ወደዚህ ሥራ የገባው በአንድ ወቅት በኤግዚቢሽን ማዕከል የቀረቡ የፅዳት ማሽኖችን አይቶ ነው:: በአነስተኛ መነሻ ካፒታል የፅዳት አገልግሎት ድርጅት ከጓደኛው ጋር በማቋቋም ወደ ሥራ ቢገባም ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑለትም:: ህብረተሰቡ ለፅዳት አገልግሎት የሚሰጠው ግምት አነስተኛ መሆን ንብረት ይበላሽብኛል ከሚል ፍራቻ ጋር ተዳምሮ በቀላሉ ወደ ገበያው መግባት አልቻለም::
ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ግን በከተማዋ በርከት ያሉ የፅዳት አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል:: ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በዘለለ የማይናቅ ካፒታልም አስመዝግቧል:: አሁን ከሚሰጣቸው የፅዳት አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎችንም አካቶ ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: የኤ ፕላስ ፅዳት አገልግሎት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ አሥራት::
አዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ሕዝብ መኖሪያ ናት። በዚያው ልክ ደረቅና ፈሣሽ ቆሻሻዎችን በገፍ ታመነጫለች። ይኼ ደግሞ መንግሥት ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ የሌሎችንም አለኝታነት ይጠይቃል። ደረቅ ቆሻሻ ከየቤቱ እንዲሰበሰብ፤ የተሰበሰበው በአግባቡ እንዲከማች እና ከከተማው ወጣ ባለ ሥፍራ እንዲወገድ ይደረጋል። በዚህ ሥራ ላይ ታዲያ ብዙዎች ተሣትፎ አድርገዋል። ውጤታማ ሥራ በመሥራት የራሣቸውን አሻራ አሣርፈዋል። ለቤቶች፣ ለቢሮዎች፣ ለሕንጻዎች የጽዳት አገልግሎት በመስጠት የሥራና የመኖሪያ አካባቢዎች ጽዱ እንዲሆኑና የሥራ ዕድልም በመፍጠር ከሚጠቀሱት መካከል አቶ ዩናስ አንዱ ሆኗል።
አቶ ዮናስ ውልደቱና ዕድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ጣሊያን ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሠሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ቤቴልሔም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በየካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል:: ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በ1997 ዓ.ም የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል:: በመቀጠልም በናሽናል ኦይል ካምፓኒ/ኖክ/ ለሁለት ዓመት ያህል ሠርቷል::
የራሱን ነገር ሁሌም የመሥራት ፍላጎት የነበረው አቶ ዮናስ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት በኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀ አንድ አውደ ርዕይ ላይ ታድሞ ከጓደኛው ጋር ሲጎበኝ ለፅዳት አገልግሎት የሚውሉ ማሽኖችን ይመለከታል:: በኤግዚቢሽኑ ላይ የፅዳት ማሽኖቹን ይዘው የቀረቡት የዱባይ ሰዎች የማሽኖቹን ሁለገብ አገልግሎት ሲያስረዱ ጠጋ ብሎ ይመለከታቸው ጀመር:: በአጋጣሚ ሰዎቹ ማሽኖቹን የመሸጥ ፍላጎት የነበራቸው በመሆኑ ማሽኖቹን በ13 ሺህ 500 ብር በመግዛትና ቀሪ የፅዳት ማቴሪያሎችን በሀገር ውስጥ በማሟላት ከጓደኛው ጋር ሆኖ የፅዳት አገልግሎት ሥራን ለመጀመር ተነሣ::
እርሱና ጓደኛው በጋራ ባዋጡት 30 ሺህ ብር መነሻ ካፒታልና ለሥራው ያዘጋጇቸውን አራት ሰዎች በመያዝ ‹‹ኤ ፕላስ›› የተሠኘ የፅዳት አገልግሎት ሥራ ጀመሩ:: ሥራውን እንደጀመሩ ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሊሆኑ አልቻሉም:: የፅዳት አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎችንም በቀላሉ አላገኙም:: ህብረተሰቡ ለፅዳት አገልግሎት የሚሰጠው ግምት አነስተኛ መሆን፣ በቀላሉ በጉልበት ሠራተኛ አሰራዋለሁ ከሚል ዝቅተኛ ግምትና ንብረት ይበላሽብኛል ከሚል ፍራቻ ጋር ተዳምሮ በቀላሉ ወደ ገበያው ለመግባትም አልቻሉም::
ይሁንና በሂደት ከሦስት ወር ብርቱ ትግል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦር ሃይሎች አካባቢ አንድ የመኖሪያ ቤትን የማፅዳት ዕድል አገኙ:: የፅዳት ሥራውን በሚገባ አከናውነውም 1 ሺህ 200 ብር ተከፈላቸው:: ይህም ገንዘብ በጊዜው ትልቅ የነበረ በመሆኑ ለበለጠ ሥራ ተነሳሱ:: ለሦስት ዓመት ያህል አብረው ከሠሩ በኋላ ጓደኛው የራሱን ፎቶ ቤት በመክፈቱ በሥምምነት ተለያይተው እርሱ የፅዳት ሥራውን አስቀጠለ::
ኤ ፕላስ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ጊዜም ከሞላ ጎደል ሁሉንም የፅዳት አገልግሎቶችን በዘመናዊ መልክ ያከናውናል:: ከመኖሪያ ቤት ፅዳት የቤት ለቤት የሦፋና ምንጣፍ ፅዳት ሥራዎች አንስቶ ጎን ለጎንም አዳዲስ ሕንፃዎችን ከግንባታና ከዕድሣት በኋላ ያፀዳል:: የቢሮ ወንበሮች፣ ጠረዼዛዎች፣ ምንጣፎችና ሌሎችንም ከ20 በላይ የሚሆኑ የፅዳት አገልግሎቶችን ይሰጣል:: የደረቅና ፍሣሽ ቆሻሻዎችን ማንሣትና ማስወገድ፣ የሕንፃ መስታወቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማፅዳት ሥራዎችንም ይሰራል::
በጥቅሉም ጠቅላላ የሕንፃ ፅዳት፣ ከግንባታ በኋላ ፅዳት፣ የቢሮ ፅዳት፣ የፍሣሽ ቆሻሻ ማንሣት፣ የላውንደሪ አገልግሎት፣ የቤትና የወለል ፅዳት፣ የግንባታ መሣሪያዎች እጥበት፣ የሆቴልና የሆስፒታል ፅዳት፣ የመኪና እና የውሃ ታንከር እጥበት እንዲሁም የአይጥና ተባይ ማጥፋት አገልግሎቶችን ይሰጣል::
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱ በአዲስ መልክ ተንቀሣቃሽ የመፀዳጃ ቤት ከነሙሉ አገልግሎቱ በኪራይ ማቅረብ ጀምሯል:: በተለያዩ ችግሮች የተበላሹ የእምነበረድ ወለሎችንና ግድግዳዎችን ወደነበሩበት ይዞታቸው የመመለስ ሥራም /ማርብል ፖሊሺንግ/ ይሠራል:: ሮፕ አክሰስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሕንፃ ስካፎልዲንግ ሣያስፈልገው የውጪ የሕንፃ መስታወቶችን ፅዳትም ያከናውናል:: የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሠተበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ከአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በግብዣ ፍቃድ አግኝቶ የፀረ ጀርም ኬሚካል ማምረትና ርጭት አገልግሎትም ይሰጣል:: ለግልና የመንግሥት ተቋማትም የራሱን የፅዳት ማቴሪያሎችን በማቅረብና ሠራተኞችን በመመደብ ቋሚ የፅዳት አገልግሎቶችን ይሠራል:: ከዚህ በተጓዳኝ ለራሱ ፍጆታ የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያዎችን (ዲተርጀንቶች) እንደ በረኪና፣ ፈሣሽ ሣሙና፣ የእጅ ሣሙናና ስኮሪንግ ፓውደሮችን ያመርታል::
በአነስተኛ ካፒታልና በትናንሽ ማሽኖች የፅዳት አገልግሎት ሥራ የጀመረው ኤ ፕላስ በአሁኑ ጊዜ ከሠላሳ በላይ የሚሆኑ የፅዳት ማሽኖችን ማፍራት ችሏል:: ከስድስት በላይ የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ባለቤት ሆኗል:: እነዚህንና ሌሎችንም ሐብቱን ጨምሮ የድርጅቱ አጠቃላይ ካፒታልም ሦስት ሚሊዮን ብር ደርሷል:: በቋሚና በጊዜያዊነት ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል:: ከዚህ ውስጥም አብዛኛዎቹ ቋሚ ናቸው::
