
ከሰሀራ በታች ያለው የአፍሪካ ቀጣና በደቡባዊ ሰሃራ ያሉትን ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ያካትታል። በዚሁ ቀጣና ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ህዝቦች እንደሚገኙም እ.ኤ.አ በ2019 በወጡ መረጃዎች ተረጋግጧል። ኢትዮጵያም በዚሁ ቀጣና ውስጥ የምትገኝ ሀገር ስትሆን የተባበሩት መንገሥታት ድርጅት የስታትስቲክስ ዲቪዥን ሱዳንን ከዚህ ቀጣና ውጪ እንድትሆን አድርጓታል።
ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ በድርቅና በረሃብ የሚጠቁ በመሆናቸው ከሌሎቹ የቀጣናው ሀገራት ጋር ሲወዳደሩ በብዙ መልኩ ልዩነት አላቸው። ከኢኮኖሚ አንፃር እንኳን ሲታዩ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርታቸውና ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በጤና፣ በትምህርትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተደራሽነትም በብዙ ይታማሉ። በርግጥ በአንፃራዊነት በኢኮኖሚ መሻሻል ያሳዩ ሀገራት ቢኖሩም አሁንም ባሉበት የሚዳክሩ አልጠፉም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እ.ኤ.አ በ2050 ለስራ ዝግጁ የሆነው የህዝብ ቁጥር በእጥፍ የሚያድግ መሆኑን ተከትሎ ለቀጠናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አጋጣሚ እንደሚሆን ተቀማጭነቱን በአሜሪካን ያደረገውና በአክሲዮኖች፣ ቦንዶች እና ሸቀጦች ላይ የፋይናንስ ምርምር እና ትንታኔዎችን የሚያወጣው ኤስ ኤንድ ፒ ገሎባል ሬቲንግ የተሰኘው ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ከሰሞኑ ዘግቧል። በዚሁ ሪፖርት ተቋሙ የቀጣናው ለስራ ዝግጁ የሆነው ህዝብ ቁጥር እድገት በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ባሉ ቁልፍ ኢኮኖሚዎችና በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ላይ የሦስት ከመቶ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ግምቱን ማስቀመጡንም ዘገባው አመልክቷል።
በኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ሬቲንግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሞያ የሆኑት ሳትያም ፓንዴይ ‹‹ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በአሁኑ ወቅት በታሪካቸው ውስጥ በጣም ጉልህ የሆነ የስነ- ሕዝብ ሽግግር እያጋጠማቸው ነው›› ሲሉ መደመጣቸውንም ጠቅሷል። ታይቶ የማይታወቅ የወሊድ ምጣኔ መቀነስ፣ የህፃናት ሞት ቁጥር አነስተኛ መሆንና አማካኝ የመኖር አድሜ መጨመር ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ አመለካከት መቀየር ለሚቀጥሉት አሥርተ ዓመታት ወሳኝ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል” ማለታቸውንም አስታውቋል።
በሁሉም የቀጠናው ሀገራት ህዝብ ውስጥ ያለው የእድሜ ስብጥር ለኢኮኖሚ አድገቱ ወሳኝ ስለመሆኑ፤ ይህም ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ላጋጠመው ክልል የስነ ሕዝብ አወቃቀር ሽግግር የመጀመር እድልን ሊያቀርብ እንደሚችል ነገር ግን ደግሞ ዋነኛው ያለመረጋጋት እና መፈረካከስ ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም የኢኮኖሚ ባለሞያው አያይዘው መግለፃቸውን ዘገባው አትቷል።
በተያያዘም ሪፖርቱ የወሊድ ምጣኔ እ.ኤ.አ በ1990 ከነበረው 6 ነጥብ 3 እ.ኤ.አ በ2019 4 ነጥብ 6 ልጆች በአንድ እናት መቀነሱን ማመላከቱንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም አንዳንድ የቀጠናው ሀገራት እ.ኤ.አ አስከ 2050 ድረስ 2 ነጥብ 1 የወሊድ ምጣኔ እንደሚኖራቸውና ይኸው ምጣኔ መቀነሱን እንደሚቀጥል መተንበዩንም ዘገባው አብራርቷል። በንፅፅርም ሪፖርቱ የደቡብ ምስራቅ እሲያና የላቲን አሜሪካ የወሊድ ምጣኔ በ2020 ከነበረው በ2 ነጥብ 2 በ2050 ወደ 1 ነጥብ 85 እንደሚወርድ፣ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ቀጠና በ2050 ከሚጠበቀው ተፈጥሯዊ የወሊድ መጠን ከ2 ነጥብ 5 በላይ እንደሚሆን መጠቆሙንም አስታውቋል። በከፍተኛ ገቢ ባላቸው የሀገራቱ ኢኮኖሚዎች ውስጥ የወሊድ ምጣኔው 1 ነጥብ 6 ገደማ ላይ ተቀምጦ ይቆያል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሪፖርቱ ማስታወቁን ዘገባው ጠቁሟል።
በሪፖርቱ ትንበያ አካሄዱ በሁሉም ሀገራት ተመሳሳይ እንዳልሆነም የተጠቀሰ መሆኑን ዘገባው ገልፆ፤ የወሊድ ምጣኔው በደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያና ኢትዮጵያ ቁልቁል እየቀነሰ ሲመጣ ከዚህ በተቃራኒ በናይጄሪያ ምጣኔው ከአምስት በላይ መሆኑን መጠቆሙንም ገልጿል። በተባሩት መንግስታት ትንበያ መሰረት ደግሞ የናይጄሪያ የህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2020 ከነበረበት 206 ሚሊዮን በ2050 400 ሚሊዮን እንደሚደርስ በዘገባው ተመላክቷል።
ከዚህ አኳያ የቀጠናው ሀገራት ለስነ ህዝብ ክፍፍል ሊዘጋጁ እንደሚገባ ማለትም ከማይሰሩት ይልቅ ለስራ ዝግጁ የሆነው ህዝብ ቁጥር ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን የኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ሬቲንግ ሪፖርት ያመላከተ ሲሆን፤ አነስተኛ ድጋፍ የሚሹ ሰዎች እንዳሉ ሆነው የሀገራቱ ጥቅል ምርት እድገት በፍጥነት የማደግ መስኮት ወለል ብሎ እንደተከፈተላቸውም አስቀምጧል።
ይሁንና የቀጣናው ሀገራትን ለስራ ዝግጁ የሆነ ህዝብ በሚገባ ለመጠቀም የመንግሥታት ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ወሳኝ መሆናቸውንና በአሁኑ ጊዜ ቀጠናው ከስነ ህዝብ ሽግግሩ ጥቅም ለማግኘት ዝግጁ አለመሆኑን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሞያው ፓንዴይ ስለመናገራቸውም ዘገባው አብራርቷል።
የወጣት ሥራ አጦች አንፃራዊ ድርሻ ስለሚጨምርና የሥራ ዕድሎች ለሁሉም ካልተፈጠሩ የስነ- ሕዝብ ክፍፍሉ የአለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም ዘገባው ተናግሮ፤ መንግስት በትምህርት ላይ መዋእለ ነዋይ ካለፈሰሰ ከፍተኛ ጥራት ያለው የትምህርት ተደራሽነት ሊኖር እንደማይችል ሪፖርቱ መጥቀሱንም አስታውቋል።
“በዚህ ሁኔታ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት እንዲኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ አይችሉም ፣ ስለዚህ የቁጠባ መጨመር የሰው ሀብትን አይጨምርም። በመሆኑም የባንክ አገልግሎት በስፋት ካልቀረበና የካፒታል ገበያ ካልዳበረ የቁጠባ መጨመር የግድ ከኢንቨስትመንት መጨመር ጋር ሊዛመድ አይችልም ሲል ሪፖርቱ ማብራራቱንም ዘገባው አመልክቷል።
የታሪክ ማስረጃዎች በተቀጠሩ ሰዎች ድርሻ እና በኢኮኖሚ ዕድገት መካከል ግልፅ የሆነ አዎንታዊ ትስስርን ቢያሳዩም ሪፖርቱ በተወሰነ ደረጃ የወሊድ ምጣኔ እያነሰ መምጣት በእድሜ የገፉ ሰዎችን ቁጥር የሚጨምር በመሆኑ የኢኮኖሚ አድገት እድል መስኮቱ የተገደበ ሊሆን እንደሚችልም ስጋቱን ማስቀመጡን ዘገባው በመቋጫው አስቀምጧል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013