ከሁሉ አስቀድመን በፍልስፍናው ዘርፍ ስለ “ስነህላዌ” ያለውን አተያይ እንመልከት።
“ስነህላዌ” (Metaphysics) ከአምስቱ አበይት የፍልስፍና ዘርፎች አንዱና ቀዳሚ ሲሆን ለዘርፉ ከሌሎቹ ሁሉ በላይ መሰረታዊው ነው። መሰረታዊነቱም “ህላዌ” ህልውና ያለውን ነገር (ሰው፣ ተፈጥሮ፣ ፈጣሪ/እግዚአብሔር፣ እውነት፣ ነፍስ፣ መናፍስት፣ ሁለንታ/ዩኒቨርስ) ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎቹ የፍልስፍና ቅርንጫፎች የሚመዘዙት ከስነህላዌ (ህልውና) ስለሆነ ነው (ለበለጠ ቢያንስ “ፍልስፍና ትምህርት ቅጽ – ፩”ን መመልከት፤ በጉዳይ ላይም ዘርዓያዕቆብ ምን ያህል ተራቆበት እንደነበር የብሩህ ዓለምነህን ቀዳሚ ስራዎች መመርመር ይጠቅማል።)
ከ”ቅድመ ሶቅራጥስ” ዘመን በፊት ከነበሩት የፍልስፍና ዘርፎች፣ ወይም ፍልስፍና ከሚመለከታቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና መሰረታዊ መሆኑ፤ ቀዳሚ በሚባሉት ፈላስፎች ዘንድም ቀዳሚ ትኩረት የነበረው መሆኑ፤ እንዲሁም ደረጃውን ሳይለቅ እዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ መዝለቁ (ወደፊትም መቀጠሉ እንዳለ ሆኖ) ህላዌን የበለጠ ተተኳሪ ያደርገዋል።
(“የሶቅራጠስ ሞት ‹‹ለፖለቲካ ፍልስፍና›› መወለድ ምክንያት ሆኗል።ፕሌቶና አሪስቶትል የሥነ መንግስት እሳቤዎች ላይ አተኩረው ማሰብ የጀመሩት ከሶቅራጠስ ሞት በኋላ ነው።ፕሌቶ ‹‹ዲሞክራሲ›› የሚባለውን የመንግስት ሥርዓት አምርሮ መተቸት የጀመረው ሶቅራጠስ የግሪክ ዲሞክራሲ መስዋዕት በመሆኑ ነው።አሪስቶትልም የዲሞክራሲ ተቺ ነበር።” በሚል ለውይይት ባመቸ መልኩ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ለንባብ የበቃውን መተከዣ ማድረግ ጠቃሚ ነው። ከ19ኛው ክ/ዘ ጀምሮ እየፈካ ከመጣው Existentialism፣ ኢማኑኤል ካንት (1780)ን፤ በማይታረቅ መልኩ ከካፒታሊዝም ጋር በተቃርኖ የቆመውን Marxism እና ሌሎችንም ከዚሁ ከ”ህልውና”ነት (ዲበአካል) አኳያ መመልከት ጠቃሚ ነው።)
ለመጀመሪያ ጊዜ በ1598 ወደ ስራ አለም የገባውን “ህልውና” ከፍልስፍና ዘውግ አንፃር ምን እንደሆነ በጨረፍታ ከተመለከትነው፤ ከዚሁ ጋር አያይዘን ብዙዎች “የአውሬ ፍልስፍና” የሚሉትንና በዚህ ጽሑፍ ብዙም የማንገፋበትን፣ የ”Darwinism” ፍልስፍና አባት ቻርለስ ዳርዊንን (ትልቁ ትንሹን የሚሰለቅጥበትን) “Survival of The Fittest” ብናስታውስ ተገቢ ሆኗል። አስተሳሰቡ ወይም ንድፈ ሀሳቡ “ዓለም የአሸናፊዎች ናት። በመሆኑም ተሸናፊዎች እየከሰሙ፤ አሸናፊዎች እየበዙና እየተባዙ ይሄዳሉ።” ባይ ነው። “But this survival of the fittest, implies multiplication of the fittest.” እንዳሉት።)
በHerbert Spencer የተፈጠረው (invent የተደረገው)ና በ”The Principles of Biology” (1864) አማካኝነት ያስተዋወቀው፤ እንግሊዛዊው ቻርለስ ዳርዊን በ”On the Origin of Species” 5ኛ እትም (1869) ዜናውና ዝናው በአለም የናኘለትን “Survival of The Fittest” (“የተፈጥሮ ምርጫ/natural selection” ወይም “ምርጫ/selection” በሚልም ይጠሩታል)ን ማስታወሰ፤ ዶ/ር ሰለሞንም ከዚሁ ፍልስፍና ጋር ቅርርብ እንዳላቸውም (ከስራዎቻቸው እንደተረዳነው) መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
(እርግጥ ነው “Survival of The Fittest” በዘመናዊ ሥነ ህይወት ተመራማሪዎች ዘንድ “እየተተወ” የመጣ ንድፈ ሀሳብ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ “ምክንያቱ Survival የአንድ ወገንን/አካልን ከፊል ገፅታ ብቻ የሚያመለክት መሆኑና ይህ ደግሞ ሁልጊዜ አስፈላጊ ሆኖ አለመገኘቱ” ነው የሚል ምላሽ ነው እየተሰጠ ያለው። (ስለ ዳርዊን ፍልስፍና ተጨማሪ ሀሳብ ለማግኘት ከዚህ በፊት በዚሁ አምድ “ፈተናው የጠናበት የዳርዊን ዳርዊኒዝም” በሚል ርእስ ለንባብ ያበቃነውን ጽሑፍ መመልከት ጠቃሚ ነው።)) የአርስቶታልና ጆን ሎክን አቋምም በዚሁ ጽሑፍ መውጫ አንቀፅ ላይ መመልከት ይቻላል።
አሁን “ህልውና”ን ወደ እናት ምድር አውርደን እንመልከት።
“አሸባሪው ህወሓት ከስልጣን ውጪ ለትግራይ ህዝብ ጥቅምና ህልውና ደንታ እንደሌለው በተግባር አሳይቷል”፤ “የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሃገራዊ ጥሪ በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን”፤ “አሁን ኢትዮጵያን በውጭና በውስጥ ከገጠማት የህልውና ፈተና ለመታደግ ህዝቦች በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።”፤ “የውክልና ጦርነት እየተካሄደብን ነው”፤ “የህልውና ዘመቻ” (የአማራ ክልል የክተት አዋጅ ስያሜ)፤ “ለውጥ ለማምጣት በዲፕሎማሲ፣ በውጪ አገር እርዳታ፣ እውነትን በማፈላለግ ተልእኮ፣ በገንዘብ፣ በተሳትፎ ድጋፍ እና ይህን በመሳሰሉ እጃችን ላይ ባሉ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ እና ምላሽ መስጠት የሚረዱ ሪፖርቶችን በማውጣትም ባለው ነገር ሁሉ እንጥራለን።” (የዩኤስኤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን) ወዘተ የዚህ ጽሑፍ የስበት ማእከላት ሲሆኑ በአሁኑ ሰዓት የአገራችን (በተለይ ከፖለቲካል ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች አኳያ) የእለት ተእለት መገለጫዎች ከሆኑም ሰነባብተዋል።
እነዚህ አይነቶቹን በአገራችን ላይ ያነጣጠሩ አደጋና ጣልቃ ገብነቶችን ነው ዶ/ር ሰለሞን አስቀድመው በ”ህልውና?”ቸው በግልፅ ነግረውን፤ ችግሩን ለመቋቋምም የህዝብ አንድ መሆንና በአንድ ልብና ተግባር መንቀሳቀስ የግድ መሆኑንም አሳስበውን የነበረው።
ከላይ ለናሙና ባቀረብናቸው ተቀራራቢ፣ ግን ደግሞ በአንድ ወሳኝ ጉዳይ (አገርና ህዝብ) ላይ ያነጣጠሩ ሀሳቦች መሰረት መረዳት እንደሚቻለው “ህልውና” ምን አይነት ትጥቅ ታጥቆ፣ መለያ ለብሶ፣ የት ቦታ፣ በስንት ቁጥር እየተጫወተ እንደሆነ ተመልክተናል።
ይህን ሁሉ እዚህ ማንሳት ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት ወደ ዶ/ር ሰለሞን አረጋ “ህልውና?” ለመንደርደር ሲሆን የደራሲውን ስራ እዚህ ከመደርደር ጥቂት ማሳያዎችን (መጽሐፉን ማንበቡ እንደሚጠቅም ለአንባቢያን በመጠቆም) ከእውኑ ዓለም ማቅረብ ይቀላል ከሚል እምነት ነው። ለግንዛቤም ቢሆን ከፈጠራውም ሆነ ሌሎች ትረካዎች ገሀዱ ዓለም የበለጠ ያስተምራልና በዚህ መንገድ መሄዱ ጠቃሚ ነው ከሚል እምነት የመጣ ነው።
ዶ/ር ሰለሞን አረጋን የንባቡ ዓለም ሰው በሚገባ ያውቃቸዋል። በተለይም ከ”አጥቢ እንስሳት” ጋር በተያያዘ ከብርቅዬነታቸውም ባለፈ በስራዎቻቸው ጥራት፣ ጥልቀትና አዲስነት (እስካሁን በአገራችን ያልነበረ) ይታወቃሉ። ምናልባትም በፖለቲካው ዓለም ብዙም ላይሆኑ ችለው ሊሆን ይችላል በአብዛኛው ሰው ዘንድ አይታወቁም። ሚዲያውም በየእለት ካሜራውን ሲደቅንባቸው፤ መቅረጸ-ድምፁን ሲወድርባቸው ስለማይስተዋልም ሊሆን ይችላልና “ሰለሞን ሰለሞን …” የሚላቸው ብዙም የለም። አይኑር እንጂ በስራዎቻቸው ግን ከፍ ብለው ሄደዋል።
እነዚህ ደራሲው ከፍ ብለው ከሄዱባቸው ስራዎች መካከል አንዱ ይሄው ልንነጋገርበት እየተንደረደርን ያለነው “ህልውና?” (1992 ዓ.ም) ሲሆን፤ መጽሐፏ ደራሲው ሁሉንም፣ የዛሬውን አገራዊ መከራና ክስተት አስቀድመው የተረዱበት በሚመስል ደረጃ ሀሳባቸውን የገለፁበት፤ ለጋራ መፍትሄም ጥሪያቸውን ያስተላለፉበት ስራቸው ነው።
ይህ የደራሲውን ብቃት፣ እውቀት፣ ልምድና ምልከታ በአንድ ያካተተ መጽሐፍ ባለ160 ገጽና 13 አበይት ርእሰ ጉዳዮችን ያስተናገደ ሲሆን፤ 13ቱም በዓለም አቀፍ ታሪክና ፍልስፍና ዳሰሳ ላይ በመመስረት በአገራችን የህልውና ችግሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ምንም እንኳን የ”ህልውና?”ን ርእስ እዚህ በዚህ መልክ እናስቀምጠው እንጂ (እሱን እንተንትን ከተባለ ሌላ እራሱን የቻለ ስራ ከመፈለጉ አኳያ) መጽሐፉ ላይ ያለው ቅምጠት ግን በዚህ መልኩ አይደለም። የርእሱ ቅምጠት ከላይ ወደ ታች “ህልውና” እና “?” እራሳቸውን ችለው የተቀመጡ ሲሆን ምናልባትም “ከ’ህልው’ና ቀጥሎ ምን ይከተል ይሆን?” የሚል ሀሳብ ትካዜን ያጭር ዘንድ ታስቦም ሊሆን ይችላልና እሱን በዚሁ እንለፈው።
“ህልውና?” በእውቀት አለም ሰው የተደረሰ ከመሆኑ አኳያ ደረጃው ከፍ ይል ዘንድ ይጠበቃል። የአስተማሪ፣ አሳዋቂነት ብቃት ይኖረው ዘንድም እንደዛው። በተለይ አገራዊ ስራ ከመሆኑ አኳያ የአገሪቱንና ህዝቧን ችግሮች ያመላከተ፣ መፍትሄዎችንም የሰነዘረ ቢሆን የሚመለከተው ሁሉ ደስታ ነው። መፍትሄውን ለሌላ ተመራማሪ በተወ መልኩም ማሻገር ከተቻለ አገራዊም ሆነ ምርምራዊ አስተዋፅኦው ከፍ ያለ ነውና ደራሲው ባለ ውለታ ናቸው ማለት ነው።
በ”መፍቻ” ገፃቸው ላይ “ህልውና”ን “Survival”፣ “ህላዌ”ን “Existence” በማለት አቻ ትርጉማቸውን በወዲያ ማዶ ቋንቋ ያሰፈሩት ደራሲው መቅድማቸው ስርም ለተለያዩ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሀሳቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የአማርኛ አቻቸውን እንዳስቀመጡም ይገልፃሉ።
ከ”ህልውና?” ገፆች ሁሉ በይበልጥ ትኩረታችንን የሚስበውና ካለንበት፣ ከአሁኑ ወቅታችን ጋር የሚገጥመው የደራሲው አስተሳሰብ ሲሆን፤ እሱም በመግቢያው ስር ከሰፈሩት አንቀፆች ሰፋና ጠብሰቅ ብሎ የቀረበው አንቀፅ ነው። እንዲህ ይላል፡-
አገራችን የገጠማት ፍዳና የመከራ እሳት፤ በጉልበተኞቹ በተለያዩ መንገዶች እየተራገበ፣ ህዝባችንን እየጠበሰው ይገኛል። ለምንድን ነው እንዲህ የሚያደርጉን? ይህንን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ እንደ ቀድሞው አሮጌና አዲሱ ቅኝ አገዛዝ ብለን በዋዛ የምንገላገለው እንዳይመስላችሁ። ጉዳያቸው ጥሬ-እቃም ገበያም አልመሰለኝም። በእነዚህ ምእራፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ይሰራሉ ብዬ አላምንም። ስጋቴ፣ ጭንቀቴ ስለ ድሮው ጉዳይ አልሆነም። የአሁኑ አያያዛቸው ስለ መኖርና አለመኖር ነው። ወደ ምድር ሰቅ መምጣት ለመኖራቸው አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት ለምድር ሰቅ ቅርብ የሆኑትን አገሮች ህዝቦች አውድመው ይተኩናል ባይ ነኝ። እንደዚህ ወደ ምድር ሰቅ የሚያስፈልስ ሁኔታስ አለ? አዎ አለ። “የበረድ ዘመን ተመልሶ ይመጣል?” [በመጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱት አንዱ ምእራፍ ነው] በሚለው ስር እንደምን እንዲያ ያለ ዘመን በምድር ላይ መልሶ መላልሶ እንደተከሰተ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። […] ያገሬ ሰዎች እንደምን ነው ይሄንን ሁኔታ ልንጋፈጥ የምንችለው? የምንከላከለው? እኔ በበኩሌ ፍርሀቴን በሚከተሉት ምእራፎች ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። መፍትሄ መሻት የሁላችንም ፋንታ ነው። […] የያዝኩትን ወርውሬያለሁ። ከዚህ ወዲያ ማንም ያሻውን ቢለኝ ግዴለኝም።
ይህ ዶ/ር ሰለሞን ይርጋ በ1992 ዓ.ም በ”ህልውና?” አማካኝነት አስቀድመው ያሰሙት የጥሪ፣ የ”ስጋት”፣ የ”ጭንቀት…” ድምጽ ሲሆን የአሁኒቷን ኢትዮጵያም በአራቱም አቅጣጫ የሚገልፅ ነው።
ከላይ እንደተመለከትነውም ሆነ እንደምናውቀው ህልውና የዋዛ ጉዳይ አይደለም። ህልውና የሞት ወይም ሽረት፣ የመኖር ወይም ያለመኖር፣ የመጥፋት ወይም ያለመጥፋት ጉዳይ ነው። ህልውና በሁለት ተፃራሪ ኃይላት መካከል ያለ የተካረረ ግጭት ወይም ጦርነት ሲሆን በሁለቱ መካከል ያለው ግብግብ ከመጥፋት በፊት ማጥፋት ላይ የተመሰረተ እኩይ የመጠፋፋት ዘዴ ነው። በሁለቱም መካከል ለውይይት፣ ድርድር፣ ሰጥቶ ለመቀበል የሚያስችል ምንም አይነት ስፍራ፤ ወይም ሶስተኛ መንገድ የለም፤ አለ ከተባለም ያለው “fives column” የሚሉት “አምስተኛ ረድፍ” ነው። ጉዳዩ “የህልውና ጉዳይ” ወይም ዘመቻው “የህልውና ዘመቻ” ነው ከተባለ በቃ ጉዳዩ የመኖር ወይም አለመኖር ጉዳይ ነው ማለት ነውና ሳይቀድመኝ ልቅደመው እርምጃን ሁሉ ያካትታል። ስለዚህ ከላይ የተመለከትናቸው በአገራችንና በእኛው ላይ የተደቀኑ አደጋዎች በሙሉ በዚህ አይነቱ መነፅር ነውና ሊታዩ የሚገባው ዶ/ር ሰለሞን እንዳሉት የጋራ መፍትሄን፤ አንድ ህዝብ መሆን፣ አንድ አቋም መያዝን ወዘተ የሚሻ ወቅታዊ፤ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
