሕጎች በመኖራቸው ነው።በአገሮቻቸው ስም ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ካሉ ኦሊምፒያኖች ጋር እንዲወዳደሩ ሕጉ ያበረታታል። አትሌቶች የትኛውን አገር መወከል እንደሚፈልጉ እንዲመርጡ ያስችላቸዋል።
ወደ ሌላ አገር ዜግነት ከመቀየራቸው በፊት ቢያንስ ለሦስት ዓመታት እንዲጠብቁ ቢያስገድድም ሁለቱም አገሮች ከተስማሙ በሚለው ምርጫው እየቀለለ ሄዷል።ዛሬ በአስተዳደራዊ በደሎች የተገፉ በርካታ አትሌቶቻችን ነገ በዚህ እድል ተጠቅመው ለሌላ አገር እየሮጡ ሜዳሊያ ሲያጠልቁ እያየን ከመንገብገብ በግለሰቦች ስሜት የሚመራውን ስፖርት መልክ ማስያዝ አንገብጋቢ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013