አሸባሪው የህወሓት ቡድን የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት የሚለውን የፖለቲካ ፅንሰ ሃሳብ ከግራ ዘመሞች የፖለቲካ ፍልስፍና ትርጓሜ አንጻር መውሰዱን ጫካ በገባ ማግስት ጀምሮ ሲያስተጋባው የነበረው ነው።ነገር ግን ከግራ ዘመሞች የወሰደው የብሄር ብሄረሰቦች መብት የሚለው ፅንሰ ሃሰብ ስላልገባው ትህነግ በስልጣን ዘመኑ ንድፈ ሃሳቡን መሬት ላይ በማውረድ ለመተግበር ሲቸገር አይተናል።
ይህንን ሲባል በምክንያት እንጂ በስሜት ላለመሆኑ አያሌ ማሳያዎችን መጥቀስ ቢቻልም ለዛሬው ግን የተወሰኑትን መርጠን እንመለክት።ትህነግ ወደ ጫካ ገብቶ መታገል ሲጀመር ራሱን እንደተራማጅ (ግራ ዘመም) ያይ ነበር።ይሁን እንጂ ትህነግ አንዴ ግራዘም ሲመስል አንዴ ቀኝ ዘመም ሲመስል የት ላይ እንኳን እንዳለ ሳያውቅ እና ራሱን ፈልጎ ሳያገኝ ከመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰ ቡድን ነው።እንደውም የብሄሮች መብት በሚል ሽፋን ለዘመናት በሰላምና በአንድነት ኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን ያቃቃረና የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ ብዙ የስራ እኩይ ቡድን መሆኑ ጊዜ አጋልጦታል።
ስለትህነግ ቀኝ ዘመምነት ወይ ግራ ዘመምነት ለመመለከት የቀኝ እና የግራ ዘመሞች ከሚለያዩባቸው አብይ ጉዳዮች ማነሳት ተገቢ ነው።የቀኝ እና የግራ ዘመሞች ከሚለያዩባቸው አብይ ጉዳዮች አንዱ አካታችነት (inclusion) ነው።አገር አፍራሹ ህወሓት የት ላይ ነው የሚለውን ለመለየት በአካታችነት ላይ ቀኝ ዘመሞች እና ገራ ዘመሞች ምን ይላሉ? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው።ግራ ዘመሞች አካታችነት (inclusion) አስመልከቶ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች ወይም ቡድኖች፤ ስደተኞች እና ወዘተ የሚባሉት በሙሉ ባለሙሉ መብት ተጠቃሚዎች ይሁኑ፣ ማንነታቸው ሰብአዊ ክብራቸው ይጠበቅ፣ የመረጡት ቦታ የመኖርና የመሥራት መብታቸው ይከበር (ነባራዊው ስርዓተ ማኅበር እየተለወጠ መሔድ አለበት) ይላሉ። ቀኝ ዘመሞች ደግሞ መጤዎች እና ስደተኞች ቢቻል እንዳይገቡ ይደረግ፣ ካልተቻለ ባሕል እንዳይበርዙ ይደረግ፣ ወይም ወደ መጡበት ይመለሱ (ነባራዊው ስርዓተ ማኅበረ “እንግዶቹን” እየዋጠ መሔድ እንጂ መለወጥ የለበትም ) ይላሉ ።
ትህነግ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በመለጠጥ እስከመገንጠል ሲል እና በማኒፌስቶው እንደገለጸው የቀኝ ዘመሞች ማሳያ ሆነውን አሃዳዊነትን እታገላለሁ ሲል እራሱን ተራማጅ ወይም ግራ ዘመም እና ለብሄር ብሄረሰቦች የቆመ አድርጎ በመሳል ነበር።ትህነግ ራሱን ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ጠበቃ፤ ጋሻ እና መከታ ያስመስል እንጂ የብሄር ብሄረሰቦች ጸር መሆኑን መገንዘብ የፈለገ ማንኛውም አካል አሸባሪው ህወሓት በራሱ ቅኝት ከርክሞ ያዘጋጃቸውን እና አሁን ላይ ክልሎች እየተጠቀሙበት ያለውን የክልሎች ህገ መንግስት በማየት ብቻ በቂ ነው። ምክንያቱም እስኪ የየትኛው ክልል ህገ መንግስት ነው «ይህ ህገ መንግስት በክልላችን የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ህገ መንግስት ነው።» የሚለው? ያለ አይመስለኝም።ምናልባት ካለም ከአስር ክልሎች ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ክልሎች ይመስሉኛል።የእነኚህም የጠራ እና ግልፅ ያለ አይደለም።
አሁን ላይ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ብሄረሰቦች የሚፈናቀሉት እና መብታቸው እየተደፈጠጠ ያለው ትህነግ ከርክሞ በቀረጸው ህግ መንግስት ነው።ታዲያ የቱ ላይ ነው ትህነግ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት የግራ ዘመሞች የሆነውን ብሄር ብሄረሰቦች በክልሎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሶ የመስራት እና የመኖር መብት ያስከበረው? ይልቁንም የቀኝ ዘመሞችን መርህ በመከተል አንዱን መጤ፤ ሌላውን ስደተኛ ወዘተ በማስባል ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ በማድረግ አበክሮ ሲሰራ ነው የኖረው።
ሌላው ትህነግ እራሱን ግራዘመም ወይም ተራማጅ አድርጎ የሚቆጥረበት ግል-ነጻነት (personal freedoms) የሚለውን ፖለቲካ መርህ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ግራ እና ቀኝ ዘመሞች ምን ይላሉ? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው።ግራ ዘመሞች ሰዎች በግላቸው እና በዕውቀት በሚወስኑት ጉዳይ መንግሥት ጣልቃ መግባት የለበትም ይላሉ።ይህም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብቶች፣ የውርጃ መብቶችን እና በአጠቃላይ ከተፈጥሮ ጋር የተጣረሱ እና ሰብአዊነት የረሱ ምግባሮችን ይጨምራል።ቀኝ ዘመሞች ደግሞ ለእምነት፣ ባሕል እና ወግ ቅድሚያ በመስጠት ዜጎች በብዙኀኑ እሴት ተቀባይነት የሌለውን የግል ጉዳይ ሳይቀር መንግሥት ሕጋዊ ማዕቀብ ሊጥልበት ይገባል ይላሉ።በነገራችን ላይ ህወሓት ግራ ዘመም መስሎ ለመታየት የሞከረው እና የተሳካለትም እዚህ ላይ ብቻ ነው።ምክንያቱም የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ማንነት በመደፍጠጥ ከጫካ ጀምሮ ስልጣን ላይ ወጥቶ መልሶ እስከሸፈተበት ድረስ እየሰራው ያለው ይህንን ባህልና ወግ አጥፊ ተግባር ነው።
በትምህርት ፖሊሲውም ላይ አተኩሮ ከሰራባቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያኖች ማንነታቸውን እንዲረሱ እና ከሃገራቸው ይልቅ የውጭ ሃገራትን እንዲናፍቁ በማድረግ ሃገር ጠል ትውልድ እንዲፈጠር ለማድረግ ነበር።
በነገራችን ላይ አሻባሪው ትህነግ የግራ እና የቀኝ ዘመም የፖለቲካ መርሆች የተፋለሱበት የማፊያዎች ጥርቅም ነው። በዚህም ሳቢያ ትህነግ ባልተገነዘበው እና በማያውቀው በሁለቱ ጎራዎች የፖለቲካ መርሆች የፖለቲካ በርሃ ገብቶ እየተርመጠጠ የኖረ ቡድን ነው።
ትህነግ ራሱ የማያውቅን የብሄር ብሄረሰቦች መብት እተገብራለሁ በሚል ቅዠት በሃገራችን በሚገኙ የተለያዩ ብሄሮች ላይ ያልፈጸመው በደል የለም።ይህንንም ስል በስሜት እንዳልሆነ ለማሳየት በትህነግ የጭካኔ በትር ክፉኛ የተጎዱ ብሄረሰቦች መቼ፣ እንዴት እና የት የሚለውን ማየት ተገቢ ነው።ለምሳሌ ህወሓት በ1968 ባወጣው ማኒፌስቶው ከገፅ 14 እስከ 18 እንደገለጸው አማራ የሚባልን ብሄረሰብ እንደ ገዥ መደብ በመቁጠር «አማራ የሚባለውን መደብ ካልጨረስን አርፈን አንተኛም» ይላል። በበረሃ እያለ ይዘፍነው የነበረውም “………..አርኪበካ ብሎ ነአሻይ አማራ” ነበር።ይሄን እኔ በአማርኛ ለመተርጎም ይዘገንነኛል።ሞራሉም የለኝም።ህወሓት ግን በበረሃ ሲጨፍረበት እና አሁን እያስጨፈረበት ያለው ማታጋያው ዘፈን ይሄው ነው።ለዚህ ዘፈን እና ማኒፌስቶ አይደል አንዳርጌ መስፍን ቅሌት በሚለው መፅሐፉ
“እነኚህ በልገኞች እዩ ሲቀናጡ ፣
አማራን አድኑት ብለው ትእዛዝ ሰጡ ።” የተሰመረበት ቃል ወርቁ”ማደን፣ ማሳደድ” መሆኑን ልብ ይሏል።እንዴት ነው አንድን ብሄር ለማጥፋት የሚታደነው ?
የወልቃይት፣ የራያ እና የመላው አማራ ህዝቦች በባዶ ስድስት ምን ያህል በአማራው ላይ ግፍ እንደተፈጸመ በአንድ ወቅት ገብረመድህን አርአያ የተባሉት የቀድሞው የህወሓት ታጋይ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ያደረጉትን ውይይት ማየቱ ብቻ በቂ ነው።እንደ ገብረ መድህን አርአያ ገለጻ፤ በባዶ ስድስት ታስቦ እና ታቅዶ በተሰራ ጉድጓድ ውስጥ የአማራ በተለይም የወልቃይቴዎች ዘር ያለቀበት ነው።
ወልቃይት አካባቢ የተሰራው የግድያ ቦታ ሰዎችን በአንዴ ለመጨረስ ታስቦበት የተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ፤ በዚያ ለሚደረገው ማናቸውም ግፍ ተቆጣጣሪው ስብሃት ነጋ እንደነበር እና ግድያውን ደግሞ የሚያስፈፅመው ጌታቸው አሰፋ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ታይተዋል።
በባዶ ስድስት የአዶልፍ ሂትለር አጃቢዎች «ኤስ ኤሶች» በአይሁዶች ላይ ከፈጸሙት ግፍ በቁጥር ያነስ እንደሆን እጅ በአገዳደሉ ጭካኔ እና ግፍ ግን የህወሓቶች አረመናዊነት ይበልጣል።በባዶ ስድስት በወንዶች የዘር ፍሬ እና በሴቶች ጡት ላይ እስከ 20 ኪሎ ግራም ጠጠር ያንጠለጥሉ ነበር።በዚህ ጊዜም የሴቶች ጡት እና የወንዶች የዘር ፍሬ ውሃ ሆኖ ፈሷል።የወንደች የዘር ፍሬ እና የሴቶች ጡት ውሃ ሆኖ እንደሚፈስ ያወቅኩት ህወሓት ሲያደርገው በነበረው ጭካኔ ነው ይላሉ አቶ ገብረመድህን አርአያ።
“በድሎ ካሱኝ ፤
እሾህ ይዞ እጄን ዳብሱኝ።”
የሚለው ትህነግ በፊት በሰራው ስራ ከመጸጸት ይልቅ አሁንም በአማራ ህዝብ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ማለቱ አሸባሪው ህወሓት ከሰውነት በታች ያለ ድርጅት መሆኑን ዋነኛ ማሳያ ነው።
ሌላው በትህነግ ግፍ ከተፈጸመባቸው ብሄሮች መካከል የአፋር ህዝብ ነው።የአፋር ህዝብም እንደ አማራ ህዝብ ሁሉ መሬቱ ተንጥቆ፣ በክልሉ የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብቱ ሲዘረፍ የበይ ተመልካች በማድረግ የግፍ ግፍ ፈፅመውበታል።በአፋር የሚገኙትን የጨው፣ የፖታሺየም ወዘተ ምርቶች ያለምንም እና ማንም ከልካይነት እንደፈለገ ያልሸጠ እና አሜሪካ እና አውሮፓ የተደላቀቀ ህይወት ያልመሰረተ የትህነግ ሰው የለም።አቶ ዩሱፍ የተባሉ የአፋር ተወላጅ ምሁር እንደተናገሩትም የአፋር ክልል የትግራይ አንድ ግዛት እስኪመስል ድረስ ህወሓቶች የፈለጉትን ሲፈጽሙ ነው የኖሩት።
ይህ ግፋቸው አልበቃ ብሎ ሰሞኑንም 240 ንጹሃን በአሸባሪው ህወሓት በግፍ ተገድለዋል።ከዚህ ውስጥ 170 የሚደርሱት ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆኑን አልጀዚራ መዘገቡ የሚታወስ ነው።በአፋሮች ላይ የደረሰውም ይህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በሰው ልጆች ላይ የተደረገ የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው።
በኦሮሚያ የፈጸሙት ግፍም እንደዚሁ እልቆ መሳፍርት የለውም።የእሩቁን እና ውስብስብ የሆነውን በኦነግ ስም የታሰሩትን እና የተገደሉትን እንተው እና በ2008 እና በ2009 ዓ.ም ብቻ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ግፍ መመልከቱ በቂ ነው።ምክንያቱም ከ2008 ዓ.ም በፊት የነበረውን ግፍ ቆጥረን ስለማንጨርሰው።
በ2009 ዓ.ም በወለጋ አንድ እናት ላይ የተፈጸመውን የትህነግ የአረመኔአዊነት ጥግ የሚረሳ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። በ2009ዓ.ም በአረመኔው የህወሓት ትዕዛዝ ወለጋ ውስጥ አንድ ህጻን ይገደላል።የእናት አንጀት ሆኖባት በትህነግ የተገደለ የልጇን አስከሬን ልታነሳ የጥይት መዓት በላያዋ ላይ እየፈሰሰ ወይኔ ልጅ ብላ ወደ አስከሬኑ ትሄዳለች።«ግፍ አይፈራ መሬት እንክርዳድ ያበቅላል» እንዲሉ ግፍ የማይፈራው ትህነግም ወደ ልጇ አስከሬን የሄደችን እናትን በማስገደድ እና በመደብደብ በልጇ አስከሬን ላይ እንድትቀመጥ በማድረግ በዓለም ላይ ተደርጎ የማይታወቅ ግፍ ፈጸመ።እንዴት ነው ልጅን ገሎ በአስከሬን ላይ አስገድዶ ማስቀመጥ።ምን አይነት አረመኔነት ነው? ይሄ ሰቆቃ መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያን አእምሮ ውስጥ የሚፋቅ አይደለም።
በሐረር አካባቢም በተመሳሳይ አንድ የኦሮሞ እናት የገጠማትን የሚረሳ ሰው ያለ አይመስለኝም።አንድ እናት በቤት የጎደላትን ከገበያ ገዝታ በማምጣት ከእርፍ ጋር ሲላፉ የሚውሉ ቤተሰቦቿን ለመመገብ ወደ ገበያ ታቀናለች።ጠዋት ስትወጣ ከእናት በስተቀር ሁሉም የቤተሰቡ አባል ማሳውን ለማረም ወደ እርሻ መሬቱ ተሰማርቷል።እናትም ለቤተሰቦቿ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ገዝታ ከጨረሰች በኋላ ማሳው ላይ ሲደክም ለዋለው ቤተሰብ ምግብ አዘጋጅታ ገበታውን እሰክታቀርብ እየተቻኮለች ወደ ሰፈሯ ትመለሳለች።ነገር ግን ገበያ ደርሳ ስትመለስ ማሳቸውን ሲያርሙ የነበሩ ቤተሰቦቿ በሙሉ ሰብአዊነት ባልፈጠረባቸው አረመኔዎች በጥይተ ታርመው የአስከሬን ክምር ጠበቃት ።
አንድ እናት አገር ሰላም ብላ ከገበያ ለቤተሰቦቿ ቆጣጥራ ስትመለስ ቤተሰብ የአስከሬን ነዶ እንደማግኘት እና ከቤተሰብነት በቅፅበት ወደ ብቸኝነት እንደመቀየር የሚዘገንን አለ እንዴ?
በአብዲ ኢሌ ታጣቂዎች ከሶማሌ የተፈናቀሉት የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች እና እንዲሁም በቢሾፍቱ እሬቻ ሲከበር በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ የሚዘነጋ ሰው አለ ብዬ አላስብም።እጅጉን ዘግናኝ ግፍ ስለነበር ።
በጋምቤላ በአኛዋክ ህዝብ ላይ የተፈጸመውስ እንዴት ሊረሳ ይችላል።የአኛዋክ ህዝብ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በገፍ ለመዝረፍ በማሰብ ጁንታው በዴሴንበር 2003 ዓ.ም በሶስት ቀናት ውስጥ 424 የአኘዋክ ብሄረሰቦች መገደላቸውን እና 16,000 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ጎረቤት ሱዳን መሰደዳቸውን The Shadow Report በሚል The International Human Rights Law Clinic Washington College of Law, Washington DC, USA በተደረገው ጥናት ተመላክቷል።
በተመሳሳይም የሶማሌ ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት በርካታ ግፎች ተፈጽመውበታል። በክልሉ ያለውን ሀብት ተቆጣጥሮ ያለማንም ከልካይ ለመመዝበር እንዲመቸው አሸባሪው ህወሓት በሶማሌ ህዝብ ላይ ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ ፈጽሟል። በራሱ አምሳል ገዳይ ቡድን በማደራጀት ንጹሐን በጠራራ ፀሐይ እንዲገደሉ አድርጓል። ቤተ ክርስቲያኖችን በማቃጠል የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ በብዙ ሠርቷል። ሰዎች ብሄራቸው እየተለየ ከቤታቸው ተጎትተው እንዲገደሉ አድርጓል። ሰዎችን ከአራዊት ጋር በማሰር በዚህ ዘመን ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ግፍን ፈጽሟል።
ኢትዮጵያን ለማዳከምና የራሱን ነፃ ሀገር ለመመስረት እንዲያመቸው በማሰብ የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚል አንቀጽ ቢያስቀምጥም፣ እንኳን ሀገር ቀርቶ ክልል ለመሆን በጠየቁ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ መብት ከማፈን ጀምሮ በርካታ ግድያና እስር ፈጽሟል። በዚህም የሲዳማ ብሄር ክልል የመሆን ጥያቄውን ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ቢጠይቅም ይህ አሸባሪ ቡድን አመራሮችን ከማሰርና ከማሰቃየት ባሻገር በርካታ ንጹሐን ዜጎችን በአደባባይ ከመረሸን አልተመለሰም።
በብሄር ብሄረሰቦች ስም ራሱን ደብቆ ብሄር ብሄረሰቦች በጭካኔ አረመኔአዊ ብትሩን ሲያሳርፍ ኖሯል።ብሄር ብሄረሰቦች ትህነግ ትክክለኛ ለብሄር ብሄረሰቦች ያልቆመ መሆኑን ሲረዱ በአንድ ድምፅ ትህነግን ከስልጣን አባረሩት።ከስልጣኑም ተባሮ “ድመት መንኩሳ” ሆነ እና ነገሩ የጥፋት ሱሱ አገርሽቶበት የብሄር ብሄረሰቦችን ወኪል እና የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን መከላከያን ከጀርባው መታ።ይህ አጋጣሚም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን በድጋሚ ሊናወጥ በሚችል የአንድነት መሰረት ላይ ማስቀመጥ ቻለ።ዛሬ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራና በደል ያልተረዳ ህዝብ የለም።ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መጠኑ ይለያይ እንጂ በብሄሩ ወይም በሃይማኖቱ ምክንያት ዘግናኝ ግፎች የተፈጸሙበት በመሆኑ የጭካኔዎች ሁሉ አባት የሆነውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ክተት አውጇል።በተፈጠረው አንድነትም የአሸባሪው ህወሓት ግብዓተ መሬት ተፈጽሞ አንድነቷ የተጠበቀና የበለጸገች ኢትዮጵያ የምናይበት ቀን እሩቅ አይሆንም።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013