የማራቶን ውድድሮችን እንኳን በኦሊምፒክ መድረክ በተራ ውድድሮች ላይም መገመት አዳጋች ነው። ከአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሮች በላይ የሚሸፍነውን አሰልቺና አታካች ፍልሚያ በወቅቱ የትኛውም በጥሩ አቋም ላይ የተገኘ አትሌት ሳይገመት ሊያሸንፍ ይችላል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በርካታ ፉክክሮችን ሲያስተናግድ የቆየው የቶኪዮ ኦሊምፒክ እየተገባደደ የመጨረሻና አለም በጉጉት የሚጠብቀው የማራቶን ፉክክር ላይ ደርሷል። ዛሬ የሚካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ሲሆን ምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች የተለመደ የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል።
በኦሊምፒክ ማራቶን እኤአ 1996 አትላንታ ላይ ለመጀመሪያ በማራቶን አንጋፋዋ አትሌት ፋጡማ ሮባ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወቃል። ከፋጡማ ድል በርካታ አመታት በኋላ አትሌት ቲኪ ገላና በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ይህን ድል ከደገመች ወዲህ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች በርቀቱ ከአሸናፊነት ርቃለች። ዛሬ ግን ወደዚህ ድል ለመመለስ በሶስት ጠንካራ አትሌቶች ትወከላለች። እነዚህ አትሌቶች ካላቸው አቅምና ባለፉት ጊዜያት ካሳዩት አቋም በመነሳትም ከኬንያውያን አትሌቶች ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ቢታሰብም ሜዳሊያ ውስጥ ለመግባት ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ባለፈው ሚያዝያ 23/2013 በሰበታ በተካሄደው የኢትዮጵያውያን የማራቶን የማጣሪያ ውድድር ሰላሳ አምስት ኪሎ ሜትሩን 1:59:23 በሆነ ሰአት ቀዳሚ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ትእግስት ግርማ የመጨረሻ የአለም አቀፍ ውድድር ውጤቷ በ2020 የቫሌንሲያ ማራቶን ስድስተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ሲሆን፣ በ2016 ሞቃት በነበረው የቤሩት ማራቶን በወቅቱ የራሷ ምርጥ የነበረውን ሰአቷን (2:32:44) በማስመዝገብ አሸንፋለች። በ2018ና 2019 የጉዋንዙና ኦታዋ ማራቶን ውድድሮችን አሸንፋለች። በአንድ አመት ውስጥ ሶስት የማራቶን ውድድሮችን በማድረግ ውጤታማ መሆን የቻለችው ትእግስት የኦታዋው ማራቶን ገና ሁለተኛ ውድድሯ ሲሆን በአጠቃላይ ከአራት ማራቶኖች የበለጠ ሳትሮጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስኬት ተሸጋግራለች። ይህም በዛሬው ውድድር ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀዳሚ አድርጓታል፡፡
የሰበታውን ማጣሪያ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ብርሃኔ ዲባባ በርቀቱ የራሷን ምርጥ ሰአት ያስመዘገበችው በ2014 የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ባጠናቀቀችበት ውድድር ሲሆን 2:22:30 ያስመዘገበችው ሰአት ነው። ከአመት በኋላም በ2015 የቶኪዮ ማራቶን ቀዳሚ ሆና ብታጠናቅቅም ያስመዘገበችው ሰአት 2:23:15 ነበር። ይህም ሰአትና ውጤቷ በ2015 የቤጂንግ የአለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክላ በርቀቱ ለመሳተፍ አብቅቷታል። ብርሃኔ በዛሬው ውድድርም በሜዳሊያ ፉክክሩ ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በሰበታው የማጣሪያ ውድድር ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ሮዛ ደረጄ 35 ኪሎ ሜትሩን ያጠናቀቀችበት ሰአት 2:00:16 ነው። እኤአ በ2019 የቫሌንሲያ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ሮዛ ደረጄ 2:18:30 በሆነ ሰአት የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰአት በርቀቱ በታሪክ አስራ ስምንተኛ ፈጣን ሰአት ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ ድሏ በፊት ትኩረት እያገኘች የመጣችው ሮዛ በተመሳሳይ አመት በዶሃ በተካሄደው የአለም ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር ይዛ ብቅ ትላለች ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ በምሽት በተካሄደው የማራቶን ውድድር ፈታኝ በነበረው የዶሃ ከፍተኛ ሙቀትና ወበቅ ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሁሉም ውድድሩን አቋርጠው በአምቡላንስ ተጭነው ለመሄድ ሲገደዱ ሮዛም አንዷ ለመሆን ተገዳለች። ሮዛ ከኢትዮጵያ ውጪ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ያደረገችው እኤአ 2015 አልጄሪያ ላይ ሲሆን በ2:34:02 አራተኛ ደረጃን ይዛ ነበር የፈፀመችው። ከአመት በኋላ ግን 2016ና 2017 ላይ የሻንጋይ ማራቶንን በተከታታይ በማሸነፍ ወደ ስኬት ተሸጋግራለች። 2018 መጀመሪያም ጠንካራ ፉክክር በሚደረግበት የዱባይ ማራቶን 2:19:17 በሆነ ሰአት አሸንፋ በርቀቱ ከሌሎች የአለም ከዋክብት ጋር ተሰለፈች። ወጣት እንደ መሆኗም በዛሬው ውድድር ምን ልትፈጥር እንደምትችል መገመት ከባድ ነው፡፡
ኬንያውያን አትሌቶች ባለፉት ጊዜዎች በተለያዩ ውድድሮች ያሳዩትን ድንቅ አቋምና ያስመዘገቡትን የተሻለ ሰአት ተከትሎ በወረቀት ላይ የተሻለ የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል። በተለይም የርቀቱ የአለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ብሪጊድ ኮስጌ ከ2018 የለንደን ማራቶን ውድድር ወዲህ በርቀቱ ሽንፈት ያላስተናገደች አትሌት መሆኗ የተሻለ የአሸናፊነት ግምት ልታገኝ ችላለች። ይህች አትሌት በዚህ አመት በኢስታንቡል ግማሽ ማራቶን ብቻ የተሳተፈች ሲሆን አምስተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። ይህም ምናልባትም በማራቶን ባለፉት አመታት ያልተሸነፈችው አትሌት ኦሊምፒክ ላይ ልትሸነፍ እንደምትችል የታየበት ምልክት ሆኖ እንዲነሳ አድርጓል። ይሁን እንጂ ሌላኛዋ ኬንያዊት ፕሬስ ጂፕቺርቺር በዛሬው ውድድር ቀላል ግምት የሚሰጣት አትሌት እንደማትሆን ይጠበቃል። ይህች አትሌት ሁለት ጊዜ የአለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮን ስትሆን ባለፈው የቫሌንሲያ ማራቶን 2:17:16 በሆነ ሰአት ማሸነፏ ይታወቃል። በሌላ በኩል የአለም ቻምፒዮኗ ሩዝ ቺፕጌቲች ባለፈው የለንደን ማራቶን ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀች አትሌት መሆኗ የሚታወስ ሲሆን ባለፈው ሚያዝያ በኢስታንቡል ግማሽ ማራቶን 64:02 የሆነ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገቧ በዛሬው ውድድር የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ልትካተት ችላለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013