እ.አ.አ በ2019 መጨረሻ ላይ የተከሰተው አስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም ከ201 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አዳርሶ ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሕልፈት ዳርጓል፡፡ በመላው ዓለም የቫይረሱ ስርጭት በቶሎ ይቀንሳል ተብሎ የተጣለው ተስፋ ብዙም ዋጋ ያለው አይመስልም፡፡ ቫይረሱ ያስከተላቸው ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶችም ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ ቫይረሱ ግዙፍ ምጣኔ ሀብትና ጠንካራ የጤና ስርዓት አላቸው በሚባሉ አገራት ላይ ያስከተለው ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ምድሪቱን አስደንግጧል፡፡
ቫይረሱ ለወራት መላውን ዓለም አዳርሶ ትንሽ ጋብ ያለ ቢመስልም በሌላ ዙር ወጀቡ ዳግመኛ ዓለምን ማስጨነቁን ቀጥሏል፡፡ የሰውነትን የመከላከል አቅምን ያሳድጋሉ የተባሉ ክትባቶች ተመርተው ለዜጎች እየቀረቡ ቢሆንም ከክትባቶቹ የስርጭት ፍጥነትና ቫይረሱ ከፈጠረው ጫና በተጨማሪ የክትባቶቹ ክፍፍል ፍትሐዊነት ላይ ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። አንዳንዶቹ ክትባቶችም ተጓዳኝ የጤና እክሎችን ይፈጥራሉ ተብለው ወቀሳ የሚቀርብባቸው ናቸው። ይባስ ብሎም ቫይረሱ በአዳዲስ ዝርያዎች (Variants) መልኩን እየቀያየረ በመከሰት ዓለምን በእጅጉ እያስጨነቀ ነው፤ለሐኪሞችና ተመራማሪዎችም መላው የጠፋ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በበርካታ አገራት የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ አገራትም ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣል የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ሙከራ እያደረጉ ነው፡፡
ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተነገረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ284 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ከአራት ሺ 400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በእርግጥ ቫይረሱ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእስያ ያደረሰውን ጉዳት ያህል ባያደርስብንም ‹‹ምንም አላደረገንም›› ማለት ግን አይደለም፡፡ ቀላል የማይባሉ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጫናዎችን አሳርፎብናል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ የደረሱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደው ውጤት ተመዝግቦባቸዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የነበረው የቫይረሱ ስርጭትና የሟቾች ቁጥር መጨመር ግን የብዙዎች ቤት በቫይረሱ መከራ እንዲፈተን አድርጓል፡፡ በትራንስፖርትና በሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም በምርጫ ቅስቀሳዎች፣ በስብሰባዎች፣ በተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎች እና በበዓላት ወቅት የተስተዋለው ግዴለሽነት እንደዋነኛ መንስዔ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ለሳምንታት ያህል ቅናሽ አሳይቶ የነበረው የቫይረሱ ተጠቂዎችና የሟቾች ቁጥር (ምርመራ ያደረጉ ሰዎች ቁጥርም ዝቅተኛ እንደነበር ሳይዘነጋ) በአሁኑ ወቅት በአስፈሪ ሀኔታ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ይህም ሦስተኛው ዙር የወረርሽኙ መቅሰፍት አገሪቱን እንዳይፈትናት ተሰግቷል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊትም ሆነ ባለፉት ሳምንታት በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የተመለከትናቸው ስብሰባዎችና ሰልፎች ከቫይረሱ ስርጭት አንፃር እጅግ አስደንጋጭ ነበሩ፡፡ ትልልቅ ስቴዲየሞች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ሞልተው፤የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ባላደረጉ ሰዎች ተጨናንቀው ተመልክተናል፡፡ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረና አዳዲስ ዝርያዎችም እጅግ በሚያስጨንቅ ፍጥነት እየተዛመቱ በሚገኙበት ወቅት፣ መሰል ሁነቶችን በማንአለብኝነትና በቸልተኝነት ማከናወን እጅግ አስገርሞናል፡፡ የሰልፎቹና የስብሰባዎቹ ባለቤቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቀመጡ ገደቦችን ጥሰው ያከናወኗቸው ድርጊቶች ውጤታቸው ምን እንደሆነ ባለፉት ወራት በተግባር ተመልክተናል፤በቀጣይም የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በነበረባቸው ወራት ያጋጠመውን ዓይነት ቀውስ እንዳንመለከት ያስፈራል፡፡
በእርግጥም እነዚህ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩና የቫይረሱን ስርጭት ከግምት ውስጥ ያላስገቡት ስብሰባዎችና ሰልፎች የቫይረሱን ስርጭት ማባባሳቸው አይቀርም፡፡ ከሁሉም ይበልጥ የሚያስገርመው ነገር የመንግሥት ተቋማትና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወጣውን መመሪያ በመጣስ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው መታየታቸው ነው። ብዙ የመንግሥት ባለስልጣናት ከመመሪያው ድንጋጌዎች በተቃራኒ ሲጨባበጡ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ተቀራርበው ሲያወሩ እንዲሁም ብዙ ቁጥር ተሳታፊ ያለውን ስብሰባ ሲያካሂዱና ሲመሩ ተመልክተናል፤አሁንም እየተመለከትን ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ ታዋቂ ናቸው የሚባሉ ሰዎችም (Public Figures) የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ በሰዎች መሐል ተገኝተዋል፤በእጅ ተጨባብጠዋል። የማኅበረሰብ መሪነት ትርጉም ከሚገለጥባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ጥንቃቄን የማስተማርና አርዓያ ሆኖ የመገኘት ተግባር ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በርካታ የአገራችን ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይህን አርዓያነት ማሳየት ሳይችሉ የቀሩባቸውን አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ ታዝበናል። የሆነው ሆኖ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በማገዝና በማስፈፀም ረገድ ግንባር ቀደም ድርሻ የነበራቸው አካላት ጥረቱን በሚያበላሽ ተግባር ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው መገኘታቸው እጅግ ያስተዛዝባል።በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት ከዚህ ቀደም ስንታዘበው እንደነበረው አሁንም ቀጥሏል፡፡ በእርግጥ ይህ መዘናጋት ቀደም ሲልም የነበረ ነው፡፡ በተለይ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ሲስተዋል የነበረው መዘናጋት እስካሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ በአገሪቱ በተለይም ሕዝብ በሚበዛባቸው እንደአዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የቫይረሱን ስርጭት ከሚያባብሱ ቦታዎች መካከል አንዱ የመጓጓዣ አገልግሎት ነው፡፡ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ለስድስት ወራት ያህል ታውጆና እየተተገበረ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እድሜው ማለቁን ተከትሎ ቀድሞ ከነበረው ብዙም ሳይለወጥ የቀጠለው የመጓጓዣ አገልግሎት ‹‹ኮሮና የሚባል ነገር የለም›› የተባለ እስከሚመስል ድረስ ችላ ተብሏል። አገልግሎቱን ለማግኘት የሚስተዋሉት መጋፋቶችና የሚታዩት የተጨናነቁ/አካላዊ ርቀትን ያልጠበቁ/ ሰልፎች ‹‹ነጋችን አስፈሪ ነው›› አስብሎን ነበር፡፡ በተሽከርካሪዎች ውስጥ ማስክ አለማድረግና አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ ብርና ሳንቲም ከተለዋወጡ በኋላ የእጅ ማፅጃ (ሳኒታይዘር) አለመጠቀም እንዲሁም ሳልና ማስነጠስን በተገቢው መንገድ አለማስተናገድ ከዚያም አልፎ ‹‹ማስክ አድርጉ›› ተብለው ሲጠየቁ በልበ ሙሉነት ‹‹ማስክ አላደርግም›› የሚሉ ሰዎች ድፍረት እጅግ ያስደነግጥና ያስፈራ ነበር፡፡
ለወትሮው ትርፍ በመጫን የሚታሙት የታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀመጡ ደንቦችን መሰረት በማድረግ መጫን ሲጀምሩ ‹‹እቸኩላለሁ፤እንደድሮው ጠጋ ጠጋ ብለን እንቀመጣለን … ችግር የለውም፤ኮሮና የሚባል ነገር የለም … ›› እያሉ ደንቦቹን ለመጣስ የሚጥሩ ብዙ ተሳፋሪዎችን ስንመለከት ተገርመናል፡፡ ‹‹የመዝናኛ›› ስፍራዎችም እንደመጓጓዣ አገልግሎቶች ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የሚያባብሱ ቦታዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ስፍራዎች የሚስተዋለው ከልክ ያለፈ ግዴለሽነት ‹‹ቫይረሱ ተሰባስበን የመብላት፣ የመጠጣትና የመዝናናት አገራዊ ልማዳችንን ጎድቶብን ቆይቷል …›› የሚል የ‹‹በቀል›› ስሜት ያዘለ ይመስላል። እኛ ‹‹በቀል›› ያስመሰልነውን መዘናጋት ቫይረሱ እጥፍ አድርጎ እንደሚመልስልን አለመገንዘባችን ግራ ያጋባል!
ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ በታወቀበት ሰሞን ይደረግ የነበረው ጥንቃቄ ከወራት በኋላ ሲቀር፣ ውሃ ተሞልተው በየቦታው ተቀምጠው የነበሩት የእጅ መታጠቢያዎች ዛሬ የውሃ ሽታ ሲሆኑ፣ አካላዊ መራራቅ ለመተቃቀፍና ለመሰባሰብ ቦታውን ሲያስረክብ እንዲሁም መጨባበጥ እንደወትሮው ሲቀጥል ቫይረሱ ስርጭት በእጅጉ እንደሚጨምርና ምናልባትም ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን የገለፁ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡
በተቋማት የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታም ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በብዙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ በግዴለሽነት የተሰባሰቡ ሰዎችን መመልከት ባለፉት ጊዜያት ለሰማነው የታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር መጨመር ምክንያት መሆኑ አይካድም፤ለነገም ያስፈራል፡፡
እነዚህ ሁሉ መዘናጋቶች ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰራጭ፣ የፅኑ ህሙማን ቁጥር በእጅጉ እንዲያሻቅብና የሟቾችም ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ መዘናጋት በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ምን ውጤት እንዳስከተለ ዐይተናል፡፡ የቫይረሱ ተያዦችና ሟቾች ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ቫይረሱ ባስከተለው ሕመምና ሞት ምክንያት የብዙ ሰዎች ቤት ከባድ ጭንቀትና ሃዘንን አስተናግዷል፡፡ የአገርና የወገን መመኪያ የሆኑ ግለሰቦችን ጭምር ተነጥቀናል፡፡
የሰውነትን በሽታን የመከላከል አቅምን ይጨምራል የተባሉ ክትባቶች መሰጠታቸው መዘናጋት እንዲፈጠር ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ የማያደርጉበትንና አካላዊ ርቀታቸውን የማይጠብቁበትን ምክንያት ሲጠየቁ ‹‹ክትባት ስለተከተብኩ ችግር የለውም›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ክትባቱ በሽታ የመከላከል አቅምን ከመጨመር በስተቀር በቫይረሱ ላለመያዝ ዋስትና እንደማይሆን አላወቁም አልያም አውቀው በግዴለሽነት እየተጓዙ ነው ማለት ነው፡፡
የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 30/2013) እየተተገበረ እንደሚገኝ ሲነገር ሰምተን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ መመሪያ ትግበራ የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ ዛሬም ደንቡን የተፃረሩ በርካታ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ነው፡፡ በደንቡ ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን መጣስ የሚያሸልምና እንደጀግና የሚያስቆጥር ይመስል ደንቡ እየተከበረ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ቀደም ሲል ይደረጉ ከነበሩት ጥንቃቄዎች መካከል ጥቂቶቹን በድጋሚ በማጠንከር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ የታመነበት ‹‹እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ›› የተሰኘ አገራዊ ንቅናቄ መጀመሩ ተነግሮ ነበር፡፡ የቫይረሱ ስርጭት በእጅጉ የመጨመሩ እውነታ ግን ንቅናቄው ምን ውጤት እንዳስገኘ እንድንጠይቅ አድርጎን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በእርግጥ የመመሪያውም ሆነ የንቅናቄው ትግበራ ምን ውጤት እንዳመጣ ራሱን የቻለ ጥናታዊ መልስ ቢያስፈልገውም ደንቦቹ ሲጣሱ መመልከታችን ግን የሚካድ አይደለም፡፡
በአሁኑ ወቅት ሦስተኛው ዙር የቫይረሱ ስርጭት ለመከሰቱ የሚጠቁሙ አመላካቾች (በጥናት የሚረጋገጡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) እየታዩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ሪፖርት እንደምንመለከተው ቫይረሱ የሚገኝባቸውና ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የጽኑ ታካሚዎች ቁጥር በእጅጉ ማሻቀቡ ደግሞ ይበልጥ ያስፈራል፡፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልም ሁሉም የጽኑ ህሙማን መታከሚያ ክፍሎች በቫይረሱ ተጠቂዎች እንደተያዙ አስታውቋል፡፡
ከሁሉም በላይ አስፈሪ የሚሆነው ደግሞ ወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታና የአየር ፀባይ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ ለሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎችና ተያያዥ ሁነቶች ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸው መድረኮች ስለሆኑ የቫይረሱን ስርጭት እንዳያባብሱት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ወቅቱ ሙቀት የማይገኝበት የክረምት ጊዜ ስለሆነ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፤በመሆኑም የምናደርገው ጥንቃቄም ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ቫይረሱ በሦስተኛ ዙር ወጀቡ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ያስፈራል፡፡ በዓለም ዙሪያ ከ201 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በቫይረሱ ተይዞና ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሚበልጠው ደግሞ በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ለሞት ተዳርጎ ሳለ፣ ከሁሉም በላይ የቫይረሱ ስርጭት በኢትዮጵያም እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ሳለ፣ የቫይረሱን ስርጭት ክፉኛ በሚያባብሱ ተግባራት ላይ መሳተፍና ስርጭቱን ለመቆጣጠር የወጡ መመሪያዎችን በትኩረት አለማስፈፀም በሌላው ዓለም ያየነውና የሰማነው አሰቃቂ መከራ በኢትዮጵያም እንዲከሰት ፈቃድ እንደመስጠት የሚቆጠር እጅ አደገኛ ተግባር ነው፡፡
ስለሆነም በሕክምና ባለሙያዎች የሚመከሩትን የመከላከያ ዘዴዎች (በተለይም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን) እንዲሁም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ በመተግበር የአስከፊውን ቫይረስ ስርጭት መቆጣጠርና ሌሎች አገራት ያጋጠማቸውን አስከፊ ቀውስ ላለማስተናገድ መጣር ይገባል! የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው አካላትም ኃላፊነታቸውን ሊወጡና አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ዛሬም የተረሳው የኮሮና ቫይረስ እንደገና እየመጣ ስለሆነ የቫይረሱ ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበንና ስርጭቱን መቆጣጠር ይገባል! እንጠንቀቅ!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም