የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ሌሎች ስምንት ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ።
የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በአምስት ኃላፊዎችና ሦስት በግል ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ላይ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸውል።
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ሰባት ክሶችን አደራጅቶ ያቀረበው ዐቃቤ ህግ በጥቅሉ 319 ሚሊዮን 475 ሺህ ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተመልክቷል፡፡
ተከሳሾቹ የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ማርኬቲንግ ሰፕላይ ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ እንዲሁም በግል ሥራ ይተዳደሩ የነበሩና ከወንጀሉ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ አቶ ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃንና አቶ ረመዳን ሙሳ ናቸው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ የስራ ኃላፊዎችና በድለላ ስራ ተሰማርተው ነበር የተባሉት ተከሳሾች በዋናነት የቀረበባቸው ክስ፣ ለአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት ከሚውሉ ትራክተሮች ግዥ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር በሜቴክ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ መሠረት ማንኛውም ግዥ በግልጽ ጨረታ መፈጸም እንዳለበት መደንገጉን እያወቁ፣ መመርያውን በመተላለፍና በርካታ ትራክተሮች እንዲገዙ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ሰባት ክሶች ውስጥ በዝርዝር አስረድቷል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በኃላፊነት የሚመሩት ተቋም፣ ከተጣለበት ተልዕኮ አንፃር ማንኛውንም ግዥ በሕጉና በመመሪያው መሠረት መከናወኑን፣ የውጭ ምንዛሪ ለተገቢ ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ያንን አለማድረጋቸውን በክሱ ተጠቅሷል።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው 15ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ሰባት ክሶች ላይ ያቀረቡትን መቃወሚያዎችን መርምሮ ብይን ሰጥቷል።
በተከሳሾች ላይ ከተመሰረተው ሰባት ክስ ላይ ከቀረቡት መቃወሚያዎች ውስጥ አምስቱን ውድቅ በማድረግ፤ሁለቱን ክሶች ደግሞ አቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ነው ትእዛዝ የሰጠው።
በዚህ መሰረትም አቃቤ ሕግ ሁለቱን ክሶች አሻሽሎ ለየካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል ሲል የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።