ቶኪዮ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ያሰናዳችውን ኦሊምፒክ ለቀጣይ ባለተራ አሸጋግራ ትኩረቷን ወደ ፓራሊምፒክ ውድድሮች አድርጋለች:: የ33ኛው ኦሊምፒክ አዘጋጅ ፓሪስም ከሶስት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ ኋላፊነቷን ተረክባ ወደ ስራ ለመግባት እየተንደረደረች ትገኛለች:: በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተሳተፉ የየሃገራቱ ብሄራዊ ቡድኖችና አትሌቶቻቸውም ወደየመጡበት በመመለስ ላይ ይገኛሉ:: አስደሳች፣አወዛጋቢ፣አሳዛኝ እና የሚያስቆጩ ጉዳዮችን ያስተናገዱትና በስፍራው የነበሩ የኢትዮጵያ ልኡካንም ውድድራቸውን አጠቃለው ከነገ ጀምሮ ወደ ሃገራቸው እንደሚገቡ ታውቋል::
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተለመደው ተሳትፎ ተቃራኒ በሆነ መልኩ 1ወርቅ፣ 1ብር እና 2 ነሃስ በጥቅሉ 4ሜዳሊያዎችን ማስመዝገቧ በስፖርት ቤተሰቡ ቅሬታን አሳድሯል:: በአንጻራዊነት አነስተኛ የሜዳሊያ ብዛት ከተመዘገበበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ አስቀድሞ ኢትዮጵያ በታላቁ የስፖርት መድረክ ያላት ተሳትፎ ምን ይመስላል የሚለውን መመልከት አስፈላጊ ይሆናል::
ኢትዮጵያ ከሜልቦርን እስከ ቶኪዮ በ14 ኦሊምፒኮች ላይ ተሳትፋለች:: በመካከል በተካሄዱ ሶስት ኦሊምፒኮች ላይ ደግሞ ልኡካኗን አላሳተፈችም፤ ይኸውም ከአፓርታይድ ጋር በተያያዘ ከደቡብ አፍሪካ ጎን በአጋርነት በመቆሟ በፍላጎቷ ያልተሳተፈችበት የሞንትሪያል ኦሊምፒክ እንዲሁም ሃገራት በሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮት ምክንያት ጎራ በለዩበት የሎስ አንጀለስ እና ሴኡል ኦሊምፒኮች እንዳልተሳተፈች ይታወቃል:: ከዚህ ባሻገር በተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች በጥቅሉ 58 ሜዳሊያዎችን በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ አስመዝግባለች:: ከእነዚህ ሜዳሊያዎች መካከልም 23ቱ ወርቅ ሲሆኑ፤ 12ቱ የብር እንዲሁም 23ቱ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያዎች ናቸው:: ይህ ቁጥርም ሃገሪቷን በዓለም የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ 41ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል:: ከዓለም አሁን የያዘችው ደረጃ የወረደው ዘንድሮ በተመዘገበው ደካማ ውጤት እንጂ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በፊት ከዓለም 36ኛ ደረጃ ላይ ነበረች::
የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪኳ የሚነሳው እአአ 1956 ከተካሄደው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ነው:: በወቅቱ ኢትዮጵያ በብስክሌትና አትሌቲክስ ስፖርቶች 12 አትሌቶችን ብታካፍልም ከጉዞ ጋር በተያያዘ ድካም እንዲሁም ከልምድ ማነስ የተነሳ ያለምንም ሜዳሊያ ነበር የተመለሰችው:: ከአራት ዓመታት በኋላ በተካሄደው የሮም ኦሊምፒክም በተመሳሳይ በብስክሌትና አትሌቲክስ ስፖርቶች 12 አትሌቶች ተካፍለው በማራቶን የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ከአዲስ የዓለም የርቀቱ ክብረወሰን ጋር በሻለቃ አበበ ቢቂላ ለማስመዝገብ ችላለች::
ከአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርቶች ባሻገር ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርትም በተወዳደረችበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም አበበ በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ችሏል:: 18 ስፖርተኞች ሃገራቸውን በወከሉበት የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ በማራቶን የወርቅ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ የጥምር ሜዳሊያዎች ባለቤት ለመሆን ችሏል:: ማሞ በቀጣዩ የሙኒክ ኦሊምፒክ ተሳትፎው በማራቶን ሃገሩን የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ሲያደርግ፤ ምሩጽ ይፍጠርም በ10ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያውን አጥልቋል:: በቀጣዩ የሞንትሪያል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ ዝግጅት ብታደርግም በውድድሩ ሳትካፈል ቀረች::
የካፒታሊስት ስርዓት ያራምዱ የነበሩ ሃገራት ከተሳትፎ በተቆጠቡበት የሞስኮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በታሪክ ከታየው ብልጫ ያለውን አትሌት ያሳተፈች ሲሆን፤ 45 ተወዳዳሪዎችና ልኡካን ተጉዘዋል:: በዚህም ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ምሩጽ ይፍጠር በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች በማሸነፍ ለሃገሩ ሁለት ክብሮችን ሊያስመዘግብ ችሏል:: መሃመድ ከድር እና እሸቱ ቱራ ደግሞ በ10ሺ እና 3ሺ ሜትር መሰናክል ሁለት ነሃሶችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያ 4 ሜዳሊያዎችን የግሏ እንድታደርግ አስችለዋል:: በቀጣዮቹ የሎስ አንጀለስ እና ሴኡል ኦሊምፒኮች ላይም ኢትዮጵያ በተከታታይ በመድረኩ አልታየችም::
ከስምንት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በባርሴሎና ኦሊምፒክ ተሳትፎ 1ወርቅ እና 2ነሃሶችን አስመዝግቦ ነበር የተመለሰው:: እርምጃን ጨምሮ ከ800ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች 16 አትሌቶች በተካፈሉበት በዚህ ኦሊምፒክ ደራርቱ ቱሉ ለራሷ፣ ለሃገሯ እና በአፍሪካ የመጀመሪያውን የ10ሺ ሜትር የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ልታስመዘግብ ችላለች:: አትሌት አዲስ አበበ እና ፊጣ ባይሳ ደግሞ በ10ሺ እና 5ሺ ሜትሮች ሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል:: በቀጣዩ የአትላንታ ኦሊምፒክ በአትሌቲክስና ቦክስ ስፖርቶች የተወከለችው ኢትዮጵያ በኋይሌ ገብረስላሴ እንዲሁም ፋጡማ ሮባ ወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ሃገሪቷ በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን የለመደችውን ክብር ለማስቀጠል ችለዋል:: ጌጤ ዋሚ ደግሞ በሴቶች 10ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያውን ያገኘች ሌላኛዋ አትሌት ናት::
ቀጣዩ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከዚያ ቀደምም ሆነ ከዚያ በኋላ ያላገኘችውን ስኬት ያስመዘገበችበት የሲድኒ ኦሊምፒክ ነው:: በዚህ ኦሊምፒክ በርካታ ልኡካን የተሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 25ቱ በተለያዩ ርቀቶች የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው:: በዚህም በ10ሺ ሜትር ወንድ እና ሴት፣ በ5ሺ ሜትር ወንዶች እንዲሁም በማራቶን 4 ወርቆች ተመዝግበዋል:: 1ብር እና 3 ነሃስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም ኢትዮጵያ በደረጃ ሰንጠረዡ ከዓለም 20ኛ ላይ መቀመጥ ችላለች:: አዳዲስ ባለ ድሎች በታዩበት የአቴንስ ኦሊምፒክም 2የወርቅ፣ 3የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል:: ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ 4የወርቅ ሜዳሊያዎችን በሰበሰቡበት የቤጂንግ ኦሊምፒክም 2የብር እና 1የነሃስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል:: በለንደን ኦሊምፒክ 8 ሜዳሊያዎች ሲቆጠሩ፤ ከእነዚህ መካከል 3ቱ የወርቅ፣ 2ቱ የብር እንዲሁም 3ቱ የነሃስ ሜዳሊያዎች ነበሩ::
ከአምስት ዓመታት በፊት በተካሄደው 32ኛው የሪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ 1የወርቅ፣ 2ብር እና 5የነሃስ በአጠቃላይ 8ሜዳሊያዎች ቢመዘገብም የወርቅ ሜዳሊያ ቁጥሩ በማነሱ ምክንያት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር:: የዘንድሮው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ ካለፈውም ኦሊምፒክ በግማሽ የቀነሰ የሜዳሊያ ቁጥር የተመዘገበበት ሆኖ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013