የማርክስን ፍልስፍና ባስረገጠ መልኩ “ብሄርን የሚሰራው ካፒታሊዝም ነው።” (በምእራፍ 10 መግቢያ ላይ “እንዴት ቢሉ ሰዎች ለስራ ብለው ጉልበታቸውን ለመሸጥ ብለው፣ ከትውልዶቻቸው ቀየዎች ወደ ሌሎች ስፍራዎች እየሄዱ እየኖሩ፣ ችግሮቻቸውና መፍትሄዎቻቸው አንድ እየሆኑ፣ እየተዋለዱ …”) የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን አሁን ላይ ከመቶ ዓመት በፊት ፋሽኑ ያለፈበትን የብሄር ፖለቲካ ሞቶ ከተቀበረበት አውጥተው “ብሄሬ፣ ብሄሬ …” በሚሉ፤ ፖለቲከኛ ባልሆኑ “የፖለቲካ/ደም ነጋዴዎች” አማካኝነት የሚቀነቀነውን አጫራሽ ፖለቲካ የማይቀበሉ ሲሆን፤ የዚህ አይነቱ፣ በአገራችን አትራፊ እየሆነ የመጣውን የዘቀጠ ፖለቲካ (ከ”የውጪ እጅ…” (ገጽ 90) ድጋፍ ጋር) ከእሳቸው ዘመን፣ “የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት” (ገጽ 94) ይቀነቀንበት ከየነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ (“የተማሪዎች እንቅስቃሴ” በሚል የሚታወቀው) ጋር በማወዳደር የአሁኑን ዘመን የፖለቲካ ሸቃጭነት የሚያጣጥሉት ሲሆን አገር ከማፈራረሱ በፊት ሁላችንም አፍ ከልብ ሆነን ልናስወግደው እንደሚገባ ያሳስባሉ። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ “አንድ ሰው – አንድ ድምጽ” (ገጽ 99) እንደሆነም (ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማለታቸው ይመስላል) ያስገነዝባሉ። ከሁሉም የላቀው መፍትሄም “አንድነት” (ለምሳሌ ገጽ 92፣ 98) መሆኑን አጥብቀው ያሳስባሉ።
ይህ በ1992 ለአደባባይ የበቃ የዶ/ር ሰለሞን ይርጋ የ”ህልውና?” ስጋት ከምን ግዜውም በላይ ስጋታችን ሆኖ የሚያግባብን (የደራሲውን አስቀድሞ የማየት ችሎታ እያደነቅን) ሰሞኑን በአገራችን በሁለት ተፃራሪ ሀይሎች መካከል የነበረው ምልልስ ሲሆን፤ እሱም ከህወሓት ቃል አቀባይ በኩል “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስ እንሄዳለን” የሚለውና ከአንድነት ኃይሎች በኩል “ኢትዮጵያን ለማዳን እስከ ሲኦል ድረስ እንሄዳለን” የሚለው ነውና ከዶክተሩ ማስጠንቀቂያ በባሰ “ከክፉ ሰውረን፤ ወደ መከራም አታግባን፣ ኢትዮጵያ ለዘላዓለም ትኑር …” የሚባለው ይሄኔ ነው እንላለን።
እንደ ፈላስፎቹ፤ “ደስተኛ ህይወት ማለት ማሰላሰል፣ በምክንያታዊነት (ሰዎችን ከሌሎች እንስሳት የሚለየው የከበረ ባህሪ) በመመራት መኖር ማለት ነው። ነገር ግን አንድ ሰው እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ ተገቢ የሆነ ማህበራዊ ከባቢ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ይህ ከባቢ ደግሞ ዕውን ሊሆን የሚችለው በጥሩ መንግስት አማካኝነት ነው።” የሚለው አርስቶትልም ሆነ በአንድ አገር የተሟላና የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠው አይነት መብት እንዲኖረው ካስፈለገ “የላቀ የመንግስት አይነት መኖር አለበት። […] “የእያንዳንዱን ሰው ደህንነት ማረጋገጥ የመንግሥት ዋነኛ አላማ” መሆን አለበት እስከሚለው ጆን ሎክ ድረስም ሆነ ከዛ በፊትና በኋላ ያሉት ሁሉ እንዳሉት (የእነዚህ ፈላስፎች ሀሳብ በማይመጥናቸው መልኩም ቢሆን በ”የፍልስፍና ሀ ሁ” ውስጥ ቀርቧል) ሰዎች አይደለም ህልውናቸው ሊፈርስና ሊደረመስ ቀርቶ ምንም አይነት የመብት ጥሰት ሳይደርስባቸው ሊኖሩ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከፈጣሪ ቀጥሎ ሀላፊነቱ የመንግስት ነውና በዚሁ እናብቃ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013