የፅዳት አገልግሎት ገና ብዙ ያልተሠራበትና የገበያ ፍላጎቱም እየጨመረ የመጣ ዘርፍ ከመሆኑ አኳያ ድርጅቱ በቀጣይ አሁን ላይ ያለውን የሰው ሀይል በመጨመር የፅዳት አገልግሎቱን በሥፋት የመሥራት ዕቅድ አለው:: በዚህ ዘርፍ ሥልጠና የወሰደ ባለሙያ እንደልብ ባለመኖሩ ከፅዳት ሙያ ጋር በተያያዘ ሥልጠናዎችን ለራሱ የመስጠትም ሐሳብ አለው:: ከዚህ በዘለለ ወደ አረብ ሀገራት ሄደው ለሚሠሩ ሴቶች ከዚሁ ሙያ ጋር በተያያዘ ተመሣሣይ ሥልጠናዎችን የመስጠትም ውጥን አለው::
ድርጅቱ እያከናወናቸው ካሉ የፅዳት አገልግሎቶች በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ራተኞች የሚችሉትን ያህል ከደመወዛቸው በፍቃደኝነት ቀንሰው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዲያዋጡ በማድረግና ለመቄዶኒያና ሠል የበጎ አድራጎት ማህበራት የነፃ የፀረ ጀርም ርጭት አገልግሎት በመስጠት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል::
በከተማዋ ካሉና በፅዳት አገልግሎት ዘርፍ በተሠማሩ ድርጅቶች አማካይነት በትንሹ ከ30 እስከ 40 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል የሚለው አቶ ዮናስ፤ ከዚህ አኳያ ዘርፉ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ መንግሥት ለሌሎች ዘርፎች ከሚሰጠው ትኩረት እኩል ለዚህም ዘርፍ በቂ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያመለክታል:: በተለይ መንግሥት የሚያበረታታቸው ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ዕቃዎች በተመሣሣይ ለዚህ ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችሉ ዕቃዎች ላይም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ይጠቁማል::
ለሥራው አጋዥ የሆኑ ተሸከርካሪዎች ዋጋም አቅምን ያገናዘቡ ሊሆኑ እንደሚገባ ይጠቅሣል:: የከተማ አስተዳደሩም ቢሆን የፅዳት ሥራውን በራሱ ከሚያከናውን በብዙ ሀገራት እንደሚታየው ለዚሁ ሥራ የሚያሠማራቸው ሠራተኞችን ጨምሮ አገልግሎቱን በዚህ ዘርፍ ላይ ለተሠማሩ ድርጅቶች በመስጠት በሌሎች ሥራዎች ላይ ማተኮር አለበት ሲል ምክረ ሐሳቡን ያካፍላል::
በፅዳት አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት 15 ዓመታት መቆየቱን የሚናገረው አቶ ዮናስ በነዚህ ዓመታት ቆይታዬ በቂ ባይሆንም በተለይ ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠሬ ደስተኛና ውጤታማ ነኝ ይላል:: በእርሱ ምክንያት ሥራ ያልነበራቸው ወደ ሥራ ተሠማርተው ኑሮን ሲያሸንፉ ማየቱ ይበልጥ ለሌሎች ሥራዎች እንዲነሣሣ ግፊት ፈጥሮለታል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሥራ የራሱንና የቤተሠቡን ኑሮ ማሻሻሉንና ይህም በሥራው ያመጣው አንዱ ውጤት መሆኑን ያስረዳል::
ሌሎችም በተመሣሣይ በዚሁ የፅዳት አገልግሎት ዘርፍ ገብተው ለሚሰሩ ሰዎች በቅድሚያ ሥራውን እንደመተዳደሪያና ገንዘብ ማግኛ ብቻ ቆጥረው መነሣት እንደሌለባቸውና ከዚህ ይልቅ የራስ ነገር እንዲኖር ከመፈለግ የመነጨ መሆን እንደሚገባው ይመክራል:: በሥራ ዘርፉ ከሚያገኘው ገቢ በላይ ደስታ የሚሰጠው ሥራው በሌላ ቢዝነስ ተደጉሞ በሥሩ ያሉ ሰዎች ሕልውና ሲቀጥል በመሆኑ ሌሎችም ሥራውን ወደውት ሊሰሩት እንደሚገባም ይጠቁማል:: በእንዲህ ዓይነቱ መንገድ ሥራውን የማከናወን ፍላጎት ያለው ሰው ሥራውን ቢሰራው መልካም መሆኑንም ይጠቅሣል::
የፅዳት አገልግሎት ዘርፍ በርካታ የሰው ሃይልን የሚያሣትፍና ለበርካቶችም የሥራ ዕድል ሊፈጥር የሚችል ከመሆኑ አንፃር በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ወሣኝ ነው:: ጉዳዩ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የግል ባለሐብቶችም በዚሁ ዘርፍ ገብተው ቢሰሩበት ከራሣቸው አልፈው ሌሎችንም መጥቀም ይችላሉ:: የእለቱ መልዕክታችን ነው። ሠላም!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013