በተለያዩ ርቀቶች በርካታ ከዋክብትና በድንቅ አቋም ላይ የነበሩ አትሌቶችን ወደ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ይዛ የተጓዘችው ኢትዮጵያ ለስምንት ወራት እንደተዘጋጀችውና እንዳላት አቅም በርካታ ሜዳሊያዎችን ሳትሰበስብ የቶኪዮ ቆይታዋን ቋጭታለች። በሰለሞን ባረጋ የ10ሺ ሜትር ወርቅ፣በለሜቻ ግርማ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ብር፣ በ5ሺ ሜትር የጉዳፍ ፀጋይ ነሐስና በለተሰንበት ግደይ የ10ሺ ሜትር ነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ የአትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዡን ከአለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ሆናም ፈፅማለች።
ከመቶ ሰማንያ በላይ አገራት ምንም አይነት ሜዳሊያ ባላስመዘገቡበት የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ይህ ውጤት የሚናቅ ባይሆንም፤ ያላትን አቅም በአግባቡ ተጠቅማ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በግልፅ የሚታዩ አስተዳደራዊ ክፍተቶች እንቅፋት መሆናቸው በርካቶችን አሳዝኗል።
በአስተዳደራዊ ክፍተቶች ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ሜዳሊያዎች ባለፉት ቀናት ብታጣም፤ የኦሊምፒኩ የመጨረሻ ውድድሮች በሆኑት የሴቶችና የወንዶች የማራቶን ውድድሮች ወርቅ ቢቀር ሌሎች ሜዳሊያዎችን ኢትዮጵያ እንደምታስመዘግብ ትልቅ ተስፋ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ አርብ ሌሊት በተካሄደው የሴቶች ማራቶን አትሌት ሮዛ ደረጄ አራተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፤ ዘይነባ ይመርና ብርሃኔ ዲባባ ውድድሩን አቋርጠው መውጣታቸው ይታወቃል። ቅዳሜ ሌሊት በተካሄደው የወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን እንደምታስመዘግብ ሲጠበቅም ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ውጤት ተመዝግቧል።
ባለፈው የለንደን ማራቶን የርቀቱን የአለማችን ኮከብ ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌን ጭምር ማሸነፍ የቻለው ሹራ ቂጣታ በውድድሩ ከዘጠኝ ኪሎ ሜትር በላይ መቆየት ሳይችል አቋርጦ መውጣቱ ያልተጠበቀ ነበር። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሳይ ለማም ከሃያ ሰባት ኪሎ ሜትር በኋላ አቋርጦ ለመውጣት ተገዷል። የርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን ሌሊሳ ዴሲሳም ከሰላሳ ኪሎ ሜትር በኋላ ውድድሩን መቀጠል ሳይችል ቀርቶ የመጨረሻዎቹ የኢትዮጵያ የሜዳሊያ ተስፋዎች ሊመክኑ ችለዋል።
የርቀቱ ቁጥር አንድ አትሌት ኪፕቾጌ 2:08:38 በሆነ ሰአት ሁለተኛውን የኦሊምፒክ ማራቶን ድል ካለ አንድ ተቀናቃኝ በመጎናፀፍ የታሪካዊውን ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላን ታሪክ መጋራት ችሏል። ኢትዮጵያ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ታሪክ በሰራባት ቶኪዮ ከሃምሳ ሰባት አመት በኋላ ታሪክ የሚደግም አትሌት አለማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ሜዳሊያ ውስጥ የሚገባ አትሌት ማጣቷ በርካቶች ያልጠበቁት ክስተት ነው።
ውድድሩን ከጀመሩት 106 አትሌቶች 76ቱ ሲጨርሱ 30 አትሌቶች አቋርጠዋል፡፡ መጀመሪያ ላይ ውድድሩን ያቋረጠው ሹራ ቂጣታ መሆኑም አስደንጋጭ ነበር።
በአትሌቲክስ የሜዳልያ ሰንጠረዡ አናት ላይ ዩናይትድ ስቴትስ በ7 የወርቅ፣ 12 የብር፣ እና 7 የነሐስ በድምሩ በ26 ሜዳልያዎች፣ ጣልያን በ5 የወርቅ፣ 0 የብር፣ እና 0 የነሐስ በድምሩ በ5 ሜዳልያዎች፣ ፖላንድ በ4 የወርቅ፣ 2 የብር፣ እና 3 የነሐስ በድምሩ በ9 ሜዳልያዎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ ኬንያ በ4 የወርቅ፣ 4 የብር፣ እና 2 የነሐስ በድምሩ በ10 ሜዳልያዎች ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆና ስትጨርስ ኡጋንዳ በ2 የወርቅ፣ 1 የብር፣ እና 1 የነሐስ በድምሩ በ4 ሜዳልያዎች ከዓለም ዘጠነኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
በ32ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያን በ4 ስፖርቶች የወከሉት 38 ኦሊምፒያኖች ናቸው። ከ30 በላይ አመራሮች ልዑክ ሆነው ተጉዘዋል። የ250 ሚሊየን ብር በጀት ወጪ ተደርጓል። በዚህም ኢትዮጵያ 1 የወርቅ ፤ 1 የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ሰብስባ በአጠቃላይ በኦሊምፒኩ ከአፍሪካ 3ኛ ከዓለም 55ኛ ሆና ጨርሳለች። ኢትዮጵያ ከሜዳሊያዎቹ በተጨማሪ 10 የኦሊምፒክ ዲፕሎማዎችን ስታስመዘግብ 11 ኦሊምፒያኖቿ ማጣሪያዎችን ማለፍ አልቻሉም። 7 ኦሊምፒያኖቿ ውድድራቸውን አቋርጠዋል።
ኢትዮጵያውያን ሜዳሊያ ማስመዝገብ ቀርቶ ውድድሩን መጨረስ በተሳናቸው የወንዶች ማራቶን በአንፃሩ በየትኛውም ውድድር ላይ አንድም ታሪክ የሌላቸው ትውልደ ሶማልያውያን የኔዘርላንድርና የቤልጂየም አትሌቶች አብዲ ናጌዬና ባሽር አብዲ እንደ ቅደም ተከተላቸው 2:09:58 እና 2:10:00 በሆነ ሰአት ተደጋግፈው የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ከኬንያውያን እጅ መንጠቃቸው አዲስ ክስተት ነበር።
ሁለቱ ትውልደ ሶማሊያውያን ለተለያየ አገር ቢሮጡም በውድድሩ ላይ ያሳዩት አስገራሚ መደጋገፍና ስኬት ከቻምፒዮኑ ኪፕቾጌ በበለጠ መነጋገሪያ አድርጓቸዋል። ኪፕቾጌን ተከትሎ በሁለተኛነት ከጨረሰ በኋላ ሌላው የአገሩን ልጅ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲያገኝ በመጠናቀቂያው አካባቢ ሲያበረታታ የነበረው ትውልደ ሱማሊያዊው አብዲ ናጌዬ የተወለደው ሞቃዲሾ ሲሆን በ 6 ዓመቱ በኔዘርላንድ በስደተኛ ተጉዘው ነበር ።ይሁንና በኔዘርላንድስ ለአራት ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ከቤተሰቡ ጋር በሶሪያ እና በሶማሊያ ተመልሰው መኖር ጀምረው ነበር። አማርኛ አቀላጥፎ የሚናገረው አብዲ በኃላም በኢትዮጵያም በስደተኝነት በመምጣት ከኖሩ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ኔዘርላንድ የጉዲፈቻ ቤተሰብ አግኝቶ ተመልሷል።
አትሌት አብዲ ናጌዬ አትሌቲክስ ውድድር ከገባ በኋላ እ.ኤ.አ በ 2016 ቦስተን ማራቶን 8 ኛ ሆኖ አጠናቋል።በዚያው ዓመት በተካሄደው በሪዮ በኦሎምፒክ ማራቶን 11 ኛ ሆኗል። በ 2018 በበርሊን ጀርመን በተካሄደው የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን ተወዳድሮ ሩጫውን መጨረስ አልቻለም ነበር።
በኋላም በኬንያ በመጓዝ ልምምዱን በማጠናከር እና ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ ጨምሮ የታዋቂው የአለማችን ስመጥር አትሌቶች ስብስብ በሆነው የኔዘርላንዱ “NN Running Team “ ቡድን አባል በመሆን ለስኬት በቅቷል።
ሌላኛው የማራቶን የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው በሱማሊያ የተወለደው ነገር ግን በቤልጅየም ከ 12 ዓመቱ ጀምሮ ዕድገቱ የሆነው ባሽር አብዲ ይባላል። አትሌት ባሽር ወደ አትሌቲክስ የገባው እ.ኤ.አ በ 2008 የሩሲያው የአውሮፓ አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ሞ ፋራህ ሲወዳደር ተመልክቶ ሩጫውን ለመጀመር በመነሳሳቱ ነበር። ባሽር የስፖርት ህይወቱን በቤልጅየም ወደ ሩጫ ከመግባቱ በፊት ተስፋ የተጣለበት የቀኝ መስመር የእግርኳስ ተጫዋች ሆኖ በታዳጊ ፕሮጀክቶች ይጫወትም ነበር።
ወደ አትሌቲክስ ስፖርት ከገባ በኋላ ባሽር በአውሮፓ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ቤልጂየምን በረጅም ርቀት ከመወከሉ በፊት በሁለት ዓመታት ጥበባዊነት የተቀላቀለበት ውሳኔን ከራሱ ጋር በመወሰን በረጅም ርቀት ሩጫ መወዳደር የቀጠለው። እ.ኤ.አ. በ 2012 በሞስኮ የዓለም ሻምፒዮና ተወዳድሮ 23 ኛ ደረጃን ከመጨረሱ በፊት በአውሮፓ ሻምፒዮና ላይ በ 10 ሺ ሜትር አራተኛ ሆኖ አጠናቋል። እ.ኤ.አ. በ 2014 የጉዳት ችግሮች አጋጥሞት ነበር። ይኸም ጉዳት በ 2015 እና በ 2016 አቋሙን ከማበላሸቱ በፊት በ 5000 ሜትር እና በ 10,000 ሜትር ውጤቱ ላይ ብዙም መሻሻል አልቻለም።
በኋላም አቋሙን በማስተካከል እና በተለያዩ በአውሮፓ ውድድሮች በመሣተፍ አቋሙን እንደገና እንዲመለስ ማድረግ ችሏል። እ.ኤ.አ በ2020 በተደረገው የብራስልስ ዳይመንድ ሊግ በታሪክ ውስጥ ሁለተኛውን ፈጣን የአንድ ሰዓት ሩጫ በማስመዝገብ ወቅታዊ አቋሙ መመለሡን አሳይቷል። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እስከመጨረሻው በመፅናት የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም