
በመጠንና በገንዘብም ግምቱ ከፍተኛ የሆነ ከዓመታት በፊት በኢንቨስትመንት ስም ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ለተለያየ ግንባታ የሚውል የብረት ክምችት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በ17 መጋዘኖች ውስጥ ማግኘቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲፈቅድ በረጅም ጊዜ እንደሀገር ሊያስገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ይገመታል። ይሁን እንጂ ግምቱ ትክክል አልነበረም ማለት ነው። ከልማት ይልቅ ጥፋት እንደነበር ግብአቱ ያለጥቅም ተከማችቶ መገኘቱ፣ ክምችቱም ወደፊት ጥቅም ላይ እንዲውል በሚያስችል መልኩ አለመቀመጡ የጉዳቱን መጠን ማሳያ ነው። በድብቅ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የቆየው ይህ የሀገር ሀብት ለታለመለት ዓላማ ካለመዋሉ በተጨማሪ ለብረት ዋጋ መናርና እጥረት መፈጠር መንስኤ መሆኑም የዘርፉ ባለሙያ በቅሬታ ይገልጻሉ።
‹‹በአሁኑ ጊዜ ከሲሚንቶ የግንባታ ግብአት ቀጥሎ ሀገሪቱ ላይ ዋጋው እየናረና እጥረትም እያጋጠመ ያለው የብረት ግብአት ነው። በአሁኑ ጊዜ ለግንባታ ተፈላጊ መጠን ያላቸው እንደ አርማታ ብረት በኪሎ ግራም ይሸጥ ከነበረበት ከ28 ብር ወደ 85 ብር ከፍ ብሎ እየተሸጠ ነው። ይህ የኢኮኖሚ አሻጥር እንጂ ምን ሊባል ይችላል። በግንባታ ዘርፉ ላይ ያሳደረው ጫናም በተለያየ መልክ ይገለፃል። ግብአቱ 28 ብር በሚሸጥበት ዋጋ ኮንትራት ወስዶ ሥራ የጀመረ ተቋራጭ ሥራውን ሳያጠናቅቅ የግብአቱ ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተቋራጩን ተጎጂ ያደርገዋል። ፕሮጀክቶቹ እንደባህሪያቸው የሚፈጥኑና የሚዘገዩ በመሆናቸው ነው ተቋራጩ ለችግሩ ተጋላጭ የሚሆነው። የግብአቱ ዋጋ መናር ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ፣ ሥራዎችም እንዲቆሙ፣ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ በዘርፉ ላይ የተሰማራው ባለሙያ ከሥራ እንዲወጣ፣ በአጠቃላይ የግንባታ ዘርፉን የጎዳና በሀገር ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑ ግልጽ ነው። በተለያየ መልኩ የብረት ዋጋ የናረው እጥረት ተፈጥሮ ሳይሆን ሰው ሰራሽ ነው። በግብአቱ ላይ በደንብ ጥናት ቢደረግ ሀገሪቱ ውስጥ በማከናወን ላይ ላለው ግንባታ መቶ በመቶ ባይባልም በአብዛኛው ግን ሊሸፍን ይችላል።›› በማለት ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወሰደው እርምጃ ቢዘገይም መደሰታቸውን የገለጹት የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም፤እንዳሉት በወቅቱ በግላቸውና በማህበራቸው አማካኝነት የብረት ክምችት ስለመኖሩና ወደፊት ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳት ጭምር በተለያየ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት፣ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትር ለነበሩ ሰው በማሳወቅ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን ሰሚ አላገኙም። ጥቆማው እየበረታ በመሄዱ ነው ፖሊስ እርምጃ ሊወስድ የቻለው። በኢንቨስትመት ስም ግብአቱን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ በወቅቱ ከመንግሥት ፍቃድ ያገኙት የአንድ አካባቢ ሰዎችና ቤተሰቦች ናቸው።ይሄም ሆን ተብሎና እነርሱን ለመጥቀም የተደረገ መሆኑ ሰው ያወቀውና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።
የግብአቱ ክምችት በሚገኝበት ክፍለ ከተሞችም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ አካባቢ አመራሮች ስለክምችቱ መረጃው አልነበራቸውም ለማለት እንደማያስደፍር ኢንጂነር ግርማ ይገልፃሉ። አጥፊዎችን አሳልፎ የመስጠት ችግር መኖሩንም ተናግረዋል። በፖሊስ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ቢቀጥል አሁን ከተደረሰበት ክምችት ባልተናነሰ ተጨማሪ ሊገኝ እንደሚችል ያምናሉ።
ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የደህንነት ግብረ ኃይል ያገኘው ብረት ክምችት በስፋት ለግንባታ የሚውል እንደሆነ በማስታወስ፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ጫና መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡኝ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ዱጋሣ ዱንፋ፤ በኢንቨስትመንት ስም የገባው ብረት ለታለመለት ዓላማ አለማዋሉ ኢንቨስትመንቱ እንዳያድግ ተጽዕኖ አሳድሯል።የኢንቨስትመንት ማበረታቻው በብዛት ሆቴል ቤቶችና የቤት ልማት ለሚያከናውኑ በመሆኑ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና ከመኖሩ በተጨማሪ በግንባታው ዘርፍ ለዜጎች ሊኖረው የሚችለው የሥራ ዕድል ሰፊ ይሆን እንደነበር ከግብአት ክምችቱ መረዳት ይቻላል። በግንባታ ዘርፉ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የሚሳተፍ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በመያዝ ከሚሰጠው ጥቅም ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቱ ደግሞ በቋሚነት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንዲሁ ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለብረቱ ግዥ የወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአት መግዣ እንዳይሆን አስችሏል። አምራች ኢንዱስትሪዎች በብዛት በግብአት እጥረት ይፈተናሉ።ግብአት አለማግኘታቸው የሚከተለው ጉዳት ሰፊ ነው። በግብአት አቅርቦት እጦት ከሚቸገሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኬሚካልና ብረታ ብረት ዘርፍ ይጠቀሳል። በአምራች ኢንዱስትሪዎቹ በውስጣቸው የሚይዙት የሰው ኃይል የሀገሪቱን የሰው ኃይል በአግባቡ ለመጠቀምም ሆነ፣ ሥራ አጥነትን በመቅረፍ ሚናቸው ከፍተኛ ሆኖ ሳለ በሚገጥማቸው የግብአት አቅርቦት የያዙት የሰው ኃይል ያለሥራ እንዲቀመጥና ሲብስም ከሥራ እስከማሰናበት ይደርሳሉ። ሰራተኛው ከሥራ መሰናበቱ ደግሞ በሥሩ የሚያስተዳድረው ቤተሰብ ለከፋ ችግር ይጋለጣል። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ይወድቃል።
የብረት ክምችቱ ብር እንዳይዘዋወር አድርጓል። ግብአቱ በወቅቱ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለግብአቱ የሚያስፈልገው ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ መልሶ ጥቅም ላይ የማይውልበት አጋጣሚ መፈጠሩን ከብረቱ አቀማመጥ መረዳት እንደሚቻል መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። ብረት ወደ አፈር የመቀየር ባህሪ ስላለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። አስፈላጊውን የህግ ሂደት በማፋጠንና ትርጉም ያለው ሥራ በመሥራት የተወሰነውን ግብአት እንኳን በማትረፍ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ካልተቻለ ጉዳቱ የከፋ መሆኑ አያጠያይቅም።
የተገኘው ክምችት በተለያየ መልኩ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራ ያሳደረ ነው ሲባል መገለጫው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ አቶ ዱጋሣ በሰጡት ምላሽ፤ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የግብአት ክምችቱን የደረሰበት ግብረ ኃይል ስራውን ሲያጠናቅቅ የተገኘውን የብረት መጠን በቶን፣ በብርም ሲተመን ምን ያህል ዋጋ ያወጣ እንደነበር ይፋ እንደሚያደርግ እንደ አንድ ባለሙያና የሥራ ኃላፊ ይጠብቃሉ። እርሳቸው እንዳሉት መጠኑንና ዋጋውን ብቻ ሳይሆን፣ ለምን አይነት ኢንቨስትመንት እንደገባ ጭምር ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል። ለህንፃ፣ ለመንገድ፣ ለውሃ ግንባታ ሊሆን ስለሚችል በእያንዳንዱ ዘርፍ ስም የገባው ግብአት ያደረሰውን ጉዳት መለየት ይቻላል። ያም ሆኖ ግን በሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ካለው የብረት ግብአት አቅርቦት አንፃርና ክምችቱንም በማየት ኪሳራው ከፍተኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ግብዓቱ ከውጭ ሀገር የመጣው ሀገሪቱ በቂ ካልሆነው የውጭ ምንዛሪ ሀብት በተለይም ለነዳጅ፣ ለመድኃኒት ግዥና ሌሎችም ቅድሚያ አስፈላጊ ከሆኑ የተረፈው ነው ለግብአት ግዥው የዋለው። ችግሩ ሲገፋም የኑሮ ውድነትን በማስከተል በሰዎች ህይወት ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከዕለት ምግብ ፍጆታ ጀምሮ ህብረተሰቡን እያማረረ ላለው ገንዘቡ ውሎ ቢሆን የኑሮ ጫናን መቀነስ ይቻል ስለነበር ነው።
ግብአቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ አስፈጻሚ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ተዋናዮች እንደሚሳተፉ ይታወቃል። የተለያዩ አካላት ይሳተፉበታል ተብሎ በሚገመተው በዚህ ሂደት ውስጥ የነበረውን ኃላፊነት የጎደለው አሰራር አቶ ዱጋሣ እንዴት ያዩታል? ‹‹ህገወጥ ሥራ የሚሰራው ህግን ከለላ በማድረግ ነው። አንድ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራ ሰው ኢንቨስትመንቱ የሚያስፈልገውን ሰነድ አሟልቶና ከብሄራዊ ባንክም የገንዘብ ብድር ለማግኘትም እንዲሁ መረጃ አቅርቦ በመሆኑ ሽፋኑ ህጋዊ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ህጋዊ ሽፋን ከለላ አድርጎ ህገወጥ ሥራ የሚሰሩ አይጠፉም። በአብዛኛውም በዚህ አይነት አካሄድ ነው ህገ ወጥነት የሚፈጸመው። ይሄ የሚሳየው የኢንቨስትመንቱ ተገቢ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው ነው። በእኔ አስተያየት ግብአቱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ አይደለም ትልቅ ችግር። ከገባ በኋላ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ኃላፊነት ወስዶ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ አካል መኖር ነበረበት። በእርግጥ በወቅቱ ግብአቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ከፍተኛ ትስስርና ረጃጅም እጆች እንደነበሩና እነርሱም በህጋዊ ሽፋን ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹና በአሰራር ውስጥ የተዘረጋ እንደነበር መገመት ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። ድርጊቱ የአንድ አካል ተሳትፎ ብቻ ባለመሆኑ አንድን አካል ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግ አይደለም። ማን ምን አደረገ የሚለውም ግብረ ኃይሉ አጣርቶ ሲደርስበት የሚታወቅ ይሆናል።›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
የተያዘው የብረት ክምችት በአያያዝ ጉድለት ጉዳት ውስጥ እንዳለ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ከቀረበው መረጃ መረዳት ይቻላል። ንብረቱን የመያዝና ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትንም መረጃ የማጣሩቱ ሂደት ጊዜ እንደሚወስድ ይታወቃል። ነገር ግን ሀገሪቱ ካለባት የግብአት አቅርቦት አንጻር ከአያያዝ ጉድለት የተረፈውን ጥቅም ላይ ለማዋል በፍጥነት መሰራት እንዳለበት ይታመናል። እንዴት? አቶ ዱጋሣ ምላሽ ሰጥተዋል። በእርሳቸው እምነት በቅድሚያ ኦዲት ወይንም የቆጠራ ሥራ ተሰርቶ የህግ ሂደቱ እየተከናወነ ወደ ሥራ ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ እንደሚሆን ሙያዊ ሀሳብ ሰጥተዋል። መንግሥትም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ይሰራል የሚል እምነት አላቸው።
ወቅታዊ ጉዳይ በመሆኑ ስለብረት ክምችትን እንዲህ አነሳን እንጂ በተመሳሳይ ብክነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ያለውን ወደኋላ መመለስ ስለማይቻል ከባለፈው ተሞክሮ ቀጣይ ላይ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይደገሙ ምን አይነት የአሰራር ሥርአት መዘርጋት እንዳለበትም ለተነሳው ሀሳብ አቶ ዱጋሣ ‹‹ብዙ ጊዜ የአሰራር ሥርአት ወይንም ሲስተም የለም እየተባለ ይተቻል። የተዘረጋውን አሰራር በማበላሸት ችግር የሚያመጣ አካል መኖሩ ትልቁ ክፍተት ሀገሪቱ ውስጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የተቋቋሙ እንደ ባንክ፣ጉምሩክና ሌሎችም ተቋማት አሉ። ትልቁ ነገር መሆን ያለበት የቡድንን ጥቅም በሚያስጠብቅና በሚያስከብር ሳይሆን፣ ሀገራዊ ስሜት ባለው ባለሙያና ኃላፊ እንዲሁም ተቋማት የሚመራበት፣ ከግለሰቦች ይልቅ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም አግባብ መፈጠር አለበት። የሚመራውም አካል የዜግነት አስተዋጽኦውን በማበርከት ኃላፊነቱን ለመወጣት የፀና አቋም ሊኖርው ይገባል›› በማለት እስካሁን በነበረው እንዲህ ያለው ነገር ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከተነሳው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚና ይኖረው እንደሆንም ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የብረት ግብአቱ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዘና ከውጭ የገባ በመሆኑ ቀጥታ የሆነ ግንኙነት የለውም። ሆኖም ግን በጉዳቱ ይገናኛል። ሚኒስቴሩ የሚደግፋቸውና የሚከታተላቸው ግብአቱን ማምረት የሚችሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ተፈጥረዋል። በውጭ የተመረተው ምርት ወደ ሀገር እንዲገባ ከሚደረግ በምትኩ የማምረቻ ግብአቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎቹ ተመቻችቶላቸው ቢሆን ኖሮ የውጭ ምንዛሪ ወጭን በማዳን በሀገር ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ይቻል ነበር። ይህ ባለመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከአቅማቸው በታች ለማምረት ተገደዋል። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተደራጀ ተቆጣጣሪ ዘርፍ አለ። ዘርፉ ገቢና ወጪ ዕቃዎችን ነው የሚቆጣጠረው።ቁጥጥሩም ደረጃውን የጠበቀ ግብአት መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው ግብአቱ ለምን ተግባር መዋል እንዳለበት አይወስንም። የብረት ክምችቱ ላይ እየሰራ ያለው ግብረ ኃይል ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ለጋራ ሥራ ይሰራል።
በብረታ ብረት አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ መሳተፍ የሚፈልጉ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ፣ የገቡት ደግሞ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ፣ በጥራትና በብዛት አምርተው ለገበያ በማቅረብ ገበያውን እንዲያረጋጉ እንዲሁም የገበያ ፍላጎትን በማጥናትና ምርምርን በመደገፍ የሚሰራው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የብረት ክምችት ግኝቱ ተቋሙ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የኢንስቲትዩቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት ኢንዱስትሪዎቹ በዓመት ከ11 ሚሊየን ቶን በላይ ብረት የማምረት አቅም ቢፈጥሩም ሀገሪቱ በገጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከውጭ በግዥ የሚገባ ግብአት ማስገባት ባለመቻላቸው በተለይም በ2012ዓ.ም እና በ2013ዓ.ም ከአቅም በታች ለማምረት ተገደዋል። ኢንዱስትሪዎቹ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ማምረት ቢችሉ ግን ምርቱን ለጎረቤት ሀገር በመላክ ጭምር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ይቻል ነበር። መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ያሉባቸውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በሀገር ውስጥ ግብአቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቸ ነው። እስካሁን በተሰራው ሥራም ለስምንት አቅራቢ ድርጅቶች ወደ አምስት ሺ ቶን ግብአት በግዥ እንዲተላለፍ ተደርጓል። ይሁን እንጂ የአርማታ ግብአትን ጨምሮ የኮንትሮባንድ ንግዱ ዘርፉን እየፈተናቸው ይገኛል። በኢንቨስትመንት ስም ወደ ሀገር ገብቶ ጥቅም ላይ ሳይውል ዓመታትን በማስቆጠር በቅርቡ የተያዘው የብረት ክምችትም ተጨማሪ ተጽዕኖ ነው። በአጠቃላይ ዘርፉን እየፈተኑት ባሉት ችግሮች ላይ ጫና ፈጥሯል። አቅም የተፈጠረለት አምራች ኢንዱስትሪ ካልሰራ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላል። ከተሰራ ግን የቴክኖሎጂ ሽግግር ይሰፋል፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ከውጭ የሚገባ ግብአት ቢያስፈልግም የሀገር ውስጥ አምራች እንዲዳከምና እጥረት እንዲፈጠር መሆን የለበትም። ሁሉም እንደአስፈላጊነቱ ጎን ለጎን መከናወን ይኖርበታል።
በጥራት ከማምረት ጋር ተያይዞ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ስለሚቀርብባቸው ቅሬታ አቶ ፊጤ በሰጡት ማብራሪያ፤ የጥራት ጉዳይን ኢንስቲትዩቱም አይደራደርም።ኢንዱስትሪውም ተወዳዳሪ በመሆኑ ለራሱ ሲል ለጥራት ይጨነቃል። እስካሁን ባለው አሰራር ከውጭ ከሚገባው ምርት ያነሰ ነው ለማለት አያስደፍርም። ለትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚውል ግብአትን በማቅረብ በኩል ግን ትልቅ ኢንቨስትመትን ይጠይቃል።ከተሰራ ግን ይሄንንም በሀገር ውስጥ ማሟላት ይቻላል። በተለይም አነስተኛ ለሆኑ ግንባታዎች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ይቻላል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013