አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ተከታታይ የሆነ የህክምና ሥልጠና ባለመኖሩ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ገለጸ። ማህበሩ 55ኛ ዓመታዊ የሕክምና ጉባዔውንና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ትናንት ባካሄደበት ወቅት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ለውጥ ያላመጣው የሕክምና ጥራት ጉዳይ መቅረፍ ያልተቻለው በዘርፉ ላሉ ሙያተኞች ተከታታይ ሥልጠና ባለመሰጠቱ ነው።
እንደ ዶክተር ገመቺስ ገለፃ፤ ችግሩን ለመቅረፍ በሕክምና ትምህርት ቤቶች የሚከወነውን የመማር ማስተማር ሂደትን አጠናክሮ መሥራት ወሳኝ ነው። በሥራ ላይ ባሉት ሙያተኞችም ላይ ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና በመስጠት የጥራት ጉድለቱን ማስተካከል ይገባል። ማንኛውም የሕክምና ባለሙያም ሕክምና ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ከመሆኑም በላይ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ለማዳን የሚደረግ ሥራ መሆኑን በመገንዘብ አስተሳሰቡንና አካሄዱን ማስተካከል ይኖርበታል።
ጤና ለሁሉም የሚለው አጀንዳ ዓመታትን ያስቆጠረና ቀን ቢቆረጥለትም መሳካት ያልቻለ ነው። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማህበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ በመጥቀስ፤ ተደራሽነትን በተመለከተ የተሠራ ሥራ መኖሩንና ጥራቱ ላይ ደግሞ ትኩረት በመስጠት ለመሥራት በሂደት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
አብርሃም ተወልደ