ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዓለም ‹‹አንድ አለኝ›› የምትለውን የአትሌቲክስና የኦሊምፒክ ተቋማትን በሚመሩ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረ መካረርና ሴራ የኢትዮጵያን የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ውጤት ሊጎዳው እንደሚችል ለአገር የሚቆረቆሩ ሁሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ሰሚ ግን አልተገኘም ፡፡ የተፈራውም አልቀረም ኢትዮጵያ በአስራ ሦስት ኦሊምፒኮች ተሳትፎዋ ካወጣችው በጀትና ካላት አቅም አንፃር ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግባ ተመልሳለች፡ ፡ አንድ ወርቅ፣አንድ ብርና ሁለት ነሐስ ብቻ ከውድድሩ አግኝታለች፡፡
በርካቶች/ አንዳንዶች ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ውጤት በኦሊምፒኩ ተወዳድረው አንዳችም ሜዳሊያ ካላገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ አገራት አኳያ በመመልከት በቂ እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ይህም ከተጠያቂነት ለመሸሽ ስፖርቱን የሚመሩት ሰዎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያፈለቁት ሃሳብ ወይም ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ያላትን ታሪክና ክብር ካለማወቅ የመነጨ እንጂ የጤና አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ ማስመዝገብ እየቻለች ካላሳካቻቸው ውጤቶች ይልቅ ሜዳሊያዎቹ ያልተመዘገቡበት ምክንያት የበለጠ ሕዝብን አሳዝኗል፣ አስቆጥቷልም፡፡
ስፖርቱን የሚመሩት ግለሰቦች ማንም ይሁኑ ማን፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ይሁን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ታሪክ ይቅር የማይላቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ከአገር ጥቅም ይልቅ ግላዊ ስሜታቸውን አስቀድመው የሕዝቡን ልብ አድምተዋል፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው በታሪክ ከፍተኛ የሆነ በጀት ተመድቦለትና ከስምንት ወራት በላይ ዝግጅት ተደርጎበት መሆኑም የበለጠ ያሳምማል፡፡
ለዚህ ኦሊምፒክ ከ250 ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተደረገ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ በአንፃሩ ከ37 እስከ 40 ሚሊየን ብር ያልበለጠ በጀት ነበር የተያዘው፡፡ ይህ በጀት በእጅጉ ያደገ ቢሆንም፣ የሜዳሊያ ቁጥር ግን ካለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ በግማሽ ያነሰ ነው፡፡
በርካቶች ገና ከጅምሩ የእውር ድንብር የሆነውን የኦሊምፒክ ጉዞ ፈር እንዲይዝ ጥረት አድርገዋል። ግፊት ለማድረግ ቢያስቡም ዘወትር በራሳቸው ልፋት አገርን የሚያስጠሩ አትሌቶች ስነልቦና ይጎዳል በሚል በይደር ትተውታል፡፡ ዛሬ ግን በኦሊምፒኩ ከተገኘው ውጤት በመነሳት የግድ ማስተዋል የሚያስፈልጉ ነጥቦችን መምዘዝ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድምታውን በጥንቃቄ ማጤኑም አገራዊ ትምህርት እንዲኖረውና መቼም፣ የትም ቢሆን እንዳይደገም ይረዳልና በኦሊምፒኩ በአመራሮች የተፈፀሙ ታሪክ ይቅር የማይላቸው ስህተቶች ሆን ብለው ይሁንም አይሁን መጠየቅ አለባቸው። ለዛሬው በኦሊምፒኩ የመክፈቻ ስርዓት ላይ የተፈጠረው አሳፋሪ ስህተት ላይ እናተኩር፡፡
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በደማቅ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ባለፈው እሁድ ተጠናቋል። በ2020 የቶክዮ የመዝጊያ ስነ- ስርአት ሲጠናቀቅ በመክፈቻው ላይ ያልታየው በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የልዑካን ቡድን በባህል ልብስ በስታዲየም ውስጥ በዛ ብሎ ታይቷል። በዋናውና አንድ አገር ከኦሊምፒክ የምታተርፍበት ትልቁ አጋጣሚ የመክፈቻው ስነስርዓት ቢሆንም በዚህ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ግን ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ አገራት ባህሏንና ራሷን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ አልታደለችም፡፡
የቱባ ባህሎች ባለቤትና ታላላቅ የኦሊምፒክ ገድሎች ያላት ኢትዮጵያ በመክፈቻው ስነስርዓት እዚህ ግባ የሚባል ባህልና ታሪክ ከሌላቸው ትንንሽ አገራት እኩል እንኳን ደምቃ መታየት አልቻለችም። በዚያ ታላቅ መድረክ ኢትዮጵያን ፈፅሞ የማይመጥንና ባህልና ታሪኳን መናገር በማይችል መልኩ የውሃ ዋና ተወዳዳሪው ቶፊቅ አብዱል ማሊክ እንዲሁም በጅንስ ሱሪና በስፖርት ጃኬት ባጀበችው የኦሊምፒክ ቡድን መሪዋ ወይዘሮ ኤደን አሸናፊ ብቻ ከመቶ ሚሊየን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በሁለት ሰው የዓለም ሕዝብ ፊት ቀርባለች።
ይህ አሳፋሪና በርካታ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋ ድርጊት የተፈፀመው የኦሊምፒክ ቡድኑ በጊዜ መርሐግብሩ ላይ ለመገኘት በገጠመው መጉላላት እንደሆነ ተጠያቂዎቹ አካላት ለማስረዳት ሞክረዋል። በጉዞ ላይ ያለው መጉላላት ለኢትዮጵያ ብቻ ነው?፣ ቀደም ብሎስ ይህ እንዳይፈጠር ማድረግ አይቻልም ነበር? የሁሉም ጥያቄ ነው። ጥያቄ ብቻም ሳይሆን ስህተቱን የፈፀሙት ተቋማትም ይሁኑ ግለሰቦች የአገርን ክብርና ዝና በችልተኝነትም ይሁን ሆን ተብሎ በዓለም አደባባይ አዋርደዋልና በህግ ጭምር የሚያስጠይቅ ነው።
ባለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ በርካታ ጀግና ኦሊምፒያን እያሉ ከፊት የኢትዮጵያን ባንዲራ ብስክሌተኛው ፅጋቡ ይዞ በመውጣቱ ብዙ ጫጫታ አስከትሎ ነበር። በእርግጥ ብዙ ጀግና ኦሊምፒያኖች እያሉ የማይታወቅ አትሌት ባንዲራ መያዙ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ በያኔው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ኢትዮጵያ እንዳሁኑ አልተዋረደችም። ያኔ የተፈጠረው ጥቃቅን ስህተት በዝምታ ታልፎ ዛሬ ላይ የገዘፈ ስህተት አስከትሎ ከፍታ ላይ የምትገኝን አገር ዝቅ አድርጎ አሳይቷል።
ለዚህ አሳፋሪ ስህተት ተጠያቂው ደግሞ ሌላ ሳይሆን የመድረኩ ባለቤትና የቡድኑ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው። የባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር በሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ጭምር ወደ ቶኪዮ አቅንቷል። የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ በዚያ ትልቅ መድረክ እንዲተዋወቅ አስቀድሞ በምን መልኩ ተዘጋጅቷል? ምንስ አቅጣጫ ሰጥቷል? ስህተቱ ባህልና ታሪክን በማጉደፉስ ምን እርምጃ ወስዷል? የሚሉት አሁንም የበርካቶች ጥያቄዎች ናቸው። ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ምናልባትም ይህን ጉዳይ በዝምታ እንደማያልፈውና ከቶኪዮ መልስ አንድ ነገር እንደሚያደርግ እንጠብቃለን።
ከቶኪዮ በፊት አስራ ሦስት ኦሊምፒኮችን የተሳተፈች አገር በኦሊምፒክ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ምን መደረግና ምን መሆን እንዳለበት በቂ ልምድና ተሞክሮ አላት። ዋነኛው ችግር በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ገፍቶ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ግለሰቦች ከጥቅም አኳያ አግበስብሶ ከመጓዝ ነው የሚነሳው። የኦሊምፒክ መክፈቻ ስነስርዓት ያለውን ዋጋ ካለመረዳትና ለአገር ክብር ካለመጨነቅ የተፈጠረ የቸልተኞች የስንፍና ውጤት ነውና ይህ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዝምታ መታለፍ የለባቸውም። ለፈፀሙት አሳፋሪ ስህተት ይቅርታ ስለጠየቁ ብቻ መታለፍ የለባቸውም። ይጠየቁ!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013