እርሳቸው ኢትዮጵያ ምድር ላይ አላደጉም። በልጅነታውም የኢትዮጵያን ውሃ አልቀመሱም። የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ሱዳንን ብቻ ነው የሚያውቁት። ምክንያቱም አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ነው ቤተሰብ በጦርነት ምክንያት ወደ ሱዳን ሲሰደድ እርሳቸውም ወደዚያው የሄዱት። ስለዚህም የልጅነት ብቻ ሳይሆን የወጣትነት ጊዜያቸውም ያለፈው በሱዳን ነው። ይሁን እንጂ ሱዳን አንድም ቀን አገራቸው እንደሆነች አስበው አያውቁም።
ቤተሰቦቻቸው አገራቸው ኢትዮጵያ እንደሆነች በየቀኑ ይነግሯቸዋል። ኢትዮጵያን ከልባቸው ማህደር ውስጥ እንዲያስቀምጧት ያደርጓቸዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የሚወዷት ብቻ ሳትሆን የኖሩባት ያህል እንዲሰማቸውም ሆነው አድገዋል። በተለይም አያታቸው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ምን እንደሚመስል፣ ምድሪቱ ምን እንደነበረ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይነግሯቸዋል። ይህ ደግሞ ምን አለ አገሬ ሄጄ በኖርኩ እያሉ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። በዚህም የአገር ፍቅራቸውን ይዘው በአለም አደባባይ ስለ ኢትዮጵያ ለመመስከር እንዲነሱ ሆነዋል።
በዓለም አቀፍ መድረኮች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው በመሞገት እና እውነታውን በማሳወቅ ረገድ ደግሞ ከመንግስት ኃላፊዎች ባለፈ በራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገራቸው ጥቅም የቆሙ ምሁር ለመሆን ችለዋል። በተለይም ለሀገራቸው ጥቅም በአባይ ጉዳይ ላይ አስረጂ ሆነው ለዓረቡ ዓለም መልዕክትን ከሚያስተላልፉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ለመሆን በቅተዋል። መካ አደም አሊን በሌላ አገር ቢታደግም ኢትዮጵያዊ ፍቅር እስከምን ድረስ እንደሚያታግል ኖረውት እያሳዩ ነውና ይህንና መሰል የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩን ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ከልምዳቸው ተማሩ ስንል ጋበዝናችሁ።
የትም ቢኮን ኢትዮጵያዊነት
የተወለዱት ሁመራ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ ዓመት ሳይሞላቸው ነው ወደ ሱዳን የሄዱት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በደርግ ጊዜ የነበረው ጦርነት ሰርቶ ለመኖር ስላላስቻላቸው ነው። ቤተሰቡ በእርሻ ሥራ የሚተዳደር ነው። ሰፋፊ መሬት ተከራይቶ ጭምር በትራክተርና መሰል ዘመናዊ እርሻ የሚያርስም ነበር። በወቅቱ ባለሀብቶች የሚይዙት አይነት መኪና ጭምር የሚይዝ አይነት ቤተሰብም ነበር። ሆኖም ያለው የጸጥታ ጉዳይ ተረጋግቶ ለመኖር አላስቻላቸውም። ስለዚህም ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ትተው ወደጎረቤት አገር ነጎዱ። እዚያም ቢሆን ካምፕ ሳይገቡ በራሳቸው ቤት ተከራይተው አብዛኛውን የማምረቻ መሳሪያቸውን ይዘው ስለሄዱና ብዙ የሚያውቋቸው ሰዎች ስለነበሯቸው ብዙም ሳይቸገሩ የቀደመ ስራቸውን መሬት እየተከራዩ መስራታቸውን ቀጠሉ። ይህ ደግሞ ለመምህርት መካ መደላደልን የፈጠረ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ልጅነታቸው ከአገራቸው ከመራቃቸው ውጪ ምንም ችግር ያረፈበት አልነበረም። የፈለጉት እየተሟላላቸው ነው ያደጉት። በተለይም የመጀመሪያ ልጅ መሆናቸው ለዚህ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። በብዙ ነገር ነጻ ሆነው እንዲያድጉ እድል ተሰጥቷቸዋል። ጨዋታ ሳይቀር በፈለጉት ጊዜ እንዲከውኑ ይፈቀድላቸዋል። ለትምህርታቸውም ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ በተቻለው ሁሉ ይደገፋሉ። የመናገር ነጻነትንም ያዳበሩት ከሚሰጣቸው ዋጋና ምክር አንጻር እንደሆነ ያነሳሉ። በትምህርት ቤት በትወናና በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ መጣጥፍ ይዘው መገኘታቸውና መሳተፋቸውም ለዚህ ነጻነታቸው ሁነኛ ሚና እንደተጫወተም ይናገራሉ።
በሱዳን ገዳሪፍ የምትባል ከተማ ላይ እድገታቸውን ያደረጉት መምህርት መካ፤ ከተማዋ በብዙ ነገር ልምድ የምታስቀስም ነች። በተለይም እንደእርሳቸው አይነት ሌላ ቦታ ተወልዶ ለመጣና ማንነቱ በኢትዮጵያዊ ስነልቦና ለተገራ ልጅ ብዙ ተሞክሮን ታቀዳጃለች። በሁለት አገራት ባህልና ወግ ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ለመልመድና ለመማር ብሎም ለመኖር ትልቅ አቅም የሚፈጥርም ሁኔታ ያለባት ነች። እናም በደንብ ተጠቅመውባታል፤ ልጅነታቸውንም አጣጥመውበታል። በእርግጥ በዚህ ሲያድጉ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንደተወለዱባት አገር አማርኛ አልነበረም። አረብኛ ነው። ስለዚህም ሁሉን ነገር የሚከውኑት በአረብኛ ነበር። አማርኛን የለመዱትም በጣም ትልቅ ከሆኑ በኋላ ነው። ምክንያቱም ከቤተሰብ ውጪ ማንም አይነጋገርበትም። ቤተሰብ ውስጥም ቢሆን እርሳቸው እንዲገባቸው በማለት በብዙ ልምምድ ውስጥ ይዘዋቸው እየሄዱ እንጂ ጭራሹኑ አይሰሙትም ነበር።
በባህሪያቸው ሩህሩህ አይነት ልጅ ናቸው። በዚህም አባታቸውን እየጎተጎቱ ሳይቀር የተቸገረ የሚረዱ ናቸው። በስራቸው ያለፈ ሁሉ ችግረኛ መስሎ ከታያቸው የቻሉትን ያህል ማድረግ ይወዳሉ። በዚህም ዘወትር አባታቸው ለማዝናናት ይዘዋቸው ከቤት ሲወጡ ኪሳቸው ተራግፎ ነው የሚገቡት። እንቢ ማለትን ደግሞ አያስተምሯቸውም። እናም ለጋሽ፣ ተጨዋችና ሰው ወዳድ ሲሆኑ፤ በተያያዘም በትምህርታቸው ደግሞ በጣም ጎበዝ ተማሪ ናቸው። ይህ ደግሞ ሱዳናውያን ጓደኞቻቸውም ሆኑ የእነርሱ ወላጆች የተለየ ትኩረት የሚሰጧቸው አይነት ልጅ ሆነው አድገዋል። እነርሱ ቤት ሳይቀር እንዲያስጠኗቸው የሚላኩት በእርሳቸው ትሁትነትና ተግባቢነት የተነሳ እንደነበር አይረሱትም።
ቤተሰቦቻቸው ሲያሳድጓቸው ቢያሞላቅቋቸውም ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ግን በምንም መልኩ አያስረሷቸውም። ስለ አገራቸው ሙሉ መረጃ በየተገኘው አጋጣሚ ይነግሯቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ማንነትን ሊገነቡ የሚችሉ ሥርዓቶችንና ስራዎችን ጭምር ያስተምሯቸዋል። ለአብነት ሱዳን እያሉ ያውም ልጅ ሆነው ስፌት ማለትም ሰፌድ፣ ሌማትና የተለያዩ ጌጣጌጦችን በደንብ ይችላሉ። ኢትዮጵያዊ ምግብ ሳይቀር ጠንቅቀው መስራት ያውቁበታል። ስለዚህ ባህሉን እያወቁ እንዲያግዟቸው የሚያደርጉት በዚህና መሰል ተግባራት ነበር። በተለይ ግን የአገር ፍቅር ጉዳይ የመጀመሪያው የማንነት መገንቢያ ነገራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹ እኛ በባዕድ አገር ነው ያለነው። ስለዚህም አገራችን ስትረጋጋ እንሄዳለን። አገራችን ከሁሉ አገር የምትበልጥና ከተሰራባት ሁሉን መመገብ የምትችል ነች። ሁሉም የሚወዳት ፣ ሁሉም የሚመኛትና ህዝቦቿም ለሰው ልጅ ሁሉ መልካም የሆኑ ናቸው››› እያሉ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸውና ራሴን ስችል አገሬን አገለግላለሁ ብለው እንዲመኙ እንዳደረጋቸው አጫውተውናል።
በልጅነታቸው ሀኪም መሆን ይፈልጉ ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ በሁለት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ሰውን መርዳት በጣም መውደዳቸው ሲሆን፤ አያታቸው ጋር መጥተው ድነው የሚመለሱ ሰዎችን ሲመለከቱ በጣም ይደሰታሉ። እናም ሰዎችን በዚህ ዘርፍ ማከም ብዙዎች እንዲደሰቱ ማድረግ ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ሁለተኛው አያታቸው ጥሩ ወጌሻ መሆናቸውና እዚያ ላይ የተሻለ አጋዥ በመሆናቸው ሙያውን ስለሚወዱት በትምህርት አግዘውት በህክምናው ዘርፍ የታመመን መርዳት ህልማቸው ሆነ።
ከሱዳን እስከ ኢትዮጵያ
የትምህርት “ሀ-ሁ”ዋቸው የተጀመረው ባደጉባት ሱዳን ውስጥ አድፋሪ ከተማ ነው። መጀመሪያ ፊደልን መቅሰም የጀመሩት ቁርዓን በመቅራት ሲሆን፤ ይህም በመስጊድ የሚከናወን ተግባር ነው። ከዚያ በሱዳን ለሚኖሩ ተማሪዎች ሁሉ በእኩል ደረጃ ትምህርት በሚሰጥበት ሱዳን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ። እስከ ስምንተኛ ክፍል ከቆዩም በኋላ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተዛወሩ። አሁንም ከሱዳን ሳይወጡ ነው እስከ 12ኛ ክፍል ለመማር ችግር ሳያጋጥማቸው የቀጠሉት። በተለይ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ መሆናቸው ለብዙ ነገር ጠቅሟቸው ነበር ትምህርቱ የተጠናቀቀው።
ጓደኞቻቸው ሱዳናውያን ጭምር ከእርሳቸው ብዙ ስለሚፈልጉ በብዙ ነገር ይተጋገዙ እንደነበርም ያስታውሳሉ። በእርግጥ ችግሩ የሚታየው ከ12ተኛ ክፍል በኋላ ነው። ምክንያቱም በሱዳን ነጻ ሆኖ መማር የሚቻለው እስከ 12ኛ ክፍል ብቻ ነው። ከዚያ በላይ ለመማር የሱዳን መታወቂያና ሱዳናዊ መሆን ግድ ይላል። ይህንን የማይፈልግ ካለ ደግሞ ገንዘብህን ይጭነቀው ይባላል። ስለዚህም እንግዳችንም በዩናይትድ ኔሽን ድጋፍ ነው መማር የቻሉት። ማለትም ከፍሎ ያስተማራቸው ዩናይትድ ኔሽን ነው። ይህም ቢሆን እንዲሁ ገደብ ነበረበት። ሜዲሲንን የመሳሰሉ የህክምና ትምህርቶችን ለመማር አይፈቅድም።
እንግዳችን ምንም እንኳን ለመማር የሚያበቃቸው ውጤትና ፍላጎታቸውም ህክምና ቢሆንም መማር የሚችሉት ግን ከዚህ ውጪ በመሆኑ የልጅነት ህልማቸውን ሳያሳኩት ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ተቀራራቢ የትምህርት መስክ ከመማር ግን ማንም አላገዳቸውም። በሱዳን ባደጉባት ከተማ በሚገኘው ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሜዲካል ላብራቶሪ ቴክኖሎጂ የትምህርት መስክ መከታተል ችለዋል። መስኩን ወደውትም የተሻለ ውጤት በማምጣትም ነው ትምህርቱን ያጠናቀቁት።
ከሦስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ አገራቸው ተመልሰው እየሰሩም ሳለ ዳግም የመማር እድሉን አግኝተው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጀመሩ። ይህም የሆነው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ የተማሩት የትምህርት መስክም በማይክሮ ባዮሎጂ ነው። አሁንም ቢሆን መማር የማይቋረጥ ሥራቸው እንዲሆን ይፈልጋሉና በቅርብ የሚመረቁበትን የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምረዋል። የመጨረሻ ዓመት ላይም ይገኛሉ። የትምህርት መስካቸው ደግሞ ሞለኪዩላር ባይሎጂ ይባላል።
ሁሌም መማር እንደሚፈልጉና ከትምህርት መራቅ መሞት ነው ብለው እንደሚያስቡ በውይይታችን መካከል ያነሱልን መምህርት መካ፤ በሥራ በቆዩባቸው ክፍተቶች ሁሉም ከትምህርት ላለመራቅ የተለያዩ ስልጠናዎችን ይወስዳሉ። በዚያ ላይ ማስተማርም መማር ነው የሚል እምነት አላቸው። ስለዚህም እኔ ሁልጊዜ ተማሪ ነኝ ይላሉ። የትምህርት ሁኔታው ለመምህር የሚቋረጥ አይደለም ባይ ናቸው። ምክንያቱም ትምህርት የዲግሪዎች ብቻ ስብስብ ወይም ልኬት አይደለም። በአቅምና በሥራ መለወጥ፤ ማደግ ነው። እናም መምህር ደግሞ ተማሪውን ሲያስተምር ይማራል፤ ለተማሪው ሲዘጋጅ ይማራል፤ ሲያነብ ይማራል፤ ሲማርም ይማራል። ስለሆነም ሁልጊዜ ልኬት ካለው ዶክተር ብቻ ሳይሆን ከዚያ የሚበልጡ ነገሮች የሚገቡት ነው። ስለዚህም እኔም ከእነዚያ መካከል ስለሆንኩኝ የትምህርት ሂደቴ የዘወትር የሥራ ውጤቴ ነውና አይቋረጥም ይላሉ።
የአገር ፍቅር የመረጠው ሥራ
የሥራ ጅማሮዋቸው ሱዳን ሲሆን፤ ካርቱም ውስጥ የሚገኘው ሳይድ አብልለኢላ ሆስፒታል ውስጥ ነው። በላብራቶሪም ለሦስት ዓመት አገልግለዋል። ይህም ቢሆን ማድረግ ስላለባቸው ያደረጉት እንጂ ፈልገውት የሆነ አልነበረም። ምክንያቱም የእርሳቸው ፍላጎት ልክ እንደተመረቁ ወደ አገራቸው መጥተው አገራቸውን ማገልገል ነው። ሁሉም በሚባል ደረጃ ቤተሰቦቻቸው ኑሯቸው አሜሪካ ነው። ሆኖም እርሳቸው ግን አገሬ ብለው ያደጉባትንና የተማሩባትን ሱዳንን ለቀው የሙያ ፈቃዳቸውን አውጥተው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን መቀላቀል ችለዋል። በዚህም ቢሆን ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ነው የሰሩት።
ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የገቡበት መስሪያ ቤት ነው። የማይክሮ ባዮሎጂ መምህር በመሆንም ነው ለሦስት ዓመት ያገለገሉት። ከዚያ ወደ ይርጋለም ሜዲካል ኮሌጅ የተዛወሩ ሲሆን፤ እስከ አሁኗ ጊዜ ድረስ በዚህ ቦታ በመምህርነት እየሰሩ ይገኛሉ። አሁን በኢትዮጵያ ስምንት ዓመታቸው እንደሆነም አጫውተውናል። ከዚህ በተጓዳኝ አገራዊ ሥራዎችንም ቢሆን ይሰራሉ። ለአብነት ቴክኖሎጂው በሚፈቅድላቸው አጋጣሚ በሙሉ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በተለይም በአረብኛ ቋንቋ መጣጥፎችን ይጽፋሉ። የሀሳብ ልውውጥ ያደርጋሉ። በተመሳሳይ ምላሽ ያስፈልጋል ብለው ባሰቡት ላይ አለማቀፍ ሚዲያው ላይ ሳይቀር እየቀረቡ ይከራከራሉ። በአብዛኛው ኢትዮጵያ በሚችሉት ቋንቋ መጥፎ እንዳትባልና ጥቅሟን እንዳታስነካ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
የህይወት ፍልስፍና
እውነተኛ ለውጥ መስካሪ አይሻም። ምስክር እንዲሆን አድርጎ ስራው ከተሰራ ራሱ ይመሰክራል። ለዚህ ደግሞ ከገዛ ራስ መታረቅ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ሥራውን የምሰራው ለእኔ ብቻ ነው ወይስ ሌሎችም ያተርፉበታል የሚለውን መመርመርም ያስፈልጋል እምነታቸው ነው። ሌላው የህይወት ፍልስፍናቸው ሰዎች ከእኔ ምን ይጠብቃሉ የሚለውን ለይቶ ያንን ለማድረግ መሞከር ሁልጊዜ ጠንካራ ሰራተኛ፤ ሌሎችን አገልጋይ ያደርጋል የሚለው ነው። በተለይም በአገር ጉዳይ የግለሰቦች ጥረትና ልፋት ህብረት ፈጥሮ ከችግር ይጠብቃል የሚል እምነት አላቸው። ሰው የቻለውን ሁሉ ማድረግ ከቻለ በህይወቱ ብቻ ሳይሆን ሞቶም ነብሱ እረፍት ታገኛለች። ደስታውን በእጁም ያደርጋልም ብለው ያምናሉ።
አገራዊ ስሜትን በተግባር
“በሰው አገር መኖርን ማንም ይመኛል የሚል እምነት የለኝም። ሰርቶ ወደ አገሩ መመለስን ነው የሚያልመው። የእኔ ቤተሰቦችም ይህ አይነት ምልከታ ነበራቸውና እኔም አገሬን እንድናፍቃት አድርጎኛል። እንደውም ገና ወደ አገሬ ስገባ መሬቷን እስማለሁ እል ነበር። ፍቅሯ በውስጤ ሁሌ ይቀጣጠል እንደነበርም አስታውሳለሁ” የሚሉት መምህርት መካ፤ አገራዊ ስሜቴን በተግባር እንዲያሳዩ የሆኑት ሱዳናዊያን ምን ያህል በአባይ ውሃ እየለሙና እያተረፉ እንዳሉ እያዩ በማደጋቸውና ዛሬ ‹‹አንቺ አይገባሽም›› የሚላት ሲበዛ በማየታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
“በእርግጥ” ይላሉ መምህርት መካ፤ “በእርግጥ የአባይን አለመጠቀም ጉዳይ የእኔ ብቻ ቁጭት አይደለም። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው። ቁጭቱም እረኛው ሳይቀር በግጥም ሲገልጽበት የቆየው ነው። ነገሮች ተቀይረውም አሁን ከሚበላው ላይ እየቀነሰ እያዋጣ የቻለውን ሁሉ እያበረከተ ቁጭቱን እየተወጣም ይገኛል። ስለዚህም ዜጋ ነኝ የሚል ሁሉ ከገንዘቡም በላይ የሚያዋጣው ሌላ ነገር ካለው ከማድረግ ወደኋላ አይልም። በተለይም የተማረ ሲሆን፤ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር የሚያብራራው ብዙ ነገር ስላለው ከጉልበትና ገንዘብ አጋርነቱ በተጨማሪ ማሳወቁን፣ እውነቱን ማስረዳቱን መስራት ላይ ግዴታው እንደሆነ ያምናል። በዚህም ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ስለዚህም እኔም ከእነዚህ መካከል አንዷ ለመሆን የድርሻዬን እያበረከትኩ ነው። ቁጭቴን ከገታልኝ በሚልም ነው እያደረኩት ያለሁት” ብለውናል።
ቀጥለውም ‹‹እኔ ሱዳን ነው የተማርኩት። ሱዳን ካርቱም ከተማ ላይ አባይ ወንዝን በተደጋጋሚ ጊዜ የማየት እድል ነበረኝ። ምን ያክል በወንዙ እየተጠቀሙበት እንዳሉ እና ከተማዋ ላይ በርካታ መዝናኛዎችን ገንብተው ገቢ እንደሚያገኙ አውቃለሁ። በተጨማሪም በወንዙ ዳር ሰፋፊ እርሻዎች ላይ እየሰሩ ብዙ ምርት ያገኛሉ። አቧራ የለበሰ አካባቢን ለምለም አድርጎ የሚመግብ ሀይል ባለቤት ሆና ሳለ ልጆቿ በችግር ሲሰቃዩ ማየት በጣም ልብ ሰባሪ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ላይ ያልተሰሩ ብዙ ስራዎች እንዳሉ አስብ ነበር። የተማረው ሀይል ለዚህ መፍትሄ እንዳልሆነም ይሰማኛል። በመሆኑም የምትነገረኝን ኢትዮጵያ በሙያዬ ብቻ ሳይሆን ማድረግ በምችለው ሁሉ ለማገዝና በአባይ ተጠቃሚ መሆንን ማንም ሊጋፋት አገባም የሚል ስሜት ስለነበረብኝ ወደ ክርክሩ ገብቻለሁ ›› ይላሉ።
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በመስራት ላይ ሳሉ ህልማቸውን እውን የሚያደርገው የህዳሴው ግድብ መሰረት ድንጋይ ተቀመጠ። በዚህም የግድቡ ግንባታ መከናወን ሲጀምር ለሱዳን ጓደኞቻቸው ጭምር ደስታቸውን ሲገልጹ ሰነበቱ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግብጾች እውን ይሆናልን ሲገምቱና የግድቡ ፕሮጀክት ላይ ጥያቄ ማንሳት ሲጀምሩም እርሳቸው ለምላሹ ተዘጋጁ። መሰናክሎቹ የሚፈቱበትን መንገድም በአለማቀፎቹ ሚዲያዎች ሳይቀር እየቀረቡ መሟገታቸውን ቀጠሉ። ስለዚህም ትግላቸው የጀመረው ግብጾች በመገናኛ ብዙሃን፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና በአካል ጭምር ስለአባይ ግድብ መርዝ የታከለበትን የተዛባ መረጃ ማሰራጨት ሲጀምሩ ነበር።
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን በአማርኛ ቋንቋ ለውስጥ ፍጆታ ብቻ መረጃዎችን እናስተላልፋለን። በአንጻሩ ደግሞ እኛ የተከበብነው በአረቡ ዓለም ነው። እናም እንደእኔ አይነቱ ቋንቋውን የሚችል ሰው ለአገሩ ድምጽ ካልሆነ አገር ብዙ ዋጋ እንደምትከፍል አምናለሁ። በዚህም ነገ ዛሬ ሳልል ከመጻፍ እስከ ቃለመጠይቅ መስጠት ድረስ በመድረስ ስለ አገሬ ያለውን እውነታ እንድመሰክር ሆኛለሁ። በእርግጥ ይህን ሳደርግ ተመችቶኝ አይደለም። ብዙ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ደረጃ ላይ ነኝ። ሆኖም ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና ጥቂቷን ሰውቼ ብዙ አተርፋለሁ በሚል ነው ስለአባይ እና ኢትዮጵያ መረጃዎችን እያስተላለፍኩ የቆየሁት›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ በአልጀዚራ አረብኛ ቋንቋ ጣቢያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሀገሬን እውነታ ለዓለም በተለይ ለአረቡ ዓለም እያሳወቅኩ ነው። ወደፊትም ቢሆን አደርገዋለሁ ብለውናል።
ስለ አገር መመስከር ከግለሰብ ይጀምራል። በአረብኛ ቋንቋ ስለአባይ እና የኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ግለሰቦች ተንቀሳቅሰው ባይናገሩ ኖሮ አረቡ አለም ሊሰማን አይችልም። በተሳሳተ መንገድም ድጋፉን ይቀጥላል። ይህ ደግሞ የማንወጣው ችግር ውስጥ ይከተናል። ከዚህም በላይ ለአገር ተቆርቋሪ ሰዎች አቅማቸውን አጠናክረው እንዳይመጡም ያደርጋል። ስለዚህም የግለሰቦች ጥረት በኋላ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከዲፕሎማቶች መካከል አንዱ በሆኑት አቶ ሱልጣን አባጊሳ በኩል በአረብኛ ስለህዳሴ ግድብ የሚጽፉ እና የሚከራከሩ ሰዎችን የማሰባሰብ ሁኔታ ተጀመረ። በተደራጀ መልኩ መስራት ቀጠለም። ይህ ደግሞ የአንድነት ድምጽ እስከማሰማት አድርሶ ሰፊ ለውጥ አመጣ። እናም አንድነት የሚሰራው ከግለሰቦች ጥረት ነውና ይህንን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ ብለውናል።
አሁን የዓረቡ ዓለም ህዝቦች የኢትዮጵያን ችግር መረዳት ጀምረዋል። የመን፣ ሱዳን እና ሌሎችም ሀገራት የኢትዮጵያን ሃሳብ ደግፈው የሚጽፉ ሰዎችንም ማፍራት ተችሏል። በቡድን ተቀናጅተን ስለኢትዮጵያ ጥቅም እና መብት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቀርበን በምናስረዳበት ወቅት ስራችንም ጎልቶ መውጣት ችሏል። ስለዚህም በቡድን መንቀሳቀሳችን ለሀገራችን መብት መከበር እና በአረቡ ዓለም ዘንድ ግብጾች የሚያሰራጩትን የተዛባ መረጃ ለማስተካከል እንድንችል እድል ፈጥሮልናል። እያንዳንዱ ሰው ጠጠር ሲወረውር ተሰባስቦ የእራሱ ውጤት ይኖረዋልና ጠጠር መወርወሩን አያቁም ይላሉ።
የሱዳንና ኢትዮጵያ ግንኙነት
ሱዳኖች ኢትዮጵያን የሚያዩት እንደ አገራቸው ነው። ምክንያቱም በእርሷ በብዙ ነገር እንደሚጠቀሙ ያውቃሉ። ሰፋፊ መሬታቸው ጠግቦ የሚያድረው ከእርሷ በሚመነጨው ውሃ እንደሆነ ይረዳሉ። እናም አባይ ወንዝም ሆኖ ግድብም ሆኖ እንደሚጠቅማቸው እንጂ እንደሚጎዳቸው አድርገው አይወስዱም። አሁን በሚሰራው ሥራም የበለጠ ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥላቸው በመጀመሪያው ዙር አይተዋልና ብዙሀኑ ህዝብ ይህንን ያምናል። ስለዚህም ተቃዋሚው ህዝቡ አይደለም። ሃሳቡም የሁሉም ሱዳናዊ ሊሆን አይችልም። የተወሰኑ የሱዳን ባለስልጣናት የእርስ በእርስ ሽኩቻ ነው።
ባለስልጣናቱ በተለያየ ጎራ የተከፋፈሉ ናቸው። መንግስት የመሰረተው አካል ጭምር ልዩነት አለ። አንዳንዱ የግብጽ አቋም ማስፈጸሚያ እስኪሆን ድረስ ተሰይሟል። ለአብነት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል መሐዲ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ስለኢትዮጵያ አንድም ጥሩ ነገር ተናግረው አያውቁም። ኢትዮጵያ ላይ የሚያሰሙት ንግግርም ጭምር የትዕቢት መልክ አለው። በዚህም ሱዳኖች ጭምር የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ይጠሯቸዋል። እናም የግብጽ የስለላ ድርጅቶች በሱዳኖቹ ላይ የእራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን በመስራታቸውና አስፈጻሚ አካላትን በማስቀመጣቸው ኢትዮጵያ ላይ የተለያየ ጫና ለማድረግ እንዲሞክሩ ሆነዋል።
ህዝቡ ሁሌም ከኢትዮጵያ ጎን ነው። አሁንም ድረስ በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያን እንዳትነኩ ፤ ከነካችሁ አንምራችሁም እያላቸው ይገኛል። ምክንያቱም ጥቅሙንና ጉዳቱን ቀምሰው አውቀውታል። ባላስልጣናትም ቢሆኑ ሌላ ጥቅም ፍለጋ ስላለባቸው እንጂ የተጠቃሚነቱ ጉዳይ አያጠራጥራቸውም። ስለሆነም ሱዳናዊ ህዝብ ውግንናው ከጥቅሙና ከጉርብትናው ጋር ነው። ባለስልጣናቱ ግን ማጭበርበራቸውን ለመቀጠልና ከግብጽ ላለመለየት ሲሉ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1959 የተፈረመው የቅኝ ግዛት የአባይ ወንዝ ክፍፍል ስምምነትን አልቀበልም ካለች እኛም በ1902 የተካሄደውን የድንበር ስምምነት አንቀበልም ይላሉ። ሆኖም በህዝቡ ትግል መቼም እንደማይሳካላቸው ያውቃሉና የእነርሱ እንቅስቃሴ ጊዜያዊ ዱብ ዱብ ነው።
የውጪ ጫና
ምዕራቡ አለም በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳረፋቸው ጉዳይ አንድና አንድ ነው። ይህም በመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ እየሆነች መምጣቷ ነው። በማንም ቀኝ ያልተገዛች አገር ጠንካራ መንግስት ገነባች ማለት አህጉሪቱ ሙሉ ጠንካራ ሆነች ማለት ነው። ስለዚህም እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት የሚገዛላቸውን ያጣሉ። የሚበዘብዙት ነገርም ያከትምለታል። ስለዚህም ያ እንዳይሆን እስከዛሬም የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ጥቅም አስከባሪ አድርገዋት የቆዩትንና ምንም ችግር ያላመጣችባቸውን ተገዢያቸውን ግብጽን መደገፍ አጠያያቂ አይሆነም። ግብጾችም ቢሆኑ ሀያልነታቸው የሚመጣው በእነዚህ አገራት ድጋፍ ነውና ጫናው እንዲበራከት የተባሉትን ብቻ ሳይሆን የፈለጉትን ሁሉ ክፍተት እየፈለጉ እንዲያደርጉላቸው ይጠይቃሉ። አሁን አሜሪካና ሌሎች አገራትም የሞት ሞታቸውን እየሰሩ ያሉት ለዚህ ነው ይላሉ።
እነዚህ አካላት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሁሉ ይፈልጉታል። በተለይም የህወሀት ሴራ ያመረተውን ክፉ ሥራ በሚገባ ለስኬታቸው ይጠቀሙበታል። እንዲያመጠልጣቸውም አይፈልጉም። ህወሀትን ከጎንህ ነን የሚሉት ሥራውን ወደውለት ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ መንግስት ፣ የተረጋጋ ህዝብ እንዳይኖር ስለሚያግዛቸው ነው። ስለዚህም ጫናው ህወሀት እስኪጠፋና ኢትዮጵያዊያን ይህንን ተረድተው አትችሉም፤ እኛ ሉአላዊት አገር ያለን ነን፤ በአንድነት ህዳሴን ብቻ ሳይሆን ሌላም እንሰራለን እስኪሉ ድረስ የሚቆይ እንጂ ቀጣይነት ያለው አይሆንም። ለዚህ ደግሞ ቀኑ አሁን ሥራ የሚጀመርበት ነውና መረባረቡ እንዲቀጥል ያሳስባሉ።
አገር ምን ትፈልጋለች
አሁን የቀደመ አንድነቷን ብቻ ነው የምትፈልገው። ለዚህ ደግሞ ጅማሮዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህን ማጠንከር ያስፈልጋል። ፖለቲከኞች ህዝቡን ለራሳቸው ጥቅም ብለው ብርሀን እንዳያይ ከማድረግ ከተቆጠቡ፤ የተማረው ሀይል ከተለመደው አሰራሩ ወጥቶ ለህዝብ መስራት ከጀመረ፤ የአንድ ሰው ስኬት የአገር ስኬት ነው ብለን ወደማመኑ ከመጣን አገር የከፍታ ማማ ላይ ለመቀመጥ ብዙ ጊዜ አትጠይቅም። በተለይም ፖለቲከኞች አገሪቱ ወደ መረጋጋት ስትገባ፣ ጥቅማቸው ሲነካ ለአገር ነው ብለው መተው ከቻሉ የከፍታ ጊዜው ሩቅ አይሆንም። እኔ ባልኩት ብቻ አገር ትመራ አስተሳሰብ በህወሀት መብቃት አለበት ሀሳባቸው ነው።
ሌላው ኢትዮጵያ በሁሉም አለም የምትታወቅበትን ሁኔታ ማስፋት ያስፈልጋል። የመገናኛ ብዙሀን የአዘጋገብ ሁኔታ ጥርት ያለና መረጃው በፍጥነት የሚዳረስ መሆን አለበት። የውጪ ሚዲያ ተከታይ ከሆንን ተአማኒነትም ሆነ እውነታውን ማስረዳት ለማንም አንችልም። ስለዚህ ቀዳሚ መረጃ ሰጪ ፤ በብዙ አለማቀፋዊ ቋንቋዎች አለሙን መድረስ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ አድርጎ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም አለም ብዙ ነገሩን የሚሸጠው በሚዲያው አማካኝነት ነውና ያንን መጠቀም ለዛሬ ችግሮቻችን፣ ለነገ ከፍታችን ሁነኛ መፍትሄ ነው።
መከፋፈል የሚለውን ነገር ማስቆም ይገባል። ህወሀት የዘራው የብሔር ክፍፍል መመሪያችን ልናደርገው አይገባም። አሁን ከአገር ይልቅ መሪው ብሔር፣ ተመራጩ ብሔር ሆኗል። ስለዚህም ወደ አንድነት ለመምጣት እጅግ ፈታኝ ነው። እናም ከዚህ አስተሳሰብ መውጣትና በተባበረ ክንድ መስራት ነው። የቀደመ ወንድማማችነትን ማጠንከር ከምንም በላይ አገርን መውደድ መፍትሄያችንም፣ መዳኛችንም ይሆናል።
መልዕክት
ተስፋ አለመቁረጥ ስኬትን ያፋጥናል። ስለዚህም የማይቻል ነገር የለምና ደጋግሞ በመስራት የቀጣይ ህይወትን ማቃናት ያስፈልጋል። በተለይም አሁን ባለው ወቅታዊ አገራዊ ችግር ዙሪያ መተባበርና ችግሮችን መፍታት ለግለሰቦች ወይም ለመንግስት ብቻ የምንጥለው አይደለምና ሁሉም ጠጠሩን መወርወር አለበት። እንደቀደሙት አባቶቻችን አንድነትን ሀይል አድርጎ የውስጥንም የውጪንም ተጽዕኖ መግታት ያስፈልጋል መልዕክታቸው ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በባህሪው አይበገሬ ነው። ከእኔ የበለጠም ባህሉንና አኗኗሩን ያውቅበታል። የሌለ ባህል እንዲላበስ ያደረገውን አካል ከውስጡ አስወግዶ እንደ አባቶቹ ታሪክ ሰሪነቱን ማሳየት ይኖርበታል። በተለይም አሁን አገራችንን በመፈተን ላይ ያለውን ጥላቻ ዘሪ ህወሀትን ደብዛውን ማጥፋት ላይ መረባረብም ይገባል። በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ ከፍታ አገርን ለማራመድ ደግሞ የቀደመ መዋደዳችንና አንድነታችን ያስፈልጋልና ይህንን ማምጣት ላይም ልንሰራ ይገባል። በተለይም የተማረው ኢትዮጵያዊ ትልቅ ሀላፊነት በየአቅጣጫው አለበትና ለራሴ ብቻ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ ለአገሬም ወደሚለው ይገባል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013