በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የአምቦ ልማት ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ ሀያት ረጀንሲ ሆቴል በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለህዝብ የሚሰራበት መሆኑን በመጥቀስ፥ ይህ ጅምር ፕሮግራም በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ለህዝብ ልማትና ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።
መንግስትም የልማት ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉና የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በቅንጅትና በትብብር የሚሰራ መሆኑን በአንክሮ ተንግረዋል ።
በዕለቱ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢየ ፕሮግራም ከ400 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የአምቦ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ ቱሉ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም ፦
1. አቶ በላይነህ ክንዴ 15 ሚሊየን ብር
2. አቶ ገምሹ በየነ 5
ሚሊየን ብር
3. አቶ ተክለብርሀን አምባዬ
1 ሚሊየን ብር
4. ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ
100 ሺህ ብር
5. ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ
100 ሺህ ብር እና ሌሎች ባለሃብቶችም ለልማቱ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ለልማቱ ገቢ ማሰባሰቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእጅ ስዓታቸውን ለጨረታ ያቀረቡ ሲሆን ፥ ጨረታውንም አቶ ገምሹ በየነ በ 5 ሚሊየን ብር ማሸነፍ ችለዋል።
በአጠቃላይ በዕለቱ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ 400 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ነው የተገለፀው።
በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ በተገኘው ገንዘብም በአምቦ ከተማ 12ሺህ ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣20 ሺህ ሰው የሚይዝ ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም፣ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የአርት ጋለሪ ግንባታና ለሌሎች ፕሮጀክቶች ስራ ማስፈፀሚያ የሚውል ነው ተብሏል ሲል ፋና ብሮድ ካስት ዘግቧል።
ለተጨማሪ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆኑ የባንክ ሒሳብ ቁጥሮችም ይፋ ተደርገዋል።
• የኢትዮጵያ
ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር-1000273326417
• የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሒሳብ ቁጥር-1014375
• የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ሒሳብ ቁጥር-1000044088421
• አዋሽ ባንክ ሒሳብ ቁጥር -01307213953401