የትውልድ ቦታው የጀግና አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው አርሲ በቆጂ ነው።የተገኘው ደግሞ ሥማቸው ከታወቀ አትሌቶች ቤተሠብ።ከታዋቂዎቹ አትሌቶች ትዕግስት ቱፋ እና መስታወት ቱፋ ወላጆች።ሰለሞን ቱፋ ነሐሴ 1 ቀን 1992 ዓ.ም ተወለደ።ለትምህርት እንደደረሰም የተወሰኑ የክፍል ደረጃዎችን አዳማ ከተማ፤ ከዚያም እዚሁ አዲስ አበባ እህቱ አትሌት መስታወት ቱፋ ጋ እየሆነ ተማረ።
ከታዋቂ አትሌቶች ቤተሰብ የተገኘው ሰለሞን ግን እንደ እህቶቹ በአትሌቲክስ ፍቅር አልከነፈም።ይልቁንም ወንድሞቹ ሲሰሩ የሚያየው የቴኳንዶ ስፖርት ቀልቡን ሳበው።እናም ገና በልጅነቱ እግሮቹን ማፍታታት ጀመረ።ነገር ግን ለቴኳንዶ የሚያመቸውን ጊዜ እና ቦታ እስኪያገኝ ድረስ እንደ ብዙዎቹ ልጆች እግር ኳስ እየተጫወተ ቀጠለ።
ሰለሞን 14 ዓመት ሲሞላው ከቴኳንዶ የሚገናኝበት ዕድል ተፈጠረ። እስከ ኦሎምፒክ ያደረሰው የወርልድ ቴኳንዶ ጉዞም ተጀመረ።ከዚያ በኋላ ስኬታማ ለመሆን ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። የስኬቱ ምክንያት ደግሞ ያለምንም መዘናጋት በሣምንት 6 ቀን በቀን 5 ሰዓት ልምምድ መስራት መቻሉ ነው።የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ያለምንም እንከን በማሸነፍ ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችም ተሻገረ።
በ2014 እ.ኤ.አ 2ተኛው የአፍሪካ የታዳጊዎች ውድድር ቦትስዋና ጋቦሮኒ ሲካሄድ በ49ኪ/ግ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። ከዓመት በኋላ በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው መላው አፍሪካ ጨዋታ በ54 ኪ.ግ ዲፕሎማ አገኘ። በዚያም ዓመት በሩሲያ በተካሄደው ሻምፒዮና ላይም ተሳታፊ ሆነ።በ2018 እ.ኤ.አ በሞሮኮ ራባት በተካሄደ የአፍሪካ ሲኒየር ውድድር ሌላ የወርቅ ሜዳሊያን አገኘ። እዚያው ሞሮኮ አጋዲር ላይ በተካሄደ ሌላ ውድድርም ሌላ ወርቅ አመጣ። ወደ ፖላንድ ዋርሶው ተሻግሮም የነሐስ ሜዳሊያ አገኘ።
ሰለሞን በተሳተፈባቸው ውድድሮች ሜዳሊያ መሰብሰቡን ቀጠለ።በመጨረሻም የሁሉም ስፖርተኛ ምኞት በሆነው ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሀገሩን ወክሎ የመሳተፍ ዕድል አገኘ።በዚህም በአንድ ጎን የእህቶቹን ታሪክ ማስቀጠል ሲችል በኢትዮጵያ ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኳንዶ ኦሎምፒክ መወዳደር የቻለ ስፖርተኛ ሆነ።በኦሎምፒኩ በ58 ኪ.ግ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ለሀገሩ ዲፕሎማም ይዞ ተመለሰ።
አሁን የእነ ሰለሞን ቤተሠብ በሁለት የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መድረክ የመወከል ዕድልን አግኝቷል።“ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች የሚወዳደሩ ስፖርተኞች የመጨረሻ ህልማቸው በትልቁ የስፖርት መድረክ ሀገራቸውን መወከል ነው።እኔም በዚህ ውድድር ላይ ሀገሬን በመወከሌ የሚሰማኝ ደስታ ከፍተኛ ነው” የሚለው ሰለሞን ስለ ማጣሪያውና እንዴት ወደ ኦሎምፒኩ እንዳለፈ እንዲህ ይናገራል። “ለማጣሪያው ለብሄራዊ ቡድን የተመረጥኩት ከዚህ በፊት በነበረኝ ውጤት መሠረት ነው።
ሁሉም ሀገራት ምርጥ የሚባሉትንና ይወክለኛል የሚሉትን የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾቻቸውን ይዘው ነበር የቀረቡት። ሁሉም ኦሎምፒክ ለማለፍ የተዘጋጀ አትሌት ነው። ሁሉም ሀገራት ማጣሪያውን አሸንፈው ለአሎምፒክ ተሳትፎ ይበቁልኛል ያሏቸውን በጣም ጠንካራ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ነበር ያሳተፉት። በእኔ ኪሎ የተሳተፉትን ተወዳዳሪዎች ከዚህ በፊት በነበሩን ውድድሮች አውቃቸዋለሁ።
ከአሰልጣኜ ጋር በመሆን በቪዲዮም ተመልክተናቸው በሚመገባ ተዘጋጅተን ነበር።ለአምስትና ስድስት ዓመት ለኦሎምፒክ ብዬ ስዘጋጅ ነበርና አሰልጣኜም ስለሚያቃቸው ከመሄዳችን በፊት በደንብ ተጠንቅቀን ነበር ልምምድ ያደረግነው። በዚህም ምክንያት ለማሸነፍ ችያለሁ። በመጨረሻው ዙር የገጠምኩት ሴኔጋላዊውን ሙስጠፋ ካማ ነበር።ስለ ሙስጠፋ እንደሰማሁት ለስድስት ዓመታት ያህል በኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ የትምህርት ዕድል ተሰጥቶት ጀርመን ሀገር ጠዋትና ማታ የወርልድ ቴኳንዶ ስልጠና የተከታተለ ነው።
ይህም ስለምንም ነገር ሳያስብ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት ቴኳንዶን ብቻ ሲሰለጥን የነበረ ልጅ ነው።ከዚህ በተጨማሪም በዓመት 10 እና 12 ጨዋታ የሚያደርግ ልጅ ነው። እኔ ግን በዛ ከተባለ ሁለት ጨዋታ ብጫወት ነው። ይህም እነዚህ ልጆች ምን ያህል ጥራት ያላቸው እንደነበሩ ያሳያል።” ብሏል።
ኦሎምፒክ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን በወርልድ ቴኳንዶ በመወከሉ በጣም ትልቅ ደስታ እንደሚሰማው የሚናገረው ሰለሞን፣ በአዓማችን ታላቁ ውድድር ላይ መሳተፉ በሁለት ነገሮች ትርጉም እንዳለው ይናገራል።“አንደኛ ማርሻል አርት ውስጥ ለምንሰራ ለእኔና ጓደኞቼ በሙሉ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በመወከሏ ለስፖርቱና ለእኛ በጣም ትልቅ ነገር ነው።ከዚህ በኋላ የመንግስት፣ የድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የባለ ድርሻ አካላት ትኩረት በትንሹም ቢሆን ወደ ወርልድ ቴኳንዶ መለስ ይላል ብለን እንጠብቃለን።
ይህ ደግሞ ለስፖርቱም ለእኛም ማደግ ጥሩ ነው። በሁለተኛ ደረጃ እኔ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ሀገሬን በኦሎምፒክ ለመወከል የበቃሁ የመጀመሪያው ሰው በመሆኔ ደግሞ እጅግ በጣም ተደስቻለሁኝ። አሁን ኢትዮጵያን በቴኳንዶ በኦሎምፒክ መድረክ በመወከሌ ብዙ ስፖርቱን የሚወዱ ህጻናት ወጣቶች ተስፋ ኖሯቸው ስፖርቱን እንዲያዘወትሩ ምክንያት ሆኛለሁ ብዬ አስባለሁ። እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ በቴኳንዶ ስፖርትም ብዙ ስፖርተኞች ሀገራችንን በትልልቅ የውድድር መድረኮች የሚወክሉበት ጊዜ ይመጣል›› ይላል።
በታሪክ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኳንዶ የወከለው ሰሎሞን እስካሁን ለደረሰበት ስኬቱ ያገዙትን ያመሰግናል።” ፈጣሪዬንና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሁሉም ነገር የሆነልኝ በእሱዋ ነውና ማመስገን እፈልጋለሁ። ማስተር አዲስ ጉርሜሣ ረዥሙን የብሄራዊ ቡድን ጊዜዬን ከእሱ ጋር ነበርኩኝና ለዚህ ስኬትም ከእኔ ጋር ለፍቷልና በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ። በመቀጠልም እናቴንና እህት ወንድሞቼን በጥሩም በመጥፎውም ሰዓት አብረውኝ ስለነበሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ አብረውኝ የነበሩትን ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ።ብሏል።
የእረፍት ቀንህን በምን ታሳልፋለህ አልነው።” ያለችኝ የእረፍት ቀን እሁድ ብቻ ናት። እሷንም በአብዛኛው የማሳልፋት በእንቅልፍ ነው። ምክንያቱም ሳምንቱ ልምምድ በጣም አድካሚ ነው። በሳምንት ስድስት ቀን በየቀኑ ለአምስት ሰዓት ልምምድ እሰራለሁ። የጂም ልምምድ አለ፤ የቴኳንዶ ልምምድ አለ፤ ሩጫ ወደ እንጦጦ በሳምንት ሁለቴ አለ። ሌላም ሌላም እና አድካሚ ስለሆነ እሁድ በእረፍት ቀኔ ብዙውን በመተኛት ነው የማሳልፈው።
ከዚያ በተረፈ ሙዚቃ በማዳመጥ እና ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የቀረውን ቀን አሳልፋለሁ” ይላል።የማንን ሙዚቃ እንደሚያዘወትር ሲገልጽም የሐጫሉ ሁንዴሣ እና እዮብ መኮንንን ሙዚቃ አብዝቶ እንደሚያዳምጥ ነግሮናል።በኦሎምፒክ ጨዋታው ላይ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ሕክምና ላይ የሆነው ሰለሞን አሁን ረዘም ያለ እረፍት የሚያደርግ ሲሆን፤ የሚወዳቸውን መዝናኛዎች ለማድረግ ብዙ ጊዜ እንዳለው ነግሮናል።
ሰለሞን ለሚወደው ስፖርት ትኩረት እንዲሰጠው ይፈልጋል። ኢትዮጵያውያን በወርልድ ቴኳንዶ ብዙ ተስፋ አለን። ግን ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት ይገባል። መልዕክቴም ለወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ትኩረት ይሰጠው የሚል ነው በማለት ሀሳቡን ገልጿል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013