አቶ ውብሸት ታዬ ላለፉት 20 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ቆይቷል፡፡ ህወሓት መራሹ መንግስት ለ27 ዓመታት በህዝቡ ላይ ሲያደርስ የነበረውን ግፍ ሲቃወም የቆየ ሲሆን፣ በዚህም ጥርስ ተነክሶበት የበቀል በትር አርፎበታል፡፡ በፀረ ሽብር ህጉ ተከሶም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ዓመታት ማረሚያ ቤት አሳልፏል። ማዕከላዊ ተብሎ በሚጠራ ስፍራም ለምርመራ ጨለማ ክፍል ውስጥ 90 ቀናት ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. 2012 የሂውማን ራይትስ ዎች አዋርድ፣ 2013 የሲ.ኤን.ኤን አፍሪካን ጆርናሊስት አዋርድ እና ፔን ቱ ፔን ፍሪደም ኦፍ ኤክስፕሬሽን አዋርድ (Pen2 Pen Freedom of Expression award 2020) የተሰኙ ሦስት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል፡፡
በማረሚያ ቤት እያለና ከእስር በኋላም የሀገሪቱን ፖለቲካ ጉዞና መፃዒ ዕድል አመላካች የሚሆኑ «የነፃነት ድምጾች ሐምሌ 2006 ዓ.ም፣ ሞጋች እውነቶች ነሐሴ 2008 ዓ.ም፣ ኢትዮጵያዊነትን የመመለስ ተጋድሎ 2010 ዓ.ም፣ ከገባንበት መውጫ ሰኔ 2012 ዓ.ም እውነቱ ሲገለጥ ነሐሴ 2012 ዓ.ም» የተሰኙ መፅሃፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ እነሆ በዛሬ ዕትማችንም እንግዳችን አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- በጋዜጠኝነት በቆየህባቸው ዓመታት ሚዲያው ለኢትዮጵያ ምን ያህል ጠቅሟል ብለህ ታስባለህ?
አቶ ውብሸት፡- ለሚዲያ ለፖለቲካው፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚየወዊ ጉዳዮች ትልቅ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነትም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ 1984 ዓ.ም የፕሬስ ህግ በወጣበት ወቅት 380 ለሚደርሱ ሚዲያዎች ፈቃድ የተሰጠበት ወቅት ነው፡፡ እንደ ጅምር መልካም ነበር፡፡ በሂደት ያለውን ግን ከፋፍለን ማየት ይቻላል። 1997 ዓ.ም እጅግ በጣም ትልቅ የሚዲያ ሚና የጎላበት ወቅት ነበር፡፡
ሚዲያ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ተመጋጋቢ ናቸው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ለሚዲያው የእምርታ ወቅት ነበር። ከዚህ በኋላ ግን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ተብሎ የወጣው 590/2011፣ የምርጫ ህግ አስመልክቶ የወጡ አፋኝ አዋጆችና ሌሎች ህጎች ደግሞ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ህግመንግስቱ ሃሳብን በነፃነት የመግልፅ መብት አጎናፅፎ በሌላ በኩል እጅግ አፋኝ ህጎች ነበሩት። የፀረ ሽብር አዋጁም ሚዲያ ላይ የተቃጣ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በርዕሰ አንቀጽ ላይ የፖለቲካ አስተሳሰብን ደግፎ መፃፍ አይቻልም ይል ነበር፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ አስተሳሰብን የሚገድብ ነገር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚያ አዋጆች ሚዲያውን በህግ አግባብ ለመግራት ወይስ ለጭቆና ዋሉ ማለት ይቻላል?
አቶ ውብሸት፡- ብዙ ክርክር ሲደረግ ነበር፡፡ 1997 ዓ.ም አጠቃላይ ፖለቲካ ምህዳሩ ለቀቅ ያለ ነበር። በወቅቱ ደግሞ አብዛኛው የመንግስት ሚዲያዎችም ለማን ሽፋን ይሰጡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ምን ያህል ከመንግስት አገልጋይነት ወጥቷል የሚለውም ገና በቂ መልስ አላገኘም፤ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ከአፍሪካ ኬኒያን ብንመለከት በጣም ርቀው ሄደዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ይቀረዋል፡፡
ልክ እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሉ ሚዲያዎች በኬኒያ፣ ሱዳንና ግብጽ አሉ፡፡ በብሄራዊ ጥቅሞቻቸው ላይ ፈጽሞ አይደራደሩም፡፡ ከዚህ በተረፈ መንግስትን መተቸት ካለባቸው አብጠልጥለው ይተቻሉ፡፡ በመሆኑም ይህን የመሠለ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በወቅቱ የሚወጣው አዋጅ ሚዲያን በህግ አግባብ ለመግራት ነው የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ መደናገጥ ነው የተፈጠረው፡፡ ‹‹የነፃነት ድምፆች›› በሚለው መፅሀፌ ላይ ሁኔታዎችን በሚገባ ለማስመቀጥ ሞክሬዋለሁ፡፡ በበርካታ ጊዜ የሚዲያ ባለሙያዎች ይታገቱ ነበር፡፡ እኔ ራሴ አራት ጊዜ ታግቻለሁ፡፡ ይህ ህጋዊ መሠረት አልነበረውም። ያለው ውርጅብኝ እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ በፀረ ሽብር ህጉ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የፕሬስ ህጉም በጣም ከባድና ፕሬሱን ወደ ጨለማ የወሰደ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ብዙ ነገሮችን ማየት ይገባል፡፡ ፕሬሱ በህግ ብቻ ሳይሆን በቴክኒካል ጉዳዮችም ይጎዳል፡፡ ታክስና የመሳሰሉት አሉ፡፡ 30 ሚሊዮን ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ ያሰማራች ሀገር ወረቀት ገበያ ላይ ስንት ነው ብሎ መጠየቅ መልካም ነው፡፡ በጎ ነገሮች አሉ፡፡ ሰዎች ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ ግን መረጃ የማግኘትና የፕሬስ ተደራሽትና ነፃነት ምን ደረጃ ላይ ነው ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ሚዲያው ለህዝብና ለመንግስት በእኩል ዓይን ያስተናግድ ነበር?
አቶ ውብሸት፡- የነበሩበትን ማሰብ አስቸጋሪ ነው። የገዢው ፓርቲ አገልጋይ የሆኑ ግን በነፃው ሚዲያ ሥም የሚሰሩ ነበሩ፡፡ የሚዲያ የበላይነት ይዘው የነበሩ አሉ። ማስታወቂያዎችን በሙሉ ይዘው ከመንግስት በጀት ተበጅቶላቸው የሚሰሩ ነበሩ፡፡ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሲጠቀሙ ነበር፡፡ ፍትሃዊ ባለመሆኑም ነው ሚዲያ ላይ ብዙ ችግር የፈጠረው፡፡ ተከፍሏቸው መንግስትን የሚያገለግሉ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ዋጋ ከፍለው ሲሰሩ ነበር፡፡ ሙያዊ የሆኑ ህጎችን አክብረው የሚሲሩ ነበሩ። በዴሞክራሲ አድገዋል የሚባሉ ሀገራት ሚዲያዎች የማን ደጋፊ ናቸው ተብሎ በሥም መፈረጅ ላይ ቢደርሱም የሙያው መሠረታዊ ጉዳይና ፍትሃዊነትን አይረሱም፡፡ የእኛ ነው ብለው የሚያስቡን ማሳደግና በሚሊዮኖች መድቦ አብሮ የመሥራት ሁኔታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ካፒታል በመጠቀም የእኔ ናቸው ብሎ ወደሚያስባቸው በተለይም የኋልዮሽ ማህበረሰባዊ ታሪካቸው ወይም ብሄር መሰረት ተደርጎ አድሎ ይፈፀም ነበር፡፡ በመሆኑም በአንድ ሜዳ ላይ እኩል ተወዳዳሪ መሆን አስቸጋሪ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የነበረው መንግስት ሚዲያውን በገንዘብ ይደልላል?
አቶ ውብሸት፡- አዎ በሚገባ ይጠይቃል፡፡ መጥተው አብረን እንስራ ይላሉ፡፡ እኔም ብዙ ሚዲያ ውስጥ ሰርቻለሁ፤ በዚህም ብዙ ነገር አይቻለሁ፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ይባል የነበረው ተቋም ይህን ሥራ ያከናውን ነበር፡፡ እኔም ይህ ገጥሞኛል። ብዙ ሚዲያዎችም የሥርዓቱ አገልጋይ ሆነዋል። ተላላኪ ሚዲያዎች መፍጠር ነበር፡፡ በመጨረሻም ሥርዓቱም 27 ዓመት ቆይቶ የፈረሰው መሰረቱ ሕጋዊ ሳይሆን የጥቅመኞች ስብስብ ስለነበር ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ውስጥ ህወሓት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በመጨረሻ ወጣቶች በጠጠር ወርውረው አባረውታል። በሚዲያው ላይ ክሶች ይበዙ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ያለበት ክስ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ እኔም የዚሁ ሠለባ ነበርኩ፡፡ ማተሚያ ቤቶች እንዳያትሙ ማድረግ፣ ሥርጭቱን ማወክና በወቅቱ የታተሙ ጋዜጦች እንዲወረሱ ይደረግ ነበር፡፡ ከፖሊስ ጣቢያ ውጭ እንታሠር ነበር፡፡ እኔም ይህ ፈተና ገጥሞኛል። ከምንም በላይ ደግሞ እኔን ጨምሮ ረጅም ዓመታት እስርም ተፈርዶብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስምንት ዓመት ማረሚያ ቤት የቆየኸው በምን ተከሰህ ነው?
አቶ ውብሸት፡- በፀረ ሽብር ህጉ ተከስሼ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ስምንት ዓመታት ማረሚያ ቤታ ነበርኩ። ማዕከላዊ ምርመራ ጨለማ ክፍል ውስጥ 90 ቀናት ቆይቻለሁ። የተለዩ ሰዎች ብቻ የሚታሰሩበት ክፍል ውስጥ ነበርኩ። በዚህ እስር ቤት ውስጥ ከባድ ድብደባ ነበር፡፡ እኔንም ደጋግመው ሲያሰቃዩኝና ሲደበድቡኝ ነበር፡፡ ምርመራ ይካሄድብኝ የነበረው ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ነበር፡፡ ይህን ምርመራ የሚያደርጉት ከሥራ ሰዓት ውጭ ሲሆን በጣም ያሰቃዩኝ ነበር፡፡ በማዕከላዊ ምርመራ በጣም መራር ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ምርመራው በጣም ሠብዓዊነት የጎደለው ነበር፡፡ በርካታ ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ህመማቸውን መናገር የማይፈልጉ ሲሰቃዩ የሚኖሩ አሉ፡፡ እኔም አሁን ቀኝ ጆሮዬን ሙሉ ቀዶ ህክምና ካልተደረገልኝ በደንብ መስማት አይችልም፡፡ እኛ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይጮሁልን ስለነበር እንደሌሎቹ ሙሉ አካላችንን አላጎደሉም እንጂ በርካቶች በጣም ዘግናኝ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ጋዜጠኛ ማዕከላዊ በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማወቅ ጥረት አላደረግህም?
አቶ ውብሸት፡- ጥናት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። በዚህ ቦታ ድብደባው የተለየ ነበር፡፡ ብዙ ሰው የሚያውቀው የተወሰኑ ታዋቂ ሰዎችን ነው፡፡ ግን በርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉ ነገራቸውን ያጡበት ሥፍራ ነው፡፡ በተለይ ከጎንደር አካባቢ የሚመጡትን 70 ከመቶ ያኮላሹ ነበር፡፡ በርካቶች ገመናቸውን ደብቀው እንጂ ብዙ ያልተወራ ነገር አለ፡፡ ለዚህ ሀገር ለውጥም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ይህን ያደርግ የነበረው ኃይል ፍርዱን ሳይቀበል ተበትኗል፡፡ ግን ይህን ሰቆቃ የሚያክም ሥራ መሠራት ነበረበት፡፡ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ አንዳንዶቹ የአዕምሮ ህመማቸውና ቁስላቸው ሳያገግሙ ነበር ስልጣን የተሰጣቸው፡፡ ቢያንስ የተወሰኑ ወራት ዕረፍት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ነበሩ፡፡
በሴቶች ላይ ይደረስ የነበረው በጣም ዘግናኝ ነበር። ገመናቸውን መናገር ስለማይፈልጉ እንጂ በአካላቸው ላይ የሚደረገው ከባድ ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልም ላይ አንዳንዶቹ ተናግረዋል፡፡ ለእኛ ቀርበው ሲናገሩ ደግሞ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ ሰዎች ያልገለፁት ብዙ ነገር አለ፡፡ አራት ሆነው አንድ ሰው ይደበድቡ ነበር፡፡ ለመናገር ዘግናኝ ነገሮች ተፈፅመዋል፡፡ በድብደባቸው የተነሳ ብዙ ሰዎች ለከባድ ጉዳት ተዳርገው እየኖሩ ነው፡፡ የማይናገሩት ብዙ ናቸው፡፡ እኔ ለሰባት ዓመታት ዝዋይ ማረሚያ ቤት ነበርኩ፡፡ በዚህ ወቅት ህክምናም ይከለከል ነበር። እኔም በዚህ ስቃይ ውስጥ አልፌያለሁ፡፡ ከለውጡ ወዲህ በካፒታል ሆቴል 400 ሰዎች በተሳተፉበት መድረክ በርካቶች ህክምና የሚያስፈልጋቸው ብዙ እንዳሉ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናግረን ነበር፡፡ በወቅቱ እሺ! ይስተካከላል ብለውን ነበር፤ ግን ምንም ሳይደረግ ዝም ተባለ፡፡ ከረጅም ዓመታት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ማህበረሰቡን ተቀላቅለው ሲሠሩ የነበሩትን ህወሓት መልሶ ገድሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከህወሓት ባህሪ አኳያ ታራሚዎችን በብሄር የማጋጨት አዝማሚያ አልነበረም?
አቶ ውብሸት፡- ሰው ማጋጨት ብቻ ሳይሆን ማስገደል ነበር፡፡ በደርግ ዘመን የማዕከላዊ መርማሪ የነበረ ሃምሳ አለቃ ተሾመ ባዩ የተባለ ሰው ማግኘት ስላልቻሉ ልጁ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ነበር፡፡ አባትየው ውጭ ነበር ያለው፡፡ አባትህ ያሰቃየን ነበር፤ የእኛን ጓዶቻችን በድሏል፣ መርምሯል ብለው ያስቡ ነበር፡፡ ግን ቀን ጠብቀው ልጁን ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ገድለውታል፡፡ ልጁን ያስፈራሩት ነበር፡፡ ልጁ ላይ አንድ ቀን ጉዳት ይደርስበታል ብለን በመስጋት ለሰብዓዊ መብቶች አመልክተን ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት አንዱን ታራሚ በታራሚ ይሰልላል የሚባለው እውነት ነው?
አቶ ውብሸት፡- በተዛባ ሁኔታ ከሆነ ቦታ የመጡና የእኛ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች አዕምሯቸውን አዛብተው በጥናት ያስገቡ ነበር፡፡ ልዩነት ለመፍጠር የሚያመጧቸው ደግሞ የአማራ ብሄር ተወላጅ፣ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ እያሉ ነበር፡፡ ምግብ ይመጣላቸዋል፤ ታራሚውን ይከታተላሉ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይወጣሉ። ስንመለከታቸውም መረበሽ ይፈጠርባቸዋል፡፡ ይህን ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የሚመለከታቸው የለም፡፡ እነርሱ ግን የመደናገጥ ባህሪ አላቸው፡፡ ስለላው በደንብ ነበር የሚሰራው፡፡ ሆን ተብሎ ልዩነት ለመፍጠር አንድ ተሰሚነት ያለውን ሰው ለጥያቄ ወደ ውጭ ከታራሚዎች መሃል በተደጋጋሚ ይጠሩ ነበር፡፡
የማረሚያ ቤት አዛዦችም ከአንድ አካባቢ የመጡ ነበሩ። በአጋጣሚ አንድ ወረቀት እኛ ውስጥ ቢገኝ ወዲያውኑ ፍተሻ ይደረግ ነበር፡፡ በመሆኑም መፃፍ በራሱ ክልክል ነበር፡፡ እኔ በዚህ ፈተና ውስጥም ሆኜ ሁለት መፅሃፍትን ፅፌ ነበር፡፡ ህግ የሚፈቅድ ቢሆንም እኔ ያለሁበት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርዓን አይገባም ነበር፡፡ የአንገት ማህተብ አውጡ ይባል ነበር፡፡ ህግ የሚባለው ነገር አልነበረም፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ከባድ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ዳኝነት የነበረው በህገ አራዊት ነው፡፡ ለማምለጥ ሞከሩ ተብሎም በጣም ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው ነበር፡፡ የሰው ልጅ መቋቋም የማይችለው ድብደባና ስቃይ ያሳለፉ ሰዎችም ነበሩ፡፡ በቃ! ህግ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ፈጣሪ ትረፍ ካለህ ትተርፋለህ፡፡ ፍርድኞችንም እየገደሉ ዝም የተባሉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ተቀይረው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ታሪክ ወደ ኋላ ከተመዘዘ ደግሞ 1997 ዓ.ም በቃሊቲ ታራሚዎች ላይ የነበረውን ጭፍጨፋ ማንሣት ይቻላል፡፡ ገድለው ነው ቤት የሰሩባቸው፡፡ በመጨረሻ ግን የህወሓት አፈንጋጭነት ባህሪ መስመር እየለቀቀ ስለመጣና ስጋት ስለነበረባቸው ወደ መቀሌ እንዲገቡ ሆኗል፡፡ ግን በዚህ ሁሉ ሂሳቡ አልተወራረደም፤ ፍትህም አልተገኘም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁሉ ጥፋት እያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው እንደ ኢህአዴግ ይቅርታ ጠይቀው ነበር፡፡ ህወሓት ለምን መቀበል ከበደው?
አቶ ውብሸት፡- በመጀመሪያ የህወሓትን ሥሪት መረዳት ይገባል፡፡ ‹‹ከአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት ጅብ ሲጮህ ይፈራርሳል›› ይባላል፡፡ አመጣጡ እንዴት ነበር ብሎ ማሰብ ግድ ነው፡፡ መስራች አመራሮቹን አብዛኞቹን ቃለመጠይቅ አድርጌላቸዋለሁ፡፡ አፈጣጠሩ 1967 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ወቅት በኢትዮጵያ በለወጥ ዋዜማ ላይ ነበር፡፡ መሬት ለአራሹ የታወጀበት ሁኔታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊውዳል ሥርዓት ለመውጣት እየለፋ ነበር፡፡
ብርሃን እየመጣ ነው በተባለ ዋዜማ የካቲት 1967 ዓ.ም ህወሓት ወደ ጫካ ገባች፡፡ ይህ ምንም መሰረታዊ ምክንያት አልነበረውም፡፡ ለትግራይ ነፃነት ብለው ነው የተነሱት። በሂደት በነበረው የራሳቸውን አባላት መጨፍጨፍና መግደል የተለመደ ነበር፡፡ ሲፈጠሩ ራዕያቸው ምን ነበር ብሎ ማየት ይገባል፡፡ ራሳቸውም የፃፏቸው አቶ ገብሩ አስራት፣ የውብዳር እና ስዬ አብርሓ የፃፉትን መፅሐፍ ማንበብ ይቻላል፡፡ የወይዘሮ አረጋሽን ቃለመጠይቆች ማየት ይጠቅማል፡፡ በርሃብ ወቅት የመጣን ዕርዳታ ለጦርነት ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ለድርር ብለው እየጠሩ ተደራዳሪዎችን የሚገሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ራዕያቸው መገንጠል ብቻ ሳይሆን በማኒፌስቷቸው የሆነ ማህበረሰብን እንደ ጠላት አድርገው ስለዋል፡፡ በእርግጥ የትግራይ ህዝብ ወንድማችን፣ ባህልና ታሪክ የምንጋራ፣ ደማችንና ስጋችን ናቸው፡፡ ትንሽ መርዝ ሙሉ ጋን መልካም ነገር እንደምትመርዘው ሁሉ እነዚህ ጥቂት የህወሓት አመራሮች የትግራይን ህዝብ መርዘዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደርገው 1978 ዓ.ም ድረስ አንድን ማህበረሰብ ጠላት አድርገው ፈርጀው ሲሠሩ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም ማኒፌስቶውን ቢቀይሩትም በውስጥ ግን ሴራውን ቀጥለውበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በተለየ ሁኔታ ለይተው የሚያጠቁት ማህበረሰብ የትኛውን ነበር?
አቶ ውብሸት፡- ዛሬ እነ ጌታቸው ረዳ ስለ ታሪክ ማወራረድ የሚያወሩት ነገር የአማራ ኤሊት በሚል ሽፋን መላ አማራውን ዒላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው። በማዕከላዊ ምርመራ የጎንደር አካባቢ ልጆችን 70 ከመቶ ያኮላሿቸው ነበር፡፡ ዘር እንዳይኖር ይደረግ ነበር፡፡ በአጋጣሚ የተደረገ ነገር አይደለም፡፡ የላሊበላ እና ወልዲያ አካባቢ ልጆችን ሆን ብለው ይጎዱ ነበር፡፡ ስሪታቸው በክፋትና በተንኮል ነው፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም ሆን ብለው ሀገሪቱን ወደብ አልባ አድርገዋል፡፡ በኤርትራ በኩል ያለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ስብሃት ነጋ ለዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ ነበር፡፡ ስለግብረ ገብና አንድነት ማውራት በጣም ነውር አድርገውት ነበር፡፡ የሰንደቅ ዓላማን ክብር ዝቅ አድርገው በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አንደበት ጨርቅ እየተባለ ይንቋሸሽ ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ብለው መጡ፡፡ የኢትዮጵያን ግብረገብነትን ለማዳከምና የወጣቱ አስተሳሰብ እንዲመክንና ብሎም እንዲዳከም በሚገባ ሲሠሩ ነበር፡፡ ጫትና አደንዛዥ እፆች አካባቢ ተለይቶ በተወሰነ ማህበረሰብ ለማፍዘዝ ታቅዶበት ሲሰራ ነበር፡፡ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዝርፊያ እና ሌሎች ላይ በስፋት በሌብነት የተሰማሩበት አካባቢ ነበር፡፡ ዝርፊያውም ዘግናኝ ነበር፡፡ ህወሓት ስልጣን ላይ እያለ ባለፉት 27 ዓመታት 30 ቢሊዮን ዶላር ማሸሻቸውን የዓለም ባንክ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ይህ በሽብርም ያስጠይቃቸው ነበር፡፡ እኔም ለመታሰሬ አንዱ ምክንያት ይህን በመፃፌ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ይቅርታ አይገባቸውም፡፡ የሚያውቁት መግደል፣ ማሳደድ ነው፡፡ የታሪክና የባህል ነውር ነው የሚያውቁት፡፡ ለታሪክ ግድ የላቸውም፤ ኢትዮጵያዊ ስሜትም አልነበራቸውም፡፡ የባህር በርን የግመል መጠጫ ብለው ይገልፁ ነበር፡፡ ቁራጭ መሬት ብለው ያወራሉ። ግን ሉዓላዊነት እንደዚህ አይገለፅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በፓርላማ ይቅርታ ሲጠይቁ እነርሱ አልተዋጠላቸውም አዲስ ነገር ነው የሆነባቸው። እነርሱ የሚያውቁት ኢትዮጵያዊነትን ማንቋሸሽ፣ ስድብ፣ ማጣጣል እና ማራከስ ስለሆነ ስለፍቅርና አንድነት ሲወራ አይገባቸውም፣ ተዓምር ነው የሆነባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመው በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተዋል፡፡ እንወደዋለን በሚሉት ሕዝብና በአዝመራ ወቅት ለምን ይህን ማድረግ ፈለጉ?
አቶ ውብሸት፡- ሁለት ነገሮችን ማንሳት አለብን። የሚጠበቅ ነገር ነበር፡፡ መጀመሪያ በነበረው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም ነበር፡፡ ሰባት ሚሊዮን የሚሆነውን ትግራይ ያለውን ህዝባችን ያለህግና ሥርዓት ማስተዳደር አይችልም ነበር፡፡ በመሆኑም የማይገባውን ጁንታው በጉልበት መቀጠል አይችልም ነበር፡፡ ሽግግር ላይ ስላለንና ኃይላችንን በየቦታው መበታተን ስለማይገባ እንጂ አንድ ቀን ይህ ነገር እንደሚመጣበት ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ወደ ዕርምጃ ገብቷል፡፡ የገዛ የትግል አጋር ይፈጁ የነበሩና ቀድሞውንም ቢሆን አካሄዳቸውን ይቃወሙ የነበሩትን ይጨፈጭፉ ነበር፡፡
ሁለተኛው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ይህን መፈፀሙ ለእነርሱ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ሰሜን ዕዝ ትልቅ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ ክምችት ያለበት በመሆኑ ይህ ዕዝ ከተመታ እንደፈለገን ኢትዮጵያን ማተራመስ እንችላለን ብለው ነው አስበው የነበረው፡፡ በእርግጥ በዚህ ዕዝ ላይ በጥናት ተደግፎ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈፅሞበታል፡፡ ይህ በጊዜው ለህዝብ ይፋ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማውራት እኔ መብቱም አቅሙም ፍላጎቱም ኃላፊነቱም የለኝም። ግን ከደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያን ብለው የሄዱትን ጀግኖች ጨፍጭፈዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሱዳን 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቃ እንድትገባ እና ተደፍረን የማናውቀው ነገር እንዲሆን ዕድሉን አመቻችተዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ላለፉት 27 ዓመታት በተጠና ሁኔታ የዘር ማጥፋት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም በየሚዲያው ሲናፈስ የሥራቸውን ውጤቱን አይተናል፡፡ ከግብጽ ጋር ያለንበት ሁኔታ ይታወቃል፡፡ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋርም ያለንበት ሁኔታ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም በማለት ነው የማቃወስ ስራ ውስጥ የገቡት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት መቀሌ የመሸገው ህዝብ ስለሚወደው ነው?
አቶ ውብሸት፡- ህዝቡ መቀሌ ውስጥ አፓርታይድ ብሎ የሚጠራው መንደር አለ፡፡ ስለዚህ እንኳስ ሌላው ማህበረሰብ ለወጡበት ማህበረሰብም ታማኝ አይደሉም። ከሀገሪቱ በዘረፉት ሃብት ቤተሰቦቻቸውን ወደ ውጭ ልከው ያኖራሉ፣ ያስተምራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኮታ የመጣው የውጭ የትምህርት ዕድል 99 በመቶ የሚሆነውን የራሳችን ሰው ለሚሉት ይሰጣሉ፡፡ 1983 ዓ.ም ወዲህ ኢትዮጵያን ባህሏን፣ ክብሯንና ታሪኳን የማናጋት ሥራ ላይ ተጠምደው ነበር፡፡ የባህር ወደብ እስከማሳጠት ነው የሄዱት፡፡ ዓለም አቀፍ ህጎችን እንኳን የባህር ወደብ ቢፈቀድልንም ከኤርትራ ጋር የሆነው ግልጽ ነው፡፡ በዚያ ዘግተው ከሱዳን ጋር ሆኑ፡፡ በሀገር ውስጥ ደግሞ በየቦታው እሳት ይለኩሱ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት አስተዳደራዊ ወሰኖች በሚል ሰበብ ግጭቶች በየቀኑ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ መሰል ግጭቶች ደብዛቸው እየጠፋ የመጣው ለምንድን ነው?
አቶ ውብሸት፡- አሜሪካኖቹም ይህንኑ ያደርጋሉ። ምዕራባውያኑ ሌላውን ዓለም በማመስ ጥቅማቸውን ያሳድዳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው እሳት ተለኮሰ፡፡ ያለፍናቸው ነገሮች ይበቁ ነበር፡፡ ሀገር ያረጋጋሉ ተብሎ ተስፋ የተጠላባቸው ምሁራን ዋነኛ እሳት አቀጣጣይ ሆኑ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚባሉትም በአሜሪካ እና የአረቦች ኤምባሲም ደጅ ይጠኑ ነበር፡፡ 24 ሰዓት ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 27 ዓመታት በየቦታው ህዝቡን ሲያናክሱ ነበር፡፡
አሁን የሚሉት እኮ ‹‹ባለቤት ሲያፍር እንግዳ ይጋዛል›› እንደሚባለው ሂሳብ እናወራርዳለን እስከመባል ደርሰዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ መች ሂሳቡን አወራረደ? አወራርደን የማንጨርሳቸው ነገሮች እኮ አሉን፡፡ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ትክክለኛው ፍትህ ለመበየን ሁኔታዎች ስላልፈቀዱ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ቃሊቲ ሲጨፈጭፉ እና ሲያስጨፈጭፉ የነበሩ የፖሊስ አዛዦችና ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ነበሩ፡፡ ያን ሁሉ ለፍትህ ማቅረብ አይቻልም ነበር፡፡ እያወራን ያለነው 27 ዓመታት ሙሉ የሆነውን ነገር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአሁን በኋላ በህወሓት ላይ ፍትህ ይበየናል ብለህ ታስባለህ?
አቶ ውብሸት፡- በጣም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ከፍትህ አያመልጡጥም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ሀገር ከናዚ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከ70 ዓመት በኋላ ለፍርድ እየቀረቡ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ወንጀል አያረጅም፤ አንድ ቀን ፍትህ ይበየናል፡፡ ›› በውስጥም በውጭም ደጋፊ ካለህ፣ መሳሪያ እና ገንዘብ ካለ ለጊዜው መንቀሳቀሳቸው አይቀርም፡፡ ይህን ሁሉ ለማቅረብ ጊዜ ይፈልጋል እንጂ ከፍትህ አመለጡ ማለት አይደለም፡፡ ማነው ለፍትህ የሚያቀርባቸው የሚለውንም ከጊዜ ጋር እናየዋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት 27 ዓመታትን ስህተት ለማስተካከል ባለፉት ሦስት ዓመታት የመጣበትን ሂደት በተለያየ ጎራ የሚያነሱ አሉ፡፡ የአንተ ምልከታስ?
አቶ ውብሸት፡- እንደ ሀገር ብዙ ውጥረቶች አሉ፡፡ አሁን በዚህም በዚያም የትምህርት ተቋማት መቀጠል አለባቸው። የትራንስፖርት፣ ጤናው ሴክተር እና ሌላው መደበኛ ህይወት መቀጠል አለበት፡፡ ደህንነቱ፣ የሀገር መከላከያው መስተካከል ነበረበት፡፡ ይህን ማስተካል ቀላል አይደለም፡፡ ሰዎች ሲማረሩ እረዳቸዋለሁ፣ ግን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነባራዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ ይገባል። በዚያው ልክ ግን በአሁኑ ወቅት በፍጥነት መከናወን ያለባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ በሃሳብ የሚታገል እና ጫካ ገብቶ የሚታገል አለ፡፡ ለዚህ ሁሉ ጊዜውን ያሰላን አይመስለኝም፡፡ 27 ዓመት ሙሉ የታገስናቸውን ነገሮች የነበረውን በሦስት ዓመት ማስተካከል ከባድ ነው፡፡
ወደ ቤተመንግስት መሣሪያ ይዞ የሄደው ወታደር ቢሳካለት ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ሰዎች ብዙ ጠብቀው ነበር፤ ግን በታሰበው ልክ ባለመሆኑ ቢያማርሩ መገረም የለብንም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ሆነው ዓላማህ ዓላማዬ ብለው ከልብ ደግፈው ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ ሆነው እጅግ በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ደግሞ በውስጥ መካሪ ሆነው የሚጎትቱ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በጣም ብዙ ይሰራል ብለው ብዙ የመጠበቅ ሁኔታ ስለነበር በህዝብ መፍረድ አይቻልም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት መሪ ሲሳደብና ሲታሠር እንጂ እንዲህ በፍቅርና መቀራረብ አልተለመደም። ከተሠሩት ያልተሰሩ ብዙ ነገሮች መኖራቸውንም ማሰብ ይገባል፡፡ ግን ደግሞ በሚዲያው፣ በፖለቲካው ምህዳር፣ በምርጫ እና የመሳሰሉት ላይ የተሠራውን እውቅና መስጠት መልካም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት የሰራችውን ግፍ ኢትዮጵ ውያን በግልጽ እየተቃወሙት የውጭ ሚዲዎች እና ማህበረሰቡ በአንድ ላይ ሆነው ጫና ለማሳደርግ የፈለጉት ለምንድ ነው?
አቶ ውብሸት፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩን የዓለም ሎሬት ብለው ሸልመው በሚዲያቸው አቆለጳጵሰው ጊዜና ቦታ አልበቃ ብሏቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ኋላ ተመልሰው በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ህወሓት ያን ሁሉ ግፍ ሲያደርስ፣ በጣም ጨኳኝ ሆኖ ለምን እያዩና እየሰሙ አለፉ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲክስ እጅግ በጣም ወሣኝ የሆነች አንድ ትንሽ ቡድን ብለው መጫን ለምን ፈለጉ የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ተላላኪ መንግስት መፍጠር ይልጋሉ። አሁን ይህ የሚሳካቸው መስሎ የታያቸው አይመስለኝም። ኢትዮጵያ በተጨባጭ ወደየት እየሄደች ነው? ሌላው እኔ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በጣም አከብራለሁ፣ እወዳለሁ። ግን እዚህ ሀገር ሲሆን የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች መብትና አገላለፁ በትክክለኛው መንገድ የተያዘ ሳይሆን ለተወሰነ ቡድን ጥቅም በስሌት የተሰራ ነው፡፡ ህወሓትን ያን ሁሉ ግፍ እያደረገ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ እየሠራ ለምን ዝም ተባለ ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ በዚህ ውስጥ ከገባን ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ግን ማወቅ የሚገባው ነገር በቀጣናው ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ የምትጓዝና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ፍላጎት የላቸውም፡፡ እነዚህ አካላት ዓላማቸው እጅግ ደካማ ግን ደግሞ ተላላኪ ሀገር መፍጠር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ ከመጣጭበት ጉዞ አኳያ ህወሓትን እንዴት ትገልፃለህ?
አቶ ውብሸት፡- ህወሓትን ዘመናት ናቸው የሚገልፁት። ትልቁን ምስል ለመሳል ከ1967 ዓ.ም የብርሃን ፍንጣቂ ሲጀምር የገቡበት ጫካ አሁን ተመልሰው የገቡበት ነው፡፡ ኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ የመራ መልሶ ጫካ የገባበት ነው፡፡ ከመጡበት ወደ መጡበት የሄዱበት ነው፡፡ ህወሓት የታሪክ ነውረኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በነውጥ የሚጠቀስ ድርጅት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፤ ተጨማሪ ሐሳብ አለህ?
አቶ ውብሸት፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡ የሀገራችን ሚዲያ ገና ብዙ መሥራት አለበት፡፡ 110 ሚሊዮን ህዝብ ይዘን ያለን ሚዲያ ገና አላደገም፡፡ ህወሓት እና ሚዲያ ዓይንና ናጫ ሆነው ነው የኖሩት፡፡ አሁን እነዚህ ነገሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ ሚዲያው እጅግ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ይህን በሚገባ መገንዘብና አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል። ሚዲያው እንደ አራተኛው መንግስት የሚታይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ፕሬስን የመሰሉ አንጋፋ ተቋማት ይዘን በዚህ ደረጃ መገኘት የለብንም፤ ሚዲያው ብዙ መደገፍ እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ ባለሃብቶችም ቢሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ ሊገቡበትና ሊደግፉት ይገባል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም