የሰሞኑን የህወሓትን እብሪት ተከትሎ በርካታ የህዝብ ድምጾች ከዛም ከዚህም እየተሰሙ ነው። አሸባሪውን የህወሓትን ቡድን በመቃወም ከመከላከያ ጎን እንቆማለን የሚሉ የሀገር ተቆርቋሪ ድምጾች በመላው የሀገሪቱ ክፍል እያስተጋቡ ይገኛል። ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደሙ፣ እኛነትን የተላበሱ ፍትህ ናፋቂ የህዝብ ድምጾች በሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ህወሓትን በመኮነን ጀግናው መከላከያ ሰራዊትን በማወደስ ስለ እውነት እየጮሁ ነው።
ህዝብ በአንድነት ከተነሳ፣ እውነት ፈላጊ ነፍሶች አንድ ላይ ከቆሙ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት። በታሪክ እንደሰማነው የእስካሁኑ የኢትዮጵያ ከፍታ በአንድነት በቆሙ ህዝቦች የተገኘ ነው። በአሸናፊነት የተጠናቀቀው የትላንቱ ታሪካችን ሁሉ በህዝብ አንድነት የተገኘ፣ የህዝብ አንድነት የወለደው የአብሮነት ውጤት ነው። ዛሬም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመጣል ህዝብ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ እየተመመ ነው። እውነት ናፋቂ፣ ፍትህን ፈላጊ የህዝብ ድምጾች እየተሰሙ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ ተነስቶ፣ ህዝብ በአንድነት ቆሞ ውጤት ያላመጣበት ታሪክ የለም። በዓድዋ እንዳየነው፣ በአንባላጌ እንደሰማነው፣ በካራማራና በኡጋዴን እንደምናውቀው አብዛኛው ታሪኮቻችን ህዝብ ወለድ ናቸው።
ዛሬም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በጋራ በመቆም ሀገር ለማፍረስ፣ ታሪክ ለማበላሸት ታጥቆ የተነሳውን የህወሓት አሸባሪ ታግሎ ለመጣል ስለ ሀገርና ህዝብ ሲሉ ክተት አውጀዋል። ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን ክፍል አሸባሪውን ህወሓት በመቃወም ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን ለመሆንና በግንባርም ተገኝቶ ለመፋለም ቁርጠኝነታቸውንም ያሳዩና በተግባራም ያረጋገጡ እልፍ አዕላፍ ናቸው። ስለ ሰው ልጅ የሚጨነቁ፣ ሰላም የተራቡ ነፍሶች የህወሓትን የጭካኔ አካሄድ በማውገዝ መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ አደባባይ የወጡ በርካታ የህዝብ ድምጾች ከሰሞኑ ተሰምተዋል። ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚጮሁ አንደበቶች፣ ኢትዮጵያን አትንኩ የሚሉ ድምጾች፣ ኢትዮጵያን ለጠላቶቻችን አሳልፈን አንሰጥም የሚሉ የጀግንነት መፈክሮች ከረጃጅሙ ሰልፍ መሀል በጉልህ ተሰምተዋል። መከላከያን ለመደገፍ በወጡ እዛም እዚህም ባሉ ኢትዮጵያውያን ነፍስ ላይ ሰውነትን የተላበሱ፣ ሰላም ናፋቂ አንደበቶችን ግዝፍ ነስተዋል። ከነዚህ ሀገራዊ ድምጾች መካከል እጅግ ያስደነቁኝና ኢትዮጵያዊነትን የሚጭሩ ጠንካራ የአንድነት መንፈስ የሚያላብሱ መፈክሮችን ያየሁ በመሆኑ እዚህ ላይ መዘርዘር ተገቢ መስሎ ስለታየኝ እንደሚከተለው አስነብባችኋለሁ። አሸባሪውን ህወሓት በመቃወምና መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ በመላ ሀገሪቱ ከተሰሙ ህዝባዊ ድምጾች መካከል የተወሰኑትን እነሆ አልኩኝ..
በእጃቸው መፈክር ይዘው ስለ ኢትዮጵያዊነት ከሚጮሁት ድምጾች መካከል ‹የኢትዮጵያ ተስፋ በአሸባሪው ህወሓት የተንኮል ሴራ አይደናቀፍም የሚል እልህ የነቀነቀው የአንድነት ድምጽ ተሰማኝ። ከድምጹ መሀል በቀይ የተጻፈ ‹ኢትዮጵያ አትፈርስም ጠላቶቿ ግን ይፈርሳሉ› የሚል ጽሁፍ አነበብኩ። ይሄን ጽሁፍ ልብ ብለን ብናየው ትልቅ መልዕክትን የያዘ ነው። በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ሀገር ለማፍረስ ባህር ተሻግረው መጥተው ፈርሰው የተመለሱ በርካታ ሀገራትን እናውቃለን። በወቅቱ በጦር ሰራዊቷ ብዛት ከዓለም ቀዳሚ የሆነችውን ጣሊያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት ኢትዮጵያን ነክተው ጉድ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ህዝቦቿን ለመለያየት ጉድጓድ ሲምሱ የነበሩ ሁሉ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ራሳቸው ገብተው የጠፉበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ።
የህወሓት የተንኮል ሴራም ከዚህ የዘለለ አይደለም። ህዝብ እያስጨነቀ፣ ከድሀ ሀገር ላይ እየዘረፈ በግፍ ያገኘውን ስልጣንና ጥሪት መቀበሪያው ካልሆነ በስተቀር እንደማይበላው የታወቀ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ነክቶ ሰላም ያገኘ ሀገርና ጠላት የለምና ነው። የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ምስጢር የህዝቦች አንድነት ነው። በብዙ ነገር ላይ ተለያይተን ይሆናል በሀገር ጉዳይ ላይ ግን ሁሌም አንድ ነን። በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ልዩነት የለንም። ለዚህም ነው ሁሌም ሊለያዩንና ሊበታትኑን በሚፈልጉ ጠላቶቻችን ላይ የበላይ ሆነን የምንገኘው። ለዚህም ነው ጠፉ ባሉን ሰዓት የምንበዛው፣ አለቀላቸው ባሉን ጊዜ ተስፋ የምንሰንቀው። ለዚህም ነው ጠላቶቻችን እያፈሩ እኛ በክብር ማማ ላይ የምንታየው።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ሌላው ትልቁና ሊሰመርበት የሚገባው የጋራ እውነታችን ኢትዮጵያውያን ሌላውን መበደል የማንወድ መሆናችን ነው። ኢትዮጵያውያን ሌሎችን ማስጨነቅ፣ ሌሎችን ማስገደድ፣ ሌላውን ጎድቶ ራስን መጥቀም የማንወድ ህዝቦች ነን። ሁሌም ቢሆን በእውነት ጎዳና ላይ የቆምን ፈርሀ እግዚአብሄር የለን ህዝቦች ነን። አላማችን እውነት ስለሆነ ሁሌም አሸናፊዎች ነን። ብዙዎቹ ጠላቶቻችን በለኮሱት እሳት ራሳቸው የሚቃጠሉ ናቸው። ከትላንት እስከዛሬ ኢትዮጵያን ነክተው በሰላም የተኙ ሀገራት የሉም። በለኮሱት እሳት ሲቃጠሉ አይተናል። እያየንም ነው። በቆፈሩት ጉድጓድ ሲቀበሩ ታዝበናል። ሊያሳፍሩን ተነስተው አፍረው የተመለሱ፣ አፍረው አንገታቸውን ያቀረቀሩ ብዙ ናቸው።
የህወሓት መጨረሻም ከዚህ የዘለለ አይደለም። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተነስቷልና ግብዓተ መሬቱ የሚፈጸምበት ቀን ሩቅ አይሆንም። በገዛ ውሃችን፣ በገዛ ገንዘባችን፣ በገዛ እውቀታችን አባይን ገድበን እንዳንለማ ሸርና ሴራ በመጠምጠም እክል ሲፈጥሩብን የነበሩት ግብጽና ሱዳንም በማፈር ላይ ናቸው። ኢትዮጵያን ነክተዋልና ውርደታቸው ሩቅ አይደለም። ኢትዮጵያን ነክተዋልና፣ ፍርድን አጉድለዋልና፣ ለራሳቸው ብቻ አስበዋልና ሳይቀጡ አይቀርም።
ሌላው አሸባሪውን ህወሓትን በመንቀፍ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ካነበብኩት የህዝብ ድምጽ መካከል ‹የትግራይ ህዝብ ወንድማችን፣ ጁንታው ጠላታችን› የሚለው መፈክር አንዱ ነው። ይህ የህዝብ ድምጽ ብዙዎቻችን የምንስማማበት የጋራ እውነታችን ነው። የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያውያን ወንድም ህዝብ ነው። ታሪክ እንደሚነግረን እኛም እንደምናውቀው ትግራይና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ዘውድና ጎፈር ናቸው። ኢትዮጵያውያን ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ቅያሜ የለውም። የኢትዮጵያ ጠላት በትግራይ ህዝብ መሀል ተደብቆ ሀገርና ህዝብ የሚያስጨንቀው አሸባሪው ህወሓት ነው። መከላከያን ለመደገፍ በወጣው ህዝብ መሀል የህዝብ ድምጽ ሆኖ ይሄን መፈክር በማየቴ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ህዝቡ ከማን ጋር እንደሚዋጋ፣ ጠላቱ ማን እንደሆነ በደንብ አውቋል።
ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በዘርና በጎሳ ለያይቶ ሲጫወትብን የነበረው ይህ ቡድን ዛሬም አመሉ ሳይለቀው እኩይ የጭካኔ ተግባሩን በሀገርና ህዝብ ላይ እያሳየ ይገኛል። ይህ ቡድን እስካልወደቀና እስካልተወገደ ድረስ ኢትዮጵያ ሰላም የላትምና ሁላችንም በተባበረ ክንድ ይሄን አሸባሪ ቡድን ታግለን መጣል ይኖርብናል። ይሄ የሚሆነው ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆምና ማንኛውንም ድጋፋችንን በመስጠት ይሆናል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ህወሓትን እንደጠላት የትግራይ ህዝብን ደግሞ እንደ ወዳጅና ቤተሰብ የተቀበሉ ሌሎች ህዝባዊ መፈክሮችም ነበሩ። ህዝብ የህወሓትን ከሀዲነት በዚህ ልክ ተቀብሎ ለአንድ አላማ በአንድ መቆሙ እጅግ የሚያስመሰግነው በጎ ተግባር ሆኖ አይቼዋለሁ። በሁሉም የድጋፍ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያዊነት የቀደመበት፣ አሸባሪው ህወሓት እንዲወድም አንድ አይነት አቋም የታየበት ህዝባዊ ንቅናቄ ነበር። እንደ ዜጋ የአሸባሪውን ህወሓትን ሀገር የማፍረስ ሴራ በተባበረ ክንድ ድባቅ በመምታት ተስፈኛዋ ሀገራችንን ማሻገር ይኖርብናል። እውነት ነው ከህወሓት ጋር እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር ትላንት፤ ዛሬም፤ ነገም አንድ ነን። የትግራይ ህዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ወንድማችን፣ ታሪካችን ነው። የተጠማን የሚያጠጣ፣ የተራበን የሚያበላ መልካም ህዝብ ነው። ጠላታችን ህወሓት ነው። የምንዋጋው ከአሸባሪው ቡድን ጋር ነው። ይህን ቡድን ታግሎ መጣል ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር ነው። ምክንያቱም ሀገርን ለማፍረስ የታጠቀ አሸባሪ ስለሆነ ነው። የትግራይ ህዝብ ትላንትም ወንድማችን ነው ዛሬም ወንድማችን ነው። ነገም ወንድማችን እንደሆነ ይቀጥላል። ለሁላችንም ግልጽ በሆነ ቋንቋ የኢትዮጵያ ጠላት ህወሓት ነው። ሀገር ለማፍረስ ታጥቆና ሸምቆ ንጹሀንን እየገደለና እያፈናቀለ ብዙዎች የሚናፍቁትን ለውጥ ወደ ኋላ ለመቀልበስ ከውጪ ሀገራት ጠላቶቻችን ጋር የሚደራደር የመላው ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ ጠላት ነው። ይህን ጡት ነካሽ ወንበዴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ለማድረግ ሁላችንም ከመከላከያ ጎን በመቆምና በመሰለፍ ግብዓተ መሬቱን ማፋጠን ይኖርብናል ስል እመክራለሁ።
ሌላውና ሶስተኛው የጋራ ድምጽ ሆኖ ያየሁት ህዝባዊ መፈክር ‹ከመከላከያ ጎን እቆማለሁ ክብር ለኢትዮጵያዊነት› የሚል ነው። ይህ ህዝባዊ መፈክር በኢትዮጵያ ትላንትና ውስጥ ሁሉም ቦታ ያለ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ የሚያደርግ የጋራ እውነት ነው። ከዛ እዚህ የደረስነው በዚህ ህዝባዊ እውነት ላይ ተረማምደን ነው። ሀገርና ህዝብ ሲነሳ አብሮ የሚነሳ አንድ ትልቅ ዋጋ ያለው እሴት ቢኖር መከላከያ ሰራዊት ነው። ያለ መከላከያ ሰራዊት ሀገርና ህዝብ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። ከትላንት እስከዛሬ በጠላቶቻችን ላይ የበላይ ሆነን የምንታየው ዳር ድንበር በሚጠብቀው ጀግና መከላከያ ሰራዊቶቻችን ነው። ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም ከሀገርና ህዝብ ጎን መቆም ነው። ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም ለራስ ክብር፣ ለራስ እውነት መገዛት ነው። ኢትዮጵያን አድምቆ መጻፍ ነው። ለኢትዮጵያዊነት መትጋት ነው። ለጋራ ጥቅም መልፋት ነው። መከላከያ ሰራዊት ሀገርን አንድ አድርጎ ያቆመ፣ እኔና እናንተን ያጸና የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነው።
ይህን ታላቅ እውነት ለሰጠን ሰራዊት ክብር መስጠትና ድምጽ መሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው ። በትላንት ታሪካችን ላይ ከጻፍናቸው ደማቅ ገድሎቻችን ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት አሻራ ትልቅ ነው። እንደ ሀገር ከፍለን የማንጨርሰው በርካታ እዳ አለብን። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ከመከላከያ ጎን በመቆም አጋርነታችንን ከማሳየት በተጨማሪም ያልተከፈለ እዳችንን መመለስ አለብን እላለሁ። እኔና እናንተ የተጻፍነው በደም ነው። ኢትዮጵያዊነት ከሚገለጽባቸው ቁም ነገሮች ውስጥም አንዱ መስዋዕትነት ነው። እኔና እናንተ በመከላከያ ሰራዊት መስዋዕትነት የተገኘን የደም ፍሬ ነን። ስለዚህም ውለታውንም ሀገር በመውደድ፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከጎኑ በመቆም ወዳጅነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል። ትላንትም ዛሬም ነገም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከሚገለጹበት መንገዶች ውስጥ አንዱ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ነው። እርሱም መከላከያ ሰራዊት ነው..እርሱም ኢትዮጵያዊነት ነው.።
‹ህወሓት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ነው… በሉዓላዊነታችን አንደራደርም› የሚል ሌላም መፈክር ከሰልፉ መሀል ማንበብ ችዬ ነበር። ሁላችንንም በሚያስማማ መልኩ ህወሓት የኢትዮጵያ ጠላት ነው። ጠላት ብቻ አይደለም አሸባሪ ወንበዴም ጭምር ነው። ትላንትና በህዝቦች መካከል የሰራው በደልና ግፍ ሳያንሰው ዛሬም ለዳግም በደል ጫካ ከገባ ሰነባብቷል። እንግዲህ ይሄን የጋራ ጠላታችንን ልንፋለም ነው በክተት አዋጅ አደባባይ የወጣነው። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ደግሞ ከጥንት እስከዛሬ በልጆቿ የተባበረ ክንድ ሲረጋገጥ የኖረ ነው። ዛሬም የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት የሆነውን ይሄን አሸባሪ ቡድን ህልውና በማሳጣት በድል የምንቆምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
እኚህ ብቻ አይደሉም አንድነትን የሚሰብኩ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያደምቁ በርካታ መፈክሮችን መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ ከወጡ ሰልፎች መካከል አንብቤአለሁ። ከብዙ ድምጾች መሀል የሰማሁትን ህዝባዊ ቃል፣ ከረጅም ሰልፍ መሀል ያየሁት መፈክር እንዲህ አካፈልኳችሁ። ሀገር ላቆመ፣ ትውልድ ለሰራ ሀገር ወዳድ ሰራዊት ፍቅራችንን ክብራችንን ብንሰጥ ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። ዛሬ ላለችው፣ ነገም ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ከመከላከያ ጎን በመቆም የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት ሀገርና ህዝባችንን እንደ ህወሓት ካሉ ከሀዲና አሸባሪ ጠላቶች ታደግ በዚህ ዘመን ትውልድ ላይ የወደቀ ዜግነት ግዴታ ነው።
ጊዜው የኢትዮጵያን ከፍታ ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ተጋፍጠን ኢትዮጵያን የምናሻግርበትና ብርሃን የምናይበት ወሳኝ ወቅት ነው። ከሁሉም በፊት በመሀከላችን ሆኖ የሚያባላንን፣ የቅርብ ጠላታችን የሆነውን አሸባሪው ህወሓትን ነቅለን መጣል አለብን። ይሄ የሚሆነው ደግሞ በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ስንቆም ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ ሀገርን የመታደጊያው ጊዜ አሁን ብቻ